ስሜቱ ይቁምና እስቲ አማራጮችን በእርጋታ እንመልከት
ግርማ ካሳ
«አበው ሲተርቱ ላም ባልዋለበት ኩመት ለቀማ ይላሉ። ሰላም ጠላቱ ከሆነ የአገዛዝ ቡድን ጋራ በሰላማዊ ትግል ገጠሞ ሰለማዊ ድል አስመዘግባለሁ ብሎ ማሰብ ከሰላማዊ ጭንቅላት የሚፈልቅ ሰላማዊ አስተሳሰብ ነው ብዬ አላምንም። ...ትግል ሱስ አይደለም። እንደ አቦል ቡና ሱስ አይደለም።
አሁን የምናየው የሰላማዊ ታጋዮች፣ የትግል ሱስ ያለባቸው አይነት ነው እንጂ ከውጤት አኳያ የፖለቲካ ምህዳሩ በጠበበት አገር ውስጥ ምንም አይነት ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉበት ሁኔታ አይታየኝም። እስካሁን የአገዛዙን እድሜ በማራዘም ረገድ አስተዋጾ እያደረጉ ነው ። ምናልባትም የታሪክ ተወቃሽነት ሊያደርጋቸውም ይችላል። ከልምዳቸውም ተነስተው ውጤት ይመጣክል ብለው ይጠብቃሉ ?»
አንድ አድምጫ ለወጣት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት፣ ም/ፕሬዘዳንቱ አቶ በላይ በፈቃዱና የሕዝብ ግንኙነት ክፍላ ሃላፊው አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ በኢሳት ያቀረቡት አስተያየት በዛሽ ጥያቄ ነበር።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ የሰብአዊ መብትን የሚረገጥ፣ ፍርድን የሚያዛባ ፍጹም አምባገነን እንደሆነ ሁላችንም የምናወቀው ነው። ታዲያ ምንድን ነው መፍትሄው ?
አራት አማራጮ ነው ያሉት።
1) በግብጽ እና በቱኒዚያ እንደታየው፣ ሕዝብን አደራጅቱ ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የእምቢተኝነት ዘመቻ በማካሄድ መንግስት ለሕዝብ ጥያቄ እንዲገዛ ማስገደድ፣
2) በደቡብ አፍሪካ የነጮች ፓርቲ የነበረው፣ ብሄራዊው ፓርቲ፣ ፒተር ቦታን አስወገዶ በምትካቸው ፍሬደሪክ ደክለርክን በማስመረጥ፣ ከጨቋኙ ፓርቲ ውስጥ ለውጦች እንዲመጣ እንደተደረገው፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፣ ጥሩ ልብ ያላቸው መልካም ሰዎች አይለው እንዲወጡና የሚፈለገው ለውጥ በኢሕአዴግ በራሱ እንዲመጣ ማድረግ፣
3) ሕወሃት/ኢሕአዴግ ደርግን እንዳደረገው መሳሪያ አንስቶ በኃይል የመንግስት ለውጥ ማምጣት፣
4) አርፎ፣ ባርነትን ተቀበሎ፣ አንገት ደፍቶ፣ እንደ እንስሳ መኖር፣
አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን አራተኛውን አማራጭ የመረጡ መሰለኝ። በተለያዩ ምክንያቶች። አንደኛው ፍርሃት ነው። ገዢው ፓርቲ ከስራቸው እንዳያባርራቸው፣ ከቤታቸው እንዳያፈናቅላቸው፣ ማዳበሪያ እንዳይከለከላቸው፣ እንዳያስራቸው ......ሁለተኛው ምክንያት ተስፋ መቆረጥ ነው። በኢሕአፓ ጊዜ፣ በቅርቡ ደግሞ በቅንጅት የነበረውን በማስታወስ «አይ ዝም ብለን ነው የምንደክመው ለውጥ እንደው አይመጣም። ተቃዋሚዎቹ ደካማ ናቸው» የሚል አስተሳሰብን በመያዝ፣ አገዛዙን አጉዝፎ የራስን ኃይል ግን አሳንሶ ማየት። ሶስተኛው ምክንያት፣ ዳያስፖራው ወይንም ደግሞ «እንዋጋለን» የሚሉ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ «ነጻ ያወጡኛል» ብሎ በመጠበቅ ቁጭ ማለትን መምረጥ ነው።
እንግዲህ እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። ይሄ አማራጭ ስብእናችንን እና ክብራችንን የሚያወርድ አማራጭ ነው። በአጭሩ «ባርነት» ነው። ከዚህ አማራጭ ፈቀቅ ብለን መሄድ ያለብን ይመስለኛል። ዘጠና ሚሊዮኖች ሆነን ጥቂቶች በአንገታችን ላይ ቀንበር አስረው፣ ተናገሩ የሚሉንን ብቻ እየተናገርን፣ ቁጭ በሉ ሲሉን እየተቀመጥን እንደ እንሥሳ መኖር የለብንም።
ሌላው አማራጭ ሶስተኛው አማራጭ ነው። ነፍጥ የሚያስነሳ ሰላማዊ ያልሆነው አማራጭ። ይመስለኛል ከላይ የጠቀሷቸው ኢትዮጵያዊ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን አጣጥለው ሲናገሩ፣ ይሄንኑ የጠመንጃ ትግል አስበው ሳይሆን እንዳልቀረ ነው። ዜጎች ግፍን ለመቃወም መሸፈት እና ነፍጥ ማንሳት ሙሉ መብታቸው እንደሆነ አያከራክርም። የትጥቅ ትግል አንስተናል የሚሉትን «ለምን አነሳችሁ» የማለት የሞራል ብቃትም የለኝም። ነገር ግን በትጥቅ ትግል አኳያ አንዳንድ መሰረታዊ ሃቆችን ለማንሳት እወዳለሁ፡
የትጥቅ ትግል ሲደረግ ወታደሮች ያሰፈልጋሉ። ወታደሮች ደግሞ ውሃ አይደለም የሚተኩስት። መሳሪያ፣ ጥይት ያስፈልጋል። ወደ ጦርነት ሲኬድ መቁሰል መጎዳት አለ። በመሆኑም መድሃኒቶች፣ የሕክምና ባለሞያዎች መኖር አለባቸው። በትጥቅ ትግሉ የተሰማሩ መልበስ፣ መብላት አላባቸው። ወታደሮችን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለማሰማራት ከባባድ የጭነት መኪናዎች፣ ናፋጣና ነዳጅ የግድ ነው። እዚህ ላይ አላበቃም። ወታደሮች የሚሰለጥኑበት ቦታ ያስፈልጋል።
ያኔ ሕወሃት እና ሻእቢያ፣ ድፍን ሱዳን ከጎናቸው ነበር። አሜሪካ፣ አረቦች የሚፈልጉትን ያስታጥቋቸው ነበር። አሁን ሽምቅ ተዋጊዎችን ሊረዱ የሚችሉት፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንደ ጠላት የሚታዩ ሻእቢያ እና ግብጽ ብቻ ናቸው። የግብጽ እና የሻእቢያ አጋር መሆን ደግሞ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚያላትም ነው። በመሆኑም አስተማማኝ ፣ ደጀን የሚሆን ፣ የሚረዳ አለ ማለት አይቻልም። ይህ የውጭ ረዳት ኃይል በሌለበት ሁኔታ ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ መውሰድ አያስኬድም።
እርግጥ ነው፣ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ኮንቬሽናል በሆነ መንገድ የትጥቅ ትግል ማድረጉ ባያስኬድም፣ ግፍ ሲበዛበት፣ ሕዝቡ ግን በየቀበሌውና በየወረዳው ጠመንጃ ሊያነሳ ይችላል። ጠመንጃም ከሌለው ቆመጥ። ይህ አይነቱ አመጽ ደግሞ አንዴ ከተለኮሰ፣ ማቆም የማይችልበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል። ሶሪያን ተመለከቱ። ለስንት አመት ሊባኖስ የሆነቸውን አስታወሱ። ሶማሊያን አስቡ። ይሄ ከእያንዳንዳችን ቁጥጥር ውጭ የሆነ፣ እንደ አማራጭ ሊወሰድ የማይችል፣ ገዢው ፓርቲ ከወዲሁ ሊስይቆመው የሚችል ጉዳይ ነው። ይሄ እንዳይሆን ጸሎቴና ሞኞቴ ነው።
እንግዲህ የተሻሉት የምላቸው አማራጭች፣ አማራጭ አንድ እና ሁለት ናቸው። ሕዝቡ ወደ ጠመንጃ ሳይዞር፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እምቢተኝነቱን እንዲገልጽ ማደራጀቱ፣ ለውጥ ከገዢው ፓርቲ ውስጥም እንዲታይ መገፋፈቱ ብቸኞቹ ጠቃሚ አማራጮች ናቸው። እነዚህ አማራጮች እንደ ተጠበቀው ውጤት ላያመጡ ይችላሉ። ጊዜ ለኢፈጁ ይችላሉ። ሶስተኛው የጦርነት አማራጭ፣ አማራጭ እንደማይሆን እየታወቀ፣ የሰላም አማራጮቹ አይሰሩም ብሎ መቀመጡ፣ አራተኛውን የባርነት አማራጭ መምረጥ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸው ኢትዮጵያዊ ወንድሜም በአገር ቤት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል በሚያጣጥሉበት ጊዜ፣ አላወቁትም እንጂ፣ «ከቻላችሁ እንደ እኔ ተሰደዱ ፤ አለበለዚያ አርፋችሁ፣ ባርያ ሆናችሁ ተገዙ» እያሉን ነው።
አንደኛውና ሁለተኛው አማራጮች፣ በተለይም በአንደኛው (ሕዝብን አደራጅቶ አገዛዙን ማስጨነቅ) እንዴት ሊሰራ እንደሚችል የሚያመላክቱ አንዳንድ ሃሳቦችን በሚቀጥለው ጊዜ ይዤ እቀርባለሁ።
(በነገራችን ላይ አይሰራም ፣ አያዋጣም የምለው የትጥቅ ትግል አማራጭ ያዋጣል የሚሉ ካሉ፣ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፤ ታዲያ ወሬና ፉከራ ሳይሆን አሳማኝ ነጥቦች ያስቀምጡልኝ። ስለጠመንጃ ማውራት ቀላል ነው። ባሩዱን ማሽተት ግን ሌላ ነገር ነው)



