ከተስፋዬ ማሩ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አንድ ጓደኛዬ ብዙ ጊዜ ስለመለስ ሲነሳ “ይሄ ሰው በጣም ጎበዝ ነው” ይለኛል። አንዳንድ ሰዎችም ስለመለስ ዜናዊ ጉብዝና ሲያወሩ ይሰማል። ከሱ ፖለቲካ ጋር እንኳ የማይስማሙና ብዙ ሥራዎቹን አምርረው የሚቃወሙ ሰዎች የተናገራቸውን ዐረፍተ ነገሮችና ሀረጎች እየደጋገሙ “በጉብዝናው” ሲገረሙ ይታያሉ። ይህ የሱ ልዩ “የአዕምሮ ብቃት” ባብዛኞች ዘንድ አከራካሪ አይደለም ማለት ነው።

 

ይህ ጉዳይ ከግለሰቦችም አልፎ ባንዳንድ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኀንም ጭምር የሚንጸባረቅ ነው። ስለመለስ እና ስለሚናገረው ነገር አዎንታዊ እንደምታ ባለው አኳኋን ከመፃፋቸው ባሻገር፣ የጋዜጠኛነት ሙያቸው በሚጠይቀው ግዴታ መሰረት በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ፍተሻ አያደርጉም።

 

እነዚህ ሰዎች የአንድን ሀገር መሪ ጉብዝና የሚመዝኑበት ሚዛን ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘመናት አንስቶ መሪዎች የሚመዘኑት ህዝቡን በሆነ መንገድ ለመጥቀም ባሳዩት ጥበብ፣ ጀግንነት፣ … ወዘተ ነው። አንድ ብዙዎቻችሁ የምታውቁትና ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ታሪክ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሰው የጥንቱ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሴፍ ነው። እንደምታውቁት ዮሴፍ ከእስረኛነት ወጥቶ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት የበቃው የግብጽን ህዝብ ወደፊት ሊመጣ ካለ ረሃብ የሚያድን ሃሳብ አፍልቆ ጥበበኛነቱን በማሳየቱ ነው።

 

የመለስ “ጉብዝና” ለአንድ መሪ ከሚያስፈልገው ጋር ሲነፃፀር ከተረት ተረትነት ያለፈ አይደለም። እንዲሁም ደግሞ ምናልባት ሰውየው የተጻፈን ነገር አንብቦ የመማር ችሎታው ከፍ ያለ ቢሆንም እና ማለቂያ የሌላቸው አጫጭር እና የሚታወሱ ዐረፍተ ነገሮችን ማምረት ቢችልም፣ ለአንድ መንግሥት መሪ የሚያስፈልገውን እውቀት እና ጥበብ የለውም።

 

በመጀመሪያ “የመንግሥት ዓላማ ምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ባጭሩ እንመልስ። መንግሥት በህዝብ መሃከል የተደረገ ኮንትራት ነው ይባላል። በዚህም ኮንትራት መሰረት መንግሥት ህዝቦች በየራሳቸው ቢሆኑ ማድረግ የማይቻሏቸውን ነገሮች እንደ ህዝብ ተወካይ ሆኖ ያደርጋል። የመንግሥት ሥራ የአንድን ሀገር ህዝብ ደህንነት መጠበቅ፣ ወደ ብልጽግና ሊያልፍ የሚችልበትን መንገድ ማፈላለግ እና ባጠቃላይ በተቻለው መንገድ ሁሉ ህዝቡ ከፍ ወዳለና ወደተሻለ እድገት የሚሄድበትን ኹናቴ ማመቻቸት ነው።

 

ለገዛ ህዝቡ እንቅፋትን መፍጠር እና ደህንነቱን በማሟላት ፈንታ ህዝቡን ማጥቃት የመንግሥት ሥራዎች አይደሉም። ከድህነት የሚያወጣ ፖሊሲ መፍጠር ባቃተ ጊዜም ህዝብ የመረጣቸው ሌሎች መሪዎች በተራቸው መጥተው እንዳይሞክሩ መንገድ ዘግቶ ህዝቡን የረሃብና የበሽታ እስረኛ አድርጎ መያዝ፤ እንዲሁም ከተጠያቂነት እራስን ማግለል የመንግሥት ሥራዎች አይደሉም። እንደዛ ከሆነ መንግሥት ዋጋ ቢስ ይሆናል። መንግሥት ለህዝብ ተፈጠረ እንጂ ህዝብ ለመንግሥት አልተፈጠረምና።

 

የመንግሥት መኖር ምክንያት ይህ ከሆነ የመሪዎች መኖር ደግሞ ያ መንግሥት የቆመበት ዓላማ ባግባቡ እንዲተገበር ማድረግ ነው። የአንድ ዘበኛ ሥራ ደጁን በትጋት መጠበቅ፤ ያስተማሪው ሥራ በእውቀት እና በሥነምግባር የታነጹ ሰዎችን ማፍራት፤ የዶክተሩም ሥራ ማከም፣ … ወዘተ ናቸው። እንደዛ ከሆነ ደግሞ የዘበኛውን የሥራ ብቃት በአስተማሪ ሚዛን፣ የአስተማሪውን በዶክተሩ ሚዛን መመዘን ትክክል አይደለምም፤ እውነተኛውንም ወጤት አያሳይም።

 

ስለዚህም የመንግሥት መሪዎች ጉብዝና መመዘን የሚገባው ህዝባቸውን ለመጥቀም እና ደህንነቱን ለመጠበቅ ባፈለቋቸው ፖሊሲዎች፣ የነዛም ፖሊሲዎች ውጤታማነት እና እነሱም ፖሊሲዎቹን በተግባር ላይ ለማዋል ባሳዩዋቸው የአመራር ብቃቶች እና በመሳሰሉት ነው። በተጨማሪም እነዚህ መሪዎች አንድን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ሃሳብ ማመንጨት ባቃታቸው ጊዜ ወይም ደግሞ ያንን ጉዳይ በተመለከተ የገቧቸው ቃልኪዳኖች ሳይፈጸሙ ሲቀሩ እራሳቸውን ለተጠያቂነት የማቅረብ ግዴታቸውን መወጣታቸው አንዱ መመዘኛ ነው። አለበለዚያ ከላይ እንደተጠቀሰው የነሱም ሥራ ሆነ የሚመሩት መንግሥትም ዋጋ ቢስ ይሆናል። መሪዎች ለህዝብ ተፈጠሩ እንጂ ህዝብ ለመሪዎች አልተፈጠሩምና።

 

ታዲያ አቶ መለስ ዜናዊ በነዚህ መስፈርቶች ላይ ሲመዘን ጉብዝናው ስንት ኪሎ ይወጣዋል?

 

በመጀመሪያ ባገራችን ግዙፍ ከሆኑ ጉዳዮች የተወሰኑትን በመዘርዘር መለስ በነዚህ ነጥቦች ላይ የወሰዳቸውን አቋሞችና እርምጃዎች፤ እንዲሁም ውጤቶቹን በማሳየት እና ከላይ በግርድፉ ከተዘረዘሩት መስፈርቶች ጋር በማገናኘት እንመዝነው። (የተቀሩትን ጉዳዮች ለመዘርዘር ቦታም ጊዜም ስለማይበቃ ላንባብያን እተዋቸዋለሁ።)

 

1. ረሃብ ህወሓት ሰሜኑን ተቆጣጥሮ ገና ወደ አዲስ አበባ ሳይገባ በፊት አቶ መለስ ዜናዊ ከፓወል ቢ. ሄንዝ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ (በራሴ ትርጉም) “ሰዎች ለረሃብተኞቹ መደረግ ስላለበት የምግብ ዕርዳታ ብቻ እያወሩ ረሃቡ እንዲከሰት ስላደረገው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ግን ለማውራት አለመፈለጋቸው ያናድደናል” ብሏል። ከዛ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ቢያንስ ሦስት ምግብ መብላት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቃል መግባቱን እናውቃለን።

 

ዛሬ አቶ መለስ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ አሥራ ስምንት ዓመት ሊሆነው ነው። ያ ደግሞ ገና ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ ጀምሮ ስለፖለቲካዊ ችግሩ ብቻ ሳይሆን ስለኢኮኖሚ ፖሊሲውም ጭምር የወቀሰውና የተዋጋው ደርግ ሥልጣን ላይ ከቆየበት ጊዜ ይበልጣል። የሥልጣን ጊዜ ርዝማኔው ብቻ ሳይሆንም በድሆች ስም ሀገር ውስጥ የገባው የዕርዳታ ገንዘብ በዕጥፍ ድርብ ይበልጣል። ረሃቡ ግን ምንም እንኳ የሚራቡትን ሰዎች ቁጥር (ዕድሜ ለመንግሥት የቁጥር ጫወታ) እቅጩን ለማወቅ ባንችልም፤ የኢትዮጵያ ሕፃናት ዳግም በዓለም ቴሌቭዥን መስኮቶች ላይ የገጠጠ አጥንታቸውን እና የተነፋ ሆዳቸውን ይዘው ብቅ ብለዋል! አቶ መለስ ሥልጣን ላይ በተቀመጠባቸው በነዚህ አሥራ ስምንት ዓመታት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያገራችን ዜጎች የእህል እርዳታ ጥገኞች ሆነዋል። እንደ ፈረንጅ አቆጣጠር በሁለት ሺህ ሦስት ቁጥራቸውን የማናውቀው ወገኖቻችን በረሃብ ሞተዋል፤ በዚህ በያዝነው ዓመትም ብዙዎች እየሞቱ ነው።

 

ዛሬ አቶ መለስ ረሃቡ እንዲከሰት የሚያደርገው የፖለቲካና የኢኮኖሚው ሁኔታ ነው ብሎ ያምናል ብዬ አላስብም። ቢሆን ኖሮ የሚከተለውን ፖሊሲ ለመመርመርና ለማስተካከል፣ እራሱንም ለተጠያቂነት ለማቅረብ ዝግጁ በሆነ ነበር። ይልቁንስ እሱና ባለሥልጣኖቹ ብልጽግና እንጂ ረሃብ እንደሌለ እያወሩ ረሃቡን የሚያጋልጡትን በተራቸው ማጥቃትን ተያይዘውታል።

 

አቶ መለስ በህዝቡ ላይ እንዲህ አይነት ውርጅብኝ ሲወርድ አቋሙን ለውጦ መፍትሔ ለመሻት የማይፈልግበት ምክንያት አንዳንዶች እንደሚሉት “ሰይጣናዊ” እና ክፉ ስለሆነ ነው ብዬ አላምንም። መልሱ ቀላል ነው - ስለማያውቅ እና ግትር ስለሆነ ነው።

 

በመጀመሪያ ቃል ኪዳኖቹን ሲገባ ካንድ ሀገር ረሃብን ለማስወገድ የሚጠይቀውን ነገር ፈጽሞ የሚያውቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም ገና ከጫካ የገባና የአስተዳደር እውቀት የሌለው፣ ቤተመንግሥት ቁጭ ብሎ ትምህርቱን እስከዛሬ የሚማር ሰው ነው። በጫካም የነበረው ልምድ፣ በማፍረስ እና በማጥፋት ላይ ያተኮረ ስለነበር ስለመገንባት እና ስለማዳን አያውቅም ለማለት እደፍራለሁ። ስለዚህ በዛን ጊዜ ረሃብን ስለማስወገድ የተናገራቸው ነገሮች ምኞቱን እንጂ ማድረግ ስለሚችላቸው ነገሮች አልነበረም።

 

ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ግን ቃል ኪዳኖቹን ደጋግሟቸዋል፤ ደጋግሞም ወድቆባቸዋል። የኢትዮጵያም ህዝብ የሌላ ሀገር ህዝብ የማይሰጠውን (በማወቅም ባለማወቅም) ዓይነት ይቅርታ እየሰጠ በትዕግስት ተጠባብቆታል። ነገር ግን አቶ መለስ ህዝቡን ካሉበት የረሃብ ማጥ ሊያወጣው አልቻለም። ያ ደግሞ የሚያሳየን ይህ ሰው ለም መሬት እና ታላቅ የሰው ጉልበት ያላትን ሀገር ከረሃብ ለማዳን የሚያስችል ፖሊሲ የማፍለቅ ችሎታ እንደሌለው እና የሌሎችን አስተያየት ተቀብሎ ስህተቱን ለማረም የሚያስችል ጥንካሬና በራስ መተማመን የሌለው ግትር ሰው እንደሆነ ነው። ባጭሩ ሥራው የሚጠይቀውን እውቀትና ህዝቡን ከረሃብ የሚያድን የዮሴፍን ጥበብ ወይም ጉብዝና የለውም።

 

2. ትምህርት ልክ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ፣ ከፖሊሲው ጋር ያልተስማሙ ፕሮፌሠሮችን በጅምላ አንስቶ አባሮ አብዛኞቹን ካገር እንዲወጡ ገፋ። ያኔ የጀመረው የምሁራን ፍልሰት ዛሬ በላቀ መልኩ ጨምሮ እንኳን አዳዲስ የሚገነቡት ዩኒቨርሲቲዎች ቀርተው እንደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ቁንጮዎች እንኳ በአስተማሪ እጥረት የትምህርት ጥራታቸው አፈር ድሜ በልቷል።

 

አቶ መለስ ይህንን የመሰሉ “ቢሄዱስ ምን እንዳይሆኑ ነው፣ በቀላሉ እንተካቸዋለን” አይነት ባዶ ኩራት የተሞሉ ብዙ ውሳኔዎችን አስተላልፏል (ከታች ይመልከቱ)። ይህም የሚያሳየው የሰውየው አስተሳሰብ ምን ያህል ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ነው። ከሀገሩ ሰዎች ጋር ከዲፕሎማሲ ይልቅ ትዕቢትን በተደጋጋሚ መርጧል። አሁንም አንዲትን ሀገር ለማስተዳደር የሚጠይቀውን ነገር የሚያውቅ አይመስልም።

 

የአቶ መለስ አስተዳደር ያደረገውን የትምህርት ፖሊሲ ለውጥ ውጤት ባጠቃላይ ስንመለከት ልብ የሚሰብር ነው። ሕፃናቱ የሚማሩትን ነገር መላ ቅጡን ሳይለዩ እየተገፉ አስረኛ ክፍል ይደርሱና ገና ሁለት ዓመት ባጠኑት እንግሊዝኛ ብሔራዊ ፈተና ይፈተናሉ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ፈተናውን አልፈው ትምህርታቸውን የሚቀጥሉት ጥቂቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው። አብዛኞቹ ወደው ሳይሆን በግድ የተለያዩ ሙያዎችን ወደማጥናት ይዞራሉ። ይህም ደግሞ ሆኖ የሚማሩት ትምህርት ጥራት ቢኖረው መልካም ነበር፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ተማሪዎች እንኳን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከዩኒቨርሲቲዎቹም ከወጡ በኋላ ለሥራው ዓለም ጭራሽ የተዘጋጁ እንዳልሆኑ ብዙ ቀጣሪዎች ይናገራሉ።

 

ቋንቋን በተመለከተ ደግሞ መንግሥት ሆን ብሎ በሚከተለው ፖሊሲ እንኳን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የጨረሱት ይቅሩና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እንኳ በዚህ ግሎባላይዜሽን እየተጠናከረ በሄደበት ዘመን፣ እንኳን ካገራቸው ውጪ ሊወዳደሩ ይቅርና ሀገር ውስጥ እንኳ ከክልላቸው ውጪ ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልጋቸውን የቋንቋ ዕውቀት የላቸውም። በዚህ አኳኋን ቁጥር የሌላቸው የኢትዮጵያ ልጆች በገዛ ሀገራቸው ዕድሎችን ከማሳደድ እየተገለሉ ነው።

 

በአጠቃላይ አቶ መለስ ሥልጣን ላይ በቆየበት ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት በአደገኛ ሁኔታ ቁልቁል ወርዷል። ይህም የሀገሪቱን የወደፊት ዕድል ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ከቷል።

 

3. ጤና ልክ እንደ ፕሮፌሠሮቹ አቶ መለስ የጤና ባለሙያዎችን ፍልሰት በተመለከተ አስተያየት ሲሰጥ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ብሏል። እነዚህ ባለሙያዎች ሀገራቸውን ለቀው የሚሄዱበትን ምክንያት መሰረት ለማወቅ ጥረት ከማድረግና ምንም እንኳ የነዚህን ሰዎች ሁሉንም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ማሟላት ባይችልም የተወሰነውን አድርጎ እነዚህ ሰዎች ሀገራቸውን ለቀው እንዳይሄዱ ሠራም አልሠራም በመለማመጥና ክብር በማሳየት ፈንታ የትዕቢትን መንገድ መረጠ።

 

በርግጥም የጤና ጉዳይ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ከማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ጋር ይገናኛል። አጠቃላይ የኢኮኖሚው ሁኔታ ካልተሻሻለ ጊዜያዊ እርምጃዎች ችግሩን ለዘለቄታው ሊቀርፉት አይችሉም። ኢኮኖሚውን ማሻሻል ወይም ሲያቅት ለሌሎች ተራውን መልቀቅ ደግሞ የመንግሥት ሥራ ነው። በተጨማሪም የህዝብን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ለመቆጣጠር መንግሥት ባለመቻሉ ይሄም በጤና ጥበቃ ሥራ ላይ ጫና ያሳርፋል።

 

ዛሬ አቶ መለስ ላለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት በመሯት ኢትዮጵያ ሊታከሙ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ይሞታሉ። ለእናትነት ምቹ በመሆን ሀገሮች በደረጃ ሲቀመጡ ኢትዮጵያ ከመጨረሻዎቹ ሀገሮች አንዷ ነች - የዚህም አንዱና ትልቁ ምክንያት የጤና ጥበቃ ብቃት ጉድለት ነው።

 

4. ሉዓላዊነት ከኢኮኖሚ ባሻገር ደግሞ የአንድ መንግሥት ሥራ የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር እና ደህንነቷን መጠበቅ፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለጥቅሟ መቆም ነው። አቶ መለስ ገና ሥልጣን ከመያዙ አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ የሀገሪቱን አንድ ክፍለ ሀገር (ኤርትራን) መገንጠል ደገፈ። ያ የሆነው ተጨማሪ ጦርነት እንዳይካሄድ ብሎ ነው ቢባል እንኳ፤ የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ ለሀገሪቱ የወደብ መብት ለመከራከር በቂ ሕጋዊ መሰረትና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እያለው፤ እንዲሁም እየተመከረ ላለመከራከር ወሰነ።

 

ከኤርትራ ጋር በባድመ ላይ በተደገው ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር ቢያሸንፍም አቶ መለስ አሁንም ጥበብ የጎደለው ውሳኔ አድርጎ ይግባኝ ማለት በማይችልበት ስምምነት ውስጥ እራሱን አሰረ። ይሄ ሲደረግም ብዙዎች መክረውት ነበር፤ እሱ ግን አልሰማም።

 

በቅርቡም መሬታችንን “እንደ አምባሻ” እየቆረጠ ለሱዳን መስጠቱ ከዚህ የሚጠቀስ ነው።

 

5. ወደብ ወደብን በተመለከተ አቶ መለስ (በራሴ ትርጉም) “ወደብ እንደማንኛውም አገልግሎት ነው፣ ከማንም ሄደን ልንገዛው የምንችለው ነገር ነው፣ ገንዘቡ አለን፣ ሄደንም እንሸምታለን” ሲል ትዕቢት የተሞላበት እና ጥበብ የጎደለው ንግግር ተናግሯል። ይህ አባባል ስለ ሰውየው የሚነግረን ብዙ ነገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ ወደብ እንደማንኛውም አገልግሎት አይደለም - ዕቃ ወደሀገር ለማስገባትና ለማውጣት ብቻ የሚጠቅም ሳይሆን ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም በቅርቡ በፃፉት ጽሑፍ እንደሚጠቅሱት ዓለማቀፍ ተሰሚነትን በተወሰነ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ በባህር ውስጥ ያለ የታወቀም ያልታወቀም ሀብት ባለቤት የሚያደርግ፣ … ወዘተ ነው። ሁለተኛ - አቶ መለስ የሚያወራው ስለምን ገንዘብ ነው?! ኢትዮጵያ እንደሁ ገንዘብ አለኝ ብላ ጉራዋን ብትነዛ ዓለም የሚስቅባት ደሃ ሀገር ነች። የራሳችን ወደብ ሊኖረን ሲገባ እሰው ወደብ ላይ ሄደን ገንዘብ ምን አስፈሰሰን? ያን ገንዘብ ለሕፃናቱ ዳቦ መግዣ ብናረገውስ ወይም ተጨማሪ ዶክተሮች ማፍሪያ? ገንዘብ ቢኖረን እንኳ ወደብን የመሰለ ሀብት ተወርውሮ አይጣልም።

 

ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ንግግሩ ብቻ የሚያሳየን ሰውየው ማንም ተራ ሰው ሳይማር እንኳ ሊያውቀው የሚችለውን ነገር እንደማያውቅ ነው። ያ ካልሆነና “ኧረ! እሱ አዋቂ ነው” ብላችሁ የምትሉኝ ተሆነ ደግሞ፤ እንግዲያውስ አውቆ የተኛና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ሳይሆን ለጥፋትዋ ዓላማ ያለው ሰው ነው ማለት ነው።

 

ገንዘብ አለን እያለ ሲታበይ የሰነበተው ሰው፣ በየዓመቱ ለጅቡቲ ወደብ ክፍያ ቡና ሽጠን ከምናገኘው ገንዘብ የበለጠ እየከፈለ ከርሟል። ያም ዋጋ ደግሞ ሳያንስ ጅቡቲ አንድ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በፈለገች ቁጥር ዋጋ ጭማሪ አደርጋለሁ እያለች እንደምታስፈራራው ባለፉት ወራት አየን። በዛኛው ጊዜ ለፕሬዝዳንቱ የእርሻ መሬት ተሰጥቷቸው ዝም አሉ፤ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ምን እንደሚፈልጉ አናውቅም። ወጣም ወረደ የትንሿ ጅቡቲ እግር ሳሚዎች ሆነን ቁጭ ብለናል። በተጨማሪም የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተሟጦ አልቆ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ዕቃ ከውጪ ማስገባት ተስኗቸዋል።

 

የግል ባህሪውስ?

 

ከመንግሥት ጋር በቀጥተኛ መንገድ ስለተያያዘው ሥራው ስናወራ ይህን ካልን ስለግል ባህሪውስ? ከአንድ ሀገር መሪ የሚጠበቁ ባህሪዎች ምንድን ናቸው? እንግዲህ በባህል፣ በኃይማኖት እና ባጠቃላይ ተቀባይነት ባላቸው አስተሳሰቦች ላይ በመመስረት ብንመዝነው፦ የአንድ ሀገር መሪ ቢያንስ ቢያንስ ስነሥርዓተኛነት፣ ህዝቡን ባንድ ሃሳብ ዙሪያ የማሰባሰብ ችሎታ ያለው፣ የህዝቡ አጽናኝ እና አበረታች እንጂ መንፈሱን ሰባሪ ያልሆነ፣ ታላላቆቹንና የህዝብን ተወካዮች የሚያከብር፣ ሀገርና ህዝብ ወዳድ፣ በህዝቡ መሃል በመልካም ሥራው የተመሰገነ፣ ቸር፣ … ወዘተ መሆን ይጠበቅበታል።

 

አቶ መለስ በነዚህ መስፈርቶች ሲለካ ስንት ኪሎ ይወጣው ይሆን?

 

ስለ መለስ ባህሪ ሲጠቀስ የማይታለፈው አንድ ነገር ተሳዳቢነቱ ነው። ይህ እንኳን ካንድ መሪ ራሳቸውን ከሚያከብሩ ተራ ዜጎች የማይጠበቅና፣ በተለይ ደግሞ በባህላችን አስኮናኝ የሆነ ነው። ከዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው ባንድ ወቅት በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ላይ ፓርላማ ውስጥ “ሞኝና ወረቀት …” የሚለውን አባባል መጠቀሙ ነው። ዶ/ር ነጋሶ በዕድሜ እሱን ከመብለጣቸውም ባሻገር በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ እና ለመሰደብ የሚያበቃ ምንም ወንጀል ያልፈጸሙ ሰው ናቸው።

 

ስለመለስ ሀገር ወዳድነት ሲነሳም እርግጠኛ ሆኖ ሀገሩን ይወዳል ብሎ ለመናገር የማያስችሉ ነገሮችን አድርጓል። ከሉዓላዊነት ጋር በተያያዙ ካደረጋቸው ውሳኔዎች በተጨማሪ ስለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ “ጨርቅ ብቻ” መሆን የተናገረው ነገር የሚጠቀስ ነው። እዚህ ጋርም ሰውየው ሀገሩን ወደደም አልወደደም፤ እንዲሁም ደግሞ ስለባንዲራ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይቺን ሀገር ለሆነ ምክንያት መምራት የፈለገ ሰው የሀገሪቱን መለያ ምስል በማጥቃት የአመራር ጊዜውን መጀመሩ ጨቅላነትን እና የጥበብን ጉድለት የሚያሳይ ነው። ይኽው ዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት ከሞላው በኋላ “የባንዲራ ቀን” ሰይሞ ባንዲራ ለህዝቡ ማከፋፈል ጀምሯል - መንቃቱ ነው እንግዲህ በሱ ቤት።

 

እንዲህ ያሉት ባህርያት በአንድ መሪ ላይ ሲታዩ የጥበብ ጉድለት ምልክት ነው። ምክንያቱም በህዝብ ዘንድ ክብርን ያሳጣልና። በህዝብ ዘንድ የማይከበርና የማይወደድ መሪ ደግሞ ህዝቡን ለሥራ ወይም ለማንኛውም ዓላማ ባንድነት ማሰባሰብ ይቸግረዋል።

 

ማጠቃለያ

 

እርግጥ ነው፣ መለስ ዜናዊን በወሬ እና በአሽሙር የሚወዳደረው ኢትዮጵያዊ አይኖር ይሆናል። ወሬ እና ነገር ግን በጥበብ እና በተጨባጭ ዕውቀት ካልተደገፉ ፋይዳ የላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ወሬ በልቶ ከሞት መዳን ይችላል? - አይችልም! የመለስ ወሬ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ትምህርት፣ ደህንነት እና ሥራ ሊሆን አልቻለም! የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተዋጊ ሹል ምላስ በረሃባችንና በድህነታችን ላይ ቢያነጣጥር ደስ ባለኝ/ን! እንዳውም ለምላሱ ብቻ ኃውልት እንሠራለት ነበር! ነገር ግን ምላሱ ያነጣጠረው በባዱ ሜዳ ወይም በኛ ላይ ከሆነ ጥቅሙ ምንድን ነው?! ረሃብና እርዛት እየተፈራረቁ የቀጠቀጡን ሳያንሰን!

 

ኦክቶበር 6 ላይ በታተመው የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ “Gossip” በሚባለው ክፍል፣ መለስ ከውጭ ሀገር ለመጡ የጦር መኮንኖች ንግግር ሲያደርግ ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ካቀዳቸው ዕቅዶች ውስጥ አንዱን ሲያስረዳ፣ አስር ሺህ ገበሬዎችን በዘመናዊ ተክኖሎጂ አሠራር አሠልጥኖ እነሱ ደግሞ እያንዳንዳቸው አስር ሰዎች እንዲያሰለጥኑ እንዳቀደ መናገሩን አንብቤአለሁ። ለመሆኑ ይህ ሰው ቃል ሲገባ የመጀመሪያው ጊዜ ነው ወይ? ከዚህ በፊት ረሃብን ስለማስወገድ ገብቶት የነበረው ቃል የት ደረሰ? ወድቆ የለም ወይ? ስለውድቀቱስ ማብራሪያ ሰጥቷል ወይ? የዛሬ ሦስት ዓመት ኢንተርኔትን በመላው ኢትዮጵያ በማስፋፋት ህዝቡን ከድህነት ስለማውጣት የገባው ቃል የት ገብቷል? ዕቅድ ሁልጊዜም ሙሉ በሙሉ አይሟላም የሚለው ክርክር እዚህ ጋ ፈጽሞ አይሠራም! ምክንያቱም 80 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሀገር ከአርባ ሺህ በታች የሆኑ የኢንተርነት ተጠቃሚዎች ማስመዝገብ ዕቅዱ ጨርሶውኑ ከተነሳበት ፈቀቅ ስለማለቱ የሚያሳየው ፍንጭ ስለሌለ!

 

ከተሰበሩ ቃል-ኪዳኖችም ባሻገር፣ ይህ ሰው እንደዚህ በሰዎች ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ዕቅድ ሲያወጣ፣ ህዝብን አስተባብሮ ለሥራ መነሳሳትን ለማስፈን የሚያስችል ተወዳጅነት አለው ወይ? መልሱ “የለውም!” ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መለስን እንደ ጠላት በሚያይበት ደረጃ ላይ ነው ያለው።

 

አቶ መለስ ዜናዊ ላለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመራ የሀገሪቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ዕድል ተሰጥቶት ነበረ። በነዚህም ዓመታት ሀገሪቱ ካላት የተፈጥሮ ሀብቶች እና የሰው ኃይል በተጨማሪ፣ ከሱ ቀደም የነበሩ መንግሥታት አግኝተውት የማያውቁትን ያህል የውጭ ዕርዳታ ባገሪቱ ስም ሰብስቧል። በየጊዜው አንድ ነገር እየተናገረ፣ እየወደቀ፣ ለሱኛው ማብራሪያ ሳይሰጥ እና ራሱን ለተጠያቂነት ሳያቀርብ ሌላ ቃል ይገባል ወይም የቀድሞውን ይደግማል። ኢትዮጵያ የግል ላቦራቶሪው፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሙከራዎቹን የሚያደርግባቸው ጊኒ ፒጎች ይመስሉ ውጤት አልባ የሆኑ ሃሳቦቹን ሲሞክርብን ከርሟል። እሱም ሆኖ ደግሞ ተምሮ ቢሻሻል መልካም ነበር፤ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል።

 

ስለዚህም እንኳን ሀገሪቱን ከድህነት ማጥ ለማውጣት፣ ራሱ የተናገራቸውን ብዙ ነገሮች የማድረግ ብቃት እንደሌለው አስመስክሯል። ለአንድ መሪም የሚያስፈልገውን ዕውቀትና ጥበብ እንደሌለው አሳይቷል። እዚህም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ዙፋኑ ቀንድ እስኪያወጣ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም። የአቶ መለስ አድናቂዎችም ምን እንደሚጠብቁ አላውቅም። እራሱ አቶ መለስም ቢሆን ያለፉትን አሥራ ስምንት የሥልጣን ዓመታቱ ምን ይመስሉ እንደነበር አይጠፉትምና፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከዚህ በኋላ ወዴት ሊመራቸው እንዳሰበ ቆም ብሎ ራሱን የመጠየቅና ሥራዎቹን የመፈተሽ ድፍረቱ ሊኖረው ይገባል።

 

ይህ ድምዳሜ ሊያከራክር የሚችልበት ብቸኛው ሁኔታ ከላይ እንደጠቀስኩት አቶ መለስ አውቆ የተኛና፣ ብዙዎች እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያን የማጥፋት ዓላማ ያለው ሰው ከሆነ ብቻ ነው።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ