አሰግድ ኣረጋ (ኮለምበስ - ኦሃዮ)
ጤፍ Teff. Photo by Peter Bregg

ሰሞኑን ስለጤፍ ምርታችን የባዕዳኑ ብዙኀን መገናኛ አጀብ እያሉን ነው፤ ለዘመናት የተደበቀው የዘሩ ገመና መጋለጡን እየነገሩን ነው፤ ስለያዘው ንጥረ ነገር፣ ስለጤናማነቱ፣ በምዕራቡ ገበያ ስለመፈለጉ፣ ከሁለም በላይ ስለ ውጭ ምንዛሪ ምንጭነቱ።

ምግብነቱ ተትረፍርፎ የኢትዮጵያ ህዝብ ማስቀመጫ - ቦታ ያጣ ይመስል፣ የወንዙ ልጆች ጭምር፣ ጤፍ-የጤፍ ዘር፣ እንጀራ፣ ብሰኩት፣ ኬክ ሆኖ ምግብ በዝቶበት ለሚቀናጣው ለውጭ ገበያ እንዲነጉድ ከምዕራባውያኑ ጋር አብረን ከበሮ እየደለቅን ነው፤ አደብ ልንገዛ ይገባል።

ባለሙያዎቹ ወቅታዊና በቂ መረጃ እስካላስጨበጡን ድረስ፣ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዕምነት፣ ምርታማነቱ ባለኽበት እርገጥ የሆነውንና - በደሃው ገበሬ ማሳ ዛሬም ሆነ የዛሬ 100 ዓመት በሄክታር ከዘጠኝ ኩንታል ያልዘለለውን፣ ተገቢ የምርምርና ጥናት እገዛ በዙሪያው ያላንዣበበውን ይህን ብቸኛ የኢትዮጵያ ልጅ - ጤፍ፣ አሁን ባለበት ደረጃ ለውጭ ገበያ በውጭ ምንዛሪ ምንጭነት በሰፊው ለማቅረብ የተያዘው እንቅስቃሴ፤ የምርቱንም ሆነ የሕብረተሰቡን የኑሮ እውነታ ያላገናዝበ፣ ከፈረሱ ኮርቻው ዓይነት ነው። በምርቱ ሕልውናና በሸማቹ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ያልተፈለገ ጦርነት ክተት የማለት ያህል ነው። በመንግሥት በኩል ቆም ተብሎ እንደገና ሊፈተሽ የሚገባ አብይ ብሔራዊ ጉዳይ ነው።


Teff, Photo by Radu Sigheti/Reuters

ጤፋችን በመሰረቱ የማንነታችን መግለጫ፣ ረሃብን ተዋጊ - ብሔራዊ ጦራችን ነው፤ ድንበር አስከባሪያችን ነው። "የዕለት እንጀራችንን አታሳጣን" እያልን ለፈጣሪ ቢያንስ በቀን አንዴ፣ ከሆነልንም ሦስቴ የምንጸልይለት የጤናችን ምሰሶ ነው፤ ከሚያመጣው ዶላር ይልቅ የሚያስታግሰው የሚሊዮን ረሃብተኛ ሆድ ሚዛን የደፋ ነው፤ በየሦስትና አራት ዓመቱ አንገት አስደፊና ብሔራዊ ውርደት የሆነውን የልመና እጅ ከመዘርጋት የሚያድን ነው። ለእኛ ለዜጎቿ ምርቱ ከቡናና ከወርቃችንም በላይ ነው፤ የሱስ ማርኪያ ወይም ሠርግና በዓል እየተጠበቀ ብቅ የሚል ማጌጫ አይደለም። ሳይተርፈን ቡናና ወርቅ ለውጭ ገበያ ብንልክ በሕብረተሰባችን ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው ቀውስ የለም፣ የሚበጅ እንጂ። ሳይተርፈን የጤፍ ዘርን በጥሬውም ሆነ በእንጀራ ለውጭ ገበያ መስደድ ግን ሀገራዊ ጥቃት ነው። እኛነታችንን ሳያስከብር ከሀገር እንዳይወጣ፣ ለባዕዳን ሲሳይ እንዳይሆን በያለንበት ዘብ ልንቆምለት ያስፈልጋል። የመስኩ ባለሙያዎች ከምርምር ጣቢያችው ወደ ሕብረተሰቡ መድረክ ወጣ ብለው ስለ ጤፍ ልዩ ባህርይ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሊነግሩንና ጥብቅና ሊቆሙ ይገባል። የጤፍ ምርት ያለበትን የምርታማነት ደረጃ ሊተነትኑልን፣ ለውጭ ምንዛሪ የመዋልን ብሔራዊ ጠቀሜታና ጉዳት ግንዛቤ ሊያስጨብጡን ያሻል፤ ብሔራዊ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ከመከላከሉ ላይ ኢትዮጵያዊ ኃይላችንን ማሳረፉ ላለውና ለመጪው ትውልድ ባለውለታ ያደርገናል።

በመሰረቱ፣ የጤፍ ዘርን ሕልውና የተፈታተነ የክተት ጥሪ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በደርግ ዘመነ መንግሥት የገበሬው የጤፍ ማሳ ምርታማነታቸው ከፍ ባሉ አዝዕርቶች እንዲተካ የሚያደርግና በመንግሥት የተደገፈ "ጥናት" ቀርቦ ለአፈጻጸሙ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክልሎች ሸብ-ረብ ተብሎ ነበር። ጥናቱ ምርታማዎቹ በቆሎ፣ ስንዴና ድንች ምርታማ ያልሆነውን የጤፍ ዘር ቢተኩ፣ የሀገሪቱን ዓመታዊ የምርት እጥረት ከመሸፈን አልፈው ለመጪው ዓመት የሚሻገር ምርት ለማከመቸት እንደሚቻል ያስረገጠ ነበር። ተግባራዊነቱ ከአንድ ዓመት አልተሻገረም። በይዘቱ ከዛሬው ጥሪ ቢለይም በገበሬው ኑሮና በጤፍ ሕልውና ላይ ጥሎት የነበረው አደጋ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ነበረው። ውሳኔውንም ሆነ አፈጻፀሙን የተቃወሙ ጥቂት ወገኖች ነበሩ፤ መድረኩም ወቅቱም ባለመፍቀዱ አልተደመጡም። ውሳኔው ከማዕከል ወጥቶ ወደ ገጠሩ - ከገበሬው ማሳ አመራ።

ገበሬው ጤፉን ወደ ጓዳው መልሶ፣ እንደታዘዘው ማሳውን በምርታማዎቹ በቆሎና ድንች አርመሰመሰው። መሰብሰብ ከሚችለው በላይ ማረስ ልምዱም ባህሉም ያልነበረው ገበሬ አቅሙና ጎተራው የሚችለውን ያህል ሰብስቦ የቀረውን ከማሳው ላይ ተወው፤ ወድሞ ቀረ። በጎተራ ያከማቸው ስንዴም በነቀዝ ተጠቃ፤ በቆሎና ድንቹ የከተሜውን ገበያ ቢያጥለቀልቀውም ዋጋው በመውደቁ ገበሬውን ለኪሳራ ዳረገው። በአርሲና ባሌ በሰፊው የታረሰው የመንግሥት እርሻ ምርትም ለተመሳሳይ አደጋ ተጋለጠ፤ አቅምን ያላገናዘበ ውሳኔ፣ በበቂ ጊዜ፣ ገንዘብ ባለሙያ ያልተደገፈ ምርትና ምርታማነትን የማሳደጉ ዘመቻ አባዜ፣ ለሌላ አስከፊ ችግር ገበሬውንም፣ ሸማቹንም መንግሥትንም ጭምር አጋልጦ አለፈ።

ከስህተት ያለመማር ባህል የተፀናወታቸው ገዥዎቻችን በመጪው የዕቅድ ዓመትም መሰረታዊ ችግሩን ባልፈታና ስሙን ብቻ በቀየረ ዕቅድ እንዲቀጥል ተቃጥቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ጥቂት ቆራጥ የሆኑ የጤፍ ምርት ተመራማሪዎች ድምፅ-አልባ የነበረውን የገበሬውን ድምፅ ከፍ አርገው በማስተጋባታቸውና በቁጥር ከሁለት ያልበለጡ የጊዜው ባለሥልጣናትን ግንዛቤ ሊያገኙ በመቻላቸው፣ ከገበሬው ጉያ ተደብቆ የሰነበተው የጤፍ ዘር በግላጭ ወጥቶ ከማሳው ሊመለስ በቃ።

ዛሬ ኢትዮጵያናችን እነዚያን የመሰሉ ለገንዘብና ለግል ሥልጣን ያላደሩ ተመራማሪዎቿንና የመንግሥት ኃላፊዎቿን በባትሪ የምትፈልግበት ወቅት ላይ ነች። አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለማረጋገጥ መረጃ ባይኖረውም፣ በዚያን ወቅት በጤፍ ዘርና ምርታማነት ጥናትና ምርምር ዙሪያ ከተሰለፉት ሳይንቲስቶቻችን መሀከል እነ ዶ/ር ሰይፉ ከተማና ባልደረቦቻቸው ለአብነት የሚጠቀሱ የሀገሪቱ ባለውለታ ናቸው። ዶ/ር ሰይፉ የጤፍ ዘር ለዘመናት አላንዳች የቴክኖሎጂና የመንግሥት ድጋፍ የመቆየት ሚስጥርን አበክሮ የሚገልጽ የምርምር ሥራ (Tef፡ Eragrostis tef, 1993) ለተነባቢነት አብቅተዋል። በዚያ ጥናታዊ ሥራቸው ገበሬውን ጭምር እማኝ በማድረግ እንደነገሩን፣ የጤፍ ዘር ከማንኛውም ምርት በተሻለ ድርቅንም ሆነ ከባድ ዝናብን የመቋቋም ልዩ ባህርይ የገበሬውን ቀልብ የሳበ ነው።

ጤፍ በምግብነቱ እንዲህ እንደዛሬው የሀብታሙ አልነበረም፤ ደሃው ችግር ሲጋፈጠው እየደበቀ፣ እየቆጠበ የሚበላው ሳር ነበር። የዘሩን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ደሃውም ሀብታሙም ገበሬ በእጅጉ ከተረዱት በኋላ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበሉት እዚህ ለመድረስ በቅቷል። በተዘራበት ማሳ እንደ ስንዴና በቆሎ በዝናም እጥረትም ሆነ ብዛት ወድሞ አይቀርም፤ ገበሬውን አመድ አፋሽ አያደርግም፤ የጠበቀውን ያህል ባያገኝም ለዘር ያህል አያሳጣውም። በጎተራ ሲከማች እንደተቀሩት ምርቶች በነቀዝ አይደፈርም፣ ጭዱ የእንስሳቱ ተወዳጅ ምግብ፣ የጎጆው ግድግዳ ማገር መመረጊያ ነው። በገቢ ምንጭነቱም አንጀት አራሽ ነው።

የጤፍ ዘር የሸማቹም ልዩ ወዳጅ ነው፤ በረከት ያለው እህል ነው፤ ግማሽ ኩንታል ጤፍ ከወፍጮ ቤት ወስዶ ሙሉ ኩንታል ዱቄት ተሸክሞ የሚመለስበት ነው፤ ለዚህም ነው ሸማቹ የዋጋ ውድነቱን አጥብቆ የሚያማርር። በምግብነቱም ቢሆን ተወዳጅና ሁለገብ ነው፤ ችግር ከመጣ አለማባያ፣ አለዚያም በወተት ተምጎ፣ በሚጥሚጣ ተረምዶ ይበላል። ማባያዎቹ ሳይደመሩ የጤፍ ዘር በራሱ አይነታቸውና መጠናቸው የተለያዩ በርካታ ለሰውነታችን ጤና ግንባታ የሚረዱ ንጥረነገሮችን (ፕሮቲን፣ አይረን፣ ካልስየም፤ ፋይበር እና የተለያዩ ቫይታሚኖችን) አዝሎ የሚገኝ ነው።

ዜናው ከምዕራቡ ዓለም የወሬ ማሰራጫ ጣቢያ ካልመጣ ጆሯችን አልሰማ ብሎ እንጂ፣ አዲስ አይደለም። የደብረዘይቱ የግብርና ምርምር ሳይንቲስቶቻችን የዛሬ 25 ዓመት አስረግጠው ነግረውን ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ተመራማሪዎች ይህን የጤፍ ዘር ባላቸው ውስን አቅም ምርታማ ለማድረግ ጥረታቸው የመቀጠሉ ተቀዳሚ ምክንያት ለምዕራባውያን የጤፍ ብስኩትና ትኩስ እንጀራ ለመሸጥ አልነበረም፤ አይደለምም። ዋና ግባቸው በሚሊዮን የሚቆጠረው የሀገሪቱ ጤፍ አምራች ገበሬ ለዘመናት ከያዘው አድካሚ አሠራር ተላቆና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆኖ ምርቱን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለበላተኛው እንዲያቀርብ ማስቻል ነው። በሀገር ውስጥ ምርቱን የማስተዋወቅ ሥራ ሳይሆን፣ ምርቱ የያዘው ንጥረ-ነገር ምን ያህል ለጤናችን አስፈላጊ እንደሆነ አግባብ ባላቸው ተቋማት በኩል ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ነው።

በጥናታዊ ጹሑፋቸው፣ የጤፍ ተመራማሪው ዶ/ር ሰይፉ እንደሚነግሩን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤፍ ምርቱ ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ምርምር የተጀመረው እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጨረሻ ግድም ሲሆን፣ የመጀማሪያው ኢትዮጵያዊው የጤፍ ሳይንቲስት ዶ/ር መላክ-ኃይለ መንገሻ ይባላሉ። እኒህ ምሁር ስለጤፍ ዘር ባህሪ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ጀምሮ በግብርና ኮሌጆችና የእርሻ ምርምር ጣቢያዎች ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ምርምሩ እንዲቀጥል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በመቀጠልም ሌላው ሳይንቲስት ዶ/ር ታረቀ በርሄ የተሰኙ በጤፍ ምርት ምርምር ሂደት ግኝቱ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውንና በምርታማነቱ ልዩ ሚና የሚጫወተውን የጤፍ ባህርይ (The Pollination Habit of Tef) ግኝት በተጨባጭ በማሳየት በሙያ አጋሮቻቸው አድናቆትን ያተረፉ የመስኩ ባልደረባ ናቸው። በእነዚህ ግኝቶች ላይ በመንተራሰ ዶ/ር ሰይፉና ባልደረቦቻቸው በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በጀመሩት የናሙና እርሻ፣ በሄክታር 8 እና 9 ኩንታል ላይ የቆመው የጤፍ ምርት ከ20 ኩንታል በላይ ለማምረት የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ሊያስመዘግቡ በቅተዋል። ይህ ድንቅና ተስፋ ፈንጣቂ ውጤት፣ ዛሬ ስለደረሰበት ሁኔታ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምቹ ሁኔታ ባይኖረውም፤ ከተጨባጩ የሀገሪቱ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው የምርታማነቱ ማነቆ አሁንም ድረስ እንዳልተፈታ ነው፤ በአብዛኛው ገበሬ ማሳ ላይ የጤፍ ምርትና ምርታማነት ባለኽበት እርገጥ ላይ ነው። በየክልሉ በድብቅና በገሀድ የረሃብ አለንጋ እየተቀጣ ያለው ሕብረተሰብም በእማኝነቱ የሚያወለዳ አይደለም።

በሌላ በኩል - የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት - የጤፍ ምርት ከሀገር ውጭም በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮጳ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካም ጭምር ለማብቀል ጥረቱ ተይዟል። በኢትዮጵያ አየርና አፈር የሚበቅለውን የጤፍ ዘር ሊተካ ባይችልም፣ ለጤፍ ምርታችን የሚበጁ ሁለት እገዛዎችን ለማድረግ ዕደሉ የሰፋ ነው። የመጀመሪያው፣ የጤፍን ምርታማነት ለማሳደግ ከበቃ፣ ለግብርናቸው የተጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ በጥንቃቄ አጢኖ ለሀገራችን ጤፍ ምርታማነት በአጋዥነት ለማሰለፍ መቻሉ ነው።

ሁለተኛው፣ የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት ሳያሟላ፣ ባልተመጣጠነ ዋጋ ከደሃው ገበሬ ተዘርፎና ከበላተኛው አፍ ተነጥቆ ወደ ውጭ በቀላሉ እየወጣ ያለውን ጤፍ ጊዚያዊ እፎይታ ለማሰጠት አቅሙ መኖሩ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቂት ባለጊዜ ባለሥልጣናትንና ነጋዴዎችን ኪስ ከመሙላት ባለፈ ብሔራዊ ፋይዳ እንደሌለው በይፋ የሚነገረለት ይህ የሀገሪቱ ጤፍ፣ ለውጭ ገበያ እንዳይውል ጥሪ የመደረጉ አንዱም መልዕክት የሀገር ቤቱን ጤፍ ለሀገር፤ የውጭውን ለውጭ የሚል ነው። በዋና ዋና ያሜሪካ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆቻቸው ከሀገር ቤት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭምር ተጭኖ የሚመጣውን ትኩስ እንጀራና ጥሬ ጤፍ ሸማቹ እንዳይገዛ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፤ በተሳታፊ ነጋዴዎችም ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ግፊት እያደረጉ ነው፤ ምላሹ ግን አጥጋቢ ሆኖ አይታይም። ምዕራባውያኑ ጤፍን እንደ ጣሊያኑ ፒሳ እስከሚለምዱት ድረስ እኛ በውጭው ዓለም ነዋሪ የሆንን ዜጎቿ የፈረጠመ ክንድ አለን፤ ከደሃው አፍ ተነጥቆ ማዕዳችንን እያጣበበ ያለውን የኢትዮጵያ እንጀራ - የጤፍ ዘር - ለማስቆም ትግሉን መቀላቀል ይጠበቅብናል፤ የይቁም ጥሪውም ቅዱስ ጥሪ በመሆኑ፤ ከጎናቸው ልንቆም ያስፈልጋል።

ጤናማውን ኦርጋኒክ ጤፍ ወደ ባዕድ ሀገር ሰደን በኬሚካል ያበደውንና ለበሽታ መራቢያነት ምቹ የሆነውን የባዕድ እህል ወደ ሀገር ከማስገባት፣ ወይም የጤፍን ኦርጋኒካዊ ይዘት ለሚያቃውሱ ባዕዳን ነጋዴዎችና ሳይንቲስቶቻቸው አጋልጠን ከመስጠት ልንድን የምንችለው፤ ዜጎቿ በአንድ ሆነን ለምርቱ ደህንነትና ምርታማነት ዘብ ስንቆም ብቻ ነው።

ሀገሪቱ ወጣት የጤፍ ሳይንቲስቶች በጥራትና በብዛት እንድታፈራ፣ የምርምርና ጥናት ዘርፉ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝና፤ በቂ የመዋዕለ ነዋይ ፈሰስ ለዘርፉ እንዲደረግለት የሚደረጉ ተከታታይ ጥረቶች ለጤፍ ምርታችን አይነተኛ ለውጥ መምጣት መሠረት የሚጥሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትሄድ የሚያስችላት ነው። ይህን ለመሆን ካበቃን፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የገበሬው ችግር ደራሽና አለኝታ ሆኖ ዛሬ ድረስ እስተንፋሱ የቆየው የጤፍ ዘራችን፣ ምርታማነቱ ከፍ ብሎና ከጥቂቶች ማዕድ ወጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ በሚሊዮን ህዝብ ማዕድ በመደበኛም ሆነ በአማራጭ ምግብነት የምናስተናግድበት ይሆናል። ከተጠነከረም፣ ሀገሪቱ ለጤፍ ምርት በሚውል መጠነ-ሰፊ መሬት የታደለች በመሆኗ፤ ዛሬ ከኢትዮጵያ አይውጣ እያልን የምንጮኽለት ጤፍ - ያኔ ለውጭ ገበያ ጭምር በመዋል - ቡናና ወርቃችን ተደምረው ከሚያገቡት የውጭ ምንዛሪ በተሻለ ገቢ አስገኚና የሀገሪቱ የልማት ገንቢ ሆኖ እንደሚቀጠል ተስፋችን በእጅጉ የፀና ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ