ዳዊት መላኩ (ከጀርመን)
አባቶች ሲተርቱ ''ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም'' ይላሉ። ዝላዬን ተከትሎ ምን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ በዝላይ አይሳተፍም ዝላይም አይወድም። የወያኔ አንባገነን መንግሥት ለምን ይሸበራል? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው። ከባዱ እና አስካሁን ብዙ በሥልጣን እንዲቆይ ያስቻለው ግን በመፍትሄው ላይ በጋራ መሥራት አለመቻላችን ነው። ወያኔ የሚሸበረው የህዝብን ሀብት ስለሚዘርፍ፤ ህዝብን ስለሚገድል፤ ህዝብን የሚጎዳ ሥራ ስለሚሰራ፤ የገንዛ ሥራው ነው ጥላ እየተከተለ እንደሸበር የሚያደርገው።

በራሱ የሚተማመን እና መልካም ሥራ የሚሰራ መንግሥት ማንም ምንም ይፃፍ ማንም የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት ይደግፍ፤ ማንም የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት ያቁዋቁም የሰራው መልካም ሥራ ዋስትናው ስለሆነ ምንም ይመጣብኛል ብሎ አይሰጋም። ወያኔ ግን ይዞት የተነሳውም ዓላማም ይሁን የሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተቆናጠጠም በኋላ የሚሰራው ሥራ የተሳሳተ በመሆኑ በራሱ ሥራ እና ክፉ ሃሳብ ዘወትር ይሸበራል።

ወያኔ ነፃ አውጪ ነኝ እያለ የዜጎችን ነፃነት በአደባባይ የሚገፍ፤ የመደራጀትና የመጻፍ መብትን የማይፈልግ፤ የራሱ ጥላ የሚያስደነብረው ተሸብሮ የሚያሸብር ድርጅት ነው። አንድ ወቅት የወያኔው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የወያኔ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው ብለው ነበር። እሳቸው ቃሉን የተጠቀሙበት ለሌላ ዓላማ ቢሆንም እውነታው ግን ወያኔ ሁሌም ክፉ ሥራው እያባነነው፤ የንጹኃን ደም እረፍት እየነሳው ሲቃዥ እንደሚድር ሳያስቡት ያጋጠማቸውን የስነልቦና ችግር ነው ባደባባይ የዘረገፉት። ለወያኔ የሽብር ምንጮች፤

1. ከመነሻው ዘርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ይዘው ሲነሱ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደቀስተ ደመና በልዩነቱ ውስጥ ባንድነት አሸብርቆ ለዘመናት ተጋብቶ ተዋልዶ አብሮ የኖር የራሱ የሆነ የፍልስፍና የባህል የአኑዋዋር ዘዴ የሚከተል በመሆኑ፤ የስታሊን ፍልስፍና ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ እንደማይተገበር ያውቃል። ስለዚህ ከመነሻው የነበረውን ታሪክ፤ ባህል፤ አንድነት ማፈራረስ በመሆኑ ሰዎች ባንድነት በሀገራዊ ስሜት የጋራ አጀንዳ ይዘው የሚመጡ፤ የህዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ጥያቄዎች ሁሉ ያሸብራቸዋል።

2. ወያኔዎች ዋናው ችግራቸው የሥልጣን ጥማት በመሆኑ ሥልጣኑንም የሚፈልጉት ህዝብን በማስተዳደር ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅም ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሥልጣንን መሰረት አድርገው የህዝብን ሀብት ያላግባብ ስለሚዘርፉ ሥልጣናቸውን ባጡ ማግስት ያን ሁሉ ነገራቸው የሚያጡ ስለሚመስላቸው የሚዘርፉት የሀብት መጠን፤ ሀብቱን ያገኙበት መንገድ ሕገወጥነት ሁሌም ከዛሬ ነገ ይነቁብናል እያሉ ይሸበራሉ።

3. የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማጥፋት በአማራው መቃብር ላይ ሥልጣናቸውን ማደላደል ስለሚፈልጉ ከዚህ ወገን የሚመጣ የህዝብ ጥያቄ ሁሌም ያሽብራቸዋል። በተለይ ጫካ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ የፈፀሙት ከፍተኛ ወንጀል ያሸብራቸዋል። ለአማራው ያላቸውን ጥላቻ ባያክልም በሌሎች ብሔረሰቦች ላይም ምንም እምነት የላቸውም። በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች አጥብቆ ይፈራቸዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኦሮምኛ ተናጋሪ አንድ ቀን ሊያምጽብኝ ይችላል መሚል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በጮኹ ቁጥር የለመደው የሽብር ዛር ተነስቶ ያንገፈግፈዋል።

4. ሌላው ወያኔን የሚያሸብረው የመገናኛ ብዙኀን ነው። ለህዝቡ እውነቱን በመደበቅ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ስለሚግተው ህዝቡ እውነቱን ካወቀ ሥልጣኔን ላጣ ነው፤ ሥልጣን ካጣሁ ደግሞ እንደሰው ለመኖርም የሚያስችለኝ መልካም ነገር ስለሌለኝ እጠፋለሁ ብሎ ማሰቡ ሌላው የሽብር ምንጩ ነው። ለዚህ ነው እንግዲህ ኢሳትን ጨምሮ የነፃው ፕሬስ ለወያኔ የሽብር ምንጭ የሚሆኑት።

5. ወያኔ ህዝብን አደንቁሮ፣ አደህይቶ እና አዋርዶ መግዛት ስለሚፈልግ ሰዎች ባወቁ ቁጥር፤ በኩራት ቀና ማለት ከጀመሩ፤ እንዲሁም የዕለት ኑሮዋቸውን ባሸነፉ ቁጥር ነገ ከምግብ ያለፈ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ብሎ በማሰብ በሰዎች ማወቅ፤ በማግኘታቸው እና በልበ ሙሉነታቸው ሁሉ ይሸበራል። ከምን ተነስቶ ነው እንዲህ ኩራት የተሰማው ማን አይዞህ ብሎት ነው ከጀርባው ምን ቢኖር ነው በማለት ይሸበራል።

6. ሌላው ትልቁ የወያኔ የሽብር ምንጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ በኩል የሚመጣው ችግር ከሁሉ የከፋ እንደሚሆን ያውቃል። የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ህዝቡን አደራጅቶ የሚመራ ሁሉን አቀፍ የሆነ የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች አንግቦ የተነሳ የፖለቲካ ድርጅት የወያኔን አንባገነን መንግሥት ነፍስ ለመውሰድ የተላከ መላከ-ሞት ስለሚመስላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት በተፈጠረ ቁጠር የወያኔ መሰረት ያናጣል። ከላይ እስከታች በከፍተኛ ሽብር ስር ይወድቃሉ።

7. ወያኔ የዜጎችን በነፃነት የማምለክ ሰብዓዊ መብታቸውን በመግፈፍ ህዝቦች እምነት የለሽ የወያኔ ተላላኪ እና ጋሻ-ጃግሬ እንዲሆኑ ስለሚፈልግ እና ማንኛውም እምነት ደግሞ መልካም ሥራን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ይቅር ባይነትን አልፎ ተርፎም ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት በማስተማር ህዝብን ለእውነት እንዲቆም ስለሚያደርጉ የምዕምናን ሕብረት ያሸብረዋል። ለዚህም ነው ማህበረቅዱሳን፣ መጅሊስ፣ ... ስማቸው በተጠራ ቁጥር የሚያንዘፈዝፈው።

8. ሌላው ወያኔን የሚያሸብረው ምርጫ ነው። በህዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ሥልጣን ከሕዝብ በሚወጣ ድምጽ ብቻ ነው ሥልጣን መያዝ ያለበት በተባለ ቁጥር መበርገግ መሸበር የሚያስገርም ነገር አይደለም። ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚይዝ የሚጨብጠውን ነው የሚያጣው። ሠራዊቱን ከቦታ ቦታ ያዘዋውራል፤ መድፍ ታንክ ሳይቀር በከተማው እንዲርመሰመስ ያደርጋል።

ከላይ ለማየት አንደሞከርነው አንድ ሻንበል ጦር የሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወያኔን ስማቸው በመጠራቱ ብቻ ያሸብሩታል። ዛሬ ወያኔ የሚሸበረው በሰማያዊ ፓርቲ፣ በአንድነት፣ በግንቦት ሰባት እና በሌሎችም ነው። እነዚህ ድርጅቶች ሠራዊት ስላላቸው፣ የጦር መሳሪያ ስለታጠቁ አይደለም ወያኔን የሚያሸብሩት። እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄዎቻቸው የህዝብ ጥያቄዎች በመሆናቸው ወያኔን ማሸበራቸው የማይቀር ነው። የሚያነሱዋቸው የፍትህ፤ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ወያኔ አስቦት የማያውቀው ነገር በመሆኑ ከራሱ የተፈጥሮ ባህሪ በመነሳት ስማቸው በተጠራ ቁጥር ይሸበራል። ነገር ግን እየተሸበረ ያለው በግድ ሳይፈልጉት ሥልጣን ኮርቻ ላይ ተቆናጦ እንደመዥገር ደም እየመጠጠ ያለው የወያኔ መንግሥት እንጅ ህዝቡ የነፃነት አየር የሚተነፍስበት ቀን እንዲመጣ በመጠባበቅ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ ባሁኑ ሰዓት አሸባሪ ድርጅት ወይም ግለሰብ ሳይኖር ወያኔ በራሱ ተሸብሮ እያሸበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃም እስካሁን ከተቋቋሙ የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አሸባሪ የተባለ ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነው። ወያኔን የሚያሸብረው እንግዲህ ክፉ ሥራው እና ፍርሃቱ ነው። እንግዲህ ለወያኔም እንዲህ እየተሸበረ ከሚኖር መፍትሄ እንዲሆነው እና ከሽብር እንዲላቀቅ የሸብር ምንጩ የሆነውን ሥልጣኑን ለህዝብ በማስረከብ፤ ፍትሕ፣ ሠላም እና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ እላለሁ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝቦች!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ