Obang, Photo: Abbay Mediaልጅ ተክሌ - ከካናዳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የታክሲ ነጂው መገረም፤ ኢትዮጵያዊ የማይመስል ኢትዮጵያዊ

አበዛኸው እንዳትሉኝ። ይሄ መነገር ያለበት ታሪክ፤ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ልናውቀው የሚገባ ክስተት ስለሆነና አላደርስ ስላለኝ ነው ተመልሼ የመጣሁት። የዛሬ አራት አመት አካባቢ አንድ ጥቁር ያለ (“ቁ” ይጠብቃል) “ኢትዮጵያዊ የማይመስል” ኢትዮጵያዊ፤ ሌላ ኢትዮጵያዊ የሚመስል ኢትዮጵያዊ በሚያሽከረክረው ታክሲ ከአንዱ የዋሽንግተን ዲ.ሲ. አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መሀል ከተማ ይጓዛል። መሰለኝ። በእንግሊዘኛ ንግግር ጀመሩ።

 

“ከየት ነህ?” ታክሲ ነጂው ጠየቀ። “እስኪ ገምት ከየት እንደሆንኩ።” መለሰ ተሳፋሪው። “ከሱዳን?”። “አይደለሁም።” “ከኬንያ?” “ተሳስተሀል። ሞክር።” “ከጅቡቲ፤ ከኤርትራ፤ ከዩጋንዳ።” ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ተጠርተው አለቁ። ተሳፋሪው ተስፋ አልቆረጠም ምርጫ ሰጠው ለሹፌሩ፤ እንዲህ ሲል ሀ- ከኢትዮጵያ ለ- ከኤርትራ ሐ- ከሶማሊያ መ- ሁሉም መልስ አይደለም የሹፌሩ መልስ መ- ነበር ሁሉም መልስ አይደለም ኢትዮጵያ ከቶም አልታሰበችምም። ያ “ኢትዮጵያዊ የማይመስለው” ኢትዮጵያዊ ግን ከኢትዮጵያ ነበር። የታክሲው ሹፌር ያ ያሳፈረው (የጫነው) ጥቁር ሰው እንኩዋንስ መጀመሪያውኑ ከኢትዮጵያ መሆኑን ሊገምት፤ ቀድሞውንም ነገር ከኢትዮጵያ ነኝ ካለው በኋላ ሊያምን አልቻለም። እንዲህ አለ ኦባንግ “ጨርሶውንም ኢትዮጵያዊ እንደማልመስል የዋሁ ኢትዮጵያዊ በየዋህነት ኢትዮጵያዊ ልሆን እንደማልችልም ነገረኝ።” ኦባንግ ፖለቲካዊ ንዝረት ተሰማው። አልተቀየመም። ግን ደግሞ ይህ ነገር አልተዋጠለትም። ችግራችን ከመንድርም ባሻገር የአገር እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህም ያ የአኝዋክን ብቻ ጉዳይ ሙጭጭ አድርጎ ይዞ የነበረው ኦባንግ የጉዞውን አድማስ ከአኝዋክ ሰማይም በላይ ካላሰፋውና ሌሎች እንደዚያ ታክሲ ነጂ ያሉትን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መድረስ ካልቻለ፤ ባንድ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ግን እንደማይተዋወቁ ያንድ እናት ያንድ አባት ልጆች ልንሆን ነው ብሎ አጀንዳውን አሰፋው። እነሆ ያኔ መገስገስ የጀመረው የኦባንግ የትግል ባቡር፤ ዛሬ ከሜኒሶታ እስከ ለንደን፣ ከዲሲ እስከሲያትል፣ ከአኝዋክ እስከ ባህርዳር፣ ከአምቦ እስከ ሀረር፣ ከኦጋዴን እስከ ጋምቤላ፣ ከቶሮንቶ እስከ ሳስኬችዋን እየገሰገሰ ነው። የሚያጅበው ካለ ይከተለው። የማይከተለውም ይከተለው። ሰሞኑንም ኦባንግ ሲበር ነበር። ማስረጃ ሲያጠናቅር፤ ማስረጃም ሲያቀብል፤ ለኢትዮጵያ ከቆሙና ገንዘብ ከማይጠይቁ ጠበቆች ሲመክር ሲሰለፍ ሲያሰልፍም ነበር። ስለኦባንግ ዓላማ ወርቃማነት እኔ ብቻ አይደለሁም፡ አልም መስክሯል፤ አለማየሁ፤ ፕሮፌሰር።

 

ፕሮፌሰር አለማየሁን ሰጠን

 

“ክፋት በላያችን እንዲሰለጥን የሚያስችለው የኛ የሴቶቹና የወንዶቹ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ ነው” ይላል የፕሮፌሰር አለማየሁ የዘወትር ኢሜል ማሳረጊያ። ባለፈው ሰሞን በጻፈው፡ “ጎበዝ እንግዲህስ መለያየት ይቅር፤ ልባችንንና አእምሮአችንን ከፍተን ተጨባብጠን ወደ ስራ እንግባ” በሚለው ጽሁፉ የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የያዛቸውን መርሆችና ዋና ዋና እምነቶች ደግፎ መጻፉ እጅግ አስደስቶናል ይላላ የጋራ ንቅናቄው ያወጣውና አቶ ኦባንግ አሳምሮ ያቀረበው ጽሁፍ። የሲያትሉ ወዳጃችን አቶ ሼክስፒር ፈይሳ ባለፈው ዓመት ሲያትል ንግግር ሊያደርግ የመጣውን ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያምን ሲያስተዋውቀው እንዲህ ብሎ ነበር። “ብዙ ሰዎች ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ምንና ማን እንደሆነ ብዙ ነገር ሲናገሩ ይደመጣል። እኔ ግን ምን እንዳልሆነ ነው የምነግራችሁ።” ሼክስፒር ቀጠለ፤ “ፕሮፌሰር አለማየሁ በቀን ውስጥ ከሀያ አራት ሰአት በላይ አለው ይላሉ። ነገር ግን ያ ሀሰት ነው። ልክ እንደኛ እሱም በቀን ውስጥ ሀያ አራት ሰአት ብቻ ነው ያለው። በነዚያ ሰኣታት ውስጥ ነው የሚሰራውን ሁሉ የሚሰራው።” ይሄ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም እንደጉድ ይጽፋል። አይሰለቸውም። እኛ ብንጣላ፣ ብንባላ፣ ብንቃላ፣ ተስፋ አይቆርጥብንም። እነሆ ባለፈው ሰሞን በጻፈው አብይ ትንታኔም እንግዲህስ የርስ በርስ ንትርካችንን ትተን ወደስራ እንግባ አለ። በዚያ አላቆመም። ይሄ በዚህ በመከራችንና ብዙ አዋቂዎች ኮርተው ወይም አኩርፈው ጥግ ይዘው በተቀመጡበት ሰአት ከጎናችን የቆመ ታላቅ ፕሮፌሰር፤ እነዚያ የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የንቅናቄያችን ምሰሶዎች ብሎ የሚላቸውን ሁለት አብይ መርሆች ማጽደቁ ኦባንግን ጨምሮ መላውን “የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ” በደስታ እንዲዘል አድርጎታል።

 

በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ለማምጣት የምናደርገው ትግል ልዩነቶቻችንን አሁን የምናጎላበት ሳይሆን ለሌላ ዘመን ለሌላ ግዜ የምናስቀምጥበትና በግልጽ ለእውነተኛ ለውጥ የምንተጋበት አዲስ አቀራረብና ስልት ይሻል። ፕሮፌሰር ቀጠለም፤ ትግላችንን የሚቃኙት ዋናዎቹ ርእዮታችን በሁለት መሰረታዊ ፍልስፍናዎች ላይ መሰረት መጣል አለባቸውም አለ። ይሄንን እንዳሻችሁ ትተርጉሙት ዘንድ በእንግሊዘኛው እንዳለ ብናስቀምጠው ይሻላል። 1) Our humanity must always rise above our ethnicity, nationality, religiosity, Africanity or Ethiopianity. 2) No one can be truly free in Ethiopia unless ALL Ethiopians are free. If we subscribe to these two core principles, open our minds and hearts and collectively pull together, we will soon find ourselves in a win-win situation. አንደኛ ነገር ሰብአዊነታችን ወይንም ሰው መሆናችን ከጎሳችን፣ ከብሄራችን፣ ከዘራችን ከሀይማኖታችን ከአፍሪካዊነታችን ይቅደም። ሁለተኛ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም አብረን ነጻ ካልወጣን ማንም እውነተኛ አርነት አይወጣም። ኢትዮጵያ ነጻ አልወጣችምና የትግራይ ነጻነት ግንባር አርነት ብሎ ይነሳ እንጂ ያ የተነሳበትን አርነት ገና ህዝቡ አልደረሰበትም ነው። ነገም የእገሌ ነጻ አውጪ፤ የእንቶኔ ነጻነት ግንባር ብለን ብንነሳ ኢትዮጵያ ነጻ እስካልወጣች ድረስ እውነተኛ የእገሌ ፣የእንቶኔ ነጻነት አይኖርም። ሁላችንም ባርነት ውስጥ ነን አይነት ነገር። ለነዚህ ሁለት መሰረታዊ መርሆች የተገዛን እለት ነው ሁላችንም አሸናፊ የምንሆነውና ተሸናፊ የማይኖረው። የናፈቀንም አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት የምናሸንፈው ዋናውን ጠላት ድንቁርናና አምባገነንነትን ብቻ የሆነበት አገር/አለም ማግኘት ነው። ያንን ደግሞ ኦባንግ እንደመጥምቁ ዮሃንስ በዚህ በኛ የመለያየት በረሀ ይሰብካል።

 

የጋራ ቀንበር፣ የጋራ መከራ፤ ስለቃላችንና ተግባራችን መገጣጠም አስፈላጊነት

 

አንዱ ላንዱ የሚቆምበትና በጋራ የምናሸንፈበት መድረክ ስላስፈለገ ነው ይሄ የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የተጸነሰው የተወለደውም። የአኝዋክ የሀዘን ድንኳን በተጣለ ግዜ ኦባንግ አኝዋኩ ከጥቂቶች ጋር ተሰለፈ። የኦሮሞ ተወላጆችም በተገደሉ ግዜ ኦሮሞው ለብቻው ተሰለፈ። ሌላውም እንደዚያው ቀጠለ። ስለዚህም ያ የዋህ ታክሲ ነጂው በየዋህነት ኢትዮጵያዊ እንደማይመስልና ሊሆንም እንደማይችል የነገረው ኦባንግ ችግራችን ስር የሰደደ ከላይ ከምናስተውለውም በላይ የጠለቀ እንደሆነ ተሰማው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ መድረስ ካልቻለ እሱ ብቻውን የሚጓዘው ጉዞ እሱንም ይሁን አኝዋክን እንዲሁም ታክሲ ነጂውን ኢትዮጵያዊ ከአውደ ነጻነት እንደማያደርሳቸው ተረዳ። ሁላችንም በጋራ የምንሰበሰብበት መድረክ እንደሚያስፈልግ አመነ። መልኩ እኛን የማይመስል ቋንቋውም ከኛ የተለየም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ መሆን የሚችልበት የጋራ መድረክ እንደሚያስፈልግ አመነ። የሚያምኑትም ሁሉ ተሰባሰቡ። እነሆ የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተወለደ። ያ ንቅናቄ የተመሰረተባቸውን መርሆች ነው ፕሮፌሰር አለማየሁ በብእሩ ይሁን፣ ይደረግ፣ ይደልወ ይደልዎ ያለው።

 

አልዋሻችሁም ከኦባንግ ጋር አልፎ አልፎ በስልክ እንጫወታለን። ስለኢትዮጵያ ያለውን ራእይ ሲነግረኝ፣ ሰለኢትዮጵያ የሚያልመውን ሲተርክልኝ፣ ስለአገሩ የሚጸልየውን ጸሎት ሲደግምልኝ ስሰማው ብውል አልጠግብም። ተንኮል የለውም። ክፋትም የለውም። ስለድርጅቶች ክፉ አይናገርም። ይሄ እኛ ጋር የከረውና ያነፈረን፤ ቆዳችንን ያደነደነው የርስ በርስ ሽኩቻ እሱ ጋር የለም። ኦባንግ ኦባንግ ነው። እነሆ በዚህ በወርኀ ሰኔ ከሀያ ቀን ጉዞው ተመልሶ መጣ። ዘገባውን ሰጠን። ኦባንግን ለማድነቅ የግድ ከሌሎች ፖለቲካ መሪዎች ጋር ማወዳደር የለብኝም። ግን ዘወትር የሚያስደንቀኝ ተፈጥሮ አለው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ሪፖረታቸውን በስንት መከራ በስንት ጉትጎታ ነው የሚያቀርቡት። ለዚያውም ካላቸው ነው። ኦባንግ ግን በየሳምንቱ ወይም እያሰለሰ የሚለውና የሚናገረው አያጣም። ዘወትር የኦባንግን ኤሜል ስናነብ፡ ከመጨረሻ ላይ እንዲህ ይላል። “ብዛት የማሸነፍ ወይም ለማሸነፍ ወሳኝ አይደለም፤ ይልቅስ በህዝብ ህሊና ውስጥ ሰደድ እሳት ለመለኮስ የሚተጉ የማይደክማቸውና የተቆጡ ጥቂቶች እንጂ።" It does not require a majority to prevail, but rather an irate, tireless minority keen to set bush fires in people's minds" by Samuel Adams። እነሆ ያለውን የሚናገረውን የሚሆንና የሚያደርግ ኦባንግ ነው። ጥቂት ደጋፊዎች ይዞ ስራውን እየሰራ ነው።

 

ኦባንግን እናፍጋው፤ ምክንያቱም ኦባንግ ራሱን ሰጥቷላ

 

ከዚህ በፊት ስለኦባንግ ተጽፎ ነበር። http://www.ecadforum.com/files/Editorial_About_Obang.pdf የኦባንግ ዓላማና መርህ እዚያ ላይ ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል። ኦባንግ “ሰብአዊ ብሄርተኝነትን” ያራምዳል። ኦባንግ ብዙ ፖለቲካዊ ሀረጎችን ተክሏል። “መንደር ወይስ አገር?” ይላል። “Humanity before ethnicity” የሚለው ነገርም አለው። ሽናሻነት፣ ከፊቾነት፣ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ አኙዋክነት ከዚያ ለጥቆ የሚመጣ ነው። ኦባንግ ኢትዮጵያዊያን ሲል ማንም በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚኖርን ሰው ነው። ሰውነት፡ ይላል ኦባንግ “is a great unifier that God gave to us when He created us—all of humankind—in His image, making us all of equal value, regardless of the superficial differences between us.” ኦባንግ ዜና አንብቦ ብቻ ቤቱ የሚቀመጥ ሰው አይደለም። ሰው ተገደለ፡ ሰዎችም ተጨፈጨፉ ሲባል ሰምቶ ቤቶ ገብቶ አማን የሚያድር ሰው አይደለም። ዜናውን ተከትሎ እርምጃም ይወስዳል። በቅርቡ በጻፈልኝ ኢ-ሜይል ላይ እንዲህ አለኝ፡ “I strongly believe that the killing, suffering, corruption, human rights abuses and the killing in Ethiopia must stop.” “ተክሌ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ግድያ፣ ስቃይ፣ ሰብአዊ መብት ገፈፋ፣ ሙስና መቆም አለበት።” ለዚህም ነው በዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኦባንግ በወዳጆቹ ረዳትነት ከዋሽንግተን ኦታዋ፤ ከቶሮንቶ ዳላስ ተንቀሳቅሶ በአወሳ፣ በቴፒ፣ በአኝዋክ፣ በኦጋዴን፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል፣ በአምቦ፣ በጅማ፣ በአዲስ አበባ፣ በቦረና በሌሎችም ቦታዎች የተፈጸሙ የዘር ማጥፋትን በሺሆች የሚቆጠሩ ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለጄኖሳይድ ዋች ፕሬዚዳንትና ይሄንን ጉዳይ በነጻ ለያዙት አራት አለም አቀፍ ጠበቆች አስተላልፏል። ማስረጃ የማሰባሰቡ ስራም ይቀጥላል ብሏል። ኦባንግ የካናዳና የአሜሪካ መንግስታትንም መጎትጎቱን ቀጥሏል። ኦባንግ እዚህ www.solidaritymovement.org ይገኛል። የኔ ሀሳብ እንግዲህ እንዲህ እንደሚከተለው ነው። ትግላችን ግቡን የማይመታበት አንዱ ምክንያት “የሙሉ ጊዜ ጠላትን በትርፍ ጊዜ ስለምንዋጋ ነው።” እንደ ኦባንግ ያለ ሰው ግን የኢትዮጵያን ጉዳይ የትርፍ ጊዜው ስራ አላደረገውም። የሙሉ ጊዜ ጉዳዩ ነው። ይሄ ግን አይቀጥልም። ኦባንግ የኛን እጅ ይፈልጋል። ይሄንን ኦባንግ አላለኝም። ግን ባይለኝም አውቀዋለሁ። ኦባንግ የረዱትንና ጉዞውን የሸፈኑለትን ሁሉ አመስግኗል። ኦባንግ ራሱን ከሰጠ እኛ ደግሞ ከራሳችን መለስ ያለንን ልንሰጥ ግድ ይሏል። ተራ ገብተን በወረፋ ኦባንግን ማፍጋት አለብን። ኪሳችንን ይጭነቀው እንጂ። እንደኦባንግ ያለ ማንም የለም አልልም። ግን እንደኦባንግ ያለ ማንም አይታየኝም።


 

ልጅ ተክሌ - ከካናዳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ