ተክለሚካኤል አበበ

በርእሱ እንዳትሸወዱ

1-      ይሄ የኔ ርእስ አይደለም፡፡ የዛሬ 15 ቀን ተክለጊዮርጊስ በተባሉ (የብእር ይሁን የምር ስም አይታወቅም) ሰው የተጻፈን ስም አጥፊ ጽሁፍ የለጠፈው ኢትዮፍሪደም ድረገጽ ወይም የጽሁፉ ደራሲ፤ የአንባቢን ትኩረት ለመሳብ ይመስላል፤ የተጠቀሙበት የመግቢያ ሀይለቃል እንጂ፡፡ ጸሀፊው ለድረገጾች ያላቸውን ቅርበት በመጠቀም፤ እንዲሁም ወያኔ የተባለው ቃል ከተጠራ አንባቢ አያጣራም፤ ወይም ግለሰቡ ላይ ዘሎ ይረባረብበታል በሚልና፤ የስም ማጥፋቱ ሰለባ የሆኑት ሰው፤ ጨዋና እንዲህ ያለው እንከሰላንቲያ ውስጥ ገብተው አይመልሱም በሚል እሳቤ ይመስላል፤ ይሄንን ርእስ ተጠቅመዋል፡፡

በርግጥም ጸሀፊው አላማቸው በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸው፤ የተሻለ ያስባሉ የምንላቸው ሰዎች ጭምር፤ ጽሁፉ ላይ የተነሰነሱትን ፎቶኮፒ አባሪዎች አይተው፤ ጸሀፊው በሚፈልገው መንገድ ሄደዋል፡፡ በዚህ ሰኣት በዚህ ርእሰ-ጉዳይ ላይ መጻፍ፤ ብዙ አንገብጋቢ ባይሆንም፤ የንጹኀን ግለሰቦችን ክብር ለመጠበቅና፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣን አጉል ባህል ለመዋጋት ስል፤ ይህንን እጽፋለሁ፡፡  

2-     ነገሩን እንዲህ ነው፡፡ እጅጉ ገዳሙ (ሻለቃ) እና ገበየሁ ይገዙ (ዶ/ር) (ሁለቱም የፈጠራ ስሞች ናቸው) ነዋሪነታቸው በሻርለት፤ ሰሜን ካሮላይና ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊን፤ ባለፉት ጥቂት አመታት ኢትዮጵያን የተመለከት ክስተት ካለ ሌሎች አጋሮቻቸውን አስተባብረው ብዙ መቶ ኪሎሜትሮችን ነድተው ለመምጣት አያመነቱም፡፡ ለምሳሌ፤ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አለ ከተባለ፤ ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር አትላንታ ድረስ ነድተው ሲመጡ ተመልክቻለሁ፡፡ የዋልድባ መታረስን/መፍረስን ከተትሎ ተቃውሞ አለ ሲባልም፤ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ ነድተው ሲመጡ አስታውሳለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ሁሉ፤ አብረው የሚሰለፉ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ነበሩ፡፡

3-     በቅርቡ ግን፤ የሻርለት ስላሴ ቤተክርስቲያን አባላትን የከፋፈለ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የክፍፍሉ ዝርዝር አይገባኝም፡፡ ግን በሌሎች በብዙ ስፍራዎች ከሚከሰቱ ውስጣዊ አለመግባባቶች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ቦታ ብዙ ግዜ ተጽፎ እንዳያችሁት፤ በተለይ ቤተክርስቲያኖቻችን በውስጣዊ ክፍፍል ሲመቱና ሲታመሱ ከርመዋል፡፡ ቀደም ሲል፤ አብዛኛው ክፍፍል፤ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ሲኖዶስ፤ እንዲሁም ገለልተኛ በሚል ምክንያት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ፤ የሻርለት ስላሴ ቤተክርስቲያን፤ ከስደተኛው ሲኖዶስ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ የተቀሩትን ምእመናን የሚያጠናክር እንጂ የሚከፋፍል ነገር ሊፈጠር አይገባም ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን፤ በሻርለትም ይሁን በሌሎች ስፍራዎች፤ ለምሳሌ በዲሲ ገብርኤል፤ በሲያትል ገብርኤል፤ በቫንኩቨር ማርያም፤ በጀርመንና በሌሎችም ስፍራዎች ጭምር፤ ቤተክርስቲያናት፤ ወደስደተኛው ሲኖዶስ መሆናቸው ከለየላቸውም በኋላ፤ ሌላ የመከፋፈልና የመካሰስ እንዲሁም የመከፋፈል ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡

4-     የበለጠ የሚያበሳጨው ግን የመከፋፈሉ ችግር ሳይሆን፤ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ወገን ለማሸነፍ የሚጠቀማቸው አግባብና ጤናማ ያልሆኑ ዘዴዎች ናቸው፡፡ ችግሩን ሲሆን ሲሆን በውይይት ያለበዚያም በፍርድቤት ለመፍታት መሞከር አንድ ነገር ነው፡፡ ገና ለገና በራስን ወገን ላይ ድል ለመቀዳጀትና፤ ማንም አሸናፊ ሆኖ የማይወጣበትን ግብግብ በጊዜያዊ ድል ለመወጣት በሚል፤ ያለበለዚም ባልበላው እጭረዋለሁ በሚል የዶሮ ስሌት፤ ስም ማጥፋት፤ በሀሰትና በፈጠራ ክስ ሰዎችን መወንጀልን እንደ ማጥቂያ መንገድ መጠቀም አግባብም፤ መንፈሳዊም፤ አዋጭም አይደለም፡፡ ያ መንገድ ቢያዋጣ፤ ኢህአፓ እስካሁን ስልጣን ይዞ ነበር፡፡ ግን አላዋጣም፡፡ ባለፈው ሁለት ሳምንት፤ በሻርለቱ ዲባቶ ሰለሞን ጉግሳ ላይ የተሰነዘረው የስም ማጥፋት የዚህ ውስጣዊ ሕጋዊ ችግርን በስምማትፋት የመፍታት ስልት አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡

5-     አቶ ተክለጊዮርጊስ (ምናለ እንደኔ ጊዮርጊስ የሚለውን ትተውት ተክለ ብቻ ቢሉ)፤ በዲባቶ ሰለሞን ላይ ያነሷቸው ክሶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ቤት ለመስራት መሬት ወስደዋል፡፡ ሁለተኛ የዋልድባ መነኩሴ አባረሩ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ያደረጉ ሰው፤ በውጭ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ውስጥ በአባልነትም ይሁን በአመራር ላይ ከተቀመጡ፤ በኢህአዴግ ለስለላ የተቀመጡ ሰው ናቸው የሚል ክስ ነው፡፡ ይሄንን ክስ ይዘው ከለጠፉት አንዳንዶቹ፤ ለካንስ ዶሮዎቻችንን አደራ የሰጠነው ለቀበሮች ሲሉ ተረቱ፡፡ አገርቤት ቤት መስራትንም ከስስትና ከራስወዳድነት ጋር አገናኙት፡፡ እንዴት ያለ የሀሳብ ድህነት ነው ባካችሁ፡፡ እንዲህ እመልሳለሁ፡፡

6-     ከቤት ስራ ጋር በተያያዘ፤ ሰው ገንዘብ ካለው፤ አገር ቤት፤ ቤት ቢገነባ በብዙ መልኩ ጠቃሚና መበረታታት ያለበት ነገር ነው፡፡ አገሪቱን፤ እንኩዋንስ እኛ፤ ማንም አረብና ህንድ እየሄደ እየተቀራመታት አይደለም እንዴ፡፡ አያት ቅድመአያታችን ባቆዩልን አገር ላይ ሄደን እንኩዋንስ ቤት፤ ምንስ ብንሰራ ክፋቱ ምን ላይ ነው፡፡ በውጭ ከምንገኝ ተቃዋሚዎች ዘመቻ ውስጥ ሁሉ የማይረባውና ስሜት የማይሰጠው፤ ለወያኔ ዶላር ስለሚያስገኝለት፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትጠቀሙና ቤት አትስሩ የሚለው ዘመቻ ነው፡፡ የምንቃወመው እኮ ስርአቱን እንጂ አገሪቱን አይደለም፡፡ ቤት መገንባትም ይሁን እንደኢትዮጵያ አየርመንገድ ያሉትን ድርጅቶች ቦይኮት ማድረግ ለትግሉ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምን ሰው ያንን ማድረግ መብቱ ነው፡፡ ሌሎች በዚህ መስመር ያልተሰለፉትን ሁሉ ግን የስርአቱ ደጋፊዎች ወይም እንደአቶ ተክለጊዮርጊስ ጽሁፍ ርእስ ወያኔ አድርጎ መመልከት፤ ወይንም በውስጣችን በሕወሀት የተተከሉ ፍልፈሎች አድርጎ መሳል፤ የትግል ሳይሆን የድንቁርና መገለጫ ነው፡፡

7-     ከስራ ከተሰናበቱት መነኩሴ ጋር በተያያዘም፤ ከዶ/ሩም ዘንድ ይሁን ከአካባቢው ካሉ ሰዎች ዘንድ ማጣራት እንደቻልኩት፤ አንደኛ ውሳኔው የተወሰነው በቤተክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ ሲሆን፤ ዶ/ሩም ይሄንን ውሳኔ የማስፈጸም ግዴታ አለባቸውና ያንን ካስፈጸሙ፤ እርምጃው ስህተት ነው የሚል ወገን ካለ፤ መውቀስ ያለበት እሳቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ሰበካ ጉባኤውን በሙሉ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የኛ ካህናት መረዳት ያለባቸው ነገር ቢኖር፤ ቤተክርስቲያናት በዚህ አገር ህግ የተመዘገቡ ድርጅቶች በመሆናቸው፤ ካህናቱም የቤተክርስቲኒቷ ተቀጣሪ ሰራተኞች እንደመሆናቸው መጠን፤ የቀጠራቸው አካል በምክንያትም ይሁን ያለምክንያት በፈለገው ሰዓት ሊያባርራቸው ወይም ሊያሰናብታቸው ይችላል፡፡ ከመነኩሴው ጋር በተያያዘ፤ የኢትዮፍሪደም ድረገጽ ባለሟል አቶ ኪሩቤል፤ መነኩሴው መባረራቸውን፤ የኢሚግሬሽን ጉዳያቸው መቋረጡን፤ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ገብተው እንዳያገለግሉም መደረጋቸውን እንደለየለት ጭካኔ አድርጎ የወሰደው ነገርም ብዙ አያስኬድም፡፡

8-     ካህኑ ይሄን አጥፍተዋል ይሄን አላጠፉም ብሎ መከራከር የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ነግር ግን፤ ሰበካ ጉባኤው፤ መነኩሴው  አብረዋቸው ሊዘልቁ የሚችሉ ካልመሰላቸው፤ በጊዜ ከስራ ቢያሰናብቷቸው፤ ያንንም ተከትሎ፤ የጀመሩላቸው የኢሚግሬሽን ማመልከቻ ካለ፤ ሰበካ ጉባኤው ራሱን ከዚያ ሂደት ቢያገል፤ ምክንታዊ ነው፡፡ እንዲሁም፤ የሳቸው ወደቤተክርስቲያን መግባት ሊያስነሳው የሚችለው ችግር ካለ፤ ያንን ለማስቀረት ሲባል በሰበካ ጉባኤው ጠያቂነት ፖሊስ ወደውስጥ እንዳይገቡ ከከለከላቸውም ለሁሉም ወገን እንደጥንቃቄ እንጂ እንደጭካኔ መወሰድ የለበትም፡፡ እንጂ፤ መነኩሴ ከዋልድባ መጣ ተብሎ፤ እንዲሁም መነኩሴ ኢህአዴግን የሚያወግዝ መፈክር አሰማ ተብሎ አይነካ የሚለው አባባል ብዙ አያስኬድም፡፡ ከመነኩሴው ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ሲከሰት እንደሰማሁት ከሆነ፤ የመነኩሴውን መሰናበት ጉዳይ ጎንደሬ ከመሆናቸው ጋር አገናኝተው የአካባቢያዊ ጸብ ቅርጽ ሊያሲዙት የሞከሩም ሁሉ ነበሩ፡፡ ደግነቱ፤ በዚህ በሻርለት በተፈጠረው ችግር ውስጥ የጳጳሳቱም/ሲኖዶሱም እጅ ስላለበትና፤ በዚህ በስደቱ ሲኖዶስ ውስጥ በሚፈጠረው ሽኩቻ ውስጥ በሁለቱም ወገን ያሉት በአብዛኛው የጎንደር ሰዎች በመሆናቸው ችግሩ በዚህ ረገድ ገፍቶ አልሄደም፡፡       

9-     ዲባቶ ሰለሞን፤ የሰሜን አሜሪካውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚሾፍሩት ፊታውራሪዎቻችን ዘንድ የታወቁ ሰው ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ባለፈው አመት በሳኡዲ በኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን በደል ተከትሎ የተቋቋመው ግሎባል አሊያንስ የተሰኘ ድርጅት አመራር አባልም ነበሩ፡፡ ግሎባል አሊያንስም፤ ዲባቶ ሰለሞን ላይ ይሄ ሁሉ ውርጂብኝ ሲወርድ አለማስተባበሉ፤ እንዲያውም እንደተባለው ካሉበት ሀላፊነት እንዲወርዱ ጫና አድርጎም ከሆነ፤ የተቃውሞ ስብስባችን ፍልስፍና ግልብና ከኢህአዴግ ያልተሻለ መሆኑን የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ቢያንስ በድርጅቱ ላይ ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ ማህተም ያለበት ደብዳቤና የቤት ስራ ማህበር አባላትን የያዘ ፎቶኮፒ ወረቀት የተነሰነሰበት ጽሁፍ ባየን ቁጥር ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው ሾልኮ የወጣና የተደበቀ በአገር ላይ የሚሰራ ሴራ አድርገን ወደመመንዘር ካዘነበልን፤ ከመካከላችን ከዚህ ክስ የሚተርፍ አንዳችም ሰው የለም፡፡ እኔ በምሳተፍበትና ይሄንን የማይረባ ጽሁፍ ባነበብኩበት የቡድን ኢሜል ስብስብ ውስጥ ካሉት የግሎባል አሊያንስ ወገን በኩል አንዳችም ሰው ማስተባበያ አለመሰማቱ፤ አሞኛል፡፡ አበበ ገላው፤ በግሉ ስለዲባቶ ሰለሞን የሰጠው ጥሩ ምስክርነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡   

10-    የዲባቶ ሰለሞንን ሁኔታ ቢያንስ ላለለፉት አራት አመታት ተከታትያለሁ፡፡ ከቤተክርስቲያናቸው ጋር በተያያዘ በወሰዱት እርምጃ የማይስማማ ይኖራል፡፡ በምንም መልኩ ግን የፖለቲካ ስብእናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ከኢህአዴግ ጋር የሚቀላቅላቸውም ምንም አይነት ፍንጭ የለም፡፡ ዲባቶ ሰለሞን፤ በ2010 ኢሳት ሲመሰረት፤ ለኢሳት ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ ከመጀመሪያው ተርታ የተሰለፉ ናቸው፡፡ ለኢሳት በመደበኛነት ከሚሰጡት ርዳታ ጎን፤ ኢሳት የመቶም ያምስትመቶም ካረድ ሲያዘጋጅ የመጀመሪው ሸማች መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ በ2012ም፤ ለኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሲደረግ፤ ዋና አስተባባሪ እሳቸው ነበሩ፡፡ እንደውም አሁን እሳቸውን ከሚከሷቸው ሰዎች አንዳንዶቹ፤ በዚያን ግዜ በቤተክርስቲያናችን የአቶ መለስ ዜናዊ ሀዘን እንዳይደረግ መከልከል፤ የሰዎችን መብት መንካት ነው ብለው፤ ወንድም ሰለሞንን ሲያስቸግሩና ሲነተርኩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡

11-     እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ዶ/ሩን ሻርለትን ወክለው በአትላንታና በዲሲ በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ሲገፋፉ የነበሩት ሰዎች፤ ዛሬ በውስጣቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት፤ ዲባቶ ሰለሞንን የጠላት ወገን አድርጎ መሳል፤ ምን ያልህ ከራሳችንም የተጣላንና የፖለቲካ አስተሳሰባችን ሁሉ ቀሽም፤ አርባ አመትም ያላደገ እንደሆንን ያመለክታል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ካርባ አመት በሁዋላም ህልውናቸው በሌላ ስራ ስለማይገለጽ፤ በአካባቢያችን ተቆጣጥረነዋል የሚሏቸው ተቋማት፤ በሌሎች ከነሱ ባልሆኑ ወገኖች የተያዙ ሲመስላቸው፤ ያንን ለማስመለስና ህልውናቸው ይገለጽ ዘንድ ወደስም ማጥፋትና የፈጠራ ክስ ያዘነብላሉ፡፡ እዚህ ውስጥም እነዚህ ባለአርባዎቹ ሳይኖሩበት አይቀርም፡፡

12-    ጎበዝ፤ ትንሽ እንብሰል፡፡ ትግላችንም፤ ትግል ካልነው ይብሰል፡፡ በቂና ግልጽ ጠላቶች ስላሉን፤ እንደሰለሞን አይነት ቀና ሰዎችን ጠላት ማድረግ፤ ወይም ጠላት ፍለጋ በባትሪ መውጣት አያስፈልገንም፡፡ እንዴት ያበሳጫል፤ በዚህ እነአንድነት ፍዳቸውን በሚያዩበት ሰዓት እንዲህ ያለውን ማስተባበያ እንድንጽፍ መገደዳችን፡፡

ተክለ (ሚካኤል)፤ ለአስተርዮ ማርያም፤ 2007/15፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ