የጋዜጠኛው ማስታወሻ Yegazetegnaw Mastaweshaከበፈቃዱ ሞረዳ

ቀድሞው የጋዜጣችን ተወዳጅ አምደኛ፤ የዛሬው እንደኔው ስደተኛ ያያ አባቦር፤ ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በተባለው መጽሐፍ ላይ ባለፈው የ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” መጽሔት ዕትም ("የአደአው ጥቁር አፈር" ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?") ባቀረበው ጽሑፍ መነሻነት ወይንም ተንኳሽነት የተጻፈ ማስታወሻ ነው ይኼ ጽሑፍ። ይህ የእኔ ማስታወሻ የተስፋዬ ገብረአብን ማስታወሻ ሥነጽሑፋዊ ወርድና ስፋት የመመርመር ተልዕኮ የለውም። ዕይታው ወዲህ ነው።

 

(ያያ አባቦር "የአደአው ጥቁር አፈር ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?" በሚል ርዕስ የፃፉትን ከዚህ ጽሑፍ በፊት ለማንበብ ከፈለጉ እዚህ መጫን ይችላሉ!) ”ከየት መጀመር ይሻለኛል? ስለተስፋዬ ልጻፍ ወይስ ስለ ”የጋዜጠኛው (የካድሬው) ማስታወሻ” መጽሐፍ? እንዴትስ ነው የአንድን ፀሐፊ ሥራ (በተለይም መጽሐፍን) ከፀሐፊው ሁሉንተናዊ ስብዕና ነጥሎ በማውጣት ማወደስ ወይንም ማንኳሰስ የሚቻለው?” የሚሉ ጥያቄዎች በውስጤ ከተተራመሱ በኋላ የመጣልኝን እንደወረደ ጻፍኩት። ለጥያቄዎቼ ሁነኛ ምላሽ መስጠቴን ግን እርግጠኛ አይደለሁም። ወትሮውንስ ቢሆን ማነው በሕይወት ዘመኑ በአዕምሮው ውስጥ ለሚተረማመሱ ሕልቆ መሳፍርት የለሽ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቶ የጨረሰውና ከዚህ ዓለም በእፎይታ የተሰናበተ?

 

ነገር ግን፤ በእኔ ላይ ቢደርስብኝ የማያስደስተኝን ነገር፣ በሌላው ላይ እንዳላደርግ ሁሌም ለሚጎተጉተኝ ኅሊናዬ ታማኝ ለመሆን የሞከርኩ ይመስለኛል።

 

”ክፍሌ ሙላትና በፍቃዱ ሞረዳ የተባሉትን ጋዜጠኞች ግን ክንፈ አጥብቆ ይጠላቸው ነበር ’ደመኛ ጠላቶች’ ይላቸውም ነበር”

ተስፋዬ ገብረአብ - ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ገጽ 208

ከተስፋዬ ገብረአብ ሥራዎች ጋር ለመተዋወቅ ግፊት ያሳደረብኝ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም. (ደርግ ሳይወድቅ በፊት) እሠራበት የነበረው የራዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ የሲሳይ ታደሰ አድናቆት ነው።

 

በሁርሶ የምድር ጦር መኮንኖች ማሠልጠኛ እጩ መኮንኖች ምረቃ ዘገባ ለመሥራት ወደ ሐረር ተልኬ የመሄድ አጋጣሚ ደግሞ ከተስፋዬ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል እንድንተዋወቅ ምክንያት ሆኖኛል። ያኔ ሳገኘው ቀጭንና ፊቱ ጥርስ በጥርስ (ሳቂታ) የሆነ ወጣት መኮንን ነበር።

 

ከፊቱ ላይ ያነበብኩት የደስታ ስሜት በመኮንንነት በመመረቁ ወይንም ለተጨማሪ የወታደራዊ ካድሬነት (የፖለቲካ ሠራተኛነት) በመታጨቱ አልመሰለኝም። ይልቁንም የሥልጠናውን ውጣውረድ መገላገሉና ከልጅነቱ ጀምሮ ይመኘው እንደነበረ የነገረንን የጋዜጠኝነት ሙያ በጦር ኃይሎች ብዙኀን መገናኛ (ሚዲያ) ውስጥ የማግኘት ተስፋ ኮርኩሮት ይሆናል።

 

በወታደራዊ ሥልጠናው ሂደት ”ደካማና ልፍስፍስ” ከሚባሉት ሠልጣኞች መሀከል ቁጥር አንድ እንደነበረ የሚነገርለት ተስፋዬ፣ በእርግጥም ከምረቃ በኋላ ወደ ጦር ግንባር የመሄድ ሕልም አልነበረውም የሚያሰኙ ምክንያቶች ቢኖሩም እዚያ ውስጥ መግባቱ ለዚህ ማስታወሻ ያለው ፋይዳ እምብዛም ነው።

 

በኮርሱ የምረቃ መጽሔት ላይ ገበየሁ ዋለልኝ የተባለ መኮንን (የተስፋዬ የቅርብ ወዳጅ ነው) ”መተላለፍ” በሚል ርዕስ የጻፈው አጭር ልብወለድ በተስፋዬ የቅድመ ካዴት አፍላ የፍቅር ገጠመኝ ላይ የተመረኮዘ እንደነበረ ገበየሁ ነግሮኛል። ጭብጡ የፍቅርና የድህነት (ደሃ የመሆን) ጣጣ ነው።

 

ወጣቱ መኮንን ሥልጠናውን (በተለይም የወታደራዊ ካድሬነቱን ሥልጠና) እንደጨረሰ በጦር ኃይሎች ራዲዮ ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል ባልደረባነት እንዲመደብ ለአለቆች ሃሳብ ቀርቦ፣ ”ጦር ግንባር ሄዶ ልምድ ይውሰድ” መባሉን ከወቅቱ አለቆቼ ሰምቻለሁ። እናም በወቅቱ ”ሰሜን ምዕራብ ዕዝ” ተብሎ ወደሚጠራው ጦር ግንባር ተላከ። ያኔ እንደሰማነው በጦር ግንባሩ ተመድቦ ሥራ በጀመረ በአሥራ ዘጠነኛ ቀኑ፣ የአንድ ወር ደመወዙን እንኳን ሳይበላ ተማረከ። ስለአመራረኩ እርሱ በመጽሐፉ ላይ የተረከልን እንደተጠበቀ ሆኖ ይባል የነበረው ደግሞ ወዲህ ነው። ይህንኑ በተመለከተ እንደጨዋታ ይኖረናል።

 

ተስፋዬ የኢህአዲግ ልሳን የነበረው የእፎይታ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ነበር፤ ”ዋለልኝ ብርሀነ” በሚል የሽፍታ ስም። በመጽሔቱ የመጨረሻ ገጾች ላይ ከየጋዜጣውና ከየመጽሔቱ የተቃረሙ ክብደት ያላቸው አንቀጾች፣ ዓረፍተ ነገሮችና ሐረጎች ይታተሙ ነበር። አንድ ቀን እኔ ከማሳትመው ጋዜጣ፣ አሁን በትክክል የማላስታውሰውን ዓረፍተ ነገር ነቅሶ በመጽሔቱ ላይ ይጽፍና (ያጽፍና) ከስሩ ”እነ መቶ አለቃ እገሌ ከሚያዘጋጁት ጋዜጣ የተወሰደ” ብሎ ይጽፍበታል። ”መቶ አለቃ” የሚለውን ነገር መጠቀም የፈለጉት ለውንጀላ ያመቻቸው ዘንድ ነው። እናም ተቃወምነው በጋዜጣችን። እንዲህ ብለን፦

 

”ስለማንኛው መቶ አለቃ ነው እፎይታ የምታወራው? መቶ አለቃውማ ካለበት አለ። ለዚያውም ጦር ግንባር በሄደ በአሥራ ዘጠነኛ ቀኑ፣ አንድ ኮዳ ውሀ፣ ሽጉጥና ያንጠለጠለውን ወንድነቱን ይዞ መሸሽ ያቃተው። እንዲያውም በዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ የገበሬ ፍየል አርዶ እየበላ ሳለ ሴት ወያኔ ደርሳበት ”እጅ ወደላይ!” ብላ ስታንባርቅበት ”እግሬንስ ወዴት ላደርገው እመቤቴ!” እያለ በፍርሃት ሱሪውን ያበላሸ መቶ አለቃ የት እንዳለ እየታወቀ ወደእኛ ጣት መቀሰሩን ምን አመጣው?” አልነው። እኛ የምናውቀው የምርኮ ታሪኩም እንደዚያ ነው።

 

ነገርዬው በታተመ በሣምንቱ ነገሩ በጣም የከነከነው መሆኑን የተረዳሁት ከብሔራዊ ቴአትር አቅጣጫ ሽቅብ ወደቸርችል ጎዳና እየነዳ ሳለ፣ ዋናው ፖስታ ቤት አካባቢ መብራት ይዞት ቆሟል። እኔ ደግሞ የመንገዱን ጠርዝ ይዤ በእግሬ አዘግማለሁ።

 

የመኪናውን መስታወት ዝቅ አድርጎ በስሜ ጠራኝና ”አንተ ምን ልሁን እያልክ ነው?” አለኝ። በወያኔያዊ ፍጥጫ ጭምር። ”እንዴ! ምን ተፈጠረ ተስፍሽ?” አልኩት፤ ምን ለማለት እንደፈለገ ልቤ ሲያውቀው። ”ለምንድነው በጋዜጣህ የምትሳደበው?” አለኝ መልሶ።

 

”ኧረ! እኔ ... እንዴትስ፤ ለምንስ ብዬ አንተን ...” ብዬ ሳልጨርስ አረንጓዴ መብራት በርቶ ገላገለኝ። ከላይ ወደጀመርነው የወግ ፍሰት እንመለስ። ወያኔዎች አዲስ አበባን በወረሩ በሰባተኛው ቀን ተይዤ ሆለታ በሚገኘው ጦር ትምህርት ቤት ውስጥ ታሰርኩ። ከሣምንት በኋላ ታጋይ ተስፋዬ ገብረአብ መጥቶ እኔንና ሌሎች ሦስት ሰዎችን ይዞን ከሆለታ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ዓላማው አዲሱን የኢህአዲግ ሠራዊት የሚያስተምርና የሚያዝናና የራዲዮ ፕሮግራም እንድንሠራ ነበር። እርሱ የተረጨውን ወያኔያዊ ጠበል ከተረጨን በኋላ።

 

ያኔ ተስፋዬ አባል የነበረበት ”የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መኮንኖች ንቅናቄ” በመባል የሚታወቀው የህወሓት ጫጩት ወደሰፈረበት በቀድሞው ቤላ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ግቢ ነበር የወሰደን። እርሱ ግቢ በደርግ የመጨረሻ ዓመታት የጀኔራል መኮንኖች ማሠልጠኛ (ስታፍ ኮሌጅ) ነበር።

 

ለአሥራ አምስት ቀናት ያህል እዚያ ግቢ በቆየሁበት ወቅት መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በጦርነቱ ወቅት ስለኢህአዲግ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ተዓማኝነት እያነሳን ተወያይተናል። ነገረ ሥራዬ ባይጥማቸው ነው መሰል ከአሥራ አምስት ቀን በኋላ እኔን ወደ ሆለታ እስር ቤት መልሰውኝ ሌሎችን አስቀሩ። ከስምንት ወራት እስራት (እነርሱ ተሃድሶ ይሉታል) በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ሥራ መፈለግ ያዝኩ። ሰፈሬም አራት ኪሎ ስለሆነ ነው መሰል በማስታወቂያ ሚኒስቴር ፕሬስ መምሪያ አካባቢ አልጠፋም። በተለይም የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን ቤተመጻሕፍት እጠቀም ስለነበር። በዚህም አጋጣሚ ነው ያኔ በሳባ ፊደል ሲዘጋጅ የነበረው በሪሳ የኦሮሚኛ ጋዜጣ ለአራሚነት የሥራ መደብ ያወጣውን ክፍት የሥራ ቦታ ያየሁት። እናም አመለከትኩ። አለፍኩም። ሆኖም መቀጠር ግን አልቻልኩም። ”እርሱን በአዲስ ዘመን ላይ የሪፖርተር ቦታ ስለምንፈልግለት በ185 ብር አራሚነት ከሚቀጠር ትንሽ ይጠብቅ” ብሎ ተስፋዬ ገብረአብ መመሪያ እንደሰጠና ቅጥሬ እንደተሰረዘ ሰማሁ። ውሎ አድሮም ለእኔም ለእርሱም ቅርብ የሆነ ሰው ሲነግረኝ ”ሰውየው ሊቀጠር አመልክቶ ነበር። ኦነግ ባይሆን ኖሮ እንቀጥረው ነበር።” አለ።

 

ተስፋዬ ገብረአብ ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ያለውን መጽሀፉን ሲጀምር ወታደር ከመሆኑ በፊት ለሥራ ፍለጋ ከደብረ ዘይት አዲስ አበባ መጥቶ የገጠመውን ተርኮልናል። የወቅቱ የፕሬስ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ሙሉጌታ ሉሌ ጎጃሜ በመሆኑ፣ ጎ ጃሜ ያልሆነው ተስፋዬ መቀጠር እንዳልቻለ በፈጣጣ አገላለጽ ነግሮናል። በእርግጥም ሙሉጌታ ሉሌ እንደዚያ አድርጎ ከሆነ ችግሩ ከእርሱ ሳይሆን ከወንበሩ መሆን አለበት። ተስፋዬ ገብረአብም በ”ኦነግነቴ” ሳይሆን በኦሮሞነቴ ምክንያት በዚያ መስሪያ ቤት ውስጥ እንዳልቀጠር አድርጎኛልና። ለእኔ ግን ከተስፋዬ ይልቅ ሙሉጌታ ታላቅ ሰው ነው።

 

ሥራ አጥ ከርታታ ሆኜ በተስፋዬ ገብረአብ በሚመራው ፕሬስ መምሪያ ደጃፍ ስመላለስ፣ አልፎ አልፎ ወደ ክፍሌ ሙላቱ ቢሮ ሰላ እል ነበር። በወቅቱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እርሱ ያዘጋጀው በነበረው ”አድማስ” አምድ ላይ አንድ ጉደኛ ግጥም ተጽፎ በመገኘቱ ነው ክፍሌ የተባረረው። ክፍሌ ሙላት በአዲስ ዘመን ላይ ይሠራ በነበረበት ወቅት የእኔንም ግጥምች ያትምልኝ እንደነበር ከምስጋና ጋር ማስታወስ እወዳለሁ። ለክፍሌ ከሥራ መባረር ምክንያት የሆነውን የመጀመሪያ ፊደሎቹ ቁልቁል ሲነበቡ ”ትግራይ እስክትለማ ሌላው አገር ይድማ” የሚለውን ግጥም የሰጠሁት ግን እኔ አይደለሁም። ግጥሙ የማን እንደሆነ የሚያውቀው ክፍሌ ብቻ ነው።

 

ተስፋዬ ገብረአብ በአዲሱ መጽሐፉ በገጽ 208 ላይ ”... ክፍሌ ሙላትና በፍቃዱ ሞረዳ የተባሉትን ጋዜጠኞች ግን ክንፈ አጥብቆ ይጠላቸው የነበረ ሲሆን ’ደመኛ ጠላቶች’ ይላቸው ነበር። ...” ብሎ አለቆቹ እኔና ክፍሌን በአንድ ቅርጫት ውስጥ እንደጨመሩ ይነግረናል። ለምን ይሆን?

 

ለእኔ እጅግ አስቸጋሪ በነበረበት በዚያ ወቅት ክፍሌ ሙላት፣ በእርሱም አቅጣጫ ጠቋሚነት ያገኘኋቸው እምሩ ወርቁ፣ ሰለሞን ለማና ሙሉጌታ ሉሌ የተባሉ አንጋፋ ጋዜጠኞች ዛሬ ላለሁበት ሕይወት ያደረጉልኝ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽዖ ከአዕምሮዬ አይጠፋም። ምናልባትም ልብ ገዝቼ የሕይወቴን ተሞክሮ ቢያንስ ለልጆቼ በመጽሐፍ መልክ ማስቀመጥ ብችል ስለእነዚህና ሌሎችም ሰዎች ውለታ እጽፍ ዘንድ እግዜር የዕድሜዬና የመንጋጋ ደሃ አያድርገኝ።

 

ተስፋዬ ከፕሬስ መምሪያ ሥራ አስኪያጅነቱ የተነሳው በብቃት ማጣት እንደነበረ እርሱ ራሱ ”የቅርብ ሰዎቼ ናቸው” የሚላቸው ይናገራሉ። እንዳያውም ፀሐፊው በውስጥ ስልክ እየደወለች ሊያነጋግረው የሚፈልግ ሰው መኖሩን ስትነግረው፣ ”ሰው ነው ወይስ ፈረንጅ?” እያለ እንደሚጠይቅና ፀሐፊው ”ፈረንጅ ነው” ካለች ”ወደ አቶ ያዕቆብን ላኪው” ይላት እንደነበር ማን እንደነገረኝ ረሳሁ። አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም በመንግሥት የተመደቡለት ልዩ አማካሪው ነበሩ። ምን ያድርግ? ሪፖርተር ሳይሆን፣ አዘጋጅ ሳይሆን፣ ... እንዲሁ ከአንዳች ዱብ ብሎ የአንድ ሀገር መንግሥት የፕሬስ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የመሾምን ያህል ምን ፍርጃ አለ? ሥልጣን ያለልምድ፣ ሥልጣን ያለዕውቀት፣ ሥልጣን ያለችሎታ እብደት ነው።

 

ከተስፋዬ ጋር ተገናኝተን ለመጨረሻ ጊዜ ያወራነው ዱከም ነው። ቀኑን ረሳሁት። እኔ ለሴሚናር ደብረዘይት ሄጄ፣ አዳራችንን አልጋ ወደተያዘልን የአትሌት ወርቁ ቢቂላ ሆቴል ወደ ዱከም መጥቼ እዚያ ሳገኘው መጽሐፍ እየጻፈ እንደሆነና ፀጥታ ፍለጋ ወደዚያ እንደመጣ ነግሮኛል። መኝታ ክፍሉ ውስጥ ሌላ ሰው ይኑር አይኑር አላየሁም። ቦታው ግን እርሱ እንደነገረኝ ፀጥታ ያለውና መጽሐፍ የሚጻፍበት አልነበረም።

 

”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተባለው መጽሐፉ ከታተመ በኋላ አዲስ አበባ ካሉ ወዳጆቹ ጋር አምተነዋል። አንድ ለእርሱ ቅርበት የነበረው ጡረተኛ እንደነገረኝ፤ ተስፋዬ በመጽሐፉ የሰጠን መረጃ ከወቅቱ በጣም የራቀ ነው። እንደወዳጄ አባባል መጽሐፉ ”የአያሌ መናኛ ሰዎች የታሪክ ድሪቶ ነው።” ተስፋዬ አጋጣሚዎችን የማሰናኘት ችሎታ እንዳለው ግን ይህ ሰው አልደበቀለትም። ስለክንፈ ገብረመድህንና ስለራሱም ግንኙነት የጻፈውም ጉዳይ ከሚታወቀው በላይ የተጋነነ ነው። ክንፈ በሕይወት ባለመኖሩ፣ ተስፋዬ የሚለው ሁሉ ትክክል ነው።

 

ሌላው ወትሮውንም የተስፋዬ ወዳጅ ያልነበረው ወዳጄ የጻፈልኝ ኢሜል ነው። ”ይሄ ሳሙና የሆነ ሰውዬ ያኔ የደርግ፣ ከዚያም የወያኔ ካድሬ ነበር። አሁን ደግሞ የሻዕቢያ ካድሬ ሆኖ ይላጥብናል እንዴ?” ሲል ጠይቆኛል። እኔ ምን ብዬ እንድመልስለት እንደፈለገ ግን አላውቅም።

 

ተስፋዬ ለኢህአዲግ ከገበረበት ጊዜ ጀምሮ የህወሓት አባል እንደሆነ ከመጽሐፉ ነግሮናል። ”ዋሽቷል” ልበል? ምክንያቱም እኔ ሳውቀው የኢህአዲግ አንድ ክፍል ተደርጎ የሚቆጠረውና የምርኮኛ መኮንኖች ስልቻ የነበረው ”የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መኮንኖች ንቅናቄ” አባልና ሥራ አስፈጻሚ ነበር። ከእነመቶ አለቃ (ዛሬ ኮሎኔል) ዘውዱ እሸቴ፣ ከእነ ዓለምእሸት ደግፌ (የአየር ኃይል አዛዥ የነበረውና በቅርቡ የጄነራልነት ማዕረጉን ተነጥቆ የተባረረው)፣ ከእነ አባዱላ ገመዳ፣ ከእነ ሱሌይማን ደደፎ (አሁን አምባሣደር) እና ከሌሎችም ጭራሮዎች ጋር የዚያ ድርጅት ጢማም ባለሥልጣን ነበር። ስለዚያ ድርጅት አመሠራረትና አከሳሰም በመጽሐፉ ውስጥ ያልጠቀሰው ለአንዳች ብልሀት ሳይሆን አይቀርም ብለን እንለፍ?

 

በማስታወሻው ስለ አቶ ደራራ ከፈኔ አሟሟት ጽፏል። ገዳዮቹም ኮሎኔል ድሪባና ሻለቃ ጀማል የተባሉ መኮንኖች እንደሆኑ ተርኳል። ዋና ገዳዩ እንደሆነ ከነገረን ከሻለቃ ጀማል ጋርም ተገናኝቶ ማውራቱን ጽፏል። እርሱ ይብላኝለት እንጂ የአምቦ ህዝብ ገዳዩቹ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ የተስፋዬን ምስክርነት አይጠብቅም፤ አይፈልግምም። ገዳዩቹንም ለመፋረድ የተስፋዬን ትዕዛዝና አዝማችነት አይሻም። ጠላቶቹ እነማን እንደሆኑ ገና ድሮ ጠንቅቆ ያውቃል። የአምቦ ህዝብ ዓይን ኮሎኔል ድሪባና ሻለቃ ጀማል ከተባሉ ተላላኪዎች አሻግሮ የሚያስተውለው ነገር አለው።

 

በቅርብ የማውቀውን ድምፃዊ ኤቢሳ አዱኛን የገደለው ጌታሁን የተባለው ኮሎኔል እንደሆነ ምናልባትም ከተስፋዬ የሰማው የደምቢዶሎ ህዝብ ተስፋዬንም፣ ኮሎኔሉንም፣ ጌቶቻቸውንም፣ ከመፋረድ የሚመለስ ከመሰለው በእርግጥም እርሱ የዋህ ነው። በመጽሐፉ ገጽ 177 ላይ እና 178 ላይ ”... ዛሬ ጉልበት አግኝተህ የምትገድለው ሰው፣ ጊዜ ጠብቆ ደሙን ይመልሳል። ... በዚህ ዘመን እጅህ ላይ ደም ይዘህ መኮብለል እንደማይቻል ከቀልቤሳ ነገዎ መማር ይቻል ነበር። የኤብሳና የደራራ ድምፅ ይጮሀል። ...” ብሏል። እውነት ነው። የኤቢሳ አዱኛ፣ የደራራ ከፈኔ፣ የአሰፋ ማሩ፣ የተስፋዬ ታደሰ፣ ... እና የሺህዎች ደም የሚጮኸው በመለስ ወይም በአባዱላ ጆሮ ላይ ብቻ አይደለም። በተስፋዬም ጆሮ ላይ እንጂ። ደሙ በተስፋዬ እጅ ላይም አለ። ማስታወሻውም በህዝብ እጅ ላይ አለ። ታሪክ ግፈኞችን ብቻ ሳይሆን ግፍ ሲሠራ እያዩና እየሰሙ ዝም ያሉትን ጭምር ነውና የሚፋረዳቸው።

 

በዚህ መጽሐፍ ገጽ 178 ላይ ፀሐፊው የተጠቀመበትን ፉሉል አገላለጽ መጥቀስ አማረኝ። ”ለገሰ አስፋው ከተባለው ድንጋይ (ሰረዝ የእኔ) የማይማር ሰው ከቶ ምን ስም ይገኝለታል?” ይላል። እርግጠኛ ነኝ ተስፋዬ በፎቶግራፍና በቴሌቪዥን ካልሆነ በስተቀር ለገሰ አስፋውን በቅርብ በዓይኑ አይቶትና አውቆት ድንጋይነቱን እየነገረን አይደለም። አለቆቹ እንደነገሩት ”ለገሰ አስፋው ሀውዜንን በአውሮፕላን አስደብድቧል።” ተስፋዬ ለለገሰ ያለው ጥላቻም ሆነ ፍቅር ይሄው ነው።

 

የታሪክ መልካም ፈቃድ ቢሆንና የኃጥያት እዳን ማውረጃ ጊዜ ቢመጣ የለገሰ አስፋው ኃጥያት ከመለስና ከበረከት፣ ከኃየሎምና ከስዬ ቢያንስ እንጂ አይበዛም። ድንጋይነት በኃጥያት ብዛት ወይንም በደም በመነከር ብልጫ ከሆነ ጌቶቹ በምን አይነቱ ድንጋይ እንደሚመሰሉ ተስፋዬ በሚቀጥለው መጽሐፉ ይነግረን ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ስለዚህ ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ስለተባለው ባለ 412 ገጽ መጽሐፍ ብዙ ማለት በተቻለ ነበር። ሁለት ነገሮች ያስቸግሩናል እንጂ። የርዕሱ የወቅታዊነት ጥያቄና የመጽሔቱ (”ናፍቆት ኢትዮጵያ”) ገጽ ውሱንነት።

 

ጽሑፌ አሰልቺ እንዳይሆን አድርጌ እንዳልጻፍኩት ይታወቀኛል። የበለጠ አሰልቺ እንዳይሆንም አንድ ሁለት ቁምነገሮችን ወጋ አድርጌ ጠቅላላ ሃሳቤን በአንድ እግሩ አቁሜው ሹልክ ልበል።

 

በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋዬ ይህን መጽሐፍ ሊጽፍ የማይችልበት ሁኔታ ነበረ? የሚለው ጥያቄ ነው። የእኔ ምላሽ አዎ! ነው። ለምን ቢሉ፣ በህወሓት መሀከል የተፈጠረው መከፋፈል ባይከሰት ኖሮ የተስፋዬ ነፍስ ፍርሐት ውስጥ አትገባም ነበር። አይሸሽምም። በተሸናፊው በዓለምሰገድ ገብረአምላክ ጎራ ውስጥ ሆኖ የበረከትና የክንፈ ሰለባም አይሆንም ነበረ። ቀድሞውኑም ሰልፉን ከእነ በረከት ጋር አስተካክሎ ቢሆን ኖሮም ምናልባት ይሾም ይሸለም እንደሁ እንጂ ዝንቡን ”እሽ” የሚልለት ”ወንድ” ባልተገኘም ነበር። ለማንኛውም እግዜር እንኳንም ”ልዩነት” የተባለውን ነገር ፈጠረ። ለወደፊቱም ልዩነት ለዘላለም ይኑር! ተፈጥሮም ነውና።

 

ሌላው ወደድንም ጠላንም፣ በክፉም በደጉም የዚህን ሰው ነገር ስናነሳ፣ ስንጥል ታሪኩን እየጻፍንለት ነው። ብልጥ ሰዎች እየነከሱንም፣ እየሳሙንም፣ እየወደዱንም፣ እያወገዙንም፣ እያወደሱንም፣ እየሰበሩንም፣ እየጠገኑንም፣ ... ታሪካቸውን ያጽፉናል። በቃልም፣ በወረቀትም። የእኛን አዳፍነን የእነሱን እንድናራግብ ይሸነቁጡናል። በእርፍናቸው ለበቅ፣ በእርድናቸው አኮርባጅ።

 

ነገር ግን፣ እያንዳንዳችን ታሪክ አለን። እያንዳንዳችን የምትጻፍ፣ የምትነበብ፣ ነፍስ አለችን። እያንዳንዳችን አንድም ጥሩ መጽሐፍ ነን። አለበለዚያም ጥሩ መጽሐፍ ይዘን ኖረን፣ ያልተጻፈ ጥሩ መጽሐፍም ይዘን እናልፋለን። መጥኔ ለዕድል!


 

ከኢትዮጵያ ዛሬ ይህንን ጽሑፍ የ”ጦማር” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ የነበረውና አሁን በስደት በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ ”እኔም ማስታወሻ አለኝ” በሚል ርዕስ በ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” በተሰኘውና በቺካጎ በሚታተመው መጽሔት ላይ ያቀረበው ጽሑፍ ነው። በፈቃዱ የያያ አባቦርን ”የአደአው ጥቁር አፈር ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?” የሚል ጽሑፍ መነሻ አድርጎ ይህንን ጽሑፍ እንደጻፈ በጽሑፉ መግቢያ ላይ ገልጿል። እነዚህን ሁለት ጽሑችን በመጥቀስ ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ በኢትዮ ሚዲያ ፎረም ላይ ”የግንቦት ማስታወሻ” በሚለው ጽሑፉ የበኩሉን ምላሽ ሰጥቷል። ሦስቱንም ጽሑፎች አቅርበናቸዋል። መልካም ንባብ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ