ሄኖክ የሺጥላ

ወዳጄ ልጅ ተክሌ የጻፈውን "የኤርትራ ነገር፣ የኛ ችግር፣ መርህ አልባ ፍቅር" የምትለዋን አየሁ። መስመር በመስመር ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩ። ከዚያ ተመለሼ ወዳጄ መሳይ መኮንን በዳላስ ስለ ኤርትራ ቆይታው ያደረገውን ውይይት ተመለከትኩ፣ እኔ በነበርኩበት በሲያትል ላይ ስላደረገው ውይይትም ለማስታወስ ሞከርኩ፣ ከዚያ የፕሮፌሰር መስፍን ወለደማርያምን ጽሑፍ በድጋሚ አነበብኩ፣ ...

ከዚያ ስለ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወለድ እና በጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወለድ የተነገሩ እና የተከተቡ ነገሮችን አነበብኩ፣ ከዚያ ያንዳርጋቸው ጽጌን ንግግር (ስለ ኢሳያስ አፈወርቂ የተናገረውን) ቪዲዮ ሄጄ ተመለከትኩ፣ ከዚያ ባንድ ወቅት (ምናልባት ከ 3 ወይም አራት ወር በፊት) ዔፍሬም ማዴቦ ከውህደቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በ ሎስ አንጀለስ አድጎት የነበረውን ንግግር ለማስታወስ ሞከርኩ (ስለ አርበኞች ግንቦት ሰባት ውህደት)፣ ከዚያ እኔ ስለ እውነት ስለ ኤርትራ መንግስት የሚሰማኝን አሰብኩ። ባንድ ወቅት ከወዳጄ መሳይ መኮንን ጋ ባደረኩት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ነበር ያልኩት። " እኔ ተኩላ ሊበላኝ ነው ብዬ ለጅብ አላመለክትም!"፣ ይህንንም ስል ወያኔ ተኩላ ሻቢያ ደሞ ጅብ ነው ማለቴ ነበር። ታዲያ ዛሬ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል ትደግፋለህ ሆይ? አዎ! ለምን " ሻእብያዎች መላእኮች እንዳልሆኑ ስለማውቅ፣ ይህም ማለት ሰይጣንነታቸውም የሚያረጅ እና የሚጃጅ መሆኑን ስለምረዳም ጭምር። የትግሉ አካሄድ ላይ ስህተት አለ ወይ፣ በደንብ። ለምሳሌ ወዳጄ ተክለሚካዔል በዚህ ከላይ ባነሳሁት ጽሑፉ ላይ ያለው በሙሉ፣ እደግመዋለሁ በሙሉ ልክ ነው!!!! ግን ሕዝቡን አያለሁ። እደግመዋለሁ ከሻዕቢያና ከኛ ብሶት ባሻገር ዔርትራውያኖችን አስባለሁ፣ ኢትዮጵያውያኖችን አስባለሁ። ሰው ጥላቻን ለምዶ ነው ጠይ የሆነው፣ ወይ ብዙ በደል ደርሶበት ወይም ብዙ የጥላቻ ወሬ ተመግቦ፣ ስለዚህ ያ ሰው ኢ- ጥላቻን ሊማር የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም።

ለምሳሌ እሳት ያድበሰበሰው ግን የሻቢያን ቁርጠኛነት ወይም ኢ-ቁርጠኛነት ሊነግረን ወይም ሊያስረዳን የሚችሉ ብዙ ተጠይቀው ያልተመለሱ፣ ወይም ያልተጠየቁ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የአሰብ ጉዳይ አንዱ ነው፣ የኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ ነገር ሌላው ነው፣ ስለ ደሚት የሰማነው ነገር የህጻን ልጅ ወሬ ነው የሚመስለው፣ ኢሳያስ ካሳ ይገባኛል ያለው ስህተት ባይሆንም፣ ለምንድን ነው ካሳ ይገባኛል ያልከው? እና ወዘተ ብሎ መጠየቅ ነበረበት። ግን ይሄንንስ ማን አየበት ከሆነ ነገሩ፣ መዝለሉ ብልህነት ባይሆንም እንደ ብልጠት ነው የማየው። ያም ሆኖ ትግሉን እደግፋለሁ! ለምን አሁንም እደግመዋለሁ "እኛ ኢትዮጵያውያኖች መሆናችንን ስለማውቅ!"፣ ታሪክ ራሱን እንደሚደግም ስለማውቅ፣ የበለጡንን መብለጥ፣ ያመኑንን ማመን እና መታመን፣ ያሴሩብን ላይ ማሴር እንደምንችል ስለማውቅ። ከምንም በላይ ሻዕቢያ ይህንን ለውጥ ለራሱ ሲል እንደሚፈልገው ስለማውቅ። ለምን? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነጻነት ፈላጊነት ባሮ ሜትር ምን እያነበበ እንደሆነ ስለሚረዳ እና ባይፈልገውም እጁን እዚህ ላይ ካልዶለ፣ እንደሚጎዳ በደንብ ስለሚያውቅ። ይሄ ኢሳያስ ኢትዮጵያን ይወዳል፣ ምናምን የሚሉትን ታሪክ "ተናጋሪውም የተነገረለትም" ሁለቱም እንደማያምኑበት መናገር ጠቃሚ አይመስለኝም።

ታዲያ ይሄም ሆኖ ሳለ ትግሉን እደግፋለሁ! ለምን? ያለም ታሪክ በአጋጣሚዎች ላይ የተጎለተ ድማሚት ስለሚመስለኝ። የማልደግፈው ግን፣ ትግሉ ከዔርትራ ብቻ መነሳት አለበት የሚለውን ነው። አቅሙ ያላቸው ሰዎች አማራጭ እንዲያዩ እመክራለሁ። ሰሞኑን ሱዳን አካባቢ አንዳንድ ጠቋሚ እና ጠቃሚ ነገር እያየሁ ነው። ሌላም ነገሮች ይኖራሉ። እርግጥ የኤርትራ መንግስት ወዳጄ መሳይ እንደነገረን ተቃዋሚዎች አንድ ሁኑ ሲባሉ አንድ አንሆንም ብለው ስላስቸገሩት ነው አንድ ሳይሆኑ የቀሩት የሚለውን "እቃቃ መሰል ወሬ"፣ እራሴን እየነቀነቅሁ ልክ ነው ልል ስብናዬ አይፈቅድም፣ ግን ከኛ ባሀሪ ስነሳ፣ አንድ ሆኖ መስራት ድሮም ስለማይሆንልን፣ እኛን ማፍረስ ቀላል ቀላል መሆኑን በደንብ እገነዘባለሁ። ለዚህም ነው በልጅ ተክሌ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ለመስማማት የፈለኩት።

በነገራችን ላይ ልጅ ተክሌን ለማታውቁት፣ እስከማውቀው ድረስ "ለአፉ ለከት የሌለው የሚመስል ግን ያልሆነ፣ የራሱ ሰው ነው"። አንዳንዴ ዝም ብሎ ሲያፈነዳም አስተውያለሁ፣ ግን ለክፉ የሚሰጡ ናቸው ብዬ አላምንም። ባጭሩ፣ ባለ ብሩህ አእምሮ እና፣ ጨዋታ የሚወድ ሰው መሆኑን ሳላውቅ አልቀርም። እንደውም ወደፊት ግንቦት ሰባትን ከኔ ጋ ሆነን ገልብጠን ሌላ ድርጅት ለመመስረት እያሰብን ነው። መነሻው የሃንሽ ደሴቶች ላይ የሆነ ባህር ኃይል፣ በሁለት ዓመት አዲስ አበባ የሚገባ ምናምን ልበል? እስቲ ተዉት!

ልጅ ተክሌ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ስያሜ ላይ የሰጠው ነቀፋ ተገቢ ነው፣ አንድም ሁለትም ናቸው የሚለው አባባል፣ እንደኔ ሚስጥረ ስላሴ ለማይገባው ኩታራ አደገኛ አገላለጽ ቢሆንም። በተጨማሪም የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ መሆኑን መቃወሙ አግባብ ይመስለኛል። ይህንንም ስል ብርሃኑ የመምራት ብቃት የለውም ለማለት ሳይሆን፣ የቄሳርን ለቄሳር፣ የየሱስን ለየሱስ እንደተባለው፣ የሜዳውን ለሜዳ፣ የ እንትኑን ለእንትን ማለት ብንችል ብዬ ነው። በተጨማሪ መሪ የሚለው ነገር ከአንድ በላይ ትርጉም ያለው ስለሚያስመስል፣ ለሱም ሲባል ቢቀር ጥሩ ነበር ብዬ አምናለሁ። ይህንን ስል፣ እንደ ብላቴና ነው አስተያየቴን እየጻፍኩ ያለሁት። ብዙ ውስብስብ ነገሮች እንዳሉ ይገባኛል። ሲጀመር ኤርትራ ሆኖ መዋጋት በራሱ ውስብስብ ነው፣ መሰንጠቅ፣ መካድ፣ አላስፈላጊ ውሳኔ መስጠት እና ወዘተ ሌላው ነው። ግን መሪው በቅርብ የሌለበት የለት ተለት ተሰራዊት እንቅስቃሴ፣ ጸብ፣ የለት ተለት የትግል ውሎ፣ ለሊቀመንበሩ ከርቀት በሚደርስ መርጃ መከወን ብዙ ጉዳቶች አሉት። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የመረጃ ፍሰት እና አጠባበቅ ነው። ለምሳሌ ምክትል ሊቀመንበሩ ከሆነ ለዋናው ሊቀመንበር መረጃ የሚያደረሰው፣ በእርግጠኝነት በሁለቱ መሃከል ስለሚደረገው ማንኛው አይነት ግንኙነት ሌላ አካል (ሻብያን ጨምሮ) ሊሰማ ወይም ሊያውቅ ይችላል። ምክትል ሊቀ መንበሩ ደሞ ምን ያህል በራሱ ነገሮችን መፈጸም ይችላል የሚለው ነገር፣ ከፋሲል የኔ ዓለም ጋ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ከሰማሁ በሁዋላ "በቃ አልተመቸኝም" (ቃለ መጠይቁ ላይ ፋሲል የኔ ዓለም ስለ ኮ/ ል ታደሰ ጥያቄ ሲጠይቅ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር የሆነው አቶ መአዛው ጌጡ "ስለዚህ ነገር አትጠይቁኝ፣ ተወኝ፣ እለፈኝ" የሚል መልስ ነው የሰጠው። ብዙ ያልተሩ ነገሮች አሉ። የዚህ ጽሑፍ አላማውም፣ ልጅ ተክሌ የጠየቀውን አስባችሁበታል ወይ ለማለት አይደለም (ምክንያቱም በደንብ እንደምታውቁት ስለማውቅ)፣ የዚህ ጽሑፍ አላማው፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት መሰሪ ፖለቲከኞች ያስፈልጉታል፣ ለዚህ ዘመን እና ትውልድ በሚመጥን መልኩ አይደለም አንዳንድ ውሸቶች እየተሰሩ ያሉት፣ እውነትም ይሁን ውሸት ጥራቱን ይጠብቅልን ለማለት። በተጨማሪ እኔም እንደ ተክሌ የፈለኩትን መናገር አልፈራም የሚልም መልክት ለማስተላለፍ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ