አዲስ አበባ ሆይ ድምጽሽን አሰሚ!
አማኑኤል ዘሰላም
በደሴ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ፍቼ፣ አዳማ/ናዝሬት፣ ሮቢ/ባሌ፣ መቀሌ፣ ወላይታ ሶዳ፣ ጂንካ፣ አርባ ምንጭ ... ሰላማዊ ሰልፎችና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በአዋሳ፣ ድሬደዋ፣ ወሊሶ፣ አሶሳና ጋምቤላ፣ እቅዱ ውስጥ የነበሩም ቢሆንም በገንዘብ አቅም ምክንያት ለጊዜው ሰልፎች ሊካሄዱ አልቻሉም።
መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም ትኩረቱ አዲስ አበባ ፊንፊኔ ይሆናል። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት የጀመረው የመጀመሪያው ዙር የሶስት ወራት እንቅስቃሴ የሚደመደምበት! ከአዲስ አበባው ሰልፍ ጋር በተገናኘ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በፖሊሶች መታሰራቸውን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በፌስቡኩ ዘግቧል።
"ፖሊስ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አሰረ። የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የታሰሩ የፓርቲውን የቅስቀሳ ቡድን አባላት ለማስፈታት ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሽሮ ሜዳ ፖሊስ ማዘዣ ጣብያ በማምራት ለፖሊሶቹ "ልጆቹ የፈጸሙት ሕገ ወጥ ድርጊት የለም፣ ሲቀሰቅሱ የነበሩትም እውቅና የተሰጠውን ሰላማዊ ሰልፍ ነው። ቅስቀሳው ህገ ወጥ ነው የምትሉም ከሆነ እነርሱን የላኳቸው እኔ በመሆኔ እኔን ልታስሩኝ ትችላላችሁ" ብለዋል።
ፖሊስ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን በማሰር ወጣቶቹን ለቅቋቸዋል። የኢሕአዴግ ፓርቲ በአንድ በኩል እየፈቀደ፣ በሌላ በኩል የፈቀደውን የሚሽር ተግባራት መፈጸሙ ብዙዎቻችንን እያስገረመ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩም ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ለዴሞክራሲ ግንባታ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጸውም ነበር። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ ሰላማዊ ሰልፎች የማድረግ፣ እስረኞችን ያለገደብ የመጠየቅ፣ የፖለቲካ ክርክሮችን በኢቲቪ የማድረግ የመሳሰሉትን፣ በመለስ ዜናዊ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር፣ የተሻሉ ሁኔታዎችን ማየት የጀመርነው።
ነገር ግን፣ በጎን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያምን ውሳኔ ለማክሸፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ እንዲጠሉ፣ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ የሚሰሩ፣ ከበስተጀርባ እየወጓቸው ያሉ፣ ከአቶ ኃይለማሪያም ሳይሆን ከሌላ ቦታ መመሪያ የሚቀበሉ ቡድኖች ያሉ ይመስለኛል። ከበስተጀርባ ሆኖ የሚሰራ ሌላ ሁለተኛ መንግስት ማለት ነው ...
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሰልፎች መደረግ አለባቸው። ሕገ መንግስቱ የሚፈቅደውን ማገድ አንችልም" የሚል መመሪያ ይሰጣሉ። ነገር ግን በጎን የኦህድድ አክራሪዎች፣ በባሌ/ሮቢ " ሰልፍ ካደረጋችሁ ደም ይፈሳል" የሚለው አይነት ዛቻ በመስጠት ሰልፉን አስተጓግለዋል። በመቀሌ ሕወሃቶች " መቀሌን እንኳን አንድነት ቅንጅትም አልደፈራትም" በማለት የመቀሌ ሕዝብ ድምጹን እንዳያሰማ አድርገዋል። በአዲስ አበባ እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች፣ የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ በርካታ የአንድነት አባላትን እና ደጋፊዎች ታስረዋል። በውስጣዊና ሚስጥራዊ አሰራር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ የመቀልበስ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነው እያየን ያለነው።
እንደዚያም ሆኖ፣ የአንድነት ፓርቲም ሆነ ሰላሳ ሶስቶቹ የመብት ጥያቄን ከማንሳት ወደ ኋላ አላሉም። በከባድ ሁኔታም ትልቅ መስዋእትነት እየከፈሉ ሕዝቡን እያደራጁትና እያንቀሳቀሱት ነው። መስክረም 19 የአዲስ አበባና አክባቢዋ ሕዝብ ድምጹን እንዲያሰማ ቅስቀሳ እየተደረገ ነው።
እንግዲህ ለአዲስ አበባ ሕዝብ መልእክት አለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የፖለቲካውን ምህዳር ለመክፈት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመደገፍ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ብሄራዊ እርቅ፣ መቻቻል፣ ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን፣ የዜጎች ሰብአዊ መብት እንዲከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሰሴ በመቀላቀል፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ በሙስናና በጥላቻ የተዘፈቁ፣ ለሕዝብ ንቀት ያላቸው፣ ያላቸውን ስልጣን ተጠቅመው ዜጎችን እያሸበሩ ያሉትን በመቃወም፣ መስከረም 19 ቀን ሰልፍ በመውጣት ድምጽህን አሰማ።
ለኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም መልእክት አለኝ። ጥያቄው የስልጣን ጥያቄ አይደለም። የፍትህ እንጂ። ጉዳዩ ኢሕአዴግን የመጥላት አይደለም። ኢሕአዴግንም ያካተተ ብሄራዊ እርቅ የማምጣትና የፍቅር እንጂ።
የአንድነት ፓርቲ ሰልፍ የጠራው ኢሕአዴግን በመቃወም አይደለም። ሰልፉ ጸረ-ኢሕአዴግ ሰልፍ አይደለም። ሰልፉ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ብሄራዊ እርቅ እንዲመጣ፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኖች እንዲፈቱ፣ በሽብርተኖች ላይ ሳይሆን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው የጸረ-ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ አሊያም እንዲሻሻል፣ የኢኮኖሚ እድገት ጥቂቶችን ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ሕዝብ ባቀፈ መልኩ እንዲቀጥል..የሚጠይቅ ሰልፍ ነው። እነዚህንም ጥያቄዎች አገራችውን የሚወዱና ልቦና ያላቸው፣ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ይጋሩታል ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም የመስክረም 19ኙን ሰልፍ እንዲቀላቀሉ አበረታታለሁ። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው። ይሄ ለፓርቲ ታማኝነት የማሳየት ወይንም ያለማሳየት ጉዳይ ሳይሆን አገርን የማዳንና ወደፊት የማስኬድ ጉዳይ ነው። ከኢሕአዴግ በፊት ኢትዮጵያ!!!! ከአንድነት ፓርቲ በፊት ኢትዮጵያ!!! ከመኢአድ በፊት ኢትዮጵያ!!!!!
በውጭ አገር ላለነው ይሄን እላለሁ። ሰሞኑን እንደምንሰማው፣ አንዳንዶች፣ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቡ እየተንቀሳቀሰ እያዩ፣ በአዲስ አበባ ሰልፎች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት፣ ከየት መጡ ሳይባሉ፣ ትኩረት በማጣታቸው ቀንተው ነው መሰለኝ፣ "መዳን በኢሳያስ አፈወርቂ ነው" እያሉን ነው። ከጋንዲ፣ ከማርቲን ሉተር ጊንግ፣ ከነአንሳ ሱንኪ፣ከነጂን ሻርፕ በልጠው፣ "ስለሰላማዊ ትግል እኛን አትጠይቁ። ከኛ የበለጠ ስለሰላም ትግል የሚያውቅ የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ትግል አይሰራም" በማለት ሲለፍፉ እየሰማናቸው ነው። መንገዱን ጨርቅ ያርግላቸው እላለሁ።
ነገር ግን ይህ አይነቱ የፖለቲካ መርዝ፣ ብዙዎችን እየበከለ እንዳለም ታዝቢያለሁ። ይሄን አይነት የጥላቻና የጦረኝነት ፖለቲካን በጭፍን ተቀብልን እያስተጋባን ያለን ጥቂቶች አይደለንም። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት ብዙ የምንወያይበት ይሆናል። ለጊዜው ግን በውጭ አገር ያለኸው ወገኔ፣ ሁሉንም በሚዛን ላይ እንድታስቀምጥ እምክርሃለሁ።
በእውኑ ተስፋህን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መጣል ይሻላል ወይንስ፣ የሚገዛውን ሕዝብ እያሰቃየና እያረዳ ባለ በአንድ የአበደ መሪ ላይ? በእውኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያን ያህል የማይረባ ሆኖ ነውን ነጻነትና ዲሞርካሲን ከሻእቢያ መጠበቅ የሚገባው? በእውኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር አመራር አባላት አድራሻቸው ጠፍቶ (ታስረውና ተገድለው)፣ በኢትዮጵያዊ ፖለቲካ አመለካከታቸው ከበሬታን ያገኙ እንደ ጄነራል ከማል ገልሺና ጀነራል ሃይሉን ጎንፋን የመሳሰሉ ወገኖች ከአገር እንዳይወጡ ታግተውና ታስረው፣ ያለምንም ችግር በቲራቮሎ አስመራር እየተመላለሱ፣ የኢሳያስ አፈወርቂን ታላቅነት የሚሰብኩንን ሰምተን፣ ፊታችንን ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እያደረገ ካለው ወሳኝ ትግል ማዞር ይኖርብናልን? እነዚህ ወገኖች በረጩትስ መርዝ ተስፋ ቆርጠን የአገር ቤቱን ወሳኝ ትግል ከመርዳት መቆጠብ ይግባናልን? እንግዲህ አገሩን የሚወድ በውጭ አገር ያለ ኢትዮጵያ ሁሉ እራሱን ይመርምር እላለሁ።
ከሕዝቡ ጎን ቆመናል የምንል ሁሉ የድርሻችህንን እንወጣ። አዲስ አበባ እየደወልን ሕዝቡ ለሰፍ እንዲወጣ እናበረታታ። የሚሊየንም ድምጽ ለነጻነት የተሰኘውን ንቅናቄ በገንዘባችን እንርዳ። ከዳር ሆነን፣ ወሬ የምንለቃቅም ተመልካቾች አንሁን። የትግሉ አካል፣ ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን!!!!!!! እኛ ካልተነሳን ማን? ዛሬ ካልተነሳን መቼ!!!!
አማኑኤል ዘሰላም
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



