ሙሉ ካሣ (ቶሮንቶ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

“… የሚያሳዝነውም የሚያሳፍረውም በአሁኑ ሰዓት በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ እየረገፈ ባለበት ወቅት ጎራ የለዩ ሁለት ቡድኖች ለጠገቡ ጠበቆች እስከ አሁን $20000 አፍስሰዋል። ወጭው ገና ይቀጥላል። ጎበዝ ይህን ኃላፊነት የጎደለውን እኩይ ተግባር የምትቀጥሉበት ከሆነ የወያኔ/ኢህአዴግን ተዕልኮ በማሳካት በኩል ላደረጋችሁት አስተዋጽዖ እና ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ወያኔ/ኢህአዴግ በጀት እንዲመድብላችሁ የመጠየቅ መብት ያላችሁ ይመስለኛል። …”

 


በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ያሉ መምህራን የረሃብን አስከፊነት ለተማሪዎቻቸው ለማስረዳት ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ማቅረባቸው የተለመደ ነው። ከስድስት ዓመት በፊት የዛኔ የሰባት ዓመት የነበረችው የጓደኛዬ ልጅ አስተማሪዋ ረሃብን በተመለከተ ስታስተምር በኢትዮጵያ የደረሰውን ስቃይና አሁንም ከዚያው መከራ አለመላቀቃችንን ስትመልስ በአጋጣሚ አባትዋ ጋር ነበርኩና እንባ እየተናነቃት “በእውነቱ ዛሬ በጣም አፈርኩ፤ እንዴት ሀገራችን ሁልጊዜ የረሃብ ምሳሌ ትሆናለች? ለምን መንግሥት መፍትሔ አይፈልግም?” ነበር ያለችው - በሕጻን አንደበቷና ምንም ባልበከለው ህሊናዋ። አባቷም ሆነ እኔ በቂ መልስ አልነበረንም አሁንም ያለኝ አይመስለኝም። በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል እያልን በየጊዜው የምናወግዛቸው ሦስቱን ሥርዓቶች (የመሣፍንቱን፣ የደርግንና የወያኔ/ኢህአዴግን) እንተዋቸውና እኛ በግል ደረጃም ሆነ በሀገሪቱ ለውጥ ማምጣት አለብን ብለው “የሚታገሉት” ድርጅቶች ለመሆኑ ምን እያደረግንና እያደረጉ ነው?

 

ሦስቱንም ሥርዓቶች ማውገዙ ብቻ የሚፈይድ ቢሆንማ ከኔ በብዙ የተሻሉ አንደበተ ርቱዕ በርካታ ወገኖች የሰላውን ብዕራችውን ካነሱ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። አዎ! የአገዛዝ ሥርዓቱ እስካልተቀየረና ህዝቡ በሕይወቱ የመወሰን ባለቤት እስካልሆነ ድረስ ከረሃብም ሆነ ከሌላ አስከፊ መከራ እንዲህ በቀላሉ መገላገል አይቻልም። ለዚህም ደግሞ ሁላችንም በግልም ሆነ በቡድን የምናደርገው እንቅስቃሴ ወሳኝነት ይኖረዋል። ባሁኑ ጊዜ በከንቱ የምናባክነውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በአግባቡ ብንጠቀምብት የህዝባችንን የመከራ ጊዜ ባሳጠርነው ነበር።

 

አንድ ግለስብ ለብቻው ጉልበቱን፣ ጊዜውንና ገንዘቡን ቢያበረክት ችግሩን በትንሹም የመቅረፍ አስተዋጽዖ ቢኖረውም ዘላቂና አመርቂ ውጤት ማምጣት ግን አያስችልም። ስለዚህም በቀናነትና በቁርጠኝነት ለጋራ ዓላማ የሚሠሩ በርካታ ዜጎችን ሕብረት ይጠይቃልና ወደዚያው ብናተኩር ይሻላል። ውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የጨለመው የሀገራችን ሁኔታ እያሳሰበን በግልም ሆነ በቡድን ሁኔታዎች እንዲቀየሩ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ ሞክረናል። አለመታደል ሆኖ በጥሩ የጀመርነው ሁሉ ፍጻሜው አስከፊ ለአንዳንዶች ተስፋ አስቆራጭ ሲሆን ይታያል። ትኩረታችን በጊዜው ካጋጠመን፣ ስሜታችንን ከነካን ጉዳይ ይሆንና ወደ መጨረሻ ዓላማችን መዳረሻ መንገዳችንን ብዙ ጊዜ እንስታለን። በመደናቀፋችንም ተስፋ ቆርጠን እንቀመጣለን።

 

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ በርካታ አካባቢዎችን መጥቀስ ቢቻልም ያለሁባት የቶሮንቶ ከተማ በአብይነት ልትጠቀስ የምትበቃባቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች ስላሏት ትኩረቴ ወደዚችው ውብ ከተማችን የኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ይሆናል። በካናዳ ነዋሪ የሆነው በአስር ሺህዎች የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊ በሀገሩ የተንሰራፋውን አምባገነናዊ ሥርዓት ለማስወገድ በሚደረገው ትግል የበኩሉን አስተዋጽዖ አድርጓል። በተለይም ምርጫ በ97 ቅንጅት የነደፈውን ፕሮግራም እንደተሻለ አማራጭ በመውሰድ ቅንጅት ድልን ይጎናጸፍ ዘንድ ከመቶ ሺህ ዶላር ያላነሰ ዕርዳታ ቶሮንቶ በሚገኘው ድጋፍ ቢሮ አማካኝነት ከደጋፊዎች ተሰብስቧል። አምባገነኑ ወያኔ/ኢህአዴግ የህዝብን ድምፅ ዘርፎ ባለድል መሪዎችን ለእስር ሲዳርግ የቶሮንቶና አካባቢው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምሬቱን ለመግለጽ የክረምቱ በረዶ ሳያግደው የታሰሩ መሪዎች እንደፈቱ ባንድነት ተቃውሞውን አሰምቷል።

 

የአንድነት ትግሉ ከቅንጅት መከፋፈል ጋር አከተመ። ቡድናዊ ጎራ ለየ። ተክል ሰውነት እንጂ መርኅ አፈር በላ። በተለየው ጎራ ሳቢያ እንካ ስላንትያው በየድረ ገጹ ሳይቀር ተራ ዘለፋዎችና ስም ማጥፋቶች በብዕር ስሞች ተዥጐደጐዱ። “ሃይ!” የሚል ጠፋ። በሁለቱም ቡድኖች ውስጥ አንቱ የሚባሉ የኮምዩኒቲ ታዋቂ ግለሰቦች ቢኖሩም ከአቅም በላይ ሆነ መሰል ምሬቱ ጎለበተ። ማኅበራዊ ግኑኝነቶች ሁሉ እንዳልነበሩ ሆኑና በጎሪጥ መተያየት ነገሠ።

 

ጎራ መለየቱም በእነሱ አልተጀመረ፤ ባይለያዩ ፍላጎታችን ነበር፣ ለመዘላለፉም እነርሱ ብቻ አይደሉም ድፍን ፖለቲከኛ ዋነኛ የትግል ስልቱ ካደረገው ዓመታትን ቆጥረናል። ባይዘላለፉና የሠለጠነውን የፖለቲካ ባህል በስደት ከሚኖሩባት ሀገር ቢቀስሙ እንዴት በወደድናችው። በጎሪጥ ለመተያየቱ ለልጆቻቸው ምን መልስ እንደሚሰጡ ካልቸገራቸው ለእኔ ግድ የለኝም። “አባዬ ለምንድን ነው እነጋሽ እከሌን ሠላም ብለህ እነጋሸ እከሌን ዝም ያልካችው? ድሮ እቤታችንም ይመጡ ነበር፤ አሁን አሁን ደግሞ እንኳን ሊመጡ ስልክም አይደውሉ። ምን ሆናችሁ?” መልስ ካላችሁ እሰየው!! ውሸት ግን እንዳታስተምሯቸው፤ አደራ!

 

በየአካባቢው ያለን ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ እስከአሁን ያስገረመን ጉዳይ መከፋፈሉ፣ መሰዳደቡ ወይም በጠላትነት መተያየታችሁ አይደለም። የደለቡ የቤይ ስትሪት ጠበቆችን ቀጥራችሁ የፍርድ ቤት ሙግት መጀመራችሁ ነው። “እኔን እኔን” ይላል አንድ የቅርብ ጓደኛዬ እንዲህ ነገር ቢጤ ስትገባው። ለመሆኑ በማን ገንዘብ ነው ሙግት የጀመራችሁት? ደጋፊዎች የገንዘብ አስተዋጽዖ ያደረግነው በውስጣችሁ ያሉትን ጥቂት “ከኔ በላይ ለአሳር” የማናለብኝነት አባዜ የተጠናዎታቸውን ግልሰቦች የሥልጣን ሩጫ ለማሳካት ሳይሆን የቅንጅትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ፤ እስሩን፣ ግርፋቱን፣ ስደቱንና አጠቃላይ በወያኔ/ኢህአዴግ እመቃ የሕይወት መስዋትነት በመክፈል ላይ ላሉ ወገኖች እንጅ።

 

ክሱ ”የቅንጅትን” ስም መጠቀም አትችሉም። ቀድመን የተቋቋምን ስለሆንንና ስሙንና ዓርማውን ያስመዘገብነው እኛ ነን ይላሉ ከሳሽ የኢንጅነር ኃይሉ ቡድን ደጋፊዎች ነን ባዮች። ይህን ክስ እንዲሞግቱ ታዋቂ ጠበቃ በ$10000 (አስር ሺህ የካናዳ ዶላር ወይም የኢትዮጵያ መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ) መድበዋል። ተከሳሾች የወ/ት ብርቱካን ደጋፊ ነን ባዮች ሲሆኑ፣ እነርሱም እንዲሁ የቀረበባቸውን ለመከላከል ጠበቃ አቁመዋል። ተመሳሳይ ገንዘብ ለጠበቃው እንደሚከፍሉ ይጠበቃል። የሚያሳዝነውም የሚያሳፍረውም በአሁኑ ሰዓት በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ እየረገፈ ባለበት ወቅት ጎራ የለዩ ሁለት ቡድኖች ለጠገቡ ጠበቆች እስከ አሁን $20000 አፍስሰዋል። ወጭው ገና ይቀጥላል። ጎበዝ ይህን ኃላፊነት የጎደለውን እኩይ ተግባር የምትቀጥሉበት ከሆነ የወያኔ/ኢህአዴግን ተዕልኮ በማሳካት በኩል ላደረጋችሁት አስተዋጽዖ እና ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ወያኔ/ኢህአዴግ በጀት እንዲመድብላችሁ የመጠየቅ መብት ያላችሁ ይመስለኛል።

 

ለመሆኑ ዓርማው በአቶ ልደቱ አያሌው ለሚመራው ኢዴአፓ-መድህን፤ ስሙ ደግሞ ለአቶ ጫሚሶ መሰጠቱን እነዚህ የቶሮንቶ ቡድኖች አልሰሙ ይሆን? በኋላስ የሚወክሏቸው ደርጅቶች ኢንጂንየሩ ወደ ቀድሞው ድርጅታቸው “መኢአድ” እንዲሁም ወ/ት ብርቱካን “አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ” በተሰኘ ፓርቲ እየተንቀስቃሱ መሆናቸውን መመሪያ አልደረሳቸው ይሆን? ከሃያ ሺህ ዶላር በላይ ለጠገቡ ጠበቆች ለእርስ በእርሱ ጥላቸው በመከስከስ ላይ ያሉ ቡድኖች በምን የሞራል ብቃት ስለኢትዮጵያ ችግርና ረሃብ መናገርስ ይችላሉ? በጽሑፌ መጀመሪያ ላይ ስለሀገሯ ያፈረችውንና የተቆጨችውን የጓደኛዬን ልጅ ህሊና አንድ መቶኛውን ያህል ይኖራቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁን?

 

ኢንጂንየር ኃይሉን በቪደዮ ከሚኒሶታ መኖሪይ ቤታቸው ሆነው ቶሮንቶ ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ያስተላለፉትን መልዕክት ተከታትለናል። አበረታች መልዕክት ነበር። አንዳንድ ደካማ ደጋፊ ነን ባይ ግለሰቦች በኢንጂንየር በአካል መገኘት አለመቻል ጋር ቁጭት አዘል ቃላትን በአዳራሹ ለተገኘን ሰዎች ማስተጋባት መሞከሩ እንደ ድጋፍ ሰጭ አካል ጽ/ቤታቸው ፈርጀ ብዙ ችግር እንዳለበት ይጠቁመናል። ወ/ት ብርቱካን እና ዶ/ር ብርሃኑም በተለያየ ወቅት በከተማችን ተገኝተው መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈው ተመልሰዋል። የሁሉም መልዕክት በጋራ ሆነን አስከፊውን ሥርዓት መታገል እንዳለብን ከፍተኛ ማሳሰቢያ ያዘለ ነበር።

 

በመጨረሻም ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በተለይም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያከብርን እንጂ የሚጣላና የሚከፋፍል አንሻም። ተባብረንም ቢሆን የሚከብድ ሀገራዊ ዕዳ እያለብን አቅማችን ባልሆነ ቦታና ሁኔታ አይባክን። ጉልበታችን፣ ገንዘባችንና ጊዜአችንን ለመከፋፈልና ለማዳከም መዋል የለበትም። ለመጥፊያችን በጀት ከወያኔ/ኢህአዴግ ጠይቁ እንጂ በእኛው ገንዘብ ልታጠፉን አትሞክሩ። መሰል ወገናችሁን ለማጥቃት ገንዘብ የምትሰጧቸው ጠበቆች በቂልነታችሁ፣ በደንቆሮነታችሁ እንደሚስቁ ካለተረዳችሁ ሊታዘንላችሁ የሚገባ ሕመምተኞች መሆናችሁን ይነግረናል። ከአሁን በኋላ የምትጫወቱበት ገንዝብ አንለግሳችሁም። ይልቁንም ለድርጅቱ የተሰበሰበው ገንዘብ ሁሉ ምን ላይ እንደዋለ የማዎቅ መብት ያለን በመሆኑና እናንተም ከህዝብ የተሰበሰበን ገንዘብ አስተዋጽዖ ላደረጉት ብቻ ሳይሆን መዝግቦ ፈቃድ ለሰጣችሁም መንግሥታዊ አካል በየወቅቱ የኦዲት ዘገባ ማቅረብ ግዴታችሁ መሆኑን አውቃችሁ በተቻለ ፍጥነት በነፃ አካላት ኦዲት የተደረገ ሪፖርት እንድታቀርቡ እጠይቃለሁ።

 

ድርጊታችሁ አስጨንቋቸው ክሱን ታቆሙ ዘንድ ሽምግልና ተቀምጠው ለነበሩት የከተማችን የኮምዩኒቲ መሪ፣ የቤተክህነት አስተዳዳሪ እና ለሌሎች ግለሰቦች ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት እየገልጽሁ፤ ምንም እንኳን በከሳሽ ወገን እምቢ ባይነት የዕርቁ ሂደት ቢቋረጥም ጥረታችሁ የመላው ቶሮንቶ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ያለው በመሆኑ ሽምግልናው እንደገና እንዲጀመር አደራ እላለሁ። ድጋፋችንም አይለያችሁም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ