ከፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም (መስከረም ፳፻፩ ዓ.ም.) 

ጥንት ስለአፍሪካ ጥሩ ነገር፣ ጥሩ ተስፋ ብቅ የሚለው ከወደ ምሥራቁ በኩል ከኢትዮጵያ ነበር። የአፍሪካ ደቡቡ ገና የኢትዮጵያ የነፃነት ጮራ ሊፈነጥቅበት እየሞከረው ነበር። በኬንያና በታንዛንያ በኩል አድርጎ፣ በዛምቢያና በዚምባብዌ ወደ ዘረኛው የጎሣ አገዛዝ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሙቀቱንና ብርሃኑን ማሰማትና ማሳየት ጀምሮ ነበር። ኔልሰን ማንዴላ በጎረምሣነታቸው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኢትዮጵያን የነፃነት ሙቀትና ብርሃን ፈልገው ነበር።

 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተቋቋመበት ሌሊት፣ አጼ ኃይለሥላሴን ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ጋር፣ አብዮታውያን ከሚባሉት ከእነናስር እና ቤን ቤላ ጋር፣ እንደ ኒዬሬሪና ኑክሩማ ያሉ ጋር፣ እንደ ኤዲ አሚን ያለውም ጋር ቆመው ሲነጋገሩ፣ ቁመታቸው በጣም ረዥም መስሎ ይታይ ነበር። አብዛኛዎቹ መሪዎች እንደ ትንሸ ልጅ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አድርገው ጎንበስ እያሉ ነበር የሚያነጋግሩአቸው። የአፍሪካ አንድነት ሠነድ ያለአጼ ኃይለሥላሴ የመንፈስ የበላይነት በምንም ዓይነት መንገድ አይፈረምም ነበር። የዓይን ምስክር ነኝ፤ ይህንን ሠነድ ሳንፈርም ከዚህ አንወጣም አሉ፤ አጼ ኃይለሥላሴ የተጣሉት ሁሉ ታረቁና ሁሉም ፈረመ። ያን ሌሊት በኢትዮጵያዊነቴ የተሰማኝ ኩራትና ደስታ ከፍተኛ ነበር። ይህንንም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ሥም በጽሑፍ በእጃቸው ሰጥቼአቸዋለሁ። ብዙ ጊዜ ለጥሩ ሥራና ለጥሩ ውጤት ዋጋውን መስጠት ያቅተናል።

 

ይኸው የአጼ ኃይለሥላሴ መንፈስ የበላይነት ነበር በምሥራቅ አፍሪካ፣ በሱዳን፣ በሞሮኮ አስታራቂ ያደረጋቸው። በሥራቸው ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ ሰዎች፣ በምድረ ኢትዮጵያ እንዳይበቅል ባይፈልጉም አምባሣደር ዘውዴ ረታ ምሥጋና ይግባውና፣ አፍሪካዊ ስብዕና በተናቀበት ዘመን፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የታላላቅ ኃይሎቹን መልዕክተኞች ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ላይ ሽንጣቸውን ገትረው እንደተሟገቷቸው አውቀናል። በስፖርቱ መድረክ ደግሞ ይድነታቸው ተሰማ፣ ለአፍሪካዊነት ሰውነትና ክብር፣ የደቡብ አፍሪካን የነጭ ዘረኛነትና የጎሠኛነት ሥርዓት፣ በዓለም መድረክ በማጋለጥና ደቡብ አፍሪካ እንዲገለል በማድረግ ያደረገው ትልቅ አስተዋጽዖ ብዙም አይታወቅ። በጦር ሜዳውም ቢሆን በኮሪያና በኮንጎ በዓለም ደረጃ ሥማቸው የተጠራ መኮንኖችን አሳይተናል።

 

ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች፣ ይችን የሚያኮሩ ሰ¬ዎች የነበሩባትን ኢትዮጵያ አያውቋትም። በትንንሽ ሰዎች ከተወረረችና በዕቅድ የሰው ምድረ በዳ ከሆነች በኋላ የደረሱ ናቸው። በሐሰት ስብከት አዕምሮአቸው እንዲደነዝዝና ኅሊናቸው በችግር እንዲተበተብ ተደርገው በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በዚምባብዌ የተደረጉትን ምርጫዎች እያዩና እየሰሙ፣ በአፍሪካዊነታቸውና በሰውነታቸው እያፈሩ፣ አንገታቸውን እንዲደፉ ቢገደዱም ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል የሚያዩበት የአፍሪካ ሀገር መኖሩ የሚያስደስትም የሚያስቀናም ነው።

 

ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ምቤኪ ያለ ምንም ግርግርና ማንገራገር ወንበራቸውን ለቀቁ። ምክትል ፕሬዝዳንታቸው በሙስና ተከስሰው ፍርድ ቤት ቀረቡና ፍርድ ቤቱ ነፃ ሲያወጣቸው፣ ዳኛው በስላጭም ቢሆን ፕሬዝዳንቱ በሕጉ ሥርዓት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል የሚል ነገር በመናገራቸው፣ በሕግ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ መግባት፣ የሀገሩን ጤና የሚያቃውስ በመሆኑ ፓርቲያቸው ወንበራቸውን እንዲለቅቁ ጠየቃቸው፤ ምቤኪም ሳያቅማሙ ተቀብለው ተሰናበቱ። ሕግ ለሁሉም ዜጋ ነው፤ ለሁልጊዜም ነው። አንድ ሰው በሁሉም ነገር ቢሆን የተወሰነ ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የቅንጅት ሰዎች ከመከሰሳቸው በፊት፣ ክሱን ብቻ ሣይሆን ፍርዱንም በቴሌቪዥን ተናግሮታል። ምን ሆነ? ለእኔ አሁን ዋናው ፍሬ ነገር ይህ አይደለም።

 

የኢትዮጵያ የነፃነት ጮራ ደቡብ አፍሪካ ደርሶ ፍሬ አፍርቶ፣ ማንዴላን አበቀለ፤ ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንዲሉ ማንዴላ በመንፈስ ልዕልና አጼ ኃይለሥላሴን በለጡ። የማንዴላ የመንፈስ ልዕልና ጥሩ መሠረት እንደጣለ፣ በደቡብ አፍሪካው ፓርቲ ውሳኔና በምቤኪ ስንብት ተረጋገጠ። የአፍሪካ ነገር ያጠራጥራልና ከዘለቀ። ነገር ግን ለጊዜውም ቢሆን በአፍሪካ ውስጥ አርቀው ለህዝብና ለታሪክ የሚያስቡ ጥቂት ሰዎች መኖራቸው፣ በጥቁሩ ጨለማ የአፍሪካ ምድር ላይ የተስፋና የነፃነት ብርሃን ይፈነጥቃል። የታሪክ አካኼድ ቀኝ-ኋላ ዙር ብሎ የተስፋና የነፃነት ብርሃን ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ አቃንቶ መታየቱ የሚያሳዝንም የሚያስደስትም ነው።

 

የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ለመላው አፍሪካ ያቀጣጠልነውን የነፃነት ብርሃንና የደፋንለትን የክብር አክሊል፣ እኛ የኋሊት መኼድን መርጠን ማጣታችን ነው። ገበናችንን የሸፈነልን ጋቢ ተቀዳዶ፣ ታሪካችን የመንፈስ ኃይሉን አጥቶ፣ ከችጋር ጋር ብቻ እየታገልን በምጽዋት የምንኖር ህዝብ ሆነናል። አጼ ኃይለሥላሴ በአፍሪካ የጫሩትን የነፃነት ብርሃንና ያሳዩትን የመንፈስ የበላይነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፈጉት። በዚህም ምክንያት ዛሬ የውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋ ለመሆን የሚጥሩት ያም አቅቷቸው የውስጥ ቀጋ፣ የውጭ ቀጋ ሆነዋል።

 

የሚያስደስተው አንድ የአፍሪካ ሀገር ውስጥ በሕጋዊ ሥርዓት የሚመሩ መሪዎች መገኘታቸው ነው። ይህ አፍሪካን ፍጹም ጨለማ ከመሆን አድኗታል። በደቡብ አፍሪካ መሪዎች እንድንቀና ግዴታ ሆኖብናል። በደቡብ አፍሪካ የዘነበው አንድ ቀን በእኛም ዘንድ ያካፋል ብለን ተስፋ እንድናደርግ ረድቶናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ