አንዱዓለም አራጌ

አቶ አንዱዓለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪ

“ኢትዮጵያ ያልሰጠናት ነገር አለ ብለን አናምንም፤ ስሜትን በሚፈትኑ ነገሮች እያለፍን፤ ራሳችንን ገዝተን፣ የአባሎቻችንን ስሜት ከፍለን ለኢትዮጵያ ሰላም ስንል ብዙ ዋጋ ከፍለናል” አንዱዓለም አራጌ

ትዕግሥት መንግሥቴ (ኢዛ)

በዘንድሮው ምርጫ 2013 ጠንካራ ተፎካካሪ ይኾናል ተብሎ በቅድሚያ ከሚጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ኢዜማ ነው። ኢዜማ ከብልጽግና ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን እጩዎች በማቅረብ ለዚህ ምርጫ የተዘጋጀም ነው። ይዞ የቀረበውም የፓርቲው ማኒፌስቶ በአገሪቱ አሉ የተባሉ ምሁራንን ጭምር በማሳተፍ ያዘጋጀው መኾኑም ይነገራል።

የፖሊሲ ዝግጅቱም ቢኾን በተመሳሳይ መልኩ በጥናት የተሰናዳ መኾኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ይሁንና የሰኔ 14ቱ ምርጫ 2013 ግን የዝግጅቱን ያህል እና ቀድሞ ፓርቲውም ኾነ ሌሎች የሰጡትን ግምት ያህል አለመኾኑ በሰፊው እየተነገረ ነው። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ከሰሞኑ እየሰጡ ያሉት አስተያየት ይህንኑ የሚጠቁም ነው።

በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ታዋቂ ምሁራን እና ታዋቂ ሰዎችን ጭምር በእጩነት ያቀረበው ኢዜማ፤ የምርጫ ቦርድ ይፋዊ ውጤት የሚጠበቅ ቢኾንም፤ ከየምርጫ ጣቢያዎች የተሰባሰቡ መረጃዎች ኢዜማ የተጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላገኘ እየተገለጸ ነው። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ መረጃ እየተጠበቀ በአዲስ አበባ ከተማ ኢዜማ እጩ ተወዳዳሪ አቅርቧቸው የነበሩት የቀድሞው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ቤቶች ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና፤ ብልጽግናን “እንኳን ደስ አለህ!” ብለዋል።

ኢዜማ በአዲስ አበባ ባያሸንፍ የከተማዋ ከንቲባ እንደሚኾኑ ሲነገርላቸው የነበሩት አቶ ክቡር ገና፤ ኢትዮጵያውያን ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኾኑላቸው ወስነዋል ማለታቸው ኢዜማ ባሰበው መንገድ ውጤት ያለማምጣቱን የሚያመለክት ነው።

ኢዜማ ትናንት ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በምርጫው ዙሪያ የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ተመሳሳይ ሐሳብ የታየበት ነበር። ኾኖም ምርጫውን በተመለከተ በመግለጫው እንደሰፈረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ሒደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለጸ ባይኾንም፤ በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር ብሏል።

በዚህ ምርጫ ዜጐች በንቃት እንዲሳተፉ የበኩሉን ማድረጉን የገለጸው ኢዜማ፤ በምርጫ ሒደቱ ግን ያጋጠሙትን ችግሮች ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከኾነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዤ እሔዳለሁም ብሏል።

ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ ግን ኢዜማ በቅድመ ምርጫና ከምርጫው በኋላ እየሔደበት ያለው ሕጋዊ መንገድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ የሚባል ታሪክ ያመለከተ ስለመኾኑ እየተመሰከረለት ነው።

ኢዜማ የያዘውን አቋም የበለጠ የሚያሳየው ደግሞ በትናንትው ዕለት (ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ..ም.) የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ነው።

በምርጫው የተሰጠውን ያህል ውጤት አላመጡም ከሚል እሳቤ በመነሳት በፓርቲ ደረጃ የሚቆጫችሁ ነገር አለ ወይ? ለሚል ጥያቄ፤ “ኢትዮጵያ ያልሰጠናት ነገር አለ ብለን አናምንም” በማለት ምላሽ መስጠት ጀምረው፤ “ስሜትን በሚፈትኑ ነገሮች እያለፍን፤ ራሳችንን ገዝተን፣ የአባሎቻችንን ስሜት ከፍለን ለኢትዮጵያ ሰላም ስንል ብዙ ዋጋ ከፍለናል” ሲሉ አክለዋል።

“ኢትዮጵያ አሸነፈች” የሚለውን ከኢዜማ ወስደው ብልጽግናዎች “ኢትዮጵያ አሸነፈች” እያሉ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አንዱዓለም፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የሠሩት ኢዜማዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።

ባልተገራ ባህልና የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አልፈው ፓርቲያቸው አዲስ የፖለቲካ ባህል ማለማመድ ስለመቻላቸውም ጠቅሰዋል።

በተለይ የምርጫው ውጤት ወደ እነርሱ (ኢዜማ) ያደላ ያለመኾኑ እየታወቀ፤ ደጋፊዎቹም ኾኑ የፓርቲው አመራሮች በተረጋጋ ሁኔታ እየተራመዱ መሔድ መቻላቸው፤ የዘንድሮው ምርጫ ሌላው መልካም ጐን ተደርጐ እየታየ ነው።

በምርጫው ሒደትና በምርጫ ወቅት ደርሰውብኛል ያለውን ችግር ለመፍታት በአመጽና በግርግር ከመነዳት ይልቅ፤ መብቴን በሕግ አስከብራለሁ ማለቱም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል መልካም አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያመላክት ነው ሊባል ይችላል።

ይህ የበለጠ የሚረጋገጠው ደግሞ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻውን ውጤት ከገለጸ በኋላ የሚከተለው ተግባሩ ይኾናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ