ኢትዮጵያ እች ናት፤ አገሬ እች ናት!!
አሌክስ አብረሃም
እናት አገርን የሚያሳምረው ህንፃ ይመስለኝ ነበር ... አገርን የሚያሳምረው መንገድ ይመስለኝ ነበር አገርን የሚያሳምረው ዛፍና ቅጠል ይመስለኝ ነበር ... አገርን የሚያሳምረው ለካ ለአንድ አላማ የተሰለፈ በአንድነትና በአብሮነት ስሜት ፈገግታና እልሁ ፊቱ ላይ የሚንቀለቀል ህዝብ ነው!! አገሬ ቆንጆ ናት ድህነት ብስቁልና መገፋት የጋረደው ፈገግታችን እንዲህ እንደ ዛሬ ከችግራችን በላይ ፈክቶ ሲታይ አልኩ ... ኢትዮጵያ እች ናት፤ አገሬ እችናት!!
ሁሉም አንድ አንዱ ሁሉም የሆነባት ... በባንዲራ የተሸቆጠቆጠ ህዝብ!! ማሸነፍ መሸነፍ አይደለም ጉዳዩ በተራ ዲስኩር የማይፈታ በማይረባ ሴራና ተንኮል ንፋስ የማይገባበት የቁርጥ ቀን ሲመጣ አብሮ የሚቆም ህዝብ አገሬ እች ናት፤ ኢትዮጵያ እች ናት!!
ውጣ እና በርህ ላይ ቁም ኢትዮጵያዊነት እንደ ክረምት ዝናብ ሲወርድ ታያለህ በየመንገዱ እንደ ፈረሰኛ ጎርፍ ፍቅር አንድነት አይበገሬ መት ሲጎርፍ ትመለከታለህ ... ጅንስ ሱሪው የተቀደደ ጫማው ያለቀ ሚስኪን በለበሰው ባንዲራ ድህነቱን ንቆ ስታይ የኢትዮጵያ ህዝብ የትኛው ምደረ ጃድረስ ቢራብና ቢገፋም በአገሩ ጉዳይ ከድህነት በላይ እንደሚገዝፍ ታያለህ!! ኢትዮጵያ እች ናት፤ አገሬ እች ናት!!
ይሄ ህዝብ ከኳስ በላይ አገሩን ይወዳ ልስልህ ያየሁትን እያየሁ ነው ... የተሰለፈው አገሩን ሊመለከት ነው ... የሚጨፍረው አገሩን እያሞገሰ ነው.... የለበሰው አገሩን ነው ... የተሰለፈው የአገሩን የክብር ቀሚስ ለመንካት ነው ... በክፉ የሚያስባትን ኩም የሚያደርግ ህዝቤ ይሄ ነው!! ኢትዮጵያ እች ናት፤ አገሬ እች ናት!!
አገሬ ህዝቤ ማንም ሳይጠራው እውነተኛ የአገር ፍቅር ስሜት የጠራው ህዝቤ ይሄው!! እኔም በህዝቤ መሃል ነኝ በዶፍ ዝናብ ውስጥ በሚሞቅ ብርድ ልብስ ጥቅልል ብሎ እንደተኛ ሰው ህዝቤን ለብሸ፤ ህዝቤን ተንተርሸ በፍፁም ምቾት ህዝቤ ጋር ነኝ!! ኢትዮጵያ እች ናት፤ አገሬ እች ናት!!
ውጤቱ ምንም ይሁን የህዝቤ ዋጋ ግን ይሄ ነው!!



