ወንድም እህቶቻችን የት አሉ?
ግርማ ካሳ

ሁለት ወንድማማቾች ናቸው። ቃየን እና አቤል ይባላሉ። በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ላይ የተጻፈው ነው። “ቃየን አቤልን ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ አቤል ላይ ተነሳበት። ገደለውም” ይለናል ቃሉ። ደም ፈሰሰ። የወንድም ደም በወንድም እጅ። እግዚአብሔር በሆነው ነገር አዘነ። ለቃየንም ጥያቄ አቀረበለት። “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። ቃየንም መለስ “ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” አለ።
የቃየን መንፈስ ደም የማፍሰስ መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ የጥላቻና የክፋት መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ምን አገባን የሚል መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ ከተማ፣ ሀገርን እና ህዝብን የሚያጠፋ የተረገመ መንፈስ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ የቃየን መንፈስ ሥር ሰዶ የብዙዎቻችንን አይምሮና ልብ የሰለበበት ሁኔታ ያለ ነው የሚመስለው። በምንኖርበት ቦታና በመስሪያ ቤቶቻችን በየጊዜው ግፍ እየተፈጸመ “እኔ ላይ እስካልደረሰ ድረስ እኔ ምን አገባኝ? እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን” ብለን ዝምታን የመረጥን እጅግ በጣም ብዙዎች ነን። ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን የምናምን ነን። ቤተ ክርስቲያናትን፣ የተለያዩ የጸሎት ቤቶችን እናዘወትራለን። ጥሩ ነው። ተገቢም ነው። ሆኖም እግዚአብሔርን ማምለክና መውደድ ሰውን ከማገልገል ጋር የተቆራኘ መሆኑን ግን በጣም ዘንግተናል። እግዚአብሔር “ወንድሞቻችሁ፣ እህቶቻችሁ የት አሉ?” ነው የሚለን።
ከራሳችን አልፈን፣ ወደ ጎን ወደ ወንድሞቻችን የማንመለከት ከሆነ፣ የተጎዱትንና የወደቁትን የማናነሳ ከሆነ፣ የፈለገ መንፈሳዊ ተግባራትን ብናደርግ፣ የፈለገ ያሬዳዊ ዜማ ብንቀኝ፣ የፈለገ ቴዎሎጂ ተምረን ግሪክና እብራይስጥን ብንተረጉም፣ የፈለገ የቤተ ከርስቲያን ሹመት ቢኖረን፣ የፈለገ ሁዳዴና ፍልሰታን ብንጾም፣ የፈለገ በየከተሞች የሚደረጉ መንፈሳዊ ኮንፈራንሶችን ብንካፈል … በጌታ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም። የተለያዩ ኃይማኖታዊና መንፈሳዊና ውጫዊ መገለጫዎች ለብቻቸው እግዚአብሔርን አያስደስቱትም። በኢሳያስ ምዕራፍ አንድ ቁጠር 13 እና 14 ላይ እንዲህ የሚል ተጽፏል ፡
«የመስዋታችሁህ ብዛት ለኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር። የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋእትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቢያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃቹህ የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቁርባን ጨምራቹህ አታምጡ፤ እጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው። መባኦቻችሁና ሰንበታችሁንም በጉባዔ መሰብሰባችሁን አልወድም … እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ አይኔን ከናንተ እሰውራለሁ። እሰውራለሁ። ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም» ለምንድን ነው እግዚአብሔር መንፈሳዊ ጉባዔያችንን የሚጸየፈውና ጸሎታችንን የማይሰማው የሚል ጥያቄ ከጠየቀን መልሱ ደግሞ በዚሁ ኢሳያስ ምዕራፍ አንድ ውስጥ ወረድ ብሎ በቁጥር 17 ላይ እናገኘዋለን። «እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል። ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ። የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ። ክፋ ማድረግን ተው። መልካም መሥራትን ተማሩ። ፍርድን ፈልጉ። የተገፋውን አድኑ። ለድሃ አደጉ ፍረዱለት። ስለ መበለቲቱ ተሟገቱ» ይላል።
አንድ ወቅት እስራዔላውያን ጾም ጸሎት አድርገው እግዚአብሔር ፊቱን ያዞረባቸው ጊዜ ነበር። የዚህን ጊዜ እየጾሙ እየጸለዩ ለምን እግዚአብሔር እንደተዋቸው መጠየቅ ጀመሩ። እግዚአብሔርም መልስ ሰጣቸው። ቃሉ እንዲህ ይላል፡ «ስለምን ጾምን? አንተም አልተመለከትከንም። ስለምን ሰውነታችህንንስ አዋረድን፣ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ። በግፍ ጡጫም ተማታላችሁ። እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን? … በእውኑ ይህ ጾም በኔ ዘንድ የተወደደ ነውን? እኔ የመረጥኩት ጾም የበደልን እሥራት ተፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንም ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራንስ ለተራበ ትቆርሱ ዘንድ፣ ስደተኞች ድሆችን ወደ ቤታችህ ታገቡ ዘንድ፣ የተራቆቱትን ብታዩ ታለብሱ ዘንድ አይደለምን?“ (ኢሳ. 58፡ 6 -7)
በሀገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ሁሉ እዚህ ለመዘርዘር በጣም አስቸጋሪ ነው። ከብዛታቸው የተነሳ። ሁላችንም የምናውቀውና የምናየው ነው። በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሃብ የተጋለጡ ናቸው። ብዙዎች በቀን አንዴ ነው የሚመገቡት። የኑሮ ውድነቱ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው። ብዙዎች በጉልበተኞች በግፍና በጭካኔ ተገድለዋል። አሁንም እየተገደሉ ነው። በቅርቡ እንኳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ጎንደር፣ በኮንሶ፣ ሕጻን፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሳይባሉ፣ እንደ ቅጠል ረግፈዋል። ነፍስ የገደሉ በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ ሲመላለሱ ወንጀል ያልሰሩ፣ በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት ፍርድ እየተዛባ፣ ፍትህ ተጓድሎ ከፍርድ ሥርዓቱ ውጭ በግፍ እየታሰሩ ነው። ብዙዎች ከመሬታቸውና እና ከቅያቸው እየተፈናቀሉ ነው። የተወሰኑት መሬታቸው ለልማት ይፈለጋል በሚል፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ ዘር ናችሁ እየተባለ።
ታዲያ ይሄ ሁሉ ግፍ፣ ኢፍትሃዊነትና ጭካኔ በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ፣ “እኛ የወንድሞቻችን ጠባቂ ነንን?“ ብለን ዝምታን ከመረጥን እና የዘመኑ ቃየኖች ከሆንን እንደ ሀገር እንዴት መዝለቅ እንችላለን?
የአሥራ ስድስት ዓመት ወጣት ነበረች። በዘጠና ሰባት፣ በኮተቤ አካባቢ፣ በጥይት ተመታ ወደቀች። ሽብሬ ደሳለኝ። እግዚአብሔር ይጠይቃል። “ሽብሬ ደሳለኝ የት ነው ያለችው?” ይላል። ሠርግ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነበር። ሰላማዊ ሴት ናት። በኦሮሚያ የተነሳውን ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ታጣቂዎች ወደ መንደሯ ገቡ። ተኮሱ። ይች ወጣት ወደቀች። ሻሺቱ ትባላለች። እግዚአብሔር ይጠይቃል ሻሺቱ የት ነው ያለችው? የ28 ዓመት ወጣት ነው። የቤት አስተዳዳሪ። በአምቦ እርሱም በጥይት ረገፈ። ፡ግርማ ረጋሳ ይባላል። እግዚአብሔር ይጠይቃል ፤ “ግርማ ረጋሳ ወዴት ነው?” ይላል።
እኛ ግን መልሳችን “የሽብሬ፣ የሻሺቱ፣ የግርማ ረጋሳ ጠባቂ ነንን?” የሚል አይነት ሆኖ ግፍ ተፈጸሞ እንዳልተፈጸመ፣ ከንፈር መጥቶ ዝም ከማለት ውጭ ብዙም ያደረገነው ነገር የለም። የዘመኑ ቃየኖች!!!!
በእውኑ “ቃየንነታችንን”፣ በኛ ወይንም በቤተሰቦቻችን በቤተሰቦቻችን ላይ ችግር እስካልደረሰ ወይንም እኛ እስካልተነካን ድረስ በሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ አይተን ዝም ማለታችን፣ እግዚአብሔር የሚወደው ነገር ነውን? በጭራሽ አይወደውም።
አንድ የተማረ ወዳጄ ከቴክሳስ ደወለ። በጨዋታችን መሃል የሀገር ጉዳይ ተነሳና «አንተ ክርስቲያን ነህ። ፖለቲካ ውስጥ ለምን ትገባለህ? ከፖለቲክ ውጣ። አርፈህ በቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሔርን አገለግል» አለኝ። እኔም መለስኩ። «የኔ ወንድም። አሁን የማደርገው እኮ ክርስቲያን ስለሆንኩኝ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ለፍትህ እንድንቆም፤ ዜጎች በግፈኞች ሲገፉ ለነርሱ እንድንሟገት፣ ድምጻቸው ለታፈነ ድምጽ እንድሆን፣ የተጣሉትን እንዳስታርቅ አዞናል። የሕሊና እሥረኞች እንዲፈቱ የማደርገው እንቅስቃሴና፣ በማንም ይሰሩ የሚሰሩ ግፎችን ማውገዜ፣ ቅዳሴ ከማስቀደስና በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ከመዘመርና ከመስበክ ያልተናነሰ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው» አልኩኝ። ይህ ሰው ሀገር ቤት ትልቅ ቢዝነስ ያለው ወንድም አለው። “እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠየቅህ። አንድ ቀን በሆነ ምክንያት ወንድምህ ቢታሰር፣ ወንድምህ እንዲፈታ በየሰልፉ ቀዳሚ ሆነህ የምትቆም፣ ፔተሽኖችን የምትፈርምና የምታስፈርም፣ በሶሻል ሜዲያ ዘመቻ የምታደረግ አትሆንም ወይ?” አልኩት። “እርሱማ ነው” አለኝ። “ታዲያ የራሳችን የሥጋ ወንድማችን ሲታሰር የምናደርገውን ነገር ሌላው ሰው ላይ ሲደርስ አለማድረግ እና አርፈን መቀመጥ አለብን ማለት ተገቢ ነው ወይ? ራስ ወዳድነት አይደለም ወይ?“ ብዬ ጠየኩ። ይህ ወዳጄ የሚመልሰውን አጣ።
ውድ ወገኖች፣ ብሶት ማውራት፣ ማጉረምረም፣ ነጻነትን እና ፍትህን ሌሎች ጥቂቶች ብቻ ሞተው፣ ጥቂቶች ብቻ ታስረው፣ ሌሎች በከፈሉት መስዋእትነት ለማግኘት መመኘት እና እየደረሰብን ላለው ችግር ራሳችንን ሳንጠይቅ በሌሎች ላይ ማሳበብ የደካሞች መንገድ ነው። የደካሞች ፖለቲካ ነው። ሁላችንም ወደ ራሳችን መመለስ አለብን። ለሀገር ነጻነት ከማሰብ በፊት ነጻነት መጀመር ያለበት ከራሳችን ነው። ራሳችንን በግለሰብ ደረጃ ከፍርሃት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከቃየን መንፈስ ነጻ ስናወጣ፤ የሌላው ሕመም ሲሰማን፣ እጆቻችን ሌላውን ለመገደል፣ ለመደብደብ ሳይሆን ሌላውን ለማንሳት ሲዘረጉ፣ ከናፍርቶቻችን ሌላውን ለመስደብ፣ ለመርገም፣ ለማሳነስና ለማዋረድ ሳይሆን ሌላውን ለማበረታታት፣ ለማጽናናትና ለመባረክ ሲከፈቱ ያኔ በርግጥም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጅማሬ ሆነ ማለት ነው። የሀገር ትልቅነት የሚመነጨው በህዝቧ ትልቅነት ነው። የህዝቧ ትልቅነት የሚመነጨው በእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅነት ነው። የእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅነት የሚመነጨው ሌላውን በማገልገልና ለሌላው በማሰብ ነው።



