ክፍል 4

ግሩም ተ/ኃይማኖት

ሰናይት ካቀረቀረችበት ቀና ማለት አሳፈራት ... ልጁ ደግሞ ደግሞ ቢያናግራትም … ቀስ ብዬ አቀፍኳት እና ”... ይህ የህይወት ሂደት ነው መውደቅ መነሳት አለ። ግን ለምን ሰኒ ልጅሽስ? ባልሽስ? እነሱን ጥለሽ ይህ አይነት ህይወት ይሻላል? ለምን ወደ ሀገር አትመለሽም? ...” ብዙ ብዙ ነገር አልኳት። ልጁ አየኝ እና ”እ … ቢዝነስ አግኝተሻል? በቃ አልማዝ ስሪ ...” አለ። ሰናይት ባህሩን ለመሻገሪያ ብቻ አማራጭ አጥታ እንደምትሰራ ነገረችኝ። ”ሳዑዲ ናት የተባለወውስ?። አልኳት።

ደ”ልክ ነው ቀጥታ ሳዑዲ አረቢያ ሄጄ ነበር።ብዙ ነገር አለው መች እንደዚህ ...” አመንትታ አቋረጠች።

”ለሳውዲ ፈትናማ ምኑ ሊወራል ሽግር ነው” አለች አጠገቧ ያለችው ጓደኛዋ ስብርብር ባለ አማርኛ። ትግሬ መሆኗ በአነጋገሯ ያስታውቃል።

”ኦኬ! ተይው አጋጣሚ ነው ብለን እንለፈው”

”ለአጋጣሚማ አይደለም” አልማዝ ትባላለች አነጋገሯ ተመችቶኛል። ለእናንተም ምችት ይበላችሁ።

”ለፈተና የተፈጠርኩ” ሰናይት ናት።

”ዋይ! ጸቂ ... ሁለና የተፈተንማ አደል?”

”ሲያቀብጠኝ ከኮንትራት ቤት ወጥቼ ...” ብላ ጀመረች። አመጣችው አለ ልቤ ለመስማት አቆብቁቦ። እንዴት አያቆቦቁብ ... ሳዑዲ ናት ሲባል የሰማሁላትን ታሪክ ገልብጣ ሱማሊያ ያውም በረከሰ ህይወት ውስጥ ሳገኛት ጥያቄ የሆነብኝን ነገር ማላሽ ለማግኘት ... ሲያንሰው ነው።

”ግሩምዬ ሙት ወድጄ አይደለም የጠፋሁት። ምን ያደርጋል ተያዝኩና ተጠረዝኩኝ። ባዶ እጄን እንዴት ወደ ቤት ልግባ? ዞሬ በዚህ ለመሄድ …” እንባ ተናነቃት። ይውጣላት ብዬ ዝም አልኩኝ። በስደት አለም እንባ ማፍሰስ ቆሻሻ ውሀ እንደመድፋት ይቆጠራል።

”በስደት አለም እንባ ማፍሰስ ቆሻሻ ውሃ የመድፋት ያህል ይቀላል። ...” ራሴ ለራሴ የጠቀስኳት ስደት ያሳወቀኝ ጥቅስ ናት።

አንብታ ሲወጣላት ”ለምን ጠፋሽ?” አልኳት። የማወቅ፣ የመስማት ጉጉቴ እያቁነጠነጠኝ።

”ከኢትዮጵያ የወሰዱኝ ሰዎች ብዙ ቤተሰብ አላቸው። ዋናው ሰውዬ 4 ሚስቶች አሉት።ከእያንዳንዳቸው ከአራት በላይ ወልዷል። የእዛን ሁሉ አፈ ሰማይ ልብስ ማጠብ፣ መተኮስ ... ቤት ማጽዳት፣ የበሉበትን ማጠብ ... ብቻ ምን ልንገርህ? ፈጽሞ ሰው አንመስላቸውም። እረፍት ሊሰጡን አይፈልጉም። ምግብ በጣም ችግር አለ። ስድቡን፣ ቁጣውን፣ ዱላውን ካሰብክማ አይጣል ነው። ያለው ጎረምሳ፣ ህጻኑ ሁሉ ጎሸም ማድረግና የስሜታቸውን ጥያቄ በማዳመጥ እኛ ላይ ለመወጣት መሞከራቸው ይበልጥ ችግር የሆነው እሱ ነው። ሁሉ ውጥረት ማርገቢያ፣ ስሜታቸውን ማስከኛ፣ ችሎታ መለኪያ፣ መለማመጃ ... ሊያደርጉን ይፈልጋሉ። ሠውየው ራሱ 4 ሚስቶቹ አልበቃ ብለውት እኛንም ይከጅላል።” ምን ሊሰማት እንደሚችል እሷን ሆኖ ገፈቱን መቅመስ አስፈላጊ አይመስለኝም።

”ለዚህ ቢበቃ ፅሩ ነበር።ለጉንተላው፣ ዱላው..እሳቸው አያርፉም።” ሰናይትን አየት አርጋ ንግግሯን ገታችው።

”እሳቸው ማናቸው?” ስላልገባኝ ነው።

”እነሱ፣ እሷ፣ እሱ..ለማለት ነው የምትጠቀመው”

”አቤት!!! ... የሴት ልጅ ፈተና” ብላ በእንጥልጥል ተወችው። ውስጤም የሰማሁትን ”አቤት!!!! ... የሴት ልጅ ፈተና ...” ሲል ደገመልኝ። ልታወራኝ የፈለገችው ነገር እንዳለ ጠረጠርኩም፣ ገባኝም። ዝምታ ሲበዛ ”ታዲያ በዚህ ሰበብ ብቻ ጠፋችሁ?” አልኩ። ጥያቄዬን ቀለል ያደረኩት እንዲቀጥሉ ፈልጌ ነው።

”አዎና! ...” በማለት ጀመረች-ሰናይት። ”አዎና! ... እረፍት የለንም። ያላገቡት ወንዶች መለማመጃ ሊያደርጉን ይፈልጋሉ። ስሜታቸውን ሊወጡብን ጥድፊያቸው መከራ ነው። ያገቡትም ሊያርፉ አይፈልጉም። ቀን በስራ ማታ ገላችን በማርከስ፤ ጉልበታችን ደክሞ፣ ህሊናችን ደምቶ መኖር ሰለቸን።

ጠፋን።

ህጋዊ ሳይሆኑ መኖር ጥንቃቄ ይሻል። ከባድ ነው። ያዙኝ አልያዙኝ ብለን ተደብቀን መኖር ይሻላል ብለን ፓስፖርታችንን፣ የሰራንበትን ጥለን ጠፋን።”

”ወዲያው ሹርጣ ያዘን” መሀል የገባችው አልማዝ ነበረች።

”ሹርጣ ምንድን ነው?”

”በአረቢኛ ፖሊስ ማለት ነው።” ልብ በሉልኝ ምስክር ናችሁ በአረቢኛ የሰማሁት የመጀመሪያው ቃል ነው።

ሰናይት ቀጠለች። ”እስር ቤት ገባን። ወደ ሀገር ቤት ተላክን። ከለበስነው ልብስ ውጭ መቶ ዶላር ይዘናል። እኔ ደግሞ ባሌ ስራ ስለፈታ ነው ልጄን ጥዬ መሰደድ ግድ ያለኝ። አስብ ስድስት ወር ቆይተናል። ቤተሰብ ጋር ባዶ እጅ መግባት አሳፈረኝ። ስሄድ የተከሰከሰው ገንዝብ ቀላል አይደለም። የእሷ እሩቅ ጋር ዘመድ ተክለሀይማት አካባቢ ስናርፍ አንድ ሰው አገኘን። ጅጅጋ ካደረሰን በኋላ ጠፋብን። ስንመጣ ያየነውን ስቃይ አትጠይቀን። ሁሉም ያዩትን ስቃይ አይተናል። መንገድ ላይ የያዝነው ብር ስላለቀ መኪና እየለመንን የደረሰብንን ሁሉ በፀጋ ተቀብለን እዚህ ደርሰናል። … ” በሴትነታቸው ብዙ ነገር እንደደረሰባቸው ገመትኩ። የደበቁኝ ነገር እንዳለ ተረድቻለሁ።

”... ሁሉም ያዩትን ስቃይ አይተናል ...” የሚለው አባባል የገለጸውን ያህል ገልጾልኛል።

ጆሮዬ ደነዘ። ጥሩ ነገር መስማት ሳይናፍቀው አይቀርም። ግን ከየት ያምጣ። እዚህ ጋር ያልዘረዘርኩትን በርካታ ነገሮች ሰምቷል። እዛች እፍንፍን ያለች ቤት ውስጥ የመጠጡ ሽታ፣ ሺሻው፣ ሲጋራው፣ የእጣኑ ጭስ ... የሰዉ ትንፋሽ፣ የሰዉ ጠረን ... ተደማምሮ አቅለሸለሸኝ። ወጥቼ ወደባህሩ ዳር መሄድ አማረኝ።

ወጣሁ።

ሁሉ ነገር ህልም ቢሆን ተመኘሁ። ምኞቴ ምኞት ነበር። እውን የማይሆን ድኩም ምኞት። ውስጤን መጥፎ ከሚባል በላይ የመጨረሻ መጥፎ ስሜት ሰቅዞታል። አልቅስ ... አልቅስ ጩህ ... ጩህ ... የሚል ስሜት ይገዳደረኛል። ብጮህ ወደድኩ ምን ሆንክ ብሎ የሚከበኝን ሰው ምን ምክንያት እሰጣለሁ? ማልቀሱ ሳያዋጣ አይቀርም ላስነካው ዳዳሁ።

”ወንድ ልጅ ሲከፋው አለያም ሆድ ሲብሰው ነው የሚያለቅሰው ለምን ታለቅሳለህ?” ያሉኝ ጅጅጋ ድረስ አብረውኝ የመጡት ሴትዬ ትዝ አሉኝ። አሁን አሁን ቶሎ ቶሎ እንባዬ እየመጣ አስቸግሮኛል። በትክክልም ሆድ እየባሰኝ፣ እየከፋኝም ነው። ምን ደህና ነገር አየሁና ደስ ይበለኝ?” ዘመድ ሲሞት ማልቀስ የማይሆንልኝን ያህል አሁን አልቅስ አልቅስ ይለኛል። ሰው በቁሙ የሚሞትበትን የስደት ህይወት መላመድ እንደሚከብደኝ አስቤም ይሁን ብቻ ባየሁት ነገር ተከፍቻለሁ። ስለስደት ያለኝ ግምት ስህተት ሆኖ ነው ያገኘሁት። ስለስደት የነበረኝም መረጃ ስህተት ነበር። ያየሁት የሰዎች ስቃይ ብቻ ሳይሆን ለእኔስ ወደፊት ምን ይገጥመኝ ይሆን? የሚለውም ጭምር ነው ውሰጤ መጥፎ ስሜት ወልዶ አልቅስ ... አልቅስ የሚል ስሜት የፈጠረብኝ። ባለቅስስ ይወጣልኝ ይሆን?? እንጃ!!! ...

ከባህሩ ዳር ተቀምጨ ንፋሱ ሽው ... እያለ ውስጤ ሀሴትን ሊፈጥር ቢጥርም፣ ኮሚክ ነርቮቼን ነካክቶ ኮርኩሮ ሊያስፈነድቀኝ ቢጥርም ያየሁት፣ የሰማሁት ውስጤን አቁስሎ ምን ደስታ ይሰማኝ? ህይወት በዚህ በኩል አስለቅሳኝ በዚህ ልታስቀኝ ይዳዳታል። ሬት ሀሞቷን እየተጋትኩ ደስታ ለጊዜያዊ ሰከንድ ሊከራየኝ ወላ ሊጎበኘኝ አልቻለም። ውስጤ ትርምስምስ ያለ ስሜት አለ። ንፋሱ ”ሿ ... ሿ ... ሿ ...” እያለ አንለከባሎ ያመጣው የሲጋራ ወረቀት አጠገቤ ደረሰ። አየሁት ... ይየኝ አይየኝ አላውቅም።ግዳጁን የጨረሰ መስሎ አጠገቤ ቆመ። ”ትፈልገኛለህ?” የሚለኝ መሰለኝ። ውስጤ የሚተራመሰውን ሀሳብ ጻፈው ... ጻፈው አለኝ። አነሳሁት ... እስክርቢቶዬን ከደረት ኪሲ መዠረጥኩት እና የሲጋራ ወረቀቱ ላይ ደፈኩት። ውስጤ የሚተረማመሰውን የማልቀስ ፍላጎት እና አለመቻሌን ከተብኩት። እነሆ፦

ዋ!!!! ... አለማንባቴ

ከአይኔ እንባ አልቆ

ውስጤ እያነባ ከላይ ደርቆ

ዋ!!! አለማንባቴ

ዧ!!! ... አድርጌ አለማሳየቴ

ሰከን እንዲል ስሜቴ

ተቃጥሎ ሲግም አካሌ

ዋ!!! ... ማንባት አለመቻሌ

ማንባት ብችልማ አንብቼ

የውስጥ እሳቴን አጥፍቼ

እፎይ ባልኩ በእንባዬ

ከምታገል ተቃጥዬ

እንባ አዋጡልኝ ሙሾዬን ላውርደው

የተጎዳሁትን እኔ ነኝ የማውቀው

ቅኔ ደርድሩልኝ ስንኙንም ቋጥሩ

እኔ እኔን ጠላሁት ውስጤ በማረሩ

ደረቴን አልደቃ እንደሰው

ፊቴንም አልነጭ ላቆስለው

ወንድ አያለቅስም ብለው

አርሬ እንድሞት አድርገው

አሁን እንዴት ላንባ

ሲከፋኝ ሆዴ ሲባባ

ዋ!! ማንባት ብችልማ

ያሉትን ይበሉ ብልማ

ጥንድ ... ጥንዱን አንዠቅዥቄ

ህቅ!!! ባልኩ ተንሰቅስቄ

ሀዘኔ በወጣ በታወቀ ለሰው

አምቄ ከማልመሰምሰው

እርዱኝ … እርዱኝ እባካችሁ

ትርፍ እንባ ያለችሁ

አልቅሱልኝ ለእኔ አሮ ሞተ ብላችሁ

ይህም ሀሳቤን አልገለጸልኝም። ወንድ ሆኖ በ3 ወንዶች የተደፈረው ልጅ፣ እያየ ሚስቱን ሲደፍሩበት እጁን የሰበሩበት የወሎው ሲራጅ፣ እህል ካዩ ከረም ያሉት ወደ 50 የሚጠጉ ጫካ ውስጥ አስረው የዘረፏቸው ክስት፣ ጥውልግ ያሉ ልጆች። የበላነውን ትራፊ የበላው አንዱ … ሁሉም በሃሳቤ ተመላለሱ። ሁሉም ሰቅጣጭ ነው። የመጀመሪያ ቀን ውሎዬን በሀዘን አጣጣምኩት። በማግስቱ ጠዋት ሰለሞን ምግብ ቤት ውስጥ በሁለት ብረት ምጣድ እንጀራ ይጋገራል። አክንባሎ ተብዬውና ጋጋሪዋ እኩል ነው ላቦት የሚያንቆረቁሩት።

ቀኑ አልገፋ ያላቸው ስደተኞች ቁርስ በልተው ካርታ መጫወት ጀምረዋል። ሴቶቹ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያወራሉ። በምን እንደተደሰቱ አልገባኝም። ይቦርቃሉ፣ ያሽካካሉ ... ያሽቃብጣሉ። አብራቸው ያለች ጓደኛቸው በስደተኛው ዘንድ ጋሽ ሰለሞን የሚባለውን አሮጌ ጣሳ የመሰለ ሰውዬ ስላገባች መደሰታቸውን ሰማሁ። ያጥላላሁት ቀንቼ ይሆን እንዴ?

”ወንድሜ ይህን ባህር ከመሻገር አረፈች” አለኝ አንዱ አጠገቤ ያለ ዞር ብዬ አየሁት የፊቱን ቅርፅ ለመናገር ይከብዳል። ከእኔ የባሰ ቅርጸ ቢስ ነው። ፒንታጎን ይሁን ሄክሳጎን እንጃ ለማወቅ ካርታ ማስነሳት የሚያስፈልገኝ መሰለኝ። ትቼዋለሁ ወደ ወጋችን እንሂድ።

”ማነች? ምን አገኘችና ነው የማትሻገረው?” ስለማን እንደሚያወራ ግራ ገባኝ ”ከመሻገር የተረፈችበትስ ምክንያቷ ምንድን ነው?” ጥያቄ ደራረብኩ።

”ያቺ ... መካከል የተቀመጠችውን እኮ ነው ጋሽ ሰለሞን ያገባው።”

”… አገባ እንዴ? ገና ልጅ አይደለች ይሄን ሽማግሌ እንዴት ታገባለች? ባህር ከመሻገር አረፈች ያልከኝስ እሱን ስላገባች ነው?” ሀሳቡ ሁሉ እንደ ፊቱ ቅርጽ የተጥመለመለ መሰለኝ። እድሉን እንደ በቆሎ እሸት ግጦ ጨርሶ በሰው እድል የሚያንቋልጥ አድርጌ ሳልኩት። ለነገሩ ሁሉም ናቸው ”ታደለች” ያሉት። አስተያየቱ በጠላትኛ መሰለኝ እንዲያውም በሆዱ ሁሉ ”እናትን ልክዳ” ብሎ ሳይሰድበኝ አይቀርም። ትክክለኛ አባባሉን እንዳልባልግ ብዬ አላሰፈርኩትም። እርሶ ከፈለጉ ”ክ” የምትለዋን ፊደል በ”ብ” ቀይሯት ኦርጅናሉን ያገኛሉ። ቢቀርቦ ይሻላል። ለነገሩ የዘንድሮ ልጅ የመሀል ጣቱን ቀስሮ አፉን የሚፈታበት አፍ መፍቻ ስድቡ ነው።

”ቢሸመግል ከዚህ በፊት ያገባት ከዚህች ያነሰች ነበረች። ደግሞስ ያለውን ገንዘብ ቀላል አደረከው? ያሳዝናል ሁለት ሚስቶች ሁለት አመት ሳይሞላ ስለሞቱበት ሀዘን ጎዳው እንጂ ምን ይወጣለታል? ...”

”እንዴ! ... ምን ይወጣለታል ይለኛል እንዴ? ይሄ ሁሉ ሴት ከወጣለት አይበቃውም?” አወራሩ ለእኔም ሊድርልኝ ያሰበ ያስመስለዋል። አንድ ፍሬ ህጻን ነው ለማለት ሲዳዳው ተነስቼ ወጣሁ። ጅብሪል ሲፈልገኝ ተገናኘን።

”ስማኝ ጅብሪል እዚህ ሀገር ኤድስ እንዴት ነው?”

”ምነው አንዷን ደፋህባት እንዴ?”

”አይ ሰለሞን ሚስቶቹ እንዴት ተከታትለው ሞቱ?”

”አንተን ምን አሳሰበህ ከሆነስ እዚሁ ኮንደም ልትሸጥ አሰብ እንዴ?”

”በባህር መጪው ሁሉ በሽተኛ እንዳልሆነ አስብ” አባባሉ ትክክል ነበር። ሰነዓ ከገባሁ በኋላ የገጠመኝ ይሄው ነው። በባህር የመጣን ሁሉም በኤድስ የተለከፈ አድርገው ማየት የተለመደ ነው። እንደዛ ቢያዩም ጨረታው ግን የዋዛ አይደለም።ሽሚያ አለ ቦታው ስደርስ እመለስበታለሁ። በኤች አይ ቪ የሚረግፈው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ቀላል አይደለም።

”አስገድዶ መደፈር ባለበት በሽታ ይጠፋል ብለህ ነው? ሰለሞን ደግሞ ያገኘውን ቀሚስ ይለብሳል። ሁሉ ልኩ ነው። ታዲያ ኤድስ ቢይዝው ምን ይደንቃል። ይህችም ብትሞት ሌላ ያገባል። እሱን የሚያስቡት ገንዘብ እንዳለው ነው።” በዝምታ መንገድ ቀጠልን። ስንቶችን ለክፎ ይሆን? ስንቶችስ ለስንቶች አካፍለው ይሆን? አገኛለሁ ተብሎ ስደት ተወጥቶ ህይወት ሲታጣ ታሰበኝ። ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? ሁሉ ጋር ጥልቅ የሚለው ነገረኛው የስሜት ህዋሴ ሌላ ቢያጣ በዚህ ወጥሮ ያዘኝ።

በፊት የሰማሁት ብዙ ነገር አሁን ከሰማሁት ጋር ተደማምሮ ውስጤ የተፈጠረው ስሜት ወዴት ነው የምንጓዘው? እየለማን ነው እየጠፋን? ስደት የሚወጣው ሰላም ፍለጋ፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው። አብዛኛው እንደ እሳት እራት በመጥፊያው ዙሪያ ሲሽከረከር፤ መጥፊያው ላይ ሲርመጠመጥ ነው ያየሁት። በሀገር ላይ ለምኖ ማደር ያቃተ ይመስል ለመለመን መሰደድ እጅግ የሚያስከፋ ነው። ትንሽዮ ጥቅም ፣የእለት ጉርስ ታይቶ ህይወትን ያህል ነገር መገበር ያሳዝናል። ቦሳሶ ያየኋቸው ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ከዚህ ባልተለየ መልኩ ነው ያገኘኋቸው። ቋሚ ተሰላፊ ሆነው አመት ሁለት አመት በልመና የቆዩ፣ ጋሪ ይዘው ወደብ ላይ የሚራገፍ እቃ አመላልሰው ከቀን ቀለብ ያላለፈ ሳንቲም አግኝተው አቧራ ጠርገው አቧራ ለብሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው የሚተኙ አጋጥመውኛል። ለሶማሊያዊያኑ ተላልከው በልተው የተረፋቸውን የሚሰጧቸው፣ ገላቸውን ሸጠው የሚያድሩ ማየት ያማል ከሚለው በላይ ነው። የተሻለ ነገር አግኝተው ቢሆን ጥሩ ነበር። ተሰደው በዚህ ሁኔታ መኖራቸው ወርቅ ጥሎ ወደ ዛገ ቆርቆሮ መሮጥ መሰለኝ። የእለት ኑሮ መሸፈኛ ለማይገኝበት ኑሮ መሰደድ።

እንደፈራሁትም ሆኖ ሰለሞን የሚባለው ሰው ከዛች ሰውነቱ ላይ ቀንሶ አልቆ ለመሞት ሁለት አመት አልቆየም። አይ ያቺ ልጅ ባህር ከመሻገር አረፈች የተባለችው ምን ዋጣት ይሆን? መጀመሪያም ከሲታ ከመሆኑ በላይ ከስቶ ... ከስቶ ሞተ ሲሉኝ ከዛ በላይ ምን አክሎ ይሆን? ስንት ሰው በክሎ ይሆን? ይህ እንደ አስተማሪ ጥያቄ መጠየቅ የማይሰለቸው የስሜት ህዋሴ ጥያቄ ያግተለትል ጀመር። መልሱ ግን መብሰክሰክ ብቻ ነው።

ብዙ ... ብዙ ስቆቃ ካየሁበት እና ለ5 ቀናት ብቻ ከቆየሁበት ቦሳሶ የወደብ ከተማ ለቅቄ ልወጣ ነው። ለጀልባ መሳፈሪያ ክፈል የተባልትን የኢትዮጵያ ሶስት መቶ ብር ከፍዬ ከከተማ ወጥቶ የሚገኘው መሳፈሪያ ቦታ ሊወስዱን የጭነት መኪና አቀረቡ።ሰናይትን የሚጎድልሽን ብር እሞላልሻለሁ እንጂ እዚህ ይህንን ህይወት ብለሽ አትቆይም ብያት ተዘጋጅታለች። አጋጣሚ ሆኖ ጓደኛዋ ከሳዑዲ አረቢያ ገንዘብ ተላከላትና እኔም ሳልሞላላቸው ለጉዞ ተዘጋጁ።

ደስ የሚል ነገር ያሳየኝን አምላክ አመሰግነዋለሁ። የጨርቆስዋ ሰናይት በጓደኛዋ ፍሬህይወት በላይ ፌስቡክ መስመር አሁን ያለችው ኢትዮጵያ መሆኑን ገልጻልኛለች።ተመስጌን አምላኬ!!! ውስጤ ደስታ አሁን ገና ሰነቀ። አንድ ሰውስ ከተረፈ ደስ አይልም? እኔ ይህንንም ጽሁፍ የምጽፈው በመጽሐፍ መልክ እስካወጣው ድረስ መንገድ ካሰቡ ሰዎች አንዱ አግኝቶ ህይወቱ ከተረፈ ብዬ አይደል?

በቀጣይ ክፍል 5 ምናቦትን ያበድሩኝ እና እርሶ በሀሳቦ እኔ ገፈቱን ያጣጣምኩትን ጉዞ በትዝታ ሰቅጣጩን የባህር ጉዞ እንጓዛለን። በቀጠሮ እንገናኝ።

ቸር እንሰንብት!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ