ሰማያዊ ፓርቲ የሚታገለው ማንን ነው?
ግርማ ካሳ
ሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ እንደጠራ አነበብኩ። ገረመኝ። መጋቢት 28 ቀን በአንድነት ፓርቲ ሰልፍ ይደረጋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕጉን ባፈረሰ መልኩ በመጋቢት 28 ቀን ሰልፍ ማድረግ እንደማይቻል ገለጸ።
የሰልፉ ቀን ወይንም ቦታ እንዲቀየር የመጠየቅ እንጂ በጥቅሉ ለቀረቡት የሰልፍ ጥያቄዎች እውቅና አንሰጥም የማለት መብት አስተዳደሩ እንደሌለው በመጥቀስ፣ በአስተዳደሩ የተላከውን ሕገ ወጥ ደብዳቤ አንድነት እንደማይቀበል አሳወቀ። አንድነት ተለዋጭ ቀን እንዲያቀርብ የሚጠይቅ፣ ሕጉን የተከተለ ሁለተኛ ደብዳቤ፣ አስተዳደሩ፣ ላከ። የአንድነት ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን ሊደረግ የታሰበውን ሰልፍ ወደ ሚያዚያ 5 ቀን ለማድረግ እንደሚፈልግ አሳወቀ። በሚያዚያ 5 ቀን፣ የሩጫ ዝግጅት ስላለ፣ ቅዳሜ ሚያዚያ 4 ቀን ሰልፉን ማድረግ እንደሚቻል፣ አስተዳደሩ በደብዳቤ ገለጸ። ግምሽ ቀን የሚሰራበት እንደመሆኑ፣ ቅዳሜ ቀን ሰልፉን ማድረግ እንደማይስማማው የአንድነት ፓርቲ ገልጸ። በሳምንቱ እሁድ ፋሲካ፣ በአስራ አምስት ቀኑ ደግሞ ዳግማይ ትንሳኤ በመሆኑ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች አክብሮቱን በመግለጽ፣ ሁለት እሁዶችን (ሚያዚያ 12 እና 19) አልፎ በሚያዚያ 26 ቀን ሰልፉን ለማድረግ ወሰነ።
ምንም እንኳን የአዲስ አበባ አስተዳደር መጀመሪያ ላይ የጻፋቸው ሕግ ወጥ ደብዳቤዎች አሳዛኝ የነበሩ ቢሆንም፣ የአንድነት ፓርቲ ሕግ ወጥ ደብዳቤዎችን እንደማይቀበል ካሳወቀበት ጊዜ በኋላ ግን፣ በአንድነት እና በአስተዳደሩ መካከል ሲደረጉ የነበሩት የደብዳቤ ልውውጦች ጤናማ መሰሉኝ። ያሉ ልዩነቶችን በሰለጠነ መልኩ ለመፍታት መሞከር ሊበረታታ የሚገባው ነው።
የአንድነት ፓርቲ ከአስተዳደሩ ጋር በዚህ ሁኔታ እየተነጋገረ ባለበት ሁኔታ፣ ሳይታሰብ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የተለየ ጥያቄዎች ቢኖሩት እሺ፣ ግን አንድነት ባቀረባቸው ጥያቄዎች ዙሪያ፣ ሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ ጠራ። ይሄም ሰማያዊ ፓርቲን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎችን እንድጠይቅ አደረገኝ።
የአንድነት ፓርቲ ሚያዚያ 19 ቀንን ያለፈው ዳግማይ ትንሳኤ ስለሆነ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ እንደ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ አካባቢ እየወሰደ ስላለው አቋም ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ፣ የታሰሩ ሙስሊም እስረኞች እንዲፈቱ፣ ጠይቋል። በዚህ ሁኔታ ለሙስሊሙ ማህብረሰብ ከበሬታ መሰጠቱ ተገቢ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ለክርስትና እምነት ተከታዮችም ከበሬታ ማሳየት አልነበረበትምን? በክርስቲያኖች ዘንድ ትልቅ አመት በዓል በሆነበት፣ በዳግማይ ትንሳኤ ቀን፣ ሰልፍ መጥራት ተገቢ ነውን? ፈረንጆች እንደሚሉት ”ሴንሲቲቭ” መሆን አልነበረበትምን? ሁሉም እምነቶች መከበር አለባቸው ባይ ነኝ። ሰማያዊ በዚህ ረገድ ትክክል አደረገ አልልም። ይሄ የመጀመሪው ነጥቤ ነው።
ሰማያዊ ፓርቲ ያነሳቸው ጉዳዮች፣ የአንድነት ፓርቲም ያነሳቸው ጉዳዮች ናቸው። የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው። ሰማያዊና አንድነት ቢዋሃዱ ጥሩ ነበር። ግን ሰማያዊ ለብቻው መጋለብ የሚፈልግ በመሆኑ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ቢኖርም፣ መዋሃድ አልተቻለም። ነገር ግን የቀረቡ ጥያቄዎች ተመሳሳይ በሆኑበት ሁኔታ፣ ሰማያዊ የራሱን ሰልፍ፣ አንድነት ሊጠራ ባሰበበት ወቅት ለማድረግ ከሚሞክር፣ ከአንድነት ጋር ተነጋግሮ፣ ቢያንስ በጋራ ሰልፍ ቢጠራ መልካም ነበር። ለምን ያ እንዳልሆነ አለገባኝም። ሰልፍ ሲጠራ እኮ አላማ ሊኖረውና ውጤት ሊያስመዘግብ ይገባል። እንደው ዝም ብሎ ሰልፍ ማድረግ በራሱ የትም አያደርስም። ሰልፍ የሚደረገው ትልቅ መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ሰልፉ የተሳካ የሚሆነውም በተቻለ መጠን ብዙ ሕዝብ ሲገኝ ነው።
ሰልፉ በጋራ በመጠራቱ፣ እርግጥ ነው ሰማያዊ ለብቻው የተለየ ክሬዲት አያስገኝለትም። አንድነትም የተለየ ክሬዲት አያገኝም። ክሬዲቱን የሚወስዱት በጋራ ነው የሚሆነው። ያ ደግሞ ችግር አለው ብዬ አላስብም። ለሕዝብ የሚያስብ ድርጅት፣ ”ድርጅቴ ብቻ ለምን አልተጠቀመም?” የሚለውን ሳይሆን ”ሕዝብን ይጠቅማል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ነው የሚያቀርበው። ከድርጅት በላይ የአገርን ጥቅም ያስቀድማል። በዚህ ረገድ ሰማያዊ መጠይቅ አለበት። ይሄ ሁለተኛ ነጥቤ ነው።
ሌላው ያስገረምኝ ነገር ቢኖር፣ ሶስተኛ ነጥቤ የማደርገው፣ የአንድነት ፓርቲ በባህር ዳር ሲያደርግ በነበረ ጊዜ፣ ማለት ሁለት ወራት ገደማ በፊት፣ ለምን ሰማያዊ በአዲስ አበባ ሰልፍ እንዳልጠራ ነው። ወይንም ደግሞ አንድነት በአዋሳ፣ ድሬዳዋ በመሳሰሉት ከተሞች ወደፊት ሰልፎች ለማድረግ ባሰበበት ወቅት፣ በአዲስ አበባ ሌላ ሰልፍ ስለማይኖር፣ ያኔ ለምን ሰልፍ እንደማይጠራ ነው። ለምን ቢያንስ፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተላበሰ፣ ፕሮፌሽናል፣ አክብሮት፣ ለአንድነት ፓርቲ አሳይም? ለምን አንድነት ሊያደርግ ባሰበበት ወቅት ሰልፍ ይጠራል? ባልጠፋ ጊዜ ለምን በዚህ ወቅት ሰማያዊ ጣልቃ ይገባል? ይህ በአንድነት ፓርቲ ላይ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በአገር ውጭ ባሉ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ንቀት እንዳላቸው አያሳይምን? ”ሰማያዊዎች የሚታገሉት አገዛዙን ሳይሆን አንድነትን ነው” የሚል ስሜትስ ሰዎች ቢኖራቸው ያስገርማልን?
እንግዲህ ለማጠቃለል ይሄን እላለሁ። ሰማያዊዎች በዚህ ረገድ ትልቅ ስህተት እየሰሩ በመሆናቸው ልብ ይገዙና ቆም ብለው ያስቡ ዘንድ እመክራለሁ። እላለሁ። የአንድነት ፓርቲ ትልቅ መሰረትና ድጋፍ ያለው ድርጅት ነው። አንድነትን ለመደፍጠጥ አስብው ከሆነ፣ የራሳቸው እግር ላይ እንደሚተኩሱ ማወቅ አለባቸው። የአንድነት ፓርቲ የሚያራምደው የሰለጠነ ፖለቲካ የማይመቻቸው፣ ”የአገርን ችግር ለመፍታት፣ አንድነት ከኢሕአዴግ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ” ማለቱ ያበሳጫቸው፣ በውጭ ያሉ ጥቂት ጽኝፈኞችና አክራሪዎች፣ አንድነት ፓርቲ ተዳክሞ፣ ሰማያዊ ፓርቲ አይሎ እንዲወጣ አችከመፈለጋቸው የተነሳ፣ ሆይ ሆይ፣ እንደሚሏቸው ይገባኛል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አገራችን የምትፈልገው እንዲሁ በስሜት የመጋለብ ፖለቲካን ሳይሆን፣ ሕዝቡን በአራቱም ማእዘናት የሚያደራጁ፣ ብስለትና እርጋታ የተሞሉ አመራሮች ያሏቸው፣ በሚስማሙባቸው ጉዳዮች አብሮ ለመስራት የተዘጋጁ፣ የሚከባበሩና የሚቻቻሉ ድርጅቶችን ነው። የጀብደኝነት ፖለቲካን ሕዝቡ አይፈልግም። ”እኔ ብቻ ነኝ የማወቀው” የሚል ግትር ፖለቲካ ቦታ አይኖረውም።



