ማነህ ባለ ሣምንት? (ልዑልሰገድ)
ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ወያኔ ሥልጣን በያዘባቸው አፍላ ዓመታት በበረሃ እያለ “ነፃ አውጭ ነኝ”፣ “ከደርግ ቀንበር ነፃ ላወጣችሁ እየመጣሁ ነው” ማለቱን ረስቶ ራሱን በደርግ ወንበር ላይ አደላደለ። ይሄኔ ነው ህዝቡ የውስጥ ብሶቱን ለመተንፈስ …
“ደርጉ ማረኝ ማረኝ
የወያኔስ ነገር ምንም አላማረኝ”
ያለው። አለመታደል ሆኖ አፄ ኃይለሥላሴ በደርግ ከተተኩም በኋላ የዚሁ ስንኝ ተመሳሳይ ውስጥ ውስጡን ተዚሞ ነበር ይባላል። ህዝቡ የባሰ ገጥሞት ምርጫ ሲያጣ ለጠላው ሥርዓት ሙገሳ እንደቀጣው ያሳያል። ብሔራዊ ጭንቀት የሚፈጥራቸው እነዚህን መሳይ ስንኞች ተበራክተዋል።
ደርግ ለምን ከአፄ ኃይለሥላሴ ስህተት እንዳልተማረ ወይም ወያኔ ለምን የደርግን ስህተቶችንና ሌላ ተጨማሪ ስህተቶች እንደሚሠራ ብዙዎቻችንን ግራ ያጋባል። ሰሞኑን ወያኔ ከተላላኪዎቹ አንዱ በሆነው “ብአዴን” የተሰኘ ክርስትና ስም የሰጠውን ድርጅት የተወሰኑ አባላት ላይ የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል። ከወያኔ ያለፉት የመከራና የመግፋታችን ዓመታት ልምድ በመነሳት የጥቃት ዒላማዎቹ ወንጀል ገብቶናል። ወያኔን ለሚያውቅ ለዚህ ብዙ ጠንቋይ መቀለብ ወይም መሆን ላይጠበቅበት ይችላል። እነዚህ ጥቂት ታጋዮች ችለው ተረግጠው ተረግጠው በአገኙዋት ጥቂት አጋጣሚ “በቃን! እስከመቼ የወያኔ አሽከር እንሆናለን? የታገልነው ህዝባችንን ጭሰኛ ለማድረግ አይደለም! …” እና ሌሎችም የአስተዳደር ችግሮችን ሲጠቃቅሱ የነበሩ ይሆናሉ። ስለ ብሔራዊ ሀገር መጨነቅ፣ ስለ አድልዎና የወያኔ የበላይነት ማውራት ለወያኔ አለቆች “በፈንጂ ወረዳ መረማመድ” የተሰኘ ዕብሪት ነው።
ሰሞኑን የወያኔ ዘመቻ ፀረ- አማራና ጥቂት የብአዴን አባላት ላይ ማነጣጠር ብዙም አያስደንቅም። በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ድርጊት “ኦህዴድ” በሚል ስም በሚጠራው የኦሮሞን ህዝብ ለመግዛት የተፈጠረው የወያኔ አሻንጉሊት ድርጅት ውስጥ የተፈጠረውም ተመሳሳይ ባህሪ አለው። የተወሰኑ የኦህዴድ አባላት አዳዲስ ስም እየተሰጣቸው ተባረሩ፣ ተሰደዱ፣ አንዳንዶችም የደረሱበት አልታወቀም። ወንጀላቸው የኦሮሞን ህዝብ የወያኔ ጭሰኛ ለማድረግ የተሰጣቸውን ግዴታ በመተው ህዝቡ ተበደለ፣ ፍትህ ተጓደለ የሚሉ አንዳንዴም ምነው ሁሉም ነገር ለወያኔ አይነት ጥያቄ ስላነሱ ነው። በተወሰነ ደረጃ አቶ መለስ ከአራት ኪሎ በሪሞት ኮንትሮል መመሪያ በሚሰጧቸው በኢህአዲግ ስር ባሉና “አጋር” በተሰኙ ታዛዥ ድርጅቶች የተከሰተ ነው።
የወያኔ የግፍና የአፈና ድርጊት ወያኔ እስካለ ድረስ ይቀጥላል። ለዚህ የሚደነቅ ያለ አይመስለኝም። የህዝብን ልብ የሚሰብረውና በደርግና በወያኔም የተደገመው ክፉ ደዌ ግን ተጠናክሮ መቀጠል ነው። ይሄ ክፉ ደዌ አንዱ አንዱን አሳልፎ ለመስጠት በባንዳነት መሰለፍ ነው። ይሔ በተቃዋሚውም ይሁን ሥልጣን ላይ ባሉት የተከሰተ ነው።
ወያኔ አሥራ ስምንት ዓመት የገዛው በመሣሪያ ኃይሉ ብቻ አይደለም። ለወያኔ ኃይል የሰጠው ለሆዱ አዳሪው የገዛ ወገኑን የሚያስበላውና የሚያሳድደው ነው። አበው ጽዋ ሲጠጡ የቀጣዩን ፅዋ አውጭ ተራ ለማብሰር “ማነህ ባለ ሣምንት?” ይላሉ። የሣምንቱ ተረኛ “አቤት!” ብሎ ይነሳል። ዛሬም ሆነ ትላንት አንዱ አንዱን አሳልፎ ሲሰጥ የሣምንት ተረኛነቱን አውቆ “አቤት!” ሲል አይታይም። ከትናንት እስከዛሬ ባለው ሕይወታችን የምናስተውለው ይሔንኑ ነው።
ወያኔ በጠባብነት ልክፍት የተያዘ በሥልጣኑ የሀገሪቱን የሥራ ቋንቋ ገሸሽ አድርጎ የሠራዊቱን፣ የደህንነቱንና የፌደራል ፖሊስን ቋንቋ ትግርኛ አድርጓል። በእነዚህ የአፈና ተቋማት የራዲዮ ግንኙነቱና፣ የበላይ መመሪያ ከዚያም አልፎ ጥብቅ ምስጢር የሚተላለፈው በትግርኛ ብቻ ነው። ይሔን ለምን ብለው የሚጠይቁ ጥቂት አንበሶችን ከወያኔ በላይ ለወያኔ ታማኝነታቸውን ለማሳየት የገዛ ወንድማቸው ላይ ምሳር የሚያነሱት ብዙዎቹ በቀጥታ የህወሓት ተላላኪ የሆኑ ሆዳሞች ናቸው።
ዶ/ር ነጋሶ ከዓመታት በፊት በአቶ መለስ የሚደረግባቸው ተፅዕኖ ሲበዛባቸው፣ ቆሜለታለሁ የሚሉት የኦሮሞ ህዝብ ወኪል አለመሆናቸው ሲገባቸው በቁጣ “መለስ መንግሥቱን መሰልከኝ” አሉ። በወቅቱ የነበረውን ግምገማ ረግጠው ሲወጡ ከወያኔ በላይ የደነገጡት፣ ለምን ወያኔ ተነካ ብለው የተሳደቡት፣ አካኪ ዘራፍ ያሉት ብዙዎቹ የኦህዴድ ቱባ ባለሥልጣናት ናቸው። “ማነህ ባለሣምንት?” መባሉ አልቀረምና ዶ/ር ነጋሶን ከተሳደቡት መካከል በጊዜው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አልማዝ መኮ ይታወሳሉ። የወ/ሮ አልማዝ ሰልፍ ዛሬ በተቃራኒው በፀረ-ወያኔነት ቢሆንም በጊዜው ባለሣምንት መሆቸው የገባቸው አይመስሉም። በወቅቱ የወ/ሮ አልማዝን ሥልጣን የተረከቡትና ዛሬም የወያኔ ፈረስ ሆነው ከሚጋለቡት የኦህዲድ ባለሥልጣን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ይገኙበታል።
ዛሬ ወያኔ የብአዴንን ፍጹም አሽከርነቱን የተቃወሙ ያላቸውን በመመንጠር ከወያኔ ጎን የቆሙት ምናልባት የነገዎቹ ባለተራዎች ናቸው። እነኝህን የመሰሉ ሆድ አደሮች ለወያኔ ጉልበት የሆኑ ገዳይና አስገዳዮች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።
ለዚህ ሌላ ጥቂት አብነቶች ላንሳ። ጊዜው አቶ ተፈራ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩበት ወቅት ነው። አቶ መለስ ብዙዎችን የወያኔ አባላት ድንገት በዝርፊያና በማጭበርበር የታቀፉትን ብር ወደ ንግድ እንዲያስገቡ ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው። ለዚህ ደግሞ የመነገጃ ቦታ ይጠባል። ወያኔ ነባሩን የንግድ ማኅበረሰብ ከቦታው ለማፈናቀል የዘየደው ከፍተኛ የቦታ ኪራይና የታክስ መጠን ጭኖ ማደህየት ነበር። እነ አቶ ተፈራና አቶ መለስ ባልታረመ አንደበታቸው ህዝቡን ሲተፉበት፣ ሲያፈናቅሉት፣ ሲዘርፉትና ሲያስሩት ከረሙ።
የንግዱ ኅብረተሰብ በጋራ ተሰብስበን አቤት ማለት አለብን ይልና አንድ ሠላማዊ ሰልፍ ይጠራል። በወቅቱ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለዘገባ በስፍራው ስለነበር ከሰልፈኛው ጋር ተቀላቅሎ አልፎ አልፎ ከተሳታፊዎቹ ያናግራል።
ከመስቀል አደባባይ የተነሳው ሰልፍ መጨረሻው የአቶ መለስ ጽ/ቤት እንዲሆን የተወሰነ ነው። ከሰልፈኞቹ መካከል ጥቂቶች በጊዜው አምስት ዓመት የሆነውን ወያኔን እና የ17ቱን ዓመት የደርግ አገዛዝ ደማምረው የ22 ዓመት ግፍ በቃን የሚል መራር ቃል በመፈክር መልክ በየመሃሉ ያሰማሉ። ከፊት ያለው ሰልፈኛ መፈክር ሌላ ነው። በዚህ ጊዜ ከተሰላፊዎቹ መካከል ጥቂቶቹ “ፖሊስ ፖሊስ” እያሉ መጮህ ጀመሩ። በዚህ ወቅት ያ ግዙፍ ሰልፈኛ አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል አካባቢ ደርሷል። ፓሊስ የጠሩት በአንድ ላይ ለምሬት ወጣን ያሉት ነበሩ። ምክንያታቸው ሊረብሹን ነው የሚል ነበር። በየምዕራፉ ከሰልፈኛው መካከል ጥቂቶች እየተለቀሙ ለፖሊስ ተሰጡ። አቶ መለስ ቢሮ ፊት ለፊት ተደረሰ። ያ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ሰልፈኛ ፀሐይ እየተንቃቃ መልዕክቱን የሚቀበለው ይጠፋል። ከብዙ መጉላላት በኋላ ሦስት የሚሆኑ መልዕክተኞች ወደ ውስጥ እንዲገቡ ተፈቅዶ በተሰጠው መልስ የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ተባለና ተበተነ።
በጊዜውም ሆነ ዛሬ የወያኔ ጉልበት ጠመንጃ ወይም ሌላ ተዓምር ሳይሆን፤ “ነግ በኔ”ን የማያውቁ ወንድማቸውን አሳልፈው በመስጠት የወያኔ አሽከር የሆኑ ከያአንዳንዱ ዘውግ የወጡ ወገን ገዳዮች ስላሉ ነው።
ከሰሞኑ የወያኔ እርስ በርሱ የተምታታ የፈጠራ ክስ በኋላ ዘመቻ ፀረ-አማራን አጠናክረው የተቀላቀሉት የብዙዎቹ ታሳሪዎች የትግል አጋር ነበርን ባዮች ናቸው። ይሄ ትናንት በደቡብ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ክልልና በጋምቤላ የታየ ነገር ነው።
በደርግ ዘመንም የአብዮቱ ሰይፍ እነሱን የማይነካ የመሰላቸው የገዛ ጓዶቻቸውን እያስበሉ ኃላ ተመልሰው የተበሉ ሞልተዋል። ‘አብዮት ልጇን ትበላለች’ ተብሎላቸው ራሳቸውን አርክሰው አልፈዋል። አንዳንዶች በቆራጥነት ደርግ ከሰጣቸው ሹመትና ሽልማት በላይ የህዝብ እምነት አስበልጠው በደርግ መሃከል ደርግ መንገዱን እንዲያስተካክል ስለመከሩ በሰይፍ ተበልተዋል። በእነዚህ ላይ ደርግ “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ብሎ ዘብቶባቸዋል።
ዛሬም አቶ መለስ ባቃዣቸው ቁጥር ወንድምህን አርደህ አምጣ የሚሏቸው ሆዳም ብአዴኖች፣ ኦህዴዶች፣ ሶህዴፓዎች፣ የቤንሻንጉል ህብረቶች፣ ደኢህዴጎች፣ የጋምቤላ ህዝብ የሚሰኙ አሻንጉሊት ድርጅቶች መካከል አባላት አላጡም። ያለእነዚህ ሆድ አደሮችና ‘ነግ በኔ’ የማይሉ ባለተራዎች ተባባሪነት ወያኔ ከትላንት እስከዛሬ በንጹኀን ደም ላይ እየተረማመደ አልመጣም።
አንዳንዶች ቆመው ለማሰቢያ ዛሬም የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ሆነው ዕድል አላቸው። ትናንት አብረው የገደሉና ያስገደሉ፣ የግፍ በትሩ አይነካኝም ብለው ሩቅ መስሏቸው የነበሩ ከወያኔ የዘረኝነት በትር አላመለጡም።
ሒትለር በማጎሪያ ጣቢያዎች አጉሮ አይሁዶችን በመርዝ ጋዝ ከፈጃቸው በኋላ ሬሳቸውን ለማቃጠል በአገልጋይነት የመረጣቸው “ሶንዶር ኮማንዶ” የተሰኙ አይሁዳውያን ነበሩ። ያንን የግፍ ታሪክ ያነበቡ ሁሉ እንደማይረሱት እነዚያ ያለፍላጎታቸው የገዛ ወገናቸውን እሳት የሚማግዱ ሶንዶር ኮማንዶዎች በአዳዲሶቹ ሶንዶር ኮማንዶዎች ይማገዱ ነበር።
ዘረኞች ዛሬም የገዛ ወገናቸውን አስገድደው ወይም በጥቅምና በጊዜያዊ የሥልጣን ፍርፋሪ ደልለው ለግድያ የሚሰማሩ የወያኔ ሆዳም ሶንዶር ኮማንዶዎች አሉ። ለእነዚህና እነዚህን ለመሰሉ ወገኖች ልናስታውሳቸው የሚገባው ሐቅ አንድ ነው፤ ትናንት ወንድማቸውን ያስገደሉ መጨረሻቸው ያው ነበር።
ወያኔን ተባብረን ካላስወገድነው በቀር ዛሬ በሌሎች ላይ ብቻ የሚበቃ የመሰለን መከራ መቆሚያ የለውም። ስለዚህም የሰሞኑን የወያኔ አፈና ተመልክተን “አንተ ደግሞ ማነህ እጅህን አጣጥፈህ የምትጠብቅ የሣምንት ተረኛ?” ልንል ይገባል። - አበቃሁ!



