ሕገ መንግሥትና ሕገ አራዊት (ፕ/ር መስፍን)
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም (ታኅሳስ 2001)
“ሕገ አራዊት” የተፈጥሮ ሕግ ነው፤ በደመ-ነፍስ የሚንቀሳቀሱ ኹሉ ለመራባት የሚያስችላቸውን ግዴታቸውን የሚፈጽሙት በሕገ አራዊት ነው። የቀደመው አሁን ከአለው አይለይም፤ የወደፊቱ ከአሁኑ እንደማይሻል የታወቀ ነው። የቀድሞውም በጉልበት ነው፤ የአሁኑም በጉልበት ነው፤ የወደፊቱም በጉልበት ነው። የሕገ አራዊት መሠረቱ ጉልበት ብቻ ነው። ምግብ የሚገኘው በጉልበት ነው፤ ጉልበት ያለው ይበላል፤ ጉልበት የሌለው ለጉልበተኛው ምግብ ይሆናል፤ ጉልበት ያለው ይንደላቀቃል፤ ጉልበት የሌለው በየጉድጓዱ ይሽሎከለካል።
የተፈጥሮ ሕግ ሕይወት ካላቸው ነገሮችም ውጭ ይታያል፤ ለምሳሌ ውሃ ቁልቁለት ሲያገኝ ጎበዝ ነው። ይሮጣል፣ ይንዳል፣ ያፈርሳል። ነፋስም እንዲሁ የማጥፋት ጉልበቱ ከፍተኛ ነው። እንዲያውም ሲመቸው ነፋስ ውሃን አለባሕርዩ አቀበት እንዲወጣ ያደርገዋል። የውሀንና የነፋስን ጉልበት አሜሪካም አልቻለውም።
በሽታ የምንለው ሁሉ በሕገ አራዊት ውስጥ የሚካተት ነው። ቢምቢዋ ምቹ ጊዜን ጠብቃ የደም ስር ፈልጋ ደም የምትመጥጠው በተፈጥሮ ግዴታ ነው። በአካላችን ውስጥ የሚታዩና የማይታዩ ሕዋሳት በፍጥነት እየተባዙ የሰውን ልጅ የሚያሰቃዩትና ወደሞት የሚገፉት በተፈጥሮ ሕግ ነው። እነሱም መኖር ስላለባቸው የሚያደርጉት ነው።
በሕገ አራዊት ሥርዓት ውስጥ ኹኖ ዕድገትና መሻሻል የሚባል ነገር የለም። ጉልበት ያለው እየበላ፤ ጉልበት የሌለው እየተበላ መቀጠል ነው። ዘመናት ቢለዋወጡ የተፈጥሮ ሕግ ፍንክች አይልም። ጉልበት በቅጽበታዊ ፍላጎትና በደመ ነፍስ የሚመራ ነው። ጉልበትንና ደመ-ነፍስን በመግራት አራዊትንም ማሠልጠን ይቻላል። ከርሞ ጥጃ ማለት ነው።
ሰው አዕምሮ ስላለው ያስባል፣ ያስተውላል፣ ያስታውሳል፣ የተሻለ ሁኔታን ያልማል፤ ችግሩን ለመቀነስ፣ ምቾቱን ለማስፋት ይጥራል። ስለዚህም ራሱንም ኾነ አካባቢውን መለወጥ ይችላል።
ሰዎች በአንድነት በአንድ ሀገር ውስጥ ሲኖሩ ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል። እያንዳንዱ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የማይነፈጉና የማይጣሱ መሠረታዊ መብቶች አሉት። አንድ ሰው በየትኛውም ሀገር ቢኖር እነዚህ መሠረታዊ መብቶት ይኖሩታል። የአንድ ሀገር ዜጎች ኾኑ ሰዎች ደግሞ በሰብዓዊ መብቶቻቸው ላይ የዜግነት መብቶች አሏቸው። የዜግነት መብቶች በመሠረቱ የባለቤትነት መብቶች ናቸው።
“… ሰው ባገሩ ሰው በወንዙ ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ
ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ። …” የሚለው የቀረርቶ ግጥም የሚያመለክተው የሰብዓዊና የባለቤትነት መብቶቻችን ነው።
በአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ሕገመንግሥት አለ፤ ነገር ግን በሥራ ላይ አይውልም። በቅርቡ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ያየናቸው ምርጫዎች ሁሉ ከሕግ ይልቅ ጉልበት ያመዘነባቸው ነበሩ። ሰሞኑን አፍሪካን ”እልል” የሚያሰኝ ምርጫ በጋና እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል። በተረፈ ከደቡብ አፍሪካ በቀር በአጠቃላይ የሚታየው አፍሪካ ከሕጋዊ ሥርዓት ጋር የተጣላ መስሎ ነው። የነጭ ዘረኞች በአፍሪካ የሚታየውን ሕግ-አልባነትና የሚባባስ ደሀነትን ከዘር ጋር ያያይዙታል። በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው በአቶ ከበደ ሚካኤል አነጋገር ”ጨካኝነቱ እንደአውሬ፣ ድንቁርናው እንደእንስሳ” መሆኑ የሚያሳዝንም የሚያሳፍርም ነው። ሰዎች ሰብዓዊ ከሆነው የማሰብ የተፈጥሮ ባሕርያቸው ሲወጡ እንስሳ እንደሚሆኑ ገና ዱሮ ዳዊት ተናግሮታል፤ ”… ወኮነ ከመ እንስሳ እስመአልቦ ልብ።”
ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት የሠለጠኑ ሰዎች የሚጠቀሙበት የዕድገታቸው ዋልታ ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ባለበት፣ ሰውን ሰው አይገዛውም፤ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መብቶችና እኩል ግዴታዎች አሉዋቸው፤ ሕግ ለዜጎች ሁሉ በእኩልነት የሚያገለግል ነው፤ ጉልበተኛ ደካማውን እንዳያጠቃ፣ ሀብታሙ ድሀውን እንዳይበድል፣ ሀብታሙ እንዲያውም የሕግ መሠረታዊ ጥቅሙ ለፍቶ ያገኘው ንብረት እንዳይዘረፍ፣ በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡ እየባለጉ በዘፈቀደ እንደልባቸው የሀገርን ሀብት እንዳይመዘብሩና በትረ ሥልጣንን የበቀል ዱላ እንዳያደርጉት፣ የአብዛኛው ህዝብ ኑሮ እየዘቀጠ ጥቂቶች በቁንጣን እንዳይታመሙ በመጠበቅ ማኅበረሰቡ በተደላደለ ሚዛን ኑሮውን እንደተሰጥዖውና እንደችሎታው እንዲያሻሽል የሚያደርገው ነው። ከሁሉም በላይ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሕግ የጥቃት መሣሪያ አይሆንም። ሕግ ጥቃትን የመከላከያ መሣሪያ እንጂ የጥቃት መሣሪያ አይደለም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነንን ሰሞኑን በግሪክ ሀገር እያየን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ወጣቶች ሠላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ስሜታቸው እየጋለ ሲሄድ ድንጋይና ቤንዚን የተሞላ ጠርሙስ በፖሊሶች ላይ መወርወር ይጀምራሉ። እንደነሱው ስሜቱ የጋለ ፖሊስ አንዱን የአሥራ አምስት ዓመት ወጣት በጥይት ይገድለዋል። ከዚያ በኋላ ፖሊሶቹን ”መለዩ የለበሱ ነፍሰ-ገዳዮች” በማለት ችግሩ ተባብሶ በብዙ ከተሞች አስተጋባና ብሔራዊ ደረጃ ላይ ደረሰ። ዛሬ (ኅዳር 30) አራተኛ ቀኑ ነው፤ ገዳዩ፣ ፖሊስ ቢያዝም፣ ገና አልበረደም። በሕገመንግሥታዊ ሥርዓት የአንድ ዜጋ ሕይወት ዋጋ አለው። ማንም የማንንም ሕይወት ያለፍርድ ለማጥፋት አይችልም።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ”በሕግ አምላክ!” ሲሉት ወንዙም ይቆማል፣ በማለት የሕግን የበላይነት ይገልጹት ነበር። የሕግ አምላክ ያልተሰበረ ሚዛን ያሳየን!



