ተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

Abay Tsehaye. አባይ ፀሐዬ

ከኦሮሚያ አመጽ ጋር በተያያዘ አባይ ፀሐዬ ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል። አንዳንድ ደንፊ ንግግሮች መናገሩንም ስናነብ ሰነባብተናል። ምን እንደነካው እንጃ እንጂ ጠባዩ እንኳ እንዲያ አልነበረም። አባይ በጠባዩ ድመት መሆኑ ነበር የሚታወቀው። ሊያጠቃ ሲፈልግ እንደ ፈረስ ጋማህን እያሻሸ እንጂ እንደ ቋረኛው ካሳ ጎራዴ አያወዛውዝም። ከታላቁ የኦሮሚያ አመጽ ጋር በተያያዘ “በሚናገራቸው ንግግሮች” ግን ስሜቱን መቆጣጠር የተቸገረ ይመስላል። ዞረም ቀረ አባይ ፀሐዬ እና ጓደኞቹ የገጠማቸውን ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት መጣራቸውን ቀጥለዋል። ይሳካላቸው ይሆን?

በአጤ ኃይለሥላሴ ዘመን ገጣሚ ዮፍታሄ ንጉሴ እንዲህ ቋጥሮ ነበር፣

ወላድ ኢትዮጵያ - ምጥ ይዟታል አሉ!

ማርያም! ማርያም! በሉ

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ በፖለቲካ ምጥ በመያዟ “ማርያም! ማርያም!” እየተባለ ነው። ከመንግሥቱ ንዋይ የታህሳስ ግርግር የጀመረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምጥ ገና አዋላጅ አላገኘም። እና “ማርያም! ማርያም!” ማለቱ እስከ ዘመናችን ዘልቆአል። በጥንታዊው የኦሮሞ ባህል እናት ልጅ ስትወልድ Bagaa miillikee walqixaate ትባላለች። “እንኳን በእግርሽ (ተስተካክለሽ) ለመቆም አበቃሽ” እንደማለት ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ (ወላይታ?) አባባሉ የተለየ ነው። ሕፃን ሲወለድ “እንኳን በገባበት ወጣ” ይባላል። እንግዲህ ወያኔ በገባበት እስኪወጣ የኦሮሞ ወጣቶች ትግሉን እንደሚቀጥሉ የቆረጡ ቢሆንም፤ በዚህ መካከል በሚፈጠር አለመተማመን እና ሽኩቻ ምክንያት ግን ዕድል ተመልሳ ከአባይ ፀሐዬ እጅ ላይ ልትወድቅ ትችላለች።

በቅርቡ የወያኔ ነባር አባል ከሆነ የቀድሞ ወዳጄ ጋር በጽሑፍ ስናወጋ፣

“የሞጋሳ ዘመዶችህ አይሳካላቸውም። አማሮች ለታክቲክም ቢሆን ከኛ ጋር ናቸው።” አለኝ።

የአባይ ፀሐዬ የፖለቲካ ቁማር በትክክል በዚሁ መንገድ የሚጓዝ ነው። ከዚያ የተሻለ አንዳችም የመቋቋሚያ ዘዴ የላቸውም። በተለይ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል አለመተማመኑን በማሳደግ ብቻ በሥልጣን የመቆየት ዕድላቸውን መጨመር ይችላሉ። ከመነሻው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራል ሥርዓት ለመጠቀም ሲነሱ በህዝቦች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ሥልጣናቸውን ለማቆየት እንደሚችሉ በማመን ነበር። በርግጥም ተጠቅመውበታል። አንዳንድ የዋህ ዜጎች፣ “አዲሳባችን ላይ ወፍ ዝር አይልባትም!” ሲሉ መሰማታቸው የቁማሩ አንድ አካል ነው።

ከኦሮሚያ አመጽ ጋር በተያያዘ ከሣምንታት በፊት ባሌ ሮቤ - መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ አንድ አማራ ተማሪ ተገድሎ ነበር። በኦሮሞና በአማራ ተማሪዎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት ተማሪው እንደተገደለ ተነግሮም ነበር። የሟቹ ተማሪ አባት ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ሲናገር፣

“... ከኦሮሞ ጎረቤቶቻችን ጋር በደስታም ሆነ በኀዘን ጊዜ በፍቅር ተከባብረን ኖረናል። ደግሞም ተማሪ ተማሪን አይገድልም። ኦሮሞ ተማሪዎች ልጄን አልገደሉትም። ልጄን የገደሉብኝ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው። የምጠረጥረውም መንግሥትን ነው።” ሲል ሴራውን ማጋለጡ የወያኔን ፍላጎት በትክክል እንድንገነዘብ ያስቻለ አንድ ማሳያ ሆኖ አልፎአል።

የኦሮሚያ አመጽ ወደ አማራና ኦሮሞ ግጭት እንዲለወጥ ያደረጉት ሙከራ እስካሁን አልተሳካላቸውም። የመሆን ዕድል ግን አለው። ለዚህም ባለማወቅና በተዘዋዋሪ ወያኔን የሚጠቅም ተግባር የሚፈጽሙ ወገኖች አስተዋጽዖ አብይ ድርሻ አለው።

እንደምንሰማው የኦሮሞ ወጣቶች (Qeerroo) አምስቱንም የፊንፊኔ በሮች የመዝጋት ልምምድ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በየዓመቱ ሲካሄዱ የከረሙት የእሬቻ በዓላት እንደ ኦሮሞ ህዝብ ኮንፈረንስ የሚታሰቡ ነበሩ። ሚሊዮናት ከተገኙበት ካለፈው ዓመት የቢሾፍቱ ኮንፈረንስ በኋላ የኦሮሞ ወጣቶች ላለፉት ሁለት ወራት የተግባር ሥልጠና ላይ ቆይተዋል። ከጥር አጋማሽ ጀምሮ በሐረርጌ ያየነው ሜንጫ (ማሽላ መቁረጫ ረጅም ማጭድ)፣ እንዲሁም የሰማነው መፈክር (ባዶ እጅ መውጣት አበቃ!) የሥልጠናው ማብቃት ምልክት ይመስላል። በርግጥም አመጹ ቀጥሎአል። ይህን መጣጥፍ እየከተብኩ ሳለ እንኳ የኦሮሞ ወጣቶች በምዕራብ ሐረርጌ፣ በቦርደዴ፣ በመኤሶ፣ በአሰቦትና በምዕራብ ሸዋ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጠመንጃ እየተፋለሙ ነው። በምስራቅ ወለጋና በሆሮ ጉዱሩ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል። ወያኔ እንደሚመኘው አመጹ ሊቆም እንደማይችል ርግጠኛ ወደመሆን ደረጃ ላይ ተደርሶአል። ወያኔ በህዝባዊው ማዕበል ከመጠረጉ በፊት በግልጽነት ቀርቦ ከሁሉም ተቃዋሚ ወገኖች ጋር ድርድር ማድረግ ይበጀዋል። ካልሆነ እንደ ደቡብ ሰዎች አባባል “እንኳን በገባበት ወጣ” ሊገጥመው ይችላል።

“ሞረሽ” ውጭ ሀገር በሚኖሩ አማሮች የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን፤ ኦሮሞ ወደ ሥልጣን ከመጣ አማራ ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል እየገለጸ ነው። ወያኔም ከአፋቸው እየቀለበ፣ “ልክ ናችሁ። ‘ከሁለት ዛፍ ያጣ - ዕድለ ቢስ ጦጣ’ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።” እያለ በእጅ አዙር ያሟሙቃል። ወያኔ የሞረሽን ስጋት ለጥቅሙ እያዋለው ነው። የአባይ ፀሐዬ ወቅታዊ የጦርነት ስልት የሞረሽ ደጋፊዎችን ከቄሮ (Qeerroo) ማላተም ይመስላል። ርግጥ ነው፤ በአብዛኛው የአንድነት ኃይሎች በሞረሽ መደራጀት ደስተኛ እንዳልሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱ ሲመሰረት ከጥቂት በላይ የአማራ ልሂቃን መቃወማቸው ትዝ ይለኛል። በርግጥ ሞረሽ በተለይ አማራው ላይ የሚካሄደውን ጥቃት ለመቋቋም መመስረቱን ይገልፃል። በቅርቡ የሞረሽ ደጋፊ መሆኑን የገለጸ ሰው ፓልቶክ ላይ እንዲህ አለ፣

“እየሩሳሌም ማለት ‘አየሩ ሰላም’ ማለት ነው። ዳረሠላም ደግሞ ‘የሠላም ዳር’ ማለት ነው። ይህም አባቶቻችን እስከ እስራኤልና ታንዛንያ ዘልቀው ያስተዳድሩ እንደነበር ምልክት ነው።”

ይህ አባባል ታሪካዊ ማስረጃ ቢኖረው እንኳ በዚህ ወቅት ምን ይጠቅማል? ወያኔ ጣና ኃይቅን፣ ራስዳሸን ተራራን እና የዋልድባ ገዳም ወንዞችን ከአማራ ይዞታ ለማላቀቅ ሌት ተቀን ሲደክም አቶ እንቶኔ ስለ ዳረሠላም ያወራል። “ዳረሠላም የኛ ነበር” ከሚለው ኩራት “ጣና ኃይቅ የኛ ነው” ወደሚል እንጉርጉሮ መውረድ መስፍን ወልደማርያም እንደሚሉት የቁልቁለት ጉዞ ነው። እንዲህ በመሆኑ ያሳዝናል። ድክመቱ የአማራ ህዝብ ሳይሆን የፖለቲከኞቹ ራዕይ ማጣት ነው። ይህም ድክመት ወያኔ በሥልጣን እንዲቆይ ሚዛን ጠብቆለታል።

የቤተ አማራን ድረገጽ ሳነብ ደግሞ ሌላ ቀልድ አገኘሁ። አንዱ ፀሐፊ፣ “መሬታችን ተቀምቶ ለሱዳን ሲሸጥ፤ ሌላው ቢቀር ጎንደር እንዴት ዝም ይላል?” ሲል ጠየቀ። አባባሉ ጎንደር በጀግንነቱ ከሌሎች ሁሉ የላቀ ነው ለማለት ይመስላል። የወያኔ አሽሟጣጭ ይህችን ከአፍ ቀልቦ፣ አፄ ቴዎድሮስ ትግሬ መሆኑን ነዛ። በአንድ ወገን ደግሞ አጤ ቴዎድሮስ ቅማንት መሆኑን የደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁንን “የታንጉት ምስጢር” ዋቢ አደረገ። እንግዲህ አንዳንድ ስራፈቶች ሥራ አገኙ ማለት ነው። “አማራ ተደፈርክ! ቴዎድሮስን ስትነጠቅ ምን ትጠብቃለህ? ከዚህ በላይ ምን ትሆናለህ? ክተት! አትነሳም እንዴ? ትግስትህ አያልቅም እንዴ?” የሚል እሪታ ጆሮአችንን ሊበሳ ደረሰ። ከቴዎድሮስ ትግሬ ሆኖ መገኘት ጋር በተያያዘ የተቆጣ ሌላ የሞረሽ ደጋፊም ትምክህቱ ነሽጦት በፈረስ ስም ተሸሽጎ ፃፈ፣

“... ዛሬ መሬታችንን እየቆረሱ የሚሸጡ ትግሬዎች፣ ትናንት ጎንደር ደጃፍ እየመጡ የሚሰግዱልን ለማኞች ነበሩ። ምልክቱም ጎንደር የሚገኘው ‘ትግሬ መጮሂያ’ አምባ ነው።”

ርግጥ ነው በጥንት ዘመን ጎንደር ደጃፍ ላይ “ትግሬ መጮሂያ” የሚባል አምባ ነበር። ትግሬዎች ለልመና ሳይሆን ለአቤቱታ ጎንደር ይሄዱ ነበር። አባባሉ ትግሬን የማናናቂያ መገለጫ ሆኖ ቆይቶአል። ይሄ ‘ትግሬ መጮሂያ’ የተባለው አምባ ግን ዛሬ ወደ ‘ትግሬ መዝናኛ’ እንደተለወጠ ፀሐፊው አልሰማም። በግልባጩ የዋልድባ ገዳም አምባ “አማራ መጮሂያ” የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶታል። በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግሥት አባይ ፀሐዬ ስኳር ምርት ላይ ሲሾም እንደተጣለ ተቆጥሮ ነበር። በስኳር ምርት ስም የአፋርና የዋልድባን ዙሪያ መሬትና ወንዞች የመቆጣጠር ምስጢራዊ ተልዕኮ ይዞ መዝመቱን የተረዳ አልነበረም። የወያኔ የመጨረሻው አንጓ አልተገመተም ነበር።

ዞረም ቀረ አባይ ፀሐዬ ገንፍሎ የመጣበትን ህዝባዊ አመጽ በማዳፈን ወደ ዋና ግቡ መጓዝ የሚችለው በርግጥም ያልነቃውን አማራና ኦሮሞ በመጠቀም ነው። በዚህ ወቅት ሌላ ዘዴ የለውም። በመሣሪያ ኃይል ማፈን አይችልም። ጨዋታው የጭንቅላት ጨዋታ ነው። ለበጎም ተጠቀመበት ለክፉ አባይ አደገኛ ጭንቅላት አለው። እና ወያኔ እንደ ሞረሽ ያሉ ቡድኖችን እንዴት ሥራ ብዙ እንደሚያደርጋቸው ያውቃል። በቀላሉ ቦይ ቆፍሮ ወደ ፈለገው መንገድ ይመራቸዋል። ለዚህ አባባሌ አንድ አብነት መጥቀስ ይቻላል ...

... ከዓመታት በፊት የወያኔ መንግሥት ባካሄደው የህዝብ ቆጠራ የአማራ ህዝብ ቁጥር ከሚታወቀው ወይም ከሚገመተው መቀነሱ ታውቆ ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሞረሽ ሰዎች ዛሬም ድረስ እሪታቸውን ያሰማሉ። በወቅቱ የአማራ ህዝብ ቁጥር ሊቀንስ የቻለበትን ዋና ምክንያት ለመደበቅ ሲባል ወያኔ የፈጠራ ምክንያት ራሱ አሾልኮ አወጣ። ይህም እንዲህ የሚል ነበር፣

“ወያኔ ሆን ብሎ የአማራን ህዝብ በHIV ኤድስ እያጠቃ ነው። በባህርዳር እና በዙሪያው ገጠር የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱ መካን የሚያደርግ መርፌ በመወጋታቸው የአማራ ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ነው።”

ይህ ክስ ዛሬም ድረስ ይነሳል። ይህንን መረጃ በመደጋገም የአማራን ህዝብ ለማነሳሳት እየተሞከረ ነው። ወያኔ ግን ክሱን አስተባብሎ አያውቅም። የአማራ ህዝብም በዚህ መረጃ ተቆጥቶ እስካሁን አልተነሳም። በመሰረቱ ወያኔ እንዲህ ያለ ድርጊት መፈፀሙ ተረጋግጦ ከሆነ፤ እናም ይህን ፈፅሞ ሳለ በሥልጣን መቆየት ከቻለ፤ በዚህ የሚወቀሰው ወያኔ ሳይሆን ወንጀሉ ተፈፀመበት የተባለው ህዝብ ነው። በየትም ዓለም አንድ ህዝብ ከዚህ የከፋ በደል ሊፈፀምበት አይችልም። አንድ ህዝብ “እንዲህ ያለ በደል ተፈፅሞብሃል” እየተባለ ዝም ካለ፤ ያ ህዝብ በድን ሆኖአል ወይም መረጃውን አላመነም ማለት ነው። እንደኔ ግምት መረጃው አልታመነም። ወያኔ በህዝብ ላይ በተጨባጭ እየፈፀመ ያለው አንድ ሺህ አንድ ክፉ ድርጊቶች እያሉ ወደ ፈጠራ ክስ መግባት ለምን አስፈለገ? በፈጠራ ክስ ሲወነጀል ወያኔ በጣም ተጠቃሚ ይሆናል። በዚህ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ አመጽ በተሳካ ሁኔታ መቀጠል የቻለው ተጨባጭነት ያለው ጥያቄ በማንሳቱ ይመስለኛል።

ከተነሳ ላይቀር ግን የአማራ ህዝብ ቁጥር ሊቀንስ የቻለባቸው አንዳንድ መረጃዎች አሉ።

እንደምናውቀው ባለፉት ሥርዓቶች (በተለይ በቅድመ ደርግ) አማራ መሆን ጥቅም እና ከለላ ያስገኝ ነበር። በዚህ ምክንያት “አማራ” ሳይሆኑ በሚሞሉ ቅፆች ላይ “አማራ” ብለው የሚሞሉ ዜጎች ነበሩ። ጄኔራል ታደሰ ብሩን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። አክሊሉ ሃብተወልድ ስለ ጄኔራሉ ማንነት የተሳሳተውና የኦሮሞን ህዝብ የሚጎዳ አሳብ የተናገረው የተሞላውን ቅፅ አይቶ ጄኔራሉ መንዜ ናቸው ብሎ በማመኑ ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ አማራ በመሆን የሚገኝ ጥቅምና ከለላ በማብቃቱ ብዙዎች ወደ ማንነታቸው ተመልሰዋል። ይህ የአማራን ህዝብ ቁጥር ከቀነሱት ምክንያቶች አንዱ ነው። ተጨማሪ ምክንያትም ይኖራል። አገው ቀደም ሲል አማራ ይባል ነበር። በዚህ ዘመን ከአማራነቱ ተቀንሶአል። ለአብነት ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ ድምፃዊቷ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ቀደም ሲል አማራ ነበሩ፤ በወያኔ ሥርዓት ግን አገው ተብለው ይታወቃሉ። አማራን የወከሉ በርካታ የብአዴን አመራር አባላት ቅፅ ሲሞሉ አገው ናቸው። ለመጥቀስ ያህል ደመቀ መኮንን፣ ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ የበረከት ስምዖን ሚስት አሰፉ ፈንቴ እንደ አማራ ቢታወቁም አገው ናቸው። የአማራን ቁጥር በመቀነስ ረገድ የፈላሻ መሄድም አስተዋጽዖ አድርጎአል። ለአብነት ጋዜጠኞቹ ዜናነህ መኮንን እና አለምነህ ዋሴ በቀድሞ ጊዜ አማራ ነበሩ። አሁን ግን አማራነታቸውን በመተው ቤተ-እስራኤል መሆናቸውን ሰምተናል። የአማራ ቁጥር ወደፊትም እየቀነሰ ይሄዳል። በጣና ኃይቅ ዙሪያ የሰፈሩት ቅማንት እና ዋታ (ወይጦ) እስካሁን በአማራነት የተመዘገቡ ነበሩ። ዳሞትና አውራምባም አማራ አይደሉም እየተባለ ነው። በወያኔ አካሄድ እነዚህም ከቤተ አማራነት እንዲሰናበቱ እየተገፉ ነው። እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ከማወቅ ይልቅ፣ “ወያኔ አማራን በኤድስ ፈጀው” የሚለውን ወያኔ ራሱ የለቀቀውን ፕሮፓጋንዳ መልሶ ማስተጋባት ከቀልድ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በማይታመነው በዚህ ክስ ተጠቃሚው ወያኔ ነው።

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የኦሮሞ ህዝብ አመጹን አጠናክሮ ቀጥሎ ብቻውን የወያኔን ሥርዓት ለማስወገድ ከበቃ ለሌላው ወገን ለፀፀት የሚያበቃ ታሪካዊ ስህተት ይሆንበታል። በአብሮ መኖር ሂደት ሌሎች የሚሉትን መስማት ቀዳሚ ጉዳይ ነው። የኦሮሚያን አመጽ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲሳተፉበት ሲጠየቁ፤ ለነገ አብሮነት በማሰብ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ብቻውን ወያኔን ማንበርከክ አይችልም ከሚል አልነበረም። ይህን አብሮ የመታገል ጥያቄ በተሳሳተ መንገድ የተገነዘቡ ወገኖች ወያኔን ሥልጣን ላይ በማቆየቱ ረገድ የማይናቅ ድርሻ እያበረከቱ ነው። የቅርብ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኦሮሚያ ላይ እድሮች መፍረስ ጀምረዋል። ከአማራ ሕብረተሰብ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሮ የመኖር ልምድ የነበራቸው የኦሮሞ አዛውንቶች እየተቀየሙ መሆኑን ተረድቻለሁ። ልጆቻቸው ከአፋኙ ሥርዓት ጋር እየተፋለሙ ሲወድቁ ሌሎች ዳር ቆመው መመልከታቸውን በመታዘብ ከእነዚህ ወገኖች ጋር በአንድ እድር መቆየት የሕሊና ቁስል እንደሆነባቸው በኦሮሞ ማኅበራዊ ድረገፆች እየተነገረ ነው። አደገኛ አዝማሚያ ይመስለኛል። ወያኔ የሚፈልገው መንገድ ይመስለኛል። ለነገው አብሮ መኖር እንቅፋት የሚሆን ይመስለኛል።

መረራ ጉዲና 2014 ላይ ባሳተመው መጽሐፍ ከጠቆማቸው ይሆናል (Scenario) አንዱ ኢትዮጵያ በማያቋርጥ ቀውስ ተንጣና በስብሳ ወደ መበታትን ልታመራ እንደምትችል ነበር። በተለይም የአማራ ልሂቃን ዋና በሽታ የቀድሞይቱን ኢትዮጵያ እንደነበረች ለማስቀጠል መፈለጋቸው መሆኑን በግልፅ ቋንቋ አስቀምጦታል። የአማራ ልሂቃን የኢትዮጵያዊነትን የምስክር ወረቀት ሰጭና ከልካይ አድርገው ራሳቸውን መሰየማቸው በጋራ የመኖር ተስፋውን እንደጎዳው መረራ ይገልፃል። በአባይ ፀሐዬ እየተመሩ ያሉት የትግራይ ልሂቃን በአንፃሩ “ሥልጣን ወይም ሞት” በሚል እብደት ላይ መሆናቸውን መረራ አስምሮበታል። በዚህ ወቅት አብዛኛው የኦሮሞ ልሂቃን ሉዓላዊት ኦሮሚያን ማየት እንደሚመኙም አልሸሸገም። ልሂቃኑ አንዱ ሌላውን ከማይሰማበት የደንቆሮዎች ውይይት (Diallogue of a deaf) ራሳቸውን ማላቀቅ ካልቻሉ መፍትሄው እየራቀ እንደሚሄድም ገልፆአል።

ከመረራ የሰላ ትችት አንፃር የሞረሽ ደጋፊዎችን ስንገመግም፤ የQeerrooን መንገድም ስንታዘብ ከፊታችን የመቻቻል ተስፋ አለ ብለን ለመናገር አንደፍርም። ተስፋ ማድረግ ግን ይገባል። ተስፋ ከሰማይ እንዲወርድ ሳይሆን ሌላው ወገን የሚፈልገውን ለመቀበል ከግማሽ መንገድ በላይ መጓዝ ያስፈልጋል። ይህም መንገድ የእርቅ መንገድ ነው። የማታለል ሳይሆን፣ የጥሎ ማለፍ ሳይሆን በሐቅ ላይ የተመሰረተ የእርቅና የመቻቻል መንገድ ነው። የአማራ ልሂቃን ቢያንስ ኦሮሚያን እንደ ክልል በማወቅ የመቀራረቡን መንገድ መክፈት ይጠበቅባቸዋል። ወያኔም ከሰመመኑ እንዲነቃ ይጠበቃል። አዲሳባ ላይ የአህዮችን መብት የሚያስከብር ቢሮ እንዲከፈት የፈቀደ መንግሥት፤ በዚያው ዓመት የመጫና ቱለማ ማኅበርን መዝጋቱ ለህዝቦች መብት መከበር ሲል የተሰዋውን የህወሓት ታጋይ መካድ ነው።

በቀድሞ ዘመን ኦሮሞን የሚንቁ ወገኖች እንደነበሩ እናውቃለን። ሳይቸግራቸው ንቀቱን የወረሱ ወጎኖች ዛሬም አሉ። እነዚህ ወገኖች ሳያውቁት ለአባይ ፀሐዬ ጦርነት ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው። ተጨባጩን እውነት መረዳት ይገባል። አዲሱ የኦሮሞ ትውልድ የንቀቱን ዘመን በታሪክ እንጂ በአካል አያውቀውም። ዛሬ እንደ ፈነዳ ወንዝ ተቆጥተው ወያኔን እያንቀጠቀጡ ያሉ ወጣቶች ከ15ኛው ክፍለዘመን ኦሮሞዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። የኦሮሞ ወጣት ፈረሰኞች ዛሬ በሐረርጌና በአመያ፣ በከረዩና በቦረና፣ በሌቃዱለቻና በሆሮጉዱሩ፣ በአምቦና በሰላሌ እንዲሁም በሌሎች የኦሮሚያ ክፍለሀገሮች ዳግም ታይተዋል። ኦሮሞነትና ኦሮሙማን፤ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር አስታርቆ ለመጓዝ መካከሉ ላይ መላ መፈለግ እንጂ የኦሮሚያን ህልውና መካድ መፍትሄ አያመጣም። ዓይናችን እያየ ዘመን ተለውጦአል። አንድ አዲስ ትውልድ ዕድሜው ለፈረስ ግልቢያ ደርሶአል። ሐጎስ ወይም ጌታቸው የተባሉ ሥርዓቶች ዛሬም እንደ ትላንት ቶለሳን በፈረቃ ለመግዛት የሚያልሙ ከሆነ ምኞታቸው ከህልም አያልፍም። ኢትዮጵያ በተባለችው ሀገር ላይ በተለይ የኦሮሞና የአማራ ሕብረተሰብ ተከባብሮ በአንድነት መኖር የሚችለው መራራም ቢሆኑ እውነታዎችንና የህዝቡን ጥያቄዎች መቀበልና መገንዘብ ሲቻል፤ በፈረቃ እያጋጩት ለመዝለቅ የሚያልሙ ወገኖችን ተንኮል በመረዳት ማክሸፍ ሲቻል ብቻ ይመስለኛል።

በመጨረሻ ይህችን መጣጥፍ መሰንዘሬ የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ በጥቅሉ ደግሞ የአፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች መጪ ዕድል ስለሚያሳስበኝ ነው። ርግጥ ነው፤ እንዲህ በግልፅነት መፃፍ ከስድብኤል ኮሌጅ ለተመረቁ ተሳዳቢዎች የስድብ ውርጅብኝ ያጋልጣል። ቢሆንም በአካባቢያችን አንዱ ስለሌላው “አያገባኝም” ሊል አይችልም። ወደድንም ጠላንም የማደግም ሆነ የመውደቅ ዕድላችን የተሳሰረ ነው። ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት መሞከር ብቸኛው ወይም የተሻለው ምርጫ ነው። በአንዱ ውድቀት ሌላው አትራፊ ሊሆን አይችልም። ጉዳያችን ለየቅል ቢሆን፣ “ምናገባኝ” ማለት በተቻለ። “ምናገባኝ” ማለት አለመቻል በእውነቱ አለመታደል ነው ...

ተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ