ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

‹መለስ በህይወት ቢኖር ራሱ የሚቃወማቸው ይመስለኛል››
‹‹አቶ ኃይለማርያም፣ የራሱን አመለካከት አሳድራለሁ ያለ ቀን፤ ወደ እነአንዱአለም ጎራ ይቀላቀላል፤ መለስ ቢኖርም ባይኖርም!!!›› አቶ ሀብታሙ አያሌው /የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ/

አሁን በእስር ላይ ማዕከላዊ ሆኖ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእግር ህመም እየተሰቃየ የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከመታሰሩ 10 ቀናት ቀደም ብሎ ለ‹‹ቀዳሚ ገጽ›› ጋዜጣ እኔ እና ባልደረባዬ አናንያ ሶሪ በ‹‹መለስ ራዕይ›› ዙሪያ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገንለት ነበር፡፡ ቃለ-ምልልሱም በጋዜጣው ላይ ተስተናግዷል፡፡ ቃለ-ምልልሱን ማንበብ ላልቻላችሁ ወገኖቼ ታነቡት ዘንድ የተወሰነውን እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡-


እሺ ወደ ቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንምጣና፡- …የ‹‹መለስ ራዕይ›› ተብሎ የሚገመተው የ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ጽንሰ ሃሳብና ሀገሪቱን ‹‹መካከለኛ ገቢ›› ያላት ለማድረግ የሚመኙት ምኞት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ላይ አንተ ያለህ አስተያየት እና ትንታኔ ምን ይመስላል?
-------------

እንግዲህ ቅድም ከጠቀስኩልህ የራዕይ ፍቺ አንጻር ስናየው፤ ‹‹የመለስ ራዕይ›› ራሱ ይሄ ነዎይ?! ነው ቀዳሚው ጥያቄ፡፡ ሰዎች ‹‹ይሄ የመለስ ራዕይ ነው›› ብለው ሊሰጡት ይፈልጋሉ - ለመለስ፡፡ ነገር ግን መለስ በህይወት ቢኖር ራሱ የሚቃወማቸው ይመስለኛል፡፡ ከሞተ በኃላ ‹‹ራዕዩ ይሄ ነው›› እያሉ ሲሉ፤ ቢኖር በእርግጠኛነት ‹‹የኔ ራዕይ ይሄ አይደለም!›› እንደሚላቸው ነው የሚሰማኝ፡፡ መለስ ‹‹ይህን …ይህን መስራት ይፈልግ ነበር›› ከሆነ፤ ሰዎች ሊሰሩ የሚፈልጉት በሙሉ ‹‹ራዕይ›› አይደለም፡፡ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የተለያየ ነገር የማድረግ/ የመስራት ፍላጎት ይኖራቸዋል፤ ያ ‹‹ራዕይ›› ብለን የምንወስደው ግን አይደለም፡፡ የመለስን ራዕይ በሚገባ ለመረዳት ካስፈለገ፤ አሁን ያልካቸው የልማት ፍላጎት፣ አገሪቷን ወደተሻለ ደረጃ መውሰድ ወ.ዘ.ተረፈ…. በሚል የሚዘበዝቧቸው እንዳልሆኑ ለመረዳት፤ ባጭሩ መለስ ማነው? የሚለውን አስቀድመን መመለስ አለብን፡፡ እንግዲህ፡- ካየነው፣ ከሰማነው፣ ካነበብነው ተነስተን መለስ በልጅነቱ ምን ዓይነት ባህርይ እንደነበረው ይብዛም ይነስም ግለ-ታሪኩን ከጻፉት ተመልክተናል፡፡

ከፍ ካለ በኃላ ግን፡- ጎበዝ ተማሪ መሆን ይፈልግ እንደነበረ፤ መማርና የሆነ ቦታ ላይ መድረስ ምኞቱ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ጎብዞ ከተማረ በኃላ ደግሞ፤ ተሸልሞ ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አዲስ አበባ መጥቷል፡፡ መሆን የሚፈልገውን ራሱ መለስ ሲናገር ‹‹ሃኪም/ ሜዲካል ዶክተር መሆንን›› ይመኝ እንደነበር ነው፡፡

ስለዚህ ‹‹የመለስ ራዕይ›› ሐኪም ወይም ሜዲካል-ዶክተር መሆን ነበረ፡፡ ነገር ግን በአንድ የህይወት አጋጣሚ፤ ሃኪም የመሆን ራዕዩን ለወጠ፡፡ ሌላ ራዕይ ደግሞ ሰነቀ፡፡ ሌላ ራዕይ የሰነቀበት ወቅትም ከሁለተኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ጫካ ሲገባ ነው፡፡

ጫካ ከገባ በኃላ ደግሞ፣ የ‹‹ትግራይ-ሪፐብሊክ›› መንግሥትን የመመስረት ራዕይ አነገበ፡፡ ይህም፡- ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠልና ራሱን የቻለ ‹‹የትግራይ ሪፐብሊክ›› መንግሥት የመመስረት ራዕይ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ይህ ራዕይ የጋራ ዓላማቸው ቢሆንም፤ መለስ ያንን ዓላማ ለማሳካት የሚሰራና ለዚያ ራዕይ የሚተጋ ሰው ነው የነበረው፡፡ የትግራይ ተወላጅ ብሔራዊ ስሜት ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ ግን፤ ይህ ትግራይን የመገንጠል ራዕይ የማይሳካ ሆነ፡፡ በተጓዳኝ ግን የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ባልጠበቁት ሁኔታ እየተዳከመ እና እየፈረሰ ሲመጣ፤ በ‹‹ትግራይ ሪፐብሊክ›› ብቻ ሳይታጠሩ መላ-ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ተገነዘቡ፡፡

ስለዚህ መለስ ቀደም ሲል የትግራይ ሪፐብሊክ መሪ የመሆን ራዕዩን የመላ-ኢትዮጵያ መሪ ወደመሆን አሻገረው፡፡ የኢትዮጵያ መሪ መሆን እንደሚቻል ሲረዳ፤ እስከ ቤተመንግሥት የሚያስመጣውን መንገድ ሁሉ ተጓዘበት፤ የሚያጠፋውን አጠፋ፣ የሚገድለውን ገደለ፣ በብልጠት የሚያልፈውን አለፈ፡፡ የኢትዮጵያ መሪም ሆኖ መጣ፡፡ ከፕሬዚዳንታዊ የሽግግር ጊዜ ጀምሮ ጠ/ሚኒስትር እስከሆነበት ድረስ፤ ለእርሱ አመቺ የሆነውን እና በሥልጣን ላይ ገዢ ሆኖ ለመቆየት የሚያስችለውን የሥርዓተ-መንግሥት አወቃቀር በመቀያየር ገዢነቱን አስጠብቆ ቀጠለ፡፡

በ1994 ዓ.ም. ህወሓት ሲከፋፈል የተቃወሙትን ሁሉ ገፍቶ ብቸኛ ጉልበታም ሆኖ ብቅ አለ፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስም መለስ ስለ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ፍልስፍና የሚያወራበት ምላስ አልነበረውም፡፡ ያውቁ የነበሩት ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም፡- ይህ ነው የሚባል ልማት በሀገሪቱ ውስጥ አልተካሄደም፡፡ ቀን ከሌት ግን መለስ ሲሰራ የነበረው ምንድን ነው? አሁን እነ አቶኤርሚያስ ለገሠን የመሰሉ የቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ እያጋለጡ እንዳሉት፤ የተወሰኑትን ከተሞች ‹‹የነፍጠኛ ከተማ›› ብሎ ፈርጆ እነርሱን እንዴት አዳክሞ እንደሚያጠፋ፣ በጠላትነት የፈረጃቸውን በሙሉ እንዴት አድርጎ አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣ፣ ብቸኛ መሪ ሆኖ እንዴት መቀጠል እንደሚችል …የመሳሰሉትን ዓይነት ነገሮች ነበር የሰራው፡፡

እነማክያቬሊና መሰሎቹ የጻፉት መጽሐፍ የሚያሳየውን አቅጣጫ እየተከተለ ለዛው ለቆመለት ‹‹ብቸኛ አምባገነን የሚፈራ መሪ›› የመሆን ራዕዩ ነበር ሲተጋ የኖረው፡፡ በ1997 ዓ.ም ያልጠበቀው ነገር ሲገጥመው፤ የሚገደለውን በትዕዛዝ አስገድሎ የሚታሰረውን አስሮ 1997ን ተሻገረው፡፡

ከዚህ በኋላ ግን አንድ ነገር አለ መለስ! ከዚህ በኋላ ‹‹ከናዳው ለማምለጥ ምን ያስፈልገናል?›› ብሎ ጠይቆ ራሱው ሲመልስ፡- ‹‹ከናዳው የፈጠነ ጉዞ ማድረግ አለብን!›› የሚል ድምዳሜ ያዘ፡፡ ከጭንቀቱ የተነሳ እና ከሥልጣን የሚያወርደውን ነገር በሙሉ ይቀለብስ ዘንድም፤ ‹‹አሁን ተጨባጭ የሆነ ሥራ መስራት አለብን!›› ብሎ ወሰነ፡፡ ስለዚህ ወደ ልማት የገባው ከልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና በመነሳት አይደለም፤ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ካናዳው ለማምለጥ ነው!
በመሆኑም፡- የልጅ ልጆቻችን ከፍለው የማይጨርሱት የውጭ ብድር እያመጣ፣ በየሳምንቱ መንገድ እያስቆፈረ፣ የባቡር ዝርጋታ እያለ …በአምስት ዓመት የሥትራቴጂክ ፕላን ውስጥ እንደኮንዶሚኒየም የመሳሰሉትን ህዝብ አማላይ ፕሮጀክቶች በማስቀመጥ በሥልጣኑ ላይ የመቆየት ቁማር ውስጥ ገባ፡፡

ስለዚህ አሁን የምናያቸው የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች የመለሰ ራዕይ አይደሉም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የመለስ ራዕይ ሳይሆኑ፤ መለስ ራዕይ አድርጎ የተነሳለትን ‹‹በሥልጣን ላይ የመቆየት የሥልጣን ጥሙን›› ለማርካት የሚያገለግሉ ወይም የሚያስፈልጉ የሥልጣን ማደላደያ ምርኩዞች ናቸው፡፡ እርሱ የያዘውን ሥልጣን እና የእሱ ቡድን የተቸረውን ልዩ ጥቅም (Power and Privilege) ለማስቀጠል የሚውሉ ግብዓቶች ናቸው - እነዚህ ልማቶች! ማሰር በነበረበት ጊዜ አስሮ ሥልጣን እና ልዩ ጥቅሙን አስቀጥሏል፡፡ መግደል በነበረበት ጊዜ ገድሎ ሥልጣን እና ልዩ ጥቅሙን አስቀጥሏል፡፡ አሁን ደግሞ እነዚህን ዓይነት ስራዎች በመስራት ሥልጣን እና ልዩ ጥቅሙን ማስቀጠል ነበረበት፡፡ በመሃል ግን ሞት ቀደመው፡፡

በመሆኑም መለስ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲሰራቸው የነበሩትን ወይም ያቀዳቸውን ተግባራት ‹‹እናስቀጥላለን›› ማለት ባጭሩ፡- ‹‹ እኛም ሥልጣን እና ልዩ ጥቅማችንን አስከብረን እቀጥላለን›› ማለት ነው፡፡

አቶ መለስ ለዴሞክራሲ እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ራዕይ ነበራቸው?
----------------
መለስ ‹‹የኢትዮጵያን ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ አደርገዋለሁ!›› ይል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ ማድረግ ካልቻለ፤ መለስ በሥልጣን ላይ መቆየት አልነበረበትም፡፡ ቃሉን አልጠበቀምና! የሆነ ሆኖ ‹‹ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን እጠብቅለታለሁ›› ብሎ አያውቅም መለስ፡፡ ምክንያቱም፡- ህዝቡ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ከተጠበቀለት፤ የዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ መለስን ከስልጣን ያወርደዋልና! ስለዚህ መለስ ስልጣኑን የሚነካበት የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጋር ዝር አይልም፡፡

በአጭሩ፡- መለስ በሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዙሪያ ዜሮ ፍላጎት የነበረው አምባ-ገነን እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም የዴሞክራሲ ጭላንጭል የሚታይበት በሩን ዘግቶና በሙሉ አጥፍቶ ከሄዱ ሰዎች መካከል አንዱና ቀንደኛው እሱው ስለነበር፡፡

መለስ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በር ከፍቼ ልለፍ ያለ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር የወሰነና ራዕይ የነበረው ሰው ቢሆን ኖሮ፤ የደህንነትና የመከላከያውን ተቋም በስሩ በአንድ ዕዝ ውስጥ አሰልፎ የተለየ አስተሳሰብ የያዙ ሰዎች የሚታሰሩበት ድብቅ እስር ቤቶች ገንብቶ አይሄድም ነበር፡፡ በመሆኑም የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጉዳይ መቼም ቢሆን ከሥልጣኑ ጋር አያይዞ ያይ የነበረ ሰው እንጂ፤ ለነዚህ መብቶች መከበር ራዕይ የነበረው ሆኖም አያውቅ!

…….
የ‹‹ መለስ ራዕይ›› የሚባለው ነገር ለምን የተፈጠረ ይመስልሃል?
-------------

ከመለስ ሞት ጋር ተያይዞ ኢህአዴግ የመበተን አደጋ ያጋጥመዋል የሚለው ስጋት ከፍተኛ ነበር፡፡ ስለዚህ፡- በመለስ ዙሪያ ተሰባስቦ የነበረውን ሃይል በራዕዩ ዙሪያ አሰባስቦ ሥልጣንን ለማቆየት የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ይሄ የሱ ራዕይ ነው፤ ይሄን ለማስቀጠል ‹‹አንበታተንም፣ አብረን እንሄዳለን›› የሚል ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፡- ከመለስ ማለፍ ጋር ተያይዞ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን መያዝ ያለበት ህወሓት ነው›› የሚሉ ተከራካሪዎች ስለነበሩ፤ ‹‹የሚቀጥለው የመለስ ራዕይ ነውና ከየትኛውም ቦታ ቢሆን መሪ እሾማለን›› በሚል ነገሩን ለማብረድ የመጣ ነው››

የ‹‹ መለስ ራዕይ›› ለኢህአዴግ አባላት የታለመ ወይስ ለኢትዮጵያ ህዝብ?
-------------
ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው ወይ? ለሚለው መልሱ ‹‹በፍጹም አይደለም›› ነው፡፡ መለስ ከኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ የሥልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበትን ካርድ ያጭበረበረ ነውና! መለስ ለኢትዮጵያ ህዝብ አልቆመምና!

የመለስ ራዕይ ለአጠቃላይ የፓርቲው አባላትም አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በፓርቲው ውስጥ የመለስ ራዕይ ትክክል አይደለም ብለው የሚምኑም ሰዎች ስላሉ፡፡ ስለዚህ መለስ በእርሱ አስተሳሰብ አምነው ከርሱ ጋር የተሰለፉትን በሙሉ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ሥርዓት ነው የዘረጋው፡፡ ይህንን ስንል፡- ከሱ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱና የሚቃወሙትን የሚያስሩ የሚገርፉ ኃይሎች ከነማሰሪያና መግረፊያ ቦታው ጭምር አዘጋጅቷል፡፡ እሱ የሚለውንና የሚያደርገውን የሚያስፈጽሙ አካላት የሚጠቀሙበት አሰራር ደግሞ ፈጥሯል፡፡ እንዴት መሬት እንደሚያገኙ፣ እንዴት የኢኮኖሚ የበላይነት እንደሚያገኙ ሰርቶበታል፡፡

ስለዚህ መለስ የያዘውን እና እርሱ የቆመለትን ራዕይ ሊያሳኩ የሚችሉ ሰዎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል፤ በተቃወሙት ጊዜ ደግሞ ሊያጠፋቸው የሚችል ራዕይ እና ሥርዓት ነው የነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ የመለስን አመለካከት እስካልተቃወመ ድረስ ስዬ አብርሃ የመከላከያ ሰራዊቱን እየመራ፣ የፈለገውን እየገላመጠ፣ የፈለገውን በኩርኩም እየመታ፣ በፈለገው መኪና እየሄደ ተቋማትን ይመራ ነበር፡፡ ከመለስ አስተሳሰብ ጋር በትንሹ እንኳ የተለየና ያፈነገጠ አስተሳሰብ ሲያመጣ ወደ ቃሊቲ ነው የተላከው፡፡

መለስ የእሱን አመለካከት የሚያስቀጥሉ ሰዎችን ወይም አሁን ኃ/ማርያም እያለ እንዳለው ‹‹ራዕዩን አስቀጥላለሁ!›› እስካለ ድረስ፤ በ ቪ. ኤይት (V-8) እየሄደ ቤተ-መንግሥት እየኖረ ጠ/ሚኒስትር እየተባለ ይኖራል፡፡ ከዚያ የተለየ የራሱ አስተሳሰብ የራሱ አመለካከት አሳድራለሁ ያለ ቀን ወደ እነአንዱአለም ጎራ ይቀላቀላል፡፡ መለስ ቢኖርም ባይኖርም!!! የሚገርመው ነገር እኮ ….. መለስ እያለ ብቻ አይደለም፤ ሳይኖር ራሱ እሱ ይፈልግ የነበረውን የሚያስቀጥሉ ኃይሎች አደራጅቷል፡፡ ከእሱ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱትን በሙሉ የሚያጠፉ ኃይሎች ገንብቶ አደራጅቶ ነው የሄደው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ‹‹እሱ የተከለው ነው›› የተባለውን ነገር የሚቃወም ማንኛውም ሰው ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ሳይኖርም ጭምር!!!

 

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ