ደረጀ ከበደ እና ኃይለገብርኤል አያሌው

እንደ አለመታደል ሆኖ አካዳሚክ እውቀት፣ የዘመናዊነት ተጽዕኖ፣ የምዕራባውያኑ በጎ ባህል ሁሉ የቅርባችን ሆኖ እያለ ልንላቀቀውና ልንተወው ካልቻልንው አሮጌ ባህላችን ውስጥ አንዱ የሆነው ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ለሚያደርጉት በጎ አስተዋጽዖ፤ በሕይወት እያሉ የማመስገንና ለተተኪው ትውልድ ያላቸውን አርኣያነት በማንሳት ማክበርና የድካማቸውን ፍሬ ሌሎች እንዲማሩበት ማድረግ ተስኖናል።

 

 

ዛሬም ብርቅዬና በቀላሉ መተኪያ እንኳ የማይገኝላቸው መልካም ሰዎች እንደ ድንገት ሲለዩን መቃብራቸው ላይ ቆመን ከንፈር መምጠጥና አቶ እከሌ እንዲህ ነበር በማለት ከማዳነቅ ያላለፈ ክዋክብቶቻችን ከነስራዎቻቸው አፈር ማልበስ የእኛ ኢትዮጽያውያን አይነተኛ መለያችን ሆኖብናል።

 

ሙሉጌታ ኃይሉ Mulugeta Hailu

 

ድንገት ባለፈው ሳምንት ሳይታሰብ የተለየን ጠንካራና ጽኑ የነጻነትና የዲሞክራሲ ታጋይ የነበረው ወንድማችን ሙሉጌታ ኃይሉ ምን ያህል ተወዳጅና የተከበረ ታላቅ ሰው እንደነበረ የቀብሩ እለት የታየው ሐዘንና የተካሄደው ስርዐት አይነተኛ ምስክር ነበረ። ይህ በዲሲፕሊን የታነጸ ለአራት አስዕርተ አመታት የማይናወጽና የማይሸራረፍ ጠንካራ አቋም የነበረው የትግል ጓዳችን መለየት ለሕግ የበላይነትና ለሕዝብ እኩልነት በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል ውስጥ ላለው ኢትዮጽያዊ ሐይል ትልቅ ጉዳትን ያስከተለ መራራ ሐዘን ሆኖ አልፋል።

 

ሀገር በዘረኞች ስትናጥ ሕዝብ ሰላም አጥቶ ሲናወጥ ወገን በረሃብና እርዛት ሲይማቅቅ ጥቂቶች ተደራጅተውና መሠሪ አሽክላቸውን በህዝብ ላይ ዘርግተው አመታትን ሲያስቆጥሩ ቀላል የማይባል ወገን ፖለቲካዊ ትጥቁን ፈቶ እጅ ሠጥቶ በአድርባይነት ሲንደፋደፍና በሕዝብ መከራና ስቃይ ላይ ተረማምዶ ለጊዜያዊ ስልጣንና ጥቅም ቃል ኪዳኑን ሲያፈርስ ሙልጌታ ኃይሉ ቅንጦትና ጥቅም ሊያምረው ይቅርና ሕይወትን እጅግ አቅልሎ የሚያይና እድሜውን ሙሉ የሃገሩና የወገኑ ጉዳይ ከራሱ በፊት ያስቀደመ ታላቅ የኢትዮጽያ ልጅ ትንሳዔዋን ሳያይ ማለፉና እፍኝ አፈሯን መነፈጉ የሚያንገበግብ ቢሆንም ሙሌ ዘመኑን ሁሉ የባጀበት ፍትሕና ነጻነት በቆራጥ የሕዝብ ልጆች አንድ ቀን እንደሚረጋገጥ አያጠራጥርም።

 

በተለይም የሙሌ ሞትን መራራ ከሚያደርገው አብይ ቁምነገር አንዱ ከዛ በአንጀኝነትና በቡድናዊ ስሜት ከተወጠረው በድርጅት ዶግማና ቀኖና ከማሰብ በላይ መራመድ ሳይችል ዘመናትን ከተሻገረው ያ የስልሳዎቹ አብዮተኛ የተማሪ ትውልድ ውስጥ ራሳቸውን ሊበራል ካደረጉት ጥቂት ነባር የያኔ ታጋይ ፋኖዎች ውስጥ ሙሉጌታ ኃይሉ ከተተኪው ትውልድና ከወቅታዊ ሐሳቦች ጋር ተስማምቶና ተጣጥሞ አብሮ ለመጓዝ የቻለ በሳል ሰው ነበር። ሙልጌታ ምንም በፖለቲካ ንቃቱ በሰፊ የትግል ተሞክሮው የዳበረና የሰከነ ፖለቲካዊ እውቀትና ማሕበራዊ ንቃት ያለው በሳል ሠው ቢሆንም የእድሜ እርቀታችን ምንም የአባትና የልጅ ያህል ቢራራቅም ይህ የእድሜና የተሞክሮ ልዩነት ሳይገድበው እንደ እኩያ ጓደኛችን ሳይከብደን አብረን እንድንሰራ ያደረገና ዘወትር በሞራልና በሐሳብ ከጎናችን የማይለይ አጋራችን ነበር።

 

በዚህ አጋጣሚ ለሙሉጌታ ቤተሰቦች መጽናናትን እየተመኝን የዚህ ታጋይ ጓዳችን አርያነት ለአዲሱ ትውልድ የሞራልና የጽናት ስንቅ እንደሚሆን እያረጋገጥን እግረ መንገዳችንን ለዚያ ለስልሳዎቹ ታጋይ ፋኖ ትውልድ ጭንቀት የወጠረው መልዕክታችንን ለማስተላልፍ እንወዳለን። አስቸጋሪው የሃገራችን ጉዞ አሳዛኙ የሕዝባችን አበሳ ከየት ወዴት እየነጎደ እንደሆነና ምን ያህል እየተወሳሰበና ፈታኝ እየሆነ እንደመጣ ለናንተ መንገሩ ለቀባሪ እንዲሉ ይሆናል ግን ደግሞ በእውቀት የዳበረ በተሞክሮ የሠላ በጊዜ ሂደት የሠከነና በእድሜ እርቀት በጥልቀት ያስተዋለ አቅማችሁን ምስኪኗ ሃገራችን ሣትጠቀምበት ሃገር ተረካቢ ትውልድ በተገቢው መንገድ ሳታዘጋጁ እየመሸ በመሆኑ በቅጡ ልታስቡበትና ከአንጀኝነትና ከድርጅት አምላኪነት ተላቃችሁ ሃገርና ወገንን ለመታደግ ምንም ቢዘገይም አሁንም ያለችውን ውስን ግዜ ተጠቅሞ በጋራና በአብሮነት በመስራት እንድ ጓዳችን ሙሉጌታ ከሁሉ ጋር አብሮ በመቆም የመከራወን መንገድ መቀነስ ይቻላል ብለን እናስባለን።

 

አምላክ የወንድማችንን የሙሉጌታን ነብስ ይማርልን!

ለቀረነውም መግባባትን ፍቅርና አንድነትን ያድለን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! አሜን!!!

ደረጀ ከበደ የቀድሞው የሕብረት ዋና ፀሐፊ እና

ኃይለገብርኤል አያሌው የቀድሞው የሕብረት ምክትል ሊቀመንበር

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ