Ethio-telecom sucks!ክንፉ አሰፋ

"የደወሉላቸው ደንበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም። ..." የምትለዋ አሰልቺ የቴሌ መልዕክት ያላጋጠመው ቢኖር ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ደውሎ የማያውቅ ሰው ብቻ መሆን አለበት። ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ቀድሞ ወዳጆቻቸው መደዋወል ጀመሩና በመሃል ተስፋ ቆረጡ አሉ።

አስር ለሚያህሉ አርሶአደሮች እና የሠራዊቱ አባላት ዘንድ ደውለው አልተሳካላቸውም። ለሁሉም ጥሪ ያገኙት ምላሽ "የደወሉላቸው ደንበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።" የሚል ሲሆንባቸው ራሳቸውን ነቀነቁ። ሰው ሁሉ የጨከነባቸው መሰላቸው። እንዲህም አሉ። "የሀገሬ ሰው እንኳን የስልክ ጥሪ፤ የእናት ሀገር ጥሪስ መች ተቀበለ።"

ለዓመታት በተከታታይ በሁለት ዲጅት እያደገች ያለች ሀገር የስልክ መስመር ችግር ይገጥማታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ችግሩን በደንብ ላልተረዳው፣ ሰው የሞባይል ስልክ የሚገዛው እንዲሁ ይዞ ለመታየት ነው ያስብል ይሆናል። ይህ አባባል በከፊል ትክክል ነው። ዘመናዊ ስልክ በመያዝ ለላንቲካነት ብቻ የሚጠቀሙበት ሰዎች አይጠፉም። የቻይናው ቀፎ ከሞዴል አርሶ አደሮች አልፎ ተራው አርሶ-አደር እጅ ላይም ገብቷል። አብዛኞቹ ግን ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አይጠቀሙበትም። ለዚህም ይመስላል በርካታ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚይዙ ሰዎች እንዲሁ ለዕይታ እና ለላንቲካ ብቻ የሚመስላቸው። አገልግሎቱን በተመለከተ ግን 99 በመቶ የሚሆነው ችግር የመዋቅር ችግር ነው።

Ethio-telecomለዓውዳመቱ ወደ ኢትዮጵያ ስልክ የደወላችሁ ካላችሁ፤ ይህ ነገር እንደገጠማችሁ እርግጥ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ቴሌ ከፍቷል። የሞባይሉ መስመርማ እንደ ዓይን እልም ብሎ ነው የጠፋው። ከበርካታ ሙከራ በኋላ መስመር ያገኘ ሰው ካለ በደስታ ይዘላል። የተቀባዩም ስልክ ካቃጨለ ተዓምር ነው የሚባለው። ከርማ ብቅ እንደምትለው የአዲስ አበባ መብራት ... ልክ እንደ ቧንቧ ውሃ፤ ስልኳም "መጣች - መጣች!" ብሎ መጨፈሩ አይቀርም። (በመከራ መስመር ሲገኝ እንዲህ ያስደስታል)

"እንኳን አደረሳችሁ!" ለማለት እኔም ወደ ሀገር ቤት ስልክ መታሁ።

"የደወሉላቸው ደንበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።" የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት። ለሁለተኛ ግዜ ስሞክር ደግሞ "የደወሉት ስልክ ለግዜው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነው።" የሚል ምላሽ አገኘሁ። ደቂቃ ባልሞላ ግዜ ውስጥ ጥሪ የማይቀበለው ስልክ ከአገልግሎት መስጫ ክልል መውጣቱ አስገረመኝ። ተስፋ ሳልቆርጥ ደጋግሜ ሞከርኩ። ቢያንስ ከአስር ግዜ ሙከራ በኋላ፤ መስመር አገኘሁና ሎተሪ የወጣልኝ ያህል ተሰማኝ።

ደስታዬ ግን ብዙም አልዘለቀም። በመሃል እንግዳ ነገር ተፈጠረ። ስልኩን የተቀበለኝ የደወልኩለት ሰው አልነበረም። የተፈጠረው ክስተት - ባለንበት የመረጃ ዘመን እንደ 17ኛው ክፍለ ዘመን "ቴሌ በኦፐሬተር መስራት ጀመረ እንዴ?" ያሰኛል። ነገሩ ግን ሌላ ነው። ስልኩን ያነሳው የተለመደው የስልክ ጠላፊ ስለመሆኑ አንዳች ጥርጥር አልነበረኝም። ሶማሌያውያን መርከብ ሲጠልፉ ፀሐዩ መንግሥታችን ደግሞ የስልክ ፓይረት መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች በዚያን ሰሞን ነግሮን ነበርና።

ውጭ ሀገር ያለ ኢትዮጵያዊ ዘመድ ለመጠየቅ መደወሉ አይቀርም። ተስፋ የማይቆርጥ፤ ደጋግሞ ይሞክራል። እንደ ዕድል የስልኩን መስመር ካገኘ ደግሞ ሌላ ችግር ይገጥመዋል። ዘው ብለው የሚገቡ የስልክ ጠላፊዎች መስመሩን ያውኩታል። ሌላው አማራጭ ደግሞ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ነው። በኢትዮጵያ ቴሌኮም አጭር መልዕክት ከመላክ ይልቅ ደብዳቤ ጽፎ በፖስታ መላኩ እየፈጠነ መጥቷል። አጭር መልዕክት የሚደርሰው ከቀናት በኋላ ነው። ከላኪው ዘንድ መልዕክቱ መድረሱ ቢረጋገጥም ተቀባዩ ጋ ጨርሶ ላይደርስም ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "የኢትዮጵያ ቴሌኮም ቴክኖሎጂ ከዴንማርክ፣ ከኖርዌይ እና በከፊል ከእንግሊዝ ቴክኖሎጂ ጋር አንድ ነው" ብለው ነበር። በዚህ መግለጫቸው አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ እንዲሁም የስልክ መስመሩ ጥራት እና አስተማማኝነት በደንብ አድርገው ነበር "ለጋዜጠኞቹ" የገለጹላቸው። ይህን ተናግረው እንዳበቁ ግን የራሳቸውም ስልክ መጠለፉን ሰማን። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ አልሰሙት ይሆናል እንጂ፤ "እኛ ሲም ካርድ፤ አንተ ደግሞ ቀፎ ነህ!" ይሏቸዋል - ከላይና ከታች ያሉ አለቆቻቸው።

የኢትዮጵያን ስልክ አገልግሎት ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና እንግሊዝ ጋር አወዳድረው ማወደሳቸው ግን ራሳቸው ካዴሬዎቹንም ሳይቀር ሳያሳፍራቸው አልቀረም። ሰውየው የኢትዮጵያን ቴሌኮም እያወዳደሩ ያሉት 99.9 በመቶ ሳያቋርጥ አገልግሎት ከሚሰጠው አራተኛው ጀንሬሽን የምዕራቡ ቴክኖሎጂ ጋር ነው። መቼም ሁሉም ይዋሻሉ። ነብሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ዜናዊም ይዋሹ ነበር። ለዛ ያለው ውሸት አለ። እጅ፣ እግርና ዓይን የሌለው ውሸትም አለ። እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ውሸት ግን እመራዋለሁ የሚሉትንም ሕዝብ እንደመናቅ ይቆጠራል። እኚህ ሰው የሞራል እሴታቸውን ሁሉ አሽቀንጥረው ሊጥሉት ይችሉ ይሆናል። ምሁራዊ ግብአታቸውንም ለተራ ፖለቲካ ጥቅም ሊያስወግዱት ይችላሉ። እምነታቸውስ እንዲህ አይነቱን ቅጥፈት ይፈቅድላቸው ይሆን?

የቴሌ የኢንተርኔት አገልግሎት የመንግሥት አልባዋ ሶማልያን አንድ መቶኛም። ኮሜዲያን ክበበው ገዳ እንደቀልድ የነገረኝ ቁም-ነገር የኢትዮጵያን ኢንተርኔት ፍጥነት በደንብ ይገልጸዋል። ክበበው ሰሜን አሜሪካ የሥራ ጉብኝቱ ወቅት ፎቶ ተነስቶ ለቤተሰቡ በኢሜይል ይልካል። የላከው ፎቶ መድረሱን ለማረጋገጥ በነጋታው ወደ አዲስ አበባ ደወለ።

"Ethio-telecomፎቶው ደረሰ?"

"አልደረሰም!"

ሌላ ቀን እንደገና ደውሎ የላከው ፎቶ እንዳልደረሰ ተነገረው። ለሦስተኛ ግዜ ደውሎ ኢሜይሉ እንደደረሰ ጠየቀ። አሁንም አልደረሰም ተባለ። እንዲህ እያለ ሣምንት ሞላው።

"በሣምንቱ እኔ ቀድሜ ደረስኩ።" ነበር ያለው ክበበው።

የኢሜይል መልዕክቱ መድረሱ ከተረጋገጠ በኋላ - ሌላ ችግር ገጠመው። ኢሜይሉ ሲከፈት ግማሽ አካሉን ነበር የሚያሳየው። ፎቶው እስኪያወርድ (ዳውንሎድ እስኪያደርግ) ደግሞ ግማሽ ቀን መፍጀቱ ግድ ነበር።

ይህንን አገልግሎት ነው አቶ ኃይለማርያም ከምዕራቡ ዓለም አገልግሎት ጥራትና ፍጥነት ጋር እያወዳደሩ የሚነገሩን። በአስር ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ በስልክ መገኛኘት ህልም በሆነበት ሀገር፤ ስለ ስልክ ጥራት መናገር ቅጥፈት ብቻ ሳይሆን የሰውየውንም የሞራል ውድቀት ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ ትልቅና ግዙፍ የሀገሪቱ ተቋም ነው። እድገቱ ግን ያሳዝናል። በአስር ዓመት ግዜ ውስጥ ብቻ እንኳን እድገቱ በ75 በመቶ ቁልቁል ወርዷል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ተቋሙ አገልግሎት መስጠቱን አቁሞ ወደ ስለላ ተቋም መቀየሩ ነው። ባለፈው ወር ይፋ የሆነው ባለ 100 ገጹ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ይህንን መንግሥታዊ የስልክ እና የኢንተርኔት ጠለፋ አረጋግጧል።

"የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የነበረን አንድ ዜጋ አፍነው ካሰሩት በኋላ ውጭ የተደዋወለበትን የስልክ ቁጥር ዝርዝር አሳዩት።" ይላል ጠቀማጭነቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሆነው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም። ሰውየው የታሰረው ያልተከፈለ የስልክ ሂሳብ ኖሮበት አልነበረም። ባለሥልጣናቱንም ዓላማም፣ ወይንም መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ አላሴረም። ወንጀሉ፤ ከውጭ ሀገር ስልክ ስለተደወለለትና ከወዳጅ ዘመዶቹ ስለተወያየ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ፍጹም እንግዳ ነገር ነው። ከተለምዶ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብም እጅግ የከፋ!

የዜጎች ሁሉ ስልክ በቴሌ በኩል ይጠለፋል። እንደ ስካይፕ እና ቫይበር ያሉ የቮይስ ኦቨር ስልኮች ደግሞ ፊን ፊሸር በተባለ የኮምፒዩተር ቫይረስ አማካኝነት ይጠለፋሉ። በዚህ አይነት በዜጎች የግል ሕይወት ሳይቀር እየገቡ ቴሌን ሙሉ በሙሉ የስለላ ተቋም አደረጉት።

ሞባይል ስልክ እና ኢንተርኔት በአፍሪካ አህጉር በእጅጉ እየተስፋፋ ይገኛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 30 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል። በኢትዮጵያ ግን የስልክ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚው ከ2.5 በመቶ አልዘለቀም። ጎረቤት የሆነችው የኬንያ ህዝብ 40 በመቶ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ነው። መንግሥት አልባዋ ሶማልያ እንኳን፣ ስድስት የቴሌፎንና ስልክ አቅራቢ ኩባንያዎች አሏት። የሶማልያ ህዝብ ጥራት ያለው የስልክ መስመር እና ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። በኡጋንዳም የዚህ አገልግሎት ሰጪ በመንግሥት ሞኖፖሊ ስር አይደለም። ከሰባት በላይ የግል ኩባንያዎች እየተፎካከሩ ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ ጠተቃሚውን ህዝብ ወደ 50 በመቶ አድርሰውታል።

ያለነው በመረጃ ዘመን ነውና ያለመረጃ እና ያለ መረጃ ቴክኖሎጂ እድገት አመጣለሁ ማለት ዘበት ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሀገሪቱን ወደ መረጃ ሳይሆን ወደ ጨለማ ዘመን ነው እየመራት ያለው። እንደምናነበው ከሆነ የኢትዮጵያን ቴሌኮም ለማስፋፋት ከሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ሆኗል። ይህ ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ ቢውል አባይንም ይገድባል። ለዚህ የእድገት ሳይሆን ይልቁንም የጥፋት ጎዳና ተባባሪ የሆነችው ቻይናም በውጭ ምንዛሪ እየተከፈላት ቴሌን ብቁ የስለላ ተቋም አድርጋዋለች። የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስትሩም ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ሀገሮች ጋር በመተባበር የቴሌ ጥራት ላይ ሳይሆን የሚሠራው የስለላ ሃርድዌር እና ሶፍትዌር ማስገባቱ ላይ ነው።

የሀገሪቱ ግብር ከፋዮች ገንዘብ መልሶ ራሳቸውን እንዲያፍን መደረጉ እጅግ ያሳዝናል።

የቴሌ መልስ መስጫ ላይ ያለው መልዕክት ግን መሻሻል አለበት። "ለግዜው" የሚለው ቢቀየር ድርጅቱን ከሐሜት ያድነዋል። እናም መልዕክቱ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፣

"የደወሉላቸው ደንበኛ 'ለሁልግዜ' ጥሪ አይቀበሉም። ..."

ከዚያ በኋላ ደዋዩም ተስፋ ቆርጦ መደወል ያቆማል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ