ዓለማየሁ ዲባባ

የሳዑዲ ሕዝቦች በአንድ የታሪክ ዘመናቸው በኃይማኖት ልዩነት እርስ በእርሳቸው ተፋጅተው ወደ ኢትዮጵያ በተሰደዱ ወቅት ተቀብለናቸው አኑረናል፣ አስጠልለን መግበናል፣ አልብሰን አርዘናል። ከለላ እና ጥበቃ ሰጥተናቸዋል።

 

እኛ ኢትዮጵያውያን ይህን እንደ ውለታ ቆጥረን ብድር መልሱ ብለን ግን አናውቅም። ይህ እንግዳ ተቀባይነታችን አሁንም ለዓለም የሰው ዘር በሙሉ የምንለግሰው የማንነታችን መገለጫ በረከት ነው።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ሴት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ወደ አረብ አገራት ለስራ መሄድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የእነዚሁ አንዳንድ የአረብ አገራት አብዛኛው ሕዝብ በወገኖቻችን ላይ በምላሽ የፈጸሙትና እያደረሱት ያለው በደል የሚያንገበግብ ሆኗል። በለግስነው ደግነታችን ዛሬ ተሳልቀዋል። ባጎረሰ እጃችን ላይ ሰይፍ መዘዋል።

በቅርቡ በሳዖዲ አረቢያ ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ በይፋ የተፈጸመውና እየደረሰ ያለው ግፍ፣ በደል፣ ስቃይና ግድያ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ቁጣና ቁጭት ቀስቅሷል።

ሳዑዲ አረባውያን በታሪክ ከቶም የማንረሳውን ይህን አስነዋሪ ጥቃት ፈጽመው ቂም እንድንይዝ አድርገዋል።

እስከዚህ ጊዜ ድረስ በወገኖቻችን ላይ በድብቅ ይፈጸሙ የነበሩት ግፎች ዛሬ እጅግ ጥላቻ በተሞላ፣ ስልጡን ባለሆነ ድርጊት፣ ሰብአዊ ባልሆነ መንገድና አሰቃቂነት በተሞላ እርምጃ ኢትዮጵያውያኑን ደብድበዋል፣ አሰቃይተዋል፣ ገድለዋል።

በኢትዮጵያዊነት፣ በማንነት፣ በመብትና ክብር ላይ የተፈጸመው ይህ ጥቃት ፈጽሞ የሚወገዝ፣ በዝምታ የማይታለፍና ምላሽ የሚያስፈልገው ነው።

ወገኖቻችን ያለርህራሄ በጥይት ሳይቀር ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተሰቃይተው ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ተደፍረዋል፣ ተዘርፈዋል።

የዚህ አሰቃቂ ግፍ ሰለባ እየሆኑ ያሉ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ድምጻቸው አለሁ ባይ በሆነው ተቆርቋሪ ሕዝባቸው ዘንድ ተደምጧል።

የወገኖቻችን ደም መንገድ ላይ እንደፈሰሰ፣ አስክሬናቸው ሳይነሳ ብዙዎች እንዲሁ ለጉዳትና ለስቃይ ተዳርገው እየታፈሱ ኢ ሰብአዊ በሆነ መንገድ በየማጎሪያ ካምፖችና እስር ቤቶች ታግዘዋል።

ደማቸው ከልብ ሆኖ፣ ወንጀል እየተፈጸመባቸው የደረሱበት ያልታወቀ ወገኖቻችን ቁጥር በርካታ ነው።

በእድሜ የገፉ እናትና አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች፣ እርጉዝ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር የዚህ ግፍ ሰለባ ናቸው።

በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ይህ የማንነት፣ የመብትና ክብር ረገጣ ጥቃት በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ሃዘን፣ ቁጭትና እሮሮ አልበረደም። ቁጣው ገንፍሏል፣ ተቃውሞው ኃይሏል።

ይሁን እንጂ የሚፈጸምባቸው ጥቃት ፈጽሞ አልቆመም። የድረሱልንና የድረሱላቸው ጩኸቱ በየቦታው በርክቷል። የሕዝብ ተቃውሞ ትግሉ በይፋ ተጀምሯል። አደባባይ ወጥቷል።

በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸመው ግፍና በድል ፈጽሞ እስኪቆምና ማነነታቸው፣ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ኢትዮጵያዊነት እስኪከበር ድረስም ይህ ትግል ይቀጥላል።

በጉዳዩ ላይ ማዘንና መናደዱ ብቻ በቂ እንዳልሆነ እምነቱ የሆነው መላው ሕዝብ አገራዊ የሆነ አቋም በመያዝ የማያወላውል እርምጃ ከመውሰድ አይቆጠብም። ሁሉን እናከብራለን፣ ከደረሱብን ግን አንተውም፣ ከነኩን ግን አንለቅም። እንከላከላለን፣ ማነነታችንን እናስከብራለን።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚያስኮራና አንገት የሚያስቀና ታሪክ፣ ሕዝብና አገር ባለቤት ነን። ድህነት፣ አለመቻቻል፣ ችግር አስገድዶ የሰው እጅ ለማየት አበቃቸው እንጂ በማንነታቸው የሚኮሩ ወገኖቻችን ናቸው። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው ሲረገጡ፣ ሲደፈሩ፣ ሲንገላቱ፣ ሲደበደቡ፣ ሲታደኑ፣ መብትና ክብራቸው ሲዋረድ ደግሞ እነሱም እኛም ማየት ፈጽሞ አንፈልግም።

የሕዝብ አገር አለን፥ የተባረከ የተመረጠ። ተፈጥሮ ሃብት ያደለው መሬትና ሰማዩን ብቻ አይደለም፥ ሕዝቡም ትሁት፣ ሰው አክባሪ፣ እንግዳ ተቀባይና ባማንነቱ የሚኮራም ጭምር እንጂ።

ጥንትም ታውቀናል ትንቢትም ተንግሮልናል አሁንም ይጠቀስልናል። እናም ገና ብዙ ይባልልናል።

በብዙ ድንቅ ነገር አልፈናል። መልካም ሆነ መጥፎ ዘመን ዘምነናል። በአገርና በሕዝብ ታሪክ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ተሰይተኛል። ድሮ ታላቅ ነበርን አሁን ተቸግረናል፥ ወደፊት ግን ዳግም ታላቅ እንሆናለን።

ይህን የማንነት ደም ውርስ፣ መብትና ክብር፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚደፍሩ ግን ሁሌም ይወድቃሉ።

በዚህ መነሻ ይህ ግጥም ተጻፈ። ...


ሰማዩ ይደለቅ መሬቱም ይመታ
ሃዘን እንቀመጥ እናልቅስ እንውጣ


አገር ቢጎሳቆል ድህነት ቢከፋ
ስቃይና ችግር መከራው ቢበዛ
ሕዝብ ተሰደደ እንጀራ ፍለጋ
ባህር ተሻገረ ባዕድ እጅ ነሳ


ቋጠሮው ቢፈታ ሳይቻቻል ቀርቶ
ሳይስማማ ቢቀር በእስር ተጠላልፎ
ሕዝብ ተበተነ አሳዶ ተሳዶ
ተናቀ በባዕድ ሳለ ነጻ ወጥቶ


እንጀራ ቢጥለው የሰው እጅ ቢያሳየው
ሁሉን ችሎ ሳለ ቢከፋው ቢመረው
ወገኔ እየለፋ ሰርቶ ጥሮ ግሮ
እናት አገር ቢጦር አንገት አቀርቅሮ
ተደፈረ ባረብ ተዋርዶ ተንቆ
ያጎረሰ እጁ በሰይፍ ተበልቶ
ውለታ የዋለው አንገቱ ተቆርጦ


ተቃጠለ በእሳት በሰይፍ ተቀላ
ወገሩት በቆመጥ በጥይት ተቆላ
ተረገጠ መሬት በጫማ ተመታ
አረከሱ ክብሩን ተካደ ውለታ


ሴቶች ተደፈሩ እናቶች አነቡ
ወንዶች ተዋረዱ አባቶች አፈሩ


ሰማዩ ይደለቅ መሬቱም ይመታ
ሃዘን እንቀመጥ እናልቅስ እንውጣ


ወገን ተቀጥቅጦ ቢታሰር ቢታጎር
እንደወጣ ቀርቶ ሳይመለስ ቢቀር
አደባባይ ወጣ ቀፎው ሲነካበት
ጭስ ሲያጨሱበት ማሩን ሲቆርጡበት
ሕዝብ ሃዘን ወጣ አገር አለቀሰ
ቁጣው ገነፈለ ዋ! አትንኩን አለ


ይብላኝ ለአረብ አባይ ወየው ለዛ ከጂ
በደም ተጨማልቆ ላይጸዳ ታጣቢ
ቁጣ ለሚያጠፋው በመዓት ተቀጪ
በመዘዘው ሰይፍ በእራሱ እጅ ጠፊ


ወየው ነው ዘንድሮ ቁጣችን አይበርድም
ተነክተን ተደፍረን ከቶ አንላቀቅም
ፍትሕ እስኪሰፈን ደም እስኪመለስ
ይቅርታ እስኪጠየቅ ወገን እስከሚካስ
አንገት እስኪቀና ሰንደቅ እስኪተከል
ሕዝብ እስኪኮራ አገር እስኪከበር
የደፈሩን ወድቀው
እስኪጠፉ ወድመው
አናርፍም ... እምዬን ብለናል
አንተኛም ... ምለን ቃል ገብተናል

መታሰቢያነቱ ለስደት ተዳርገው በባዕድ አገር ለስቃይ፣ ለግፍና ለሞት ለታደረጉ ወገኖቻችን

ዓለማየሁ ዲባባ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ