ክንፉ አሰፋ
በተንጣለለ ቪላ ውስጥ ከበድ ያሉ እንግዶች "ጸዳ" ባሉ ምግብና መጠጦች እየተስተናገዱ ነው። ታዋቂ ግለሰቦች፤ ባለሥልጣናት እና አርቲስቶች የቀረበላቸውን ቡፌ በልማታዊ ወጋቸው እያወራረዱ ሳሉ፤ አንድ እንግዳ ነገር በመሃላቸው ተከሰተ። ሞቅ ባለው የአይቴ ነጋ ገብረእግዚአብሔር ድግስ ላይ ያልተጋበዙ ሁለት ሰዎች ዘው ብለው ከግብዣው ክፍል ገቡ። የፌዴራል ፖሊስ አባላት ነበሩ።

 

በዚህ ያልተለመደ ክስተት የአቶ ነጋ እንግዶች አልተደናገጡም ነበር። ይልቁንም የፌዴራል ፖሊሶቹ ለተጨማሪ ጥበቃ የመጡ ነበር የመሰላቸው። አንድ ብርጌድ ያህል ጦር አስከትለው የመጡት ፖሊሶች ግን አቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔርን አስጠሯቸው። አቶ ነጋም ለጥሪው እንደወትሮው በመወጣጠርና ፍፁም ትዕቢት በተሞላበት አነጋገር ምላሽ ሰጡ። በፖሊስ አባላቱ እና በአቶ ነጋ መካከል የኃይለ-ቃል ልውውጥ ተጀመረ። እሰጥ አገባው አንድ፣ ሁለት እያለ ሄደና በመጨረሻ ተካረረ። በዚህ ሰዓት አቶ ነጋ ስልክ መደዋወል ያዙ። ከፍተኛ የሚባሉ ባለሥልጣናትና ምኒስትሮች ጋ ደወሉ። ከዚያም በመቀጠል፣ ጀነራሎች ጋ ደወሉ፣ ... የጦር መኮንኖች፣ የፓርቲ ባለሥልጣናት፣ ... ሁሉም ጋ ተደወለ። የባለሥልጣናቱ ምላሽ ግን ጥሩ እንዳልነበር ከአቶ ነጋ ፊት ላይ ይነበብ ነበር። ወዳጆቻቸው ሁሉ እንደ ቱኒዚያው ቤን አሊ በአንድ ጊዜ ከዷቸው።

"በል - ና - ውጣ!" አለ አንደኛው የፖሊስ አባል፣ የስልኩን ሽርጉድ በጥሞና ከተከታተለ በኋላ።

"ምን ማለትህ ነው? እኔኮ ነጋ ነኝ። ነጋ ታሪኩ!" አሉ። አነጋገራቸው የጀምስ ቦንድን ይመስል ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ እጃቸውም አላረፈም። ከጎን ያሸጎጡትን መሣሪያ ለማውጣትም ዳዳቸው።

በቅጽበት ግን ፌዴራል ፖሊሱ ቀደማቸው። በድንገት "ጯ!" የሚል ድምጽ አዳራሹን አናጋው። የፖሊሱ አይበሉባ የግራ መንጋጭላቸው ላይ ሲያርፍባቸው ጊዜ፤ አይቴ ነጋ ነገር አለሙ ተደበላለቀባቸውና እጅ መስጠትን መረጡ። ግብር ሊያበሉ በጠሯቸው የክብር እንግዶቻቸው ፊት፣ ከዚህ በላይ መዋረድ አልፈቀዱም። ሁለት እጃቸውንም ወደ ፖሊሱ በመዘርጋት ለብረት ማሰርያው ራሳቸውን አመቻቹ። እጃቸው የኋሊት ከተጠፈረ በኋላም አቶ ነጋ እንዲህ አሉ። "በቃ! ህወሓት አበቃለት!"

"ባለሀብቱ" በዚህ ሁኔታ በፖሊስ መኪና ተጭነው ወደ እስር ቤት ሲሄዱ፣ ተጋባዥ እንግዶቹም እግሬ-አውጭኝ እያሉ ከስፍራው አፈተለኩ። ይህ ታሪክ ድራማ ሊመስል ይችላል። ግን በእውን የተፈጸመ ሐቅ ነው። ታሪኩን ያጫወተኝ ሰውም እዚያ ግብዣ ላይ ግብር ሊበላ ተገኝቶ ነበር። እንደ አግራሞቱም "ይህ መቼም የፈጣሪ ሥራ ነው።" ከማለት ውጪ ስለ ጉዳዩ እንድምታ የሰጠው ማብራሪያ የለም።

ነጋ ገብረእግዚአብሔር የነፃ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ (ሰዎች ያልተወሰነ ይሉታል) የግል ማኅበር ባለቤት ነበሩ። ድርጅታቸውም እንደስሙ ከሁሉም ነገር ነፃ ነበር። ከግብር ነፃ፤ ከቁጥጥጥር ነፃ፤ ከፍተሻም ነፃ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች እቃ ጭነው በየኬላው ሳይፈተሹ እንዲያልፉ የተሰጠ ልዩ መብት ሁሉ እንደነበራቸው ይነገራል። ዛሬ ፈጣሪ ሲፈርድባቸው በኢፍትሃዊ መንገድ ቢልየነር ያደረጋቸው ሥርዓት፤ ያው ሥርዓት ሰለባ አደረጋቸው ... ነጋ ገብረእግዚአብሔር ለአቶ መለስ ዜናዊ እና ለባለቤታቸው ለወ/ሮ አዜብ መስፍን ቅርብ - በጣም ቅርብ ነበሩ። ለጉምቱ ባለሥልጣናት ይሰጡት የነበረው እጅ መንሻ ከዚህ አይነት ውርደት እና እስራት ሊያድናቸው አልቻለም። በትግራይ ውስጥ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ አውጥተው በስማቸው ያሰሩት የቴክኒክ ኮሌጅም እንደ ውለታ አልተቆጠረላቸውም። ...

ይህችን አጭር መጣጥፍ ለመጫር እንደተቀመጥኩ አንድ ዜና በኢሜይል ደረሰኝ። የዜናው ርዕስ "ጀነራል ባጫ ደበሌ የአዋሽ ባንክ ሰራተኞችን ከሥራ እንዲባረሩ አደረጉ!" ይላል። ባጫ ደበሌ የባንክ ሰራተኞቹን ያባረሩዋቸው ''እኔ ጀነራል ባጫ ደበሌን እንዴት አታውቁኝም?'' በሚል በሰራተኞቹ አለመታወቃቸው አበሳጭቷቸው ነበር። ወደ ፌስ ቡክ ጎራ ስልም አንዳንዶች በዜናው ላይ ሲወያዩ አስተዋልኩ። ይህ እኮ አዲስ ክስተት አይደለም። ለብዙ ጊዜ የሚደጋገም እና የተለመድ ነገር ዜና ሊሆን አይችልም። ውሻ ሰውን ሲነክስ ዜና አይሆንም። በተቃራኒው ግን ሰው ውሻን ከነከሰ ዜና ይሆናል።

እንዲህ አይነቱ ክስተት ስር የሰደደ የሥርዓቱ ባህርይ ነው። ባጫ ደበሌ እነዚያን ሰዎች ማስገደል የሚያስችልም ሥልጣን እና መብት ያላቸው የአዜብ ሰው መሆናቸውን አንዘንጋ። ጀነራል ባጫ በተልዕኮ ትምህርት ከአንድም ሁለተኛ ዲግሪ እንዲገዛላቸው ካደረጉ በኋላ፣ ለምርቃታቸው ሥነ-ሥርዓት፣ ሰንጋዎች ጥለው፣ የሙዚቃ ባንድም አስመጥተው፣ መንገድ ሁሉ እንዲዘጋ አድርገው ሲያበቁ፤ በተለመደው ብሬክ ዳንሳቸው መንደሩን የቀወጡ ሰው ናቸው። በብርሃን ፍጥነት ከኪነት ጓድነት ወደ ጀነራል የተሸጋገሩት ባጫ ደበሌ በመደበኛ የሥራ ጊዜያቸው ጫት ይነግዳሉ። በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ በዜጋው ላይ እንዲሁ እንደዋዛ እየቀለዱ እስካሁን አሉ። የነገውን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። የፍትህ ሳይሆን የግለሰቦች የበላይነት የሰፈነበት ሀገር ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ሙስና ሊደንቀን አይገባም። የፍትሃዊ ሥርዓት መጥፋት ነው ሙስና።

ፕሮፌሠር አል ማርያም ባለፈው መጣጥፉ ስለሙስና ሲጽፍ ከሙስና ሁሉ በላይ ሙስና የሚሆነው የፍትህ መጓደል እንደሆነ አስነብቦናል። የፍትህ መጥፋት ስብዕናን፣ ነፃነትንና ንብረት ማጣትን ያስከትላልና። In my view, denial of due process (fair trial) is the highest form of corruption imaginable in the "justice sector" because it results in the arbitrary deprivation of a person's life, liberty and property. (Al Mariam)

ከሰሞኑ ደግሞ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተሃል በመባል ተወንጅሎ ወህኒ የወረደው የወልደሥላሴ ወልደሚካኤልም ዜና በስፋት እየተሰራጨ ነው። ወልደሥላሴ ሌላኛው የአዜብ መስፍን የቅርብ ሰው ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ዳዊት ከበደ በስፋት ትንታኔ ስለሰጠበት እዚህ ላይ አልደግመውም። ወልደሥላሴ ግን ከህወሓት የጫካ ትግል ጀምሮ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ተመድቦ የሠራና - የመለስ ቀኝ እጅ የነበረ ሰው ነው። ታማኝ አገልጋይም ስለነበረ በህወሓት ውስጥ ወሳኝ ቦታ ነበረው።

ከወልደሥላሴ እስር በኋላ ብዙዎች በህወሓት ውስጥ ውጥረት እንዳለ መናገር ጀምረዋል። ውስጥ ለውስ እየተንከባለለ ያለው ውጥረትማ ከከረረ ትንሽ ዘግየት ያለ ይመስላል። በውጥረቱ የተነሳም በባለሥልጣናቱ መካከል እርስ በርስ መተማመን ከጠፋ ቆየ። አንድ ውስጥ አዋቂ ስለዚህ ሁኔታ ሲያጫውተኝ አባላቱ በምሽት ሲወጡ እንደ ጅብ ጎን ለጎን ነው የሚሄዱት። ጅብ ስለሚፈራ ብቻውን አይሄድም። ሁሌም ተጠራርቶ በቡድን ይሄዳል። ከባልንጀራው ጋር አብሮ ሲሄድ ደግሞ ጎን ለጎን መሆን አለበት። ፊትና ኋላ ከሆኑ እርስ በርስ ይበላላሉ።

በአሁኑ የህወሓት አሰላለፍ ግን አንደኛው ወገን ከኋሊት መጥቶ የቀደመ ይመስላል። ከፊት ያለው የኋላውን መብላት ጀምሯል። ተገላቢጦሽ የሆነው ይህ አስገራሚ ክስተት ነው ውጥረቱን ይበልጥ ያከረረው። የአዜብን ቡድን የማጥፋቱ ሂደት ላይ ግን ከፍተኛ ጥናት ሳይደረግ አልቀረም። የፖለቲካ ኃይል አሰላለፉ ላይ ሚዛን የደፋው አንደኛው ቡድን ከደሙ ንጹኅ ባይሆንም የሙስናውን ወንጀል ለብቀላ መጠቀምያ ማድረጉ የአደባባይ ምስጢር ነው።

አንዳንድ የዋሆች ታዲያ ይህ የፀረ-ሙስና ዘመቻ አቶ መለስን ለማሳጣት እየተደረገ ያለ ድራማ እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንም የሚያመሰግኑም አልጠፉም። አቶ ኃይለማርያም ብዙውን ክስተት እንደ ተራው ሰው በዜና እንደሚሰሙ የሚያውቁት በቅርብ ያሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ለነገሩ እሳቸውም አስቀድመው "የእኔ ሥራ ከፊትም ሆነ ከኋላ የሚሰጠኝን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ማስፈጸም ብቻ ነው።" ብለዋል። ከፊትና ከኋላ ብቻ ሳይሆን ከላይና ከታችም መመሪያ እየተቀበሉ ያስፈጽማሉ። በሙስናው ስም የሚካሄደው ጨዋታ ከሳቸው ራዳር ውጭ ያለ መሆኑን ለመረዳት የፖለቲካ ጥበብን አይጠይቅም።

አቦይ ስብሃት በአንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ስለዚህ ጨዋታ ሲናገሩ "የ10 ሚሊዮኑ ዘራፊ ቁጭ ብሎ የ10 ሺው መታሰር የለበትም" ብለው ነበር። አቦይ ስብሃት እውነት ብለዋል። ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ቤት ተገኘች ተብላ በኢቲቪ ጭምር ስትታይ የነበረችው 26 ሺ ኢሮ ኢምንት ናት። Global Financial Integrity (GFI) በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ግልጸኝነት ተቋም ከ2001 እስከ 2010 እ.ኤ.አ. ብቻ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ወደውጭ የወጣው ገንዘብ 16.5 (አስራ ስድስት ነጥብ አምስት) ቢሊየን ዶላር ነው ሲል መረጃውን ከነማስረጃው ይፋ አድርጓል። ይህ ድርጊት ደግሞ በሙስና ከዘቀጡ ሀገራት ኢትዮጵያን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ልብ በሉ! 16.5 ቢሊየን ዶላር ከአራት በላይ የ"ህዳሴ" ግድቦችን ያሠራል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መላው አውሮፓን ከውድቀት ያስነሳው የማርሻል ፕላን በጀት 20 ቢሊየን ዶላር ነበር። ከኢትዮጵያ በስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ የወጣው 16 ቢሊየን ዶላር ደግሞ አፍሪካ ካለችበት ውድቀት ሊያስነሳት የሚችል ገንዘብ እንደሆነ የኢኮኖሚ ጠበብት ይናገራሉ።

ኤ.ቢ.ሲ ኢንተርናሽናል የተባለው የማድሪድ ጋዜጣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ቀን ግብይት ብቻ ለልብሷ 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣች ዘግቧል። አዜብ መስፍን ባለፈው የህወሓት ስብሰባ ላይ ተገኝታ ስትናገር ግን የአቶ መለስ የወር ደሞዝ 250 ዶላር እንደሆነ ነበር የተናገረችው። አዜብ የ1.5 ሚሊዮን ዶላር ልብስ በአንዲት ምሽት ስትሸምት መንግሥት ድጎማ አድርጎላት ከሆነ ይኸው በይፋ ይነገር። በ250 ዶላር የወር ገቢ በሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረግ የሚቻልበት ሚስጥር የአባባ ታምራት ገለታ ምትሃት ካልሆነ ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል? ይህንን መራራ ሐቅ የፀረ-ሙስናው ኮሚሽንን የሚነዳው ቡድን እንዴት ችላ ሊለው ቻለ? በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ታዛቢዎች የሚሰጡት አስተያየት የሚያስኬድ ይመስላል። ቡድኑ በቅድሚያ ወደ እነ አዜብ ሰፈር የሚወስደው መንገድ ላይ ያሉ ከእንቅፋቶችን ሁሉ ማጥራት አለበት።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደ ቀልድ የሚነገሩ አንዳንድ እውነታዎች ለማመን የሚከብዱ ናቸው። አንዱ 'ልማታዊ ባለሀብት' በሪል ስቴት ስም የተመራው ቦታ ሲሰላ ከጅቡቲ የቆዳ ስፋት በልጦ ተገኘ። ይህ ሰው ትንሽ ቆይቶ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም የመገንጠል ጥያቄም ሊያነሳ ይችላል እያሉ ያወሩ ነበር - በዚያ የቀኑት ባልንጀራዎቹ። በመጨረሻ ግን "ባለሀብቱ" በሙስና ታሰረና ይዞት የነበረው መሬት ለነ ቱሬ ዘመዶች በሄክታር ሁለት ብር ሂሳብ ተቸበቸበ። ለነገሩ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከዜጋው እየተቀማ ለውጭ ዜጎች በተቸበቸበባት ሀገር ይህ ምንም ላይደንቀን ይችላል።

የሙስና ሰለባ የሆነው የሌላኛው ባለሥልጣን ቤት ሲበረበር ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ይመስል ነበር። እዚያ ቤት ውስጥም የዓለም መገበያያ ገንዘብ ተገኘ። ዶላር፣ ኢሮ፣ ድራም፣ የን፣ ፓውንድ፤ ክሮና፤ ፍራንክ፣ ዲናር፣ ረንቢኒ፣ ... እንዲያውም የኤርትራ ናቅፋ በገፍ ነበር። ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ 26 ሺ ዶላር ተጋንና በቲቪ ስትቀርብ የዚህኛው ንግድ ፈቃድ የሌለው ባንክ በግል እጅ ሲገኝ ሚዲያም ዝም ማለትን መረጠ። በዚህ ጊዜ ነበር የአሳሪው ቡደን ኃላፊ የኮሎኔል መንግሥቱን ንግግር የተጠቀመው። "ደፍረውናል፣ ንቀውናል። ... ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል።"

አነጋገሩ ለምን ሀገር ተዘረፈ ሳይሆን፤ እኛ ታግለን ለዚህ የደረስን የቁርጥ ቀን ታጋዮች ቁጭ ብለን እንዴት ከኋላ የመጣው ሊበልጠን ቻለ ለማለት ነበር። የሙስናው ዘመቻ ድራማ ቁልፍ እዚህ ላይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በሰፊው እሄድበታለሁ። ለአሁን ግን በአቶ ኤርምያስ አመልጋ የሚደነቅ ታሪክ ጽሁፌን ልቋጭ።

በዚያ ሰሞን የአክሰስ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅና የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ኤርምያስ ጠቅል አመልጋ፣ በተለይ በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ከሰበሰቡ በኋላ፣ ከሀገር መጥፋታቸው ተዘግቦ ነበር። ታዲያ አቶ ኤርምያስን የሚረግሙ ጌጃ ዲያስፖራዎች እንዳሉ ሁሉ እሳቸውን የሚያደንቁም አልጠፉም። ስለአቶ ኤርምያስ በቀልድ እየተመሰለ ብዙ ነገር ይወራል። የተከበሩ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን እና አቶ ኤርምያስን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁለቱም የተዋጣላቸው ሰዓሊያን መሆናቸው ነው ተብሏል። ለላሜ ቦራው ዲያስፖራ እንዲሰሩ ገንዘብ የተከፈለባቸው ቤቶች ሁሉ ባማሩ ስዕሎች በወረቀት ላይ ዱቅ ብለዋል። በንዴት ገንዘቡን ሊያስመልስ የሚሄደው ሁሉ በስዕሎቹ እና በአቶ ኤርምያስ ምትሃታዊ ንግግር እየተማረከ እንዲያውም ለሁለተኛና ሦስተኛ ቤት የከፈለው ዲያስፖራ ቁጥር ትንሽ አይደለም። አቶ ኤርምያስ በአንድ በኩል በሙስና ክስ እየተፈለጉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገር በቦሌ አድርገው እንዲወጡ የተደረጉ "ጀግና" ባለሀብት ናቸው።

ለፖለቲካው እንግዳ ለሆኑ ሰዎች፤ እነዚህ ሁሉ ፈጠራ ሊመስሉ ይችላሉ። ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የዕለት ተለት ገጠመኞች ውስጥ አንድ እጅ እንኳን የማይሞሉ እውነታዎች ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ