ባለቤት የሌለው መሬት – ቤጌምድር!
ዳዊት ከበደ ወየሳ
የመከላከያ ሰራዊት በትግራይ እና አማራ ተዋጊዎች መካከል ሰፈረ (ከዚያስ?)
በሰሜን ጎንደር, አርማጭሆ አውራጃ ልዩ ስሙ “ገ’ጨው” በተባለው ስፍራ የመከላከያ ሰራዊት ከትላንት ጀምሮ እንዲሰፍር ተደርጓል፡፡ ማዶ እና ማዶ ሆነው እየተዋጉ ባሉት የትግራይ ወታደሮች እና በአማራ ህዝብ መካከል መከላከያ ሰራዊት ከሰፈረ በኋላ ጦርነቱ አሁን ለጊዜው ጋብ ብሏል፡፡ የቀድሞ የህወሃት ወታደሮችን ሁመራ ላይ በማስፈር አካባቢውን ለራሱ ያደረገው ህወሃት – አሁን ደግሞ በአርማጭሆ መስፋፋት በመጀመሩ ነው – በአካባቢው ከሚኖረው የአማራ ህዝብ ጋር ግጭቱ የተቀሰቀሰው፡፡
ሰሞኑን ግጭቱ ከመባባሱ በፊት የአማራው ህዝብ ተዋጊዎች – ህወሃት በአጭር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ሆኖም የህወሃት ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው ባለመሄዳቸው በተለይ በማይ’እምቧ በርካታ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ – ህወሃት አባላት ሞተዋል። በወያኔዎቹ ላይ የደረሰው አደጋ ያስደነገጣቸው እና ወደ አርማጭሆ ያመሩት ሌሎች የህወሃት አባላት – ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ጦርነት ሲያደርጉ ነበር የከረሙት። በዚህ ጦርነት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም የተኩስ ልውውጡ ከፍተኛ ነበር። አሁን የመከላከያ ሰራዊት በሁለቱ ወገኖች መካከል ከሰፈረ በኋላ ግን ጦርነቱ ለጊዜው ጋብ ብሏል። ሆኖም ሁለቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች – ማለትም የህወሃት እና ብአዴን አመራሮች ውስጥ ውስጡን እየተናቆሩ ናቸው።
ህወሃት በድንበር ጉዳይ ካደረጋቸው የአገር ውስጥ ጦርነቶች ይሄኛው ጠንከር ያለ ነው። ከዚህ ቀደም የህወሃት ወይም የትግራይ ታጣቂዎች የአማራውን መሬት ሲወስዱ – ህዝቡ “በህግ አምላክ” ብሎ እየጮኸ ከመሞት ውጪ ብዙ ምርጫ አልነበረውም። አሁን ግን እየጮኸ ሳይሆን ጥይት እያጮኸ መሞትን የመረጠበትን አጋጣሚ ለማየት እየበቃን ነው። አሁን የደረንበትን የቅርቡን ታሪክ እንዳየነው ከሆነ – ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የአማራውን ህዝብ ከሁመራ እና ጠለምት: ከበየዳ, ከወልቃይት, ከድብ ባህር, ከአብደራፌ, ከብራ ዋድያ, ከሻግኔ እና ላሄን እያፈናቀሉ መሬቱን ለቀድሞ የወያኔ ወታደሮች ሲሰጡ ቆይተዋል። በአካባቢው የአማራው መሬት ብቻ አይደለም የተወሰደው። ወንዶቹን እያፈናቀሉ: ያንገራገረውን እየገደሉ ሚስቶቻቸውን እና ሴት ልጆቻቸውን በሙሉ ነው ነጥቀው የወሰዱት።
ባለቤት የሌለው መሬት – ቤጌምድር!
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለዚህ አካባቢ እኩል ግንዛቤ ላይኖረው ይችላል። በመሆኑም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ስለዚህ አካባቢ ታሪካዊ ዳራ ማሳየት አስፈላጊ ሆኗል። እናም በታሪክ መንኮራኩር ትንሽ ወደኋላ መሄድ ሊኖርብን ነው።
ይህ የሰሜን አውራጃ ከጥንት ጀምሮ ቤጌምድር ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በራሱ መሪዎች ይተዳደር የነበረ ስፍራ ነው። በደርግ ዘመን ስሙ ተቀይሮ ስሜን ጎንደር ሲባል በወቅቱ ከፍተኛ ክርክር የተደረገ ቢሆንም; ቀስ በቀስ ቤጌምድር መባሉ ቀርቶ ስሜን ጎንደር የሚለውን ስያሜ ይዞ ዘልቋል። ይህ የቤጌ ምድር ክልል በሰሜን ከኤርትራ ጋር በመረብ ወንዝ, ከትግራይ ጋር ደግሞ በተከዜ ወንዝ ተፈጥሮአዊ ድንበር ሰርቶ ይተዳደር ነበር። አጼ ቴዎድሮስ ይህንን ስፍራ በፍቅር እንጂ በጦርነት አሸንፈው አልገዙትም። ላዩን ሁመራ እና ወልቃይትን ካልሆነ በቀር ወደ አርማጭሆ ዘልቆ የአካባቢውን ህዝብ ያስገበረ መንግስት የለም። እዚህ ህዝብ ውስጥ ዘልቆ የፖለቲካ ስራ የሰራ አካል ቢኖር መጀመሪያ ኢዲዩ ከዚያ በኋላ ደግሞ ኢህዴን የተባለው የኢህአፓ ሁለተኛ እርከን አመራር ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ራስ ሚካኤል ስሁልም ሆኑ አጼ ዮሃንስ የተከዜን ወንዝ ሲሻገሩ – ከትግራይ ወጥተው ቤጌምድር መግባታቸውን ያውቁት ነበር።
የድሮውን ታሪክ ካነሳን ካልቀረ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የአክሱማዊት ገዢ የነበረው ንጉሥ ኢዛና – በአውደ ነገሥቱ ከ4ሺህ በላይ የሚቆጠር ሰራዊቱ የ”ቤጃ”ን ምድር መቆጣጠሩ ተጽፏል። ወደ መካከለኛው ዘመን ስንሻገር በ1530ዎቹ ንጉሥ ልብነ ድንግል ለፖርቱጋል ንጉሥ ደብዳቤ ሲጽፉ “ቤጌምድር” ድረስ ግዛታቸው መሆኑን ገልጸው ነበር። ከዚያ በኋላ በነበረውም ታሪክ ቢሆን በ18ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ እስከ 1788 ድረስ የየጁው ራስ አሊ አስተዳድረውታል። እንዲህ እንዲህ እያልን ዘመነ መሳፍንትን አልፈን በአጼ ቴዎድሮስም ሆነ አጼ ዮሃንስ ወይም አጼ ምኒልክ ዘመን ቤጌምድር ራሱን የቻለ ግዛት ሆኖ ቆይቷል።
በራስ ኃይሉም ሆነ, ራስ መንገሻ አቲከም ወይም ራስ ወልደጊዮርጊስ አቦዬ ዘመን ቤጌምድር የትግራይ ክልል የሆነበት ወይም እንዲሆን የተጠየቀበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ሌላው ቀርቶ ራስ ወልደጊዮርጊስ አቦዬ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በ1909 ዓ.ም. የንጉሥነት ዘውድ ሲጭኑ – ቤጌምድር ራስ ገዝ ክልል መሆኑ ታውቆለት ነበር። በነደጃዝማች አያሌው ብሩም ሆነ በነ ክፍሌ ዳዲ ሲተዳደርም ቤጌምድር ነበር – ስያሜው።
እስከ ቡያ ድረስ, በሃከርን ጨምሮ አብደራፊ የቤጃዎች ምድር እንጂ ሱዳንም ትግራይም ሆኖ አያውቅም። የጎንደር ነገሥታት ለሰራዊታቸው እህል እና ከብት እስከፈለጉት ድረስ የሚጫንላቸው ከዚሁ የቤጃ ምድር (ቤጃ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች መጠሪያ የነበረ ነው) ወይም ከቤጌምድር ነበር። ጣልያን አካባቢውን ሲቆጣጠር – ማይጨው ድረስ ዘምተው የወጉትን እነደጃች ጎላን ራስ ጎላ ብሎ መልሶ የሾመው ወልቃይት እና ጠገዴን በጸብ ሳይሆን በፍቅር ለመግዛት ካለው ፍላጎት በመነሳት ነው።
በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን በ1943 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ ጭምር – በአዋጅ ቤጌምድር በወቅቱ ከነበሩት 13ቱ ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ አንደኛው ነበር። (ነጋሪት ጋዜጣ 1943/1 አንብብ)። ጠቅላይ ግዛት ከሆነ በኋላ ጎንደርን ዋና ከተማው አደረገ። በተለይ ሁመራ መልማት ሲጀምር የወልቃይት እና ጠገዴ ህዝብ ጭምር የትራክተር እና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ባለቤት ሆኖ አካባቢውን ማልማት ጀመረ። በዚያን ወቅት የመሃል አገሩም ሆነ የጎንደር እና የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ቤጌምድር ተሻግረው አካባቢውን አልምተዋል። በሱዳን በኩል መሃዲ ሉግዲ ተራራን ሲወጣ – ወይም በኤርትራ በኩል ጀብሃ መረብን ተሻግሮ ሲመጣ – ሁሉም በአማራው እና በትግራይ በተለይም በወልቃይት ህዝብ እየተቀጡ ተመልሰዋል። ነገር ግን ከመቆየት ብዛት አካባቢው የቤጃዎች መሆኑ ቀርቶ በትግራይ ሰዎች እጅ ወደቀ። ቤጌምድር መባሉ ቀረና “ምዕራብ ትግራይ” የሚል ስያሜ ተሰጠው።
ሌላ ተጨማሪ ነገር እዚህ ላይ ማከል ያስፈልጋል። ከቤጌምድር በታች ያሉ ሰዎች የቤጃዎችን ምድር “ስሜን” እያሉ መጥራት ያዘወትሩ ነበር። (በኋላ ላይ North ለሚለው አቻ ፍቺ – አማርኛ ሰሜን የሚለውን ቃል የተዋሰው ከስሜን ነው)። ነገሮችን በደምሳሳው እንለፋቸውና ወደ ደርግ ዘመን እንሻገር። በደርግ ዘመን ከሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ይልቅ በአዲሱ ወታደራዊ አስተዳደር “አንገዛም” ብሎ መጀመሪያ የሸፈተው የቤጌምድር ህዝብ ነው። አብዛኛውም ህዝብ በኢዲዩ ፓርቲ ስር በመሰባሰብ በነራስ መንገሻ ስዩም መሪነት የትጥቅ ትግል ያደረገው እዚህ ምድር ላይ ነው። የኢህአፓ ሰራዊት ከትግራይ አሲምባ ከወጣ በኋላ የመጨረሻ ምሽጉን ያደረገው ጠለምት, በለሳ እና አርማጭሆን የመሳሰሉ የቤጌምድር ስትራቴጂ ቦታዎች ላይ ነው። የአካባቢው ህዝብ ከማዕከላዊ መንግስት የራቀ በመሆኑ ህጋዊ ገንዘብ ጥቅም ላይ ያልዋሉባቸው የገጠር አካባቢዎች ጭምር ነበሩ። እስከቅርብ ዘመን ድረስ በተለይ በአርማጭሆ የባርያ ንግድ ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም ነበር። በኋላ ላይ ኢህዴን አካባቢውን ሲቆጣጠር ብዙ ባሮች ነጻ ወጥተዋል።
ቤጌምድር እውቅና ተነፍጎት – የመንግስት አስተዳዳሪዎች በግድ እየተጫኑበት በሺዎች የሚቆጠሩ የግል ትራክተሮች እና እህል መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ዝገው እና አፈር በልቷቸው የቀሩት በተለይ በደርግ ዘመን ነበር። የግል እርሻዎች በ”መሬት ላራሹ” አዋጅ ሲወረሱ የቤጌምድር ሰዎች ለክብር እና ለአፈራቸውን ደማቸውን ገበሩ – ብዙዎች ሰማዕት ሆነው በትግል ሜዳ ህይወታቸው አለፈ። የተቀሩት ወደ ሱዳን ተሰደዱ። አገሩ ያለ አራሽ እና ያለባለቤት ቀረ። ይህ ግን እዚያው የቀሩትን ጭሰኞች – በተለይም ተከዜን ተሻግረው ሁመራ ላይ እገዛ ያደርጉ የነበሩትን የትግራይ ሰዎች ጠቀማቸው። በመሬት ላራሹ አዋጅ የትግራይ ሰዎችን ተጠቃሚ አደረገ። ቆይቶ ደግሞ ቤጌምድር የሚለው ስያሜ በመቀየሩ ታሪካዊ ስህተት ተሰራ።
ነገሮችን ለማጠቃለል ያህል – በደርግ ዘመን ቤጌምድር ስያሜው ተቀይሮ ስሜን ጎንደር ሲባል ብዙ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። ሆኖም በወቅቱ ጎንደርን ያስተዳድር ለነበረው ሻለቃ መላኩ ተፈራ “ቤጌምድር” የሚለውን ስያሜ መሰረዝ በጣም ቀላሉ ነገር ነበር። ነገሩ የሆነው በቤጌምድር ሰዎች “አልገዛም” ባይነት ነበር። በወቅቱ የቤጌምድር ስያሜ እንዲቀር በመደረጉ – ህዝቡ ሰሚ የሌለው ተቃውሞ አድርጎ ነበር። ግን የአካባቢው ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ለደርግ ያልተገዛ በመሆኑ – የአገሩን ሽማግሌዎች ጆሮ ሰጥቶ የሚሰማቸው አላገኙም። እናም ቤጌምድር የሚለው ስም ያለ አዋጅ እና ያለ ህግ ቀስ በቀስ ከህዝቡ ጆሮ እና ህሊና እየጠፋ መጣ።
የዚህ አካባቢ ህዝብ … ቀን ጠብቆ የሚጥል እና የሚያነሳ ለመሆኑ – የአጼ ቴዎድሮስን ነገር ምሳሌ በማድረግ – እንግሊዛዊው ሄንሪ ብላንክ የጻፈውን መግለጹ አሰልቺ ይሆናል እንጂ እውነትነት ያለው ነው የሚመስል። በራስ አሊ ያኮረፈው የቤጌምድር ህዝብ – አጼ ቴዎድሮስ ለስልጣን ከመብቃታቸው በፊት ፍቅር ነበሩ። ንጉሡም የቤጌምድር ባላባቶችን አክብረው ነው የቀረቧቸው። ንጉሠ ነገሥቱ ቤጌምድር ላይ ደብረ ታቦር ከተማን ሲገነቡም ሆነ ላስታን አልፈው ሸዋ ድረስ ሲዘልቁ ቤጌምድሮች አብረዋቸው ነበሩ። በኋላ ላይ ግን ኩርኩም ሲበዛባቸው ለአጼ ቴዎድሮስ መገበር አቁመው ንጉሡ እንዴት እንዳዳከሟቸው ሄንሪ ብላንክ በዝርዝር ይተነትናል። “ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ በደርግ ያኮረፈው የዚህ አካባቢ ህዝብ – ኢህዴን እና ህወሃትን ጋሻ ሆኖ መክቶላቸዋል። ለስልጣንም በቅተዋል። ሆኖም በዚህ ህዝብ ላይ ነው ዳግም ግፍ እና በደል እየተፈጸመ ያለው። የህዝቡን መሬት ህወሃት መውሰዱ ሳያንስ ለሱዳን እየሸነሸነ በመስጠት ላይ ነው።
በሚገርም ሁኔታ ወደትግራይ የተከለለው የቀድሞው የቤጌምድር መሬት አሁንም ድንበሩን ሉግዲ ተራራ አድርጎ ወደ ሱዳን የሄደ መሬት እንደሌለ ይነገራል። ወረድ ብሎ አማራውንና ሱዳንን የሚያገናኘው ድንበር ግን በህወሃት ታጣቂዎች አጋፋሪነነት ከ አርማጭሆ ማዶ ባህረሰላምን ይዘን ጣያ, ሽንፋ, ከአቡጢር እስከ አብደራፊ ድረስ ለሱዳን ተሰጥቷል። ሱዳን በ1956 ነጸ እንደወጣች የጠየቀቻቸውን መሬቶች (በጋምቤላ በኩል ጠይቃ ከነበረው መሬት በቀር) ሌሎቹን አንድ በአንድ እያገኘች ያለች ይመስላል።
ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ቤጌምድር እንደ አንድ ጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ አገር ስም እና ማንነቷን እንድታጣ; በውስጧ የነበሩት ወረዳ እና አውራጃዎች ያለ ጠያቂ እንዲበታተኑ በመደረጋቸው ነው። ህዝቡ በታሪኩ ቀርቶ በስሙ እንኳን እንዳይኮራ ሆኗል። ወንዶቹን አባረው አስረው እና ገድለው; ሴቶቻቸውን ወስደው ከነሱ የሚወለዱት ልጆች አዲስ ማንነት እንዲያበጁ እየተደረጉ ነው። ወደድንም ጠላን – ስሙን ብቻ ሳይሆን ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ ተደርጓል – በዚህ ህዝብ ላይ።
አሁን በቀደም…. የትጥቅ ትግሉ አብቅቶ ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር – ህወሃት የቤጌምድርን ግዛት “ምዕራብ ትግራይ” ብሎ ሰየመው። ከደርግ ጋር ሲዋጉ የነበሩ በጣም ብዙ ሺህ የሰራዊቱን አባላት የጡረታ ገንዘብ ከፍሎ መሬቱን ከዳር እስከዳር ሸንሽኖ ሰጣቸው። ወልቃይት ጠገዴ እና ጸለምት ጭምር በህወሃት ሰራዊት ተወሰዱ። አሁን የመስፋፋቱ ነገር እየገፋ መጥቶ የራስ ዳሽን ተራራን አንደኛውን ወገን ጭምር ጠቀለሉት። የቀድሞው ስሜን አውራጃ – የቀድሞው ቤጌምድር ቀስ በቀስ በህወሃት ሰዎች ቁጥጥር እየዋለ መጥቶ አርማጭሆ ድረስ ዘለቀ። በዚህ ጉዳይ ከህወሃት ሰዎች ጋር ስንነጋር “ህዝቡን እንጂ መሬቱን ለምን ታያላቹህ” ይሉናል። ‘ነባሩን ህዝብ እያጠፉት አዲሱን ሰፋሪ በግድ ተቀበሉ’ – አይነት አባባል የቀድሞው የህወሃት አባል አቶ ገብሩ አስራት ጭምር ደግመውልን – አንገታችንን የደፋንበት አጋጣሚ አለ።
ዛሬ በስሜን የአማራ ክልል እየታየ ያለው የመተራመስ አደጋ አርማጭሆ ሲደርስ ከጥይት ጩኸት ጋር እንስማው እንጂ የህዝቡ ብሶት እና አቤቱታ – ለቅሶ እና እግዚኦታ ማስተጋባት ከጀመረ በጣም ብዙ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ለጊዜው በመከላከያ ሰራዊት ቢሰክን እንኳን ሙሉ ለሙሉ የሚቆም አይነት አይሆንም። ወደፊት ይህ አካባቢ ጥይት ሳይሰማበት በሰላም ይኑር ከተባለ – የህወሃት ህገ ወጥ መስፋፋት መቆም ይኖርበታል። እስካሁን የወሰደውን መሬት ለታሪክ ፍርድ ትተን “ለምን?” ብለው የመብት ጥያቄ በመጠየቃቸው የታሰሩትን መፍታት – ለሞቱት የደም ካሳ መክፈል ይኖርበታል። ከጥንትም ቢሆን – በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ጭምር ቤጌምድር – በፍቅር ካልሆነ በቀር በግድ እና በጦርነት ተገዝቶ አያውቅምና ልብ ያለው ልብ ይበል!
ከላይ በታሪካዊ ዳራው ለማሳየት እንደሞከርነው ቤጌምድር (ቅማንትንም መጨመር ይቻላል) በአማራው እና በትግራይ ህዝብ ሲለማ ቆይቷል። ህዝቡ በጋብቻ እና በቋንቋ እርስ በርሱ የተሳሰረ ነው። ችግር እየተፈጠረ ያለው – መሬቱም ሚስቱም ጠመንጃ በያዙ የህወሃት ሰዎች መነጠቁን ሲቀጥል ነው። ስለሆነም ስሜን ጎንደር ወይም ቤጌምድር ላይ እርቅ እና ሰላም እንዲመጣ የህወሃት ሰራዊት በህገ ወጥ መንገድ መስፋፋቱን ማቆም አለበት። ስለተገደሉት ነዋሪዎች “ይቅርታ” መጠየቅ አለበት። በአካባቢው ዘላቂ የሆነ ሰላም ማምጣት ካስፈለገ ደግሞ ይህ በኢትዮጵያዊነቱ ፍጹም ኩራት ያለው ህዝብ – (ሰሜን ወይም ምእራብ ሳይባል) ከመረብ በታች ከተከዜ ወዲህ ያለው ህዝብ ቢያንስ ራሱን እንዲያስተዳድር እድል ሊሰጠው ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ስሜን ላይ የተጀመረው የአማራው እና የትግራይ የግዛት ጦርነት – የግዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም ዘመን መልኩን ሊቀይር እንደሚችል – በውድም ሆነ በግድ የምንቀበለው እውነት ነው።



