Yedenekachew Kebede ይድነቃቸው ከበደይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ)

የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በየትኛውም ሀገር እንደ አገሩ ወግና ልማድ በድቅመት የሚከበር በዓል ነው፤ በእኛ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ደግሞ ልማድና ወጋቻን እጅግ ከመጠንከሩ የተነሳ ለአዲስ ዓመት ወይም ለዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ዝግጅታችንም ሆነ አከባበራችን እጅግ በጣም ጠንካራና ደስ የሚል ነው።

 

አዲስ ዓመት የሁሉ ነገር መጀመሪያ ነው ለዚህም ነው ብዙ እቅዶቻችን ከመስከረም ወር የሚጀምረው፤ ያቀድነው ነገር በዓመቱ መጨረሻ ሊሳካ ወይም ላይሳካ ይችል ይሆናል ቁም ነገሩ ግን በዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለማሳካት የታሰበ እቅድ መኖሩ ነው፤ ለእቅዱ አለመሳካት ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ እነዚህን እንቃፋት የሆኑ ምክንያቶች ለይቶ ማወቅ በራሱ የእቀዱ አንድ አካል በማደረግ እንደገና ለመጪው አዲስ ዓመት ለተሸለ እቅድ ግባት ይሆናል።

የዘንድሮ አዲስ ዓመት ከግለሰባዊ ፋይዳ በላይ ሀገራዊና ህዝባዊ የለውጥ ፋይዳ የበዛ እንደሚሆን ምልክቶቹ አብዝተው ይታያሉ፤ እነዚህ ምልክቶች ከባለፈው ዓመት ለዘንድሮዎ የተሸጋገሩ የለውጥ ምልክቶች ናቸው፤ በመሆኑም ለለውጥ የተነሳሳው ለወጥ ፈላጊ ለውጡኑ የሚያከሽፍበት አንዳችም ምክንያት ስለመኖሩ እጠራጠራለው ክሽፈት ቢያጋጥም እንኳን ወድቆ ለመነሳት ብዙ ጊዜ የሚባክን አይመስለኝም።

መውደቅ መነሳት ከሚንቀሳቀስ ነገር የሚጠበቅ ክስት ነው መንቀሳቀስ ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጪ በሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ ፖለቲከኞች፣ በአይማኖት ተቋመት፣ በሲቪክ ማህበራት እና በመሳሰሉት እንቅስቃሴው መሰልቸትና ድካም የማይታይበት ጠንካራ እንቅስቃሴ ነው፤ ይህ እንቅስቃሴ ከባለፉት ወድቆ መነሳት እንቅስቃሴ ት/ት የተቀሰመበት ስለመሆኑ ከምልክቶቹ መካከል አንዱ ነው።

በሀገራችን ለለውጥ የሚገፋፉ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም ከብዙ ምክንያቶች በዋንኝነት ትኩረትን የሚስቡት የለውጡን አይቀሪነት አሳበቂ ምክንያቶች ከሆኑት ውስጥ፡-

1ኛ. በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ እምነቶች መካከል ክርስትና እና እስልምና ዋንኞቹ ናቸው፤ እነዚህን እምነቶች በመቀበል እኛ ኢትዮጵያዊያን ከቀዳሚዎቹ መካከል እንገኛለን ክርስትናን እና እስልምና እምነትን መቀበላችን ብቻ ሣይሆን የተቀበልነው እምነት ህግና ሥርዓት አክብሮ በማስከበር ወደር አይገኝልንም። ይሁን እንጂ መንግሥት በልማት ስም የአምልኩ ቦታዎችን በመጋፋት ቤተ ክርስቲያንን ተዳፍሯል፤ ይህ ነገር ተገቢ አይደለም ያሉ የኃይማኖት አባቶች ተደብድበዋል፣ ተገለዋል እንዲሁም ከሀገር ተሰደዋል።

መንግሥት በኃይማኖት ኃይማኖት በመንግሥት ጣልቃ አይገባም የሚለውን ህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ መንግሥት በመጣስ በሙስሊም እምነት ዘው ብሎ በመግባት የእመንቱን መሪዎች እስከመምረጥ ደረጃ ተደርሷል፤ ይህን አይቶ ዝም አለማለት እስላማዊ ግዴታ እንደመወጠት የቆጠሩ እንቢ ለእምነቴ ያሉ በእስር እና በስቃይ ላይ ይገኛሉ። በእነዚህ ታላላቅ እምነቶች መንግሥት እጁን በማስገባት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ ምን አለ? በተለይ በሙስሊሞች ላይ እተየፈፀመ ያለው በደል እና በእምነቱ ተከተዮች የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ ያለጥፋታቸው በሐሰት በመወንጀል አሸባሪ ብሎ በእስር ማሰቃየቱ እጅን ጨብጦ ጥርሱን ነክሶ ያልተቆጨ ማነው?

2ኛ. ኢትዮጵያ ሀገራችን የብዙ ሺህ ዓመት አኩሪ ታሪክ ያላት እና የተለያዩ ንዎች የሚነገርባት ህዝቧ የቋንቋ ልዩነት ሣይገድበው አንዱ ከሌላው የተዋለደባት እጅግ ውብ እና ማራኪ ቋንቋ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ወግ፣ አለባበስ እና አመጋገብ ወዘተ ... የሚታይባት ድንቅ ሀገራችን ናት። ይሁን እንጂ የኢህአዴግ መንግሥት ይህ ቦታ የናተ አይደለም በማለት ዜጎችን በማፈናቀል ሀብትና ንብረት በማውደም ጎጠኝነትና ዘረኝነት በማስፋፋት ላይ ይገኛል፤ እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ተግባር በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ በዘመቻና በእቅድ በመንግሥት የተፈፀመ ህገወጥ ተግባር ነው። በመሆኑም ከኢትዮጵያዊነት በላይ መንደረኝነት እንዲነግስ በመንግሥት እየተደረገ ያለው ዘመቻ ያላስቆጨው፣ ያላንገበገበው ማነው? ይህን ቁጭቱን እና በደሉን ለመግለፅ ጊዜና አጋጣሚውን እየጠበቀ ያለው ስንቱ ነው?

እኛ ኢትዮጵያዊያን በእድሜና በውቀታቸው ከፍ ላሉ ሰዎች ያለን ከበሬታ እጅግ የላቀ ነው፤ ለዚህም ነው ለሽምግልና ጉዳይ ቶሎ እጅ የምንሰጠው በሽምግልና ካጣነው ነገር በላይ ያተረፍነው የበዛ ነው። ይሁን እንጂ የቆየውና ጠቃሚ የሽምግልና ወገና ሥርዓት በመጠበቅ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የጋምጎፋ (ቆጫ ወረዳ) እና የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው ለታየው አስተዳዳሪያዊ ችግር መፍትሔ ለመሻት ከታችኛው የአስተዳደር አካል እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥረት ውጤት አልባ ነበር፤ ከምንምንም በላይ የሽምግልና ክብር በመጋፋት መንግሥት ጠቃሚ የሆነውን ወግና ሥርዓት ለመናድ የሄደበት መንገድ ሽማግሌዎችንና የተወከሉበትን ማህበረሰብ ምን ያህል ነው ያስከፋው?

3ኛ. "በኑሮ ውድነት የጎበጠው ትከሻችን እረፍት ይሻል" ኑራችን አላምር ሲል መፈክራችን ማማሩ የሚገርም ነው! ይህ መፈክር ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ባካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ከፍ ብሎ የተሰማ ጥያቄ ነወ፤ እውነትም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኑሮ ውድነት ትከሻውን ከማስጉበጥ አልፎ ህይወቱን እየነጠቀወ ነው። ባለ ሁለት ሃአዝ እድገት በመንግሥት ተደጋግሞ የሚነገር አስማታዊ እድገት ምግብም መጠጥም አልሆን ብሎ በመንግሥት የሚነገረው እድገትና የምንኖረው ሕይወት ሆድና ጀርባ ሆኖ አልገጥም እያለ ተቸግረናል።

የስራ አጥነት ቁጥሩ በጣም የበዛ ነው፣ ሰራተኛም ሰርቶ የሚከፈለው ወራዊ ደሞዝ ወሩን ሙሉ የሚያቆይ አይደልም፣ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት 2.5 ሚሊዩን ዜጎች ለጎዳና ተዳዳሪነት መዳረጋቸው የመንግሥት መስሪያ ቤት የሆነው የማህበራዊ ዋስትና ድርጅት ባስጠናው ጥናት መሰረት ይፋ አድረጎኃል፤ ጎዳና ያልወጡ እቤታቸው ጎዳና የሆነባቸው ዜጎች ቤት ይቁጠራቸው።

በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ምስቅልቅል የበዛበት የኑሮ ውድነት ዋንኛው መንስሄ ብልሹ የመንግሥት አስተዳደር ስለመሆኑ የእኛ መንገስትና ኑራችን ዋንኛ ማስረጃ ነው፤ ስለሆነም እንዲህ አይነቱ ብልሹ የመንግሥት አስተዳደር አቅፎና ደግፎ ይዞ የሚሄድ ጉልበትም ሆነ አንጀት ከወዴት ይምጣ?

4ኛ. አሁን ያለው የአባገነን ሥርዓት የተረጋጋና ጉልበት አልባ መሆኑ ሌላኛው የለውጡን አይቀሪነት አሳበቂ ምክንያት ነው። ከእሳቸው ሞት በፊት ይታይ የነበረው የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ከእሳቸው ሞት በኃላ የሥርዓቱ ፊት አውራሪዎች ከመብዛታቸውም በላይ በቡድን የተከፈሉና እኛ እናተ መባባላቸው ከጥጋባቸው በላይ የስልጣን ጥማታቸውን የሚያሳይ ነው፤ ግን በሁለት ሆዳሞች መሃል እህል ይደፋል እንጂ ማንም አይበላውም።

ሌላው የሥርዓቱ የፊት ሰዎች ከውስጣዊ ሹኩቻ ባለፍ በአደባባይ አንዱ ለሌላው በሙስና እና በስልጣን መባለግ ስም ማሰርና መክሰስ ሌላኛው ሀገር ጥሎ መሄድ መሳ ለመሳ እየተካሄደ ያለ ውስጣዊ ሹኩቻ ነው፤ በእንዲ መልኩ በውስጥ የተወጠረው የአባገነን ሥርዓት በተጠናከረ እና ሠላማዊ በሆነ ህዝባዊ ግፊት ፈንድቶ ውስጣዊ ሰንኮፉ የማይነቀልበት ምክንያት ምንድነው?

5ኛ. ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም የመደራጀት መብት ዓለም አቀፍ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። በመሆኑም አንዱአለም አራጌ፣ ናትናሄል መኳንን፣ በቀለ ገራባ፣ ኦልባና ለሊሳ እና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች እንደማንም ኢትዮጵያዊ የራሰቸው ኑሮ እና ህይወት ያላቸው ናቸው፤ ይሁን እንጂ ነፃነት እና ፍትህ ለነሱ ሁለተኛ ጉዳይ አይደለም የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ነው! ከራስ ወዳድነት አልፈው ይህ ጥያቄ የኛ ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው በማለት በአደባባይ ስለነፃነት እና ፍትህ የዘመሩ በዚህም አኩሪ ተግባራቸው በእኛ የኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ቦታ የምንሰጣቸው ነን። የታሰሩበት እና የሚሰቃዩበት ጉዳይ የኛም ጉዳይ ነው የሚሉ ቁጥራቸው መብዛቱ ሠላማዊ ትግሉ አባገነን ሥርዓቱን የሚበላ እሳት መሆኑ ማሳያ ነው።

ይህ በእንዲ እንዳለ በሀገር እና በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደል ማቆም አለበት መንግሥት እየወሰዳቸው ያለው እርምጃ የዜጎች ሰብአዊ እና ዲሞክራሳዊ መብቶችን የጣሱ ናቸው፤ በማለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው ከምንም በላይ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ጠብቀው ሚዛናዊ መረጃ ለእዝብ ያደረሱ ዓለም ዓቀፍ ተሸላሚ የሆኑ ጋዜጠኖች በእስር ላይ ይገኛሉ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ እርዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬ በስራቸው ዓለም ያደነቃቸው አድናቆቱም በሽልማት የታጀበ መሆኑ ለማናችንም ግልፅነው። ይሁን እንጂ እነዚህ የዓለም ህዝብ ቆሞ ያጨበጨበላቸው ጋዜጠኞች አባገነኑ መንግሥት በሽብርተኝነት ወንጅሎ በማሰር እያሰቃያቸው ይገኛል። ይህ ስቃያቸው ያልተሰማው ማነው? ከዚህ ስቃይ እንዲወጡ ምን ባደርግ ይሻላል እያልን እራሳችንን ያልጠየቅን ስንቶቻችን ነን? በሆነውስ ነገር ያልተቆጨ ማነው?

6ኛ. በውጪ የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅኖ ሌላው ለአባገነኑ ሥርዓት የእግር እስታ መሆን ነው፤ በውጪ የሚገኙ ዜጎች በሀገር ውስጥ ለታየው ብሉሹ አስተዳደር ፊት ከመንሳት ባለፈ በተደራጀና በሚያስደንቅ ሁኔታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴውም ከሌላው ጊዜ በተሸለ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካው ስኬታማ መሆኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለያየ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ እና መንግሥት በሰጠው መግለጫ በውጪ በሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን መንግሥት መሸነፉን የሚያሳብቅ ነው።

በመሆኑም ከላይ በማሳያነት የቀረቡ የለውጡ ግፊት ኃይል ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ የተጨለፈ ቢሆንም በመንግሥት የአስተዳደር ብሉሹነት ምክንያት ይህ አስተዳደር በቃኝ ለማለት ምክንያቱ ብዙ ነው። ስለሆነም መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈናድ ለውጥ ፈላጊ የፈለገውን ለውጥ ላለማጣት ከባለፈው ዓመታት ት/ት በመውሰድ በዘንድሩ አዲስ ዓመት ከግለሰባዊ ፋይዳ በላይ ሀገራዊና ህዝባዊ ለውጦች የምናይበት ዓመት ይሆናል።


ይድነቃቸው ከበደ
(የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ