ኤሊያስ ገብሩ -ጋዜጠኛ

‹‹በዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋዜጠኝነትን ለመስራት ምን ያህል ተጠቀምንባቸው?!››ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
‹‹በሙያችን ለሀገራችን አበርክቶት መስጠት ይጠበቅብናል።›› ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ
‹‹...ብዙዎቻችን የምንሻው ነጻነት የሚመጣው ጥቂቶች በሚከፍሉት ዋጋ ብቻ አይደለም››ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
ባሳለፍነው ረቡዕ ጥር 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍቃዱ ማህተመወርቅ እና ሳሙኤል አበበ ጋር ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት አምርተን ነበር። ፍቃዱም ወደዞን አንድ፣ ሳሙኤል ወደዞን እኔ ደግሞ ወደዞን ሶስት ለጥየቃ ገባን። ከታሰሩ አንድ ዓመት ሊሞላቸው ያሉትን ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም የዞን 9 ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀን አስጠራኋቸው።

ያው ንግግር አዳማጭ በመሆን ከግራ እና ከቀኜ ቆመው፣ ጆሯቸውን በመቀሰር ቢያዳምጡንም አንዳንዴ ጸጥ፣ አንዳንዴ ሳቅ፣ አንዳንዴ ደግሞ ንድድ እያልን ከተስፍሽ፣ ናቲና አስሚቲ ጋር አውግተን ነበር። በጠያቂ እና በተጠያቂ መካከል ያለን ንግግር ሌላ አካል በግልጽም ይሁን በስውር የማዳማጥ መብት ሕግ ይፈቅድለት ይሆን? ...ለማንኛውም ሶስቱም ከጋሩኝ ሀገራዊ ቁምነገሮች መካከል በጥቂቱ እንዲህ ላስነብባችሁ ወደድኩ።

‹‹የ‹አዲስ ነገር› ጋዜጣን ሳስብ ኩራት ይሰማኛል። የጋዜጣዋ አባልም ሆኜ ከዚያ ጥሩ ስብስብ ጋር በመስራቴም በጣም ደስተኛ ነኝ። በአሁንም ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ በጣም በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም ዓለም ሰፊናትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፣ ይጠበቅብናል። በዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋዜጠኝነትን ለመስራት ምን ያህል ተጠቀምንባቸው?! [ኢትዮጵያኖች] ያልሄድንባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። እነሱን በደንብ መሞከር ይጠበቅብናል። በሀገር ውስጥ፣ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተገኝተው በጋዜጠኝነት ሙያ ለመስራት የሞከሩት እና የተፍጨረጨሩትን ሁሉ እንደማደንቃቸው ሁሉ፣ ከሀገር ውጪም በስደት ላይ ተገኝተው ጋዜጠኝነትን በመስራት ለሕዝባቸው መረጃ የሚያደርሱትንም ከልብ አከብራቸዋለሁ፤ ሊከበሩም ይገባል። ከሀገር ወጥተው፣ ‹ጋዜጠኝነትን በቻልነው ሁሉ እንሰራለን› ብለውን መስራት ያልቻሉት ያናድዱኛል። ባለህበት ቦታ ሆነህ ጋዜጠኝነትን ለመስራት መጣር ያስፈልጋል።››
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ

‹‹በ ‹አዲስ ጉዳይ›› መጽሔታችን ብዙ እንሰራለን ብለን በአጭሩ ተቀጭተናል። ሀሳባችን ብዙ ነበር፤ ግን ሳይሆን ቀረ። በመረጃ ዕጥረት ሳቢያ ያስከፋናቸው ጥቂት ወገኖች ይኖራሉ። በፈለከው መጠን መረጃ አታገኝም። በሥራችን የሚያመሰግኑንም ብዙዎች ነበሩ። በቻሉት ሁሉ በጋዜጠኝነት ሙያ ሕዝብን ለማገልገል መታገል ወሳኝ ነው። እኔም አንድ ቀን ከእስር ወጥቼ ከምወደው ሙያ ጋር ዳግም እንደምገናኝ አስባለሁ። በሙያችን ለሀገራችን አበርክቶት መስጠት ይጠበቅብናል።››
ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ

‹‹አሁን ላይ በሀገራችን የነጻነት ጥያቄ ፊት ለፊት ፍጥጥ ብሎ መጥቷል ብዬ አስባለሁ። ለነጻነት ለሚከፈል ዋጋ እና መስዋዕትነት [ግላዊ] ፈቃደኝነትን ይሻል። የነጻነት ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ ሙያዊ ነገሮችን ወደ ጎን ገፋ ማድረግም ያስፈልጋል እላለሁ። በግሌ በዚህ ሀሳቤ ከሰው ልለይ እችላለሁ። ...ብዙዎቻችን የምንሻው ነጻነት የሚመጣው ጥቂቶች በሚከፍሉት ዋጋ ብቻ አይደለም። ሁሉም የበኩሉን ሚና መጫወት ይገባዋል››

[በዚህች የናቲ ሀሳብ ጋዜጠኛ አስማማው ‹‹ጥያቄ አለኝ?›› በማለት አቋርጦት ‹በሙያችን (በጋዜጠኝነት) እያበረከትን በነበረው ሂደት ላይ ዋጋ ከፍለናል፣ እየከፈልንም እንገኛለን። በእኔ አመለካከት ‹ሙያዊ ነገር ወደጎን ገፋ ሊደረግ አይገባም› የሚል እምነት አለኝ›› ሲል ለናቲ ገልጾለት ነበር። በወቅቱ አስማማውም ሆነ ናትናኤል የሀሳብ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ በመግለጽ ሲከራከሩ መመልከቴ አስደስቶኛል]
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ

በተጨማሪም፣ ከቂሊንጦ መልስ በቃሊቲ ዞን 4 ተገኝተን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ‹‹መዝገቡ ላይ ስማችሁ የለም› በሚል ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። የሚገርመው ነገር ሶስታችንም ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ እስከንድርን ጠይቀነው እናውቃለን። መዝገብ ላይም ስማችን ይገኝ ነበር። መዝገቡ ላይ ስማችንን በደንብ ለመፈለግ ከመዝጋቢው ፖሊስ ጎን የነበሩት ጠና ያሉ ሰውዬ ጥቂት ተነሳሽነት እንኳን አልነበራቸውም።

‹‹እስክንድርን ከዚህ በፊት ጠይቀነው እናውቃለን። ስማችንም መዝገቡ ላይ ይገኛል›› ብለን በትህትና ብንጠይቅም እኚህ ሰውዬ እኛን ለመስማት ዝግጁ አልነበራቸውም።

‹‹እንዲህ ከምታደርጉ እሱን መጠየቅ አይቻልም ለምን አትሉም?›› ሲል ፍቃዱ ተናድዶ ጠየቃቸው። ሰውየውም ‹‹ምን ታመጣላችሁ፣ ልትጠይቁት አትችሉም በቃ!›› በማለት በትግርኛ ቋንቋ ወደመናገር ተሸጋግረዋል ዋናውን የመግቢያ በር ወደመዝጋት አመሩ። በቦታው የነበሩ ሌሎች ፖሊሶች (ወደቤታቸው እየሄዱ የነበሩ) ‹‹በቃ ተውት›› በማለት እኛን ሊያግባቡ ሲሞክሩ አስተውለናል።
መልካም እሁድ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ