ግርማ ሠይፉ ማሩ

"የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ለምን ያስፈራል?" በሚል ርዕስ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ ነሓሴ 5 ህትሙ ረጅም ፅሁፍ አሰነበቦናል። ፀሐፊው በቦነያ ሰ. በሚል አቶ/ወሪት/ወሮ ይሁን በማይታወቅ ስም ነው ያወጡት። ይዘቱን ሳነበው የምናውቃቸው የኢህአዴግ ሹሞች በብዕር ስም ልከውት ያው የኢህአዴግ አቋም ነው ብዬ ለመውሰድ ዝግጁ ሆኜ ንባቤን ሳጠናቅቅ፤ ፀሐፉው የሕግ ባለሞያ እንዲሁም በተለያየ የመንግሥትና መንግታስዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በሙያቸው ሰርተዋል የሚለው የአዘጋጁ ማስታወሻ መልስ እንድሰጥ ጋበዘኝ።

 

 

የግርጌ ማስታወሻው ሰርተዋል ስለሚል አሁን እየሰሩ አለመሆኑን ገመትኩና አሁን የሙሉ ጊዜ የኢህአዴግ ካድሬ እንደሆኑ ገመትኩኝ። ሹመኛ ካልሆኑ ማለቴ ነው። ግምቴ ከመሬት ተነስቶ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ጥላቻ በፅሁፉ ውስጥ በማየቴ ነው። ካድሬም ቢሆን እንዲ መሆን አለበት ብዬ አላምንም፣ እንዳለመታደል ሆኖ የኢህአዴግ ካድሬዎች ባህሪ የዚህ ዓይነት መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። የኢህአዴግ ካድሬም አባልም አይደለሁም ካሉ ደግሞ በጣም ያበሳጫል።

 

በፅሁፋቸው መሃልና መውጫ ላይ ህዝብ ህዝብ እያሉ ለህዝብ አሳቢ መስለው በፅሁፋቸው ሲያምታቱ መግቢያ ላይ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት የገለፁበትን እረስተውት ይመስላል። እንዲህ ይላሉ፤ "የፓርቲው አመራሮችና የሕግ ደቀ መዛሙርቶቻቸው እጅግ በጣም አሳፊሪ የሆነ አቋም እያራመዱ ናቸው።" ይልና በማስከተልም "እንዲያውም በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ፀረ ሽብር ሕጉ ይሰረዝ ከሚሉት ግለሰቦች ያልተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው እንድናውቅ ዕድሉን ሰጥተውናል።" በማለት የራሳቸውን ሊቅነትና የህዝቡን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና በሳቸው መስመር የሌሉ የሕግ ባለሞያዎችን ነውረኛ በሆነ መልኩ ይዘልፋሉ። ኢህአዴግን ደግፎ የሚወጣ ሕዝብ ሲባል፤ ተቃዋሚን ደግፎ የሚወጣ ደግሞ ግለሰቦች ነው የሚባሉት እነርሱ ሰፈር። ስንት ግለሰቦች ሲሆን ህዝብ እንደሚሆን እስከአሁን የተረጋገጠ ትርጉም የለም።

 

ወደ ዝርዝር ለመግባት ቦነያ በሰጡት ርዕስ አንፃር ሃሳባቸውን ስንመዝነው ብዙ ጉዳዮችን እንመለከታለን። ኢትዮጵያ ለሽብር ተጋላጭ ነችን? በሚለው መጠይቅ የጀመሩት ፀሐፊው ለሽብርተኝነት ተጋላጭ ለመሆን ሁለት ዋና ዋና ጭብጦችን ሰጥተውናል። አንደኛው በሀገር ውስጥ የህዝቦች ተጠቃሚነትን የማያረጋግጥ ሥርዓት መኖሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እኔ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በውስጥና በውጭ የሚኖሩ ምቀኞች (በእርሳቸው አገላለጽ ኢትዮጵያ በልማትና በዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን የማይፈልጉ ውስጣቸው የታወኩ ኃይሎች ሌት ተቀን የሚተጉላት ሀገር ነች) የሚሉ ናቸው።

 

"በአገራችን ውስጥ የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ ያለ መንግሥት እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።" በማለት የመጀመሪያው ተጋላጭነት ምንጭ ያሉትን ያመክኑታል፤ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለሽብር ተጋላጭ አደለችም ብለው። በእኔ እምነት በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት እርሳቸው እንደሚሉት የዘመናት ጥያቄ እየመለሰ ያለ መንግሥት ሳይሆን ለዘመናት የሚዘልቅ ችግር እየፈለሰፈ ያለ ነው የሚል ነው። ይህ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ በዚህ ምክንያት ለሽብር ተጋላጭ አይደለችም የሚለው መደምደሚያ ግን አንድ ዓይነት ነው። በእኛ እምነት ኢትዮጵያዊያን በእምነታችንም ሆነ በባሕላችን የመንግሥትን ሥርዓተ አልበኝነት ለማሻሻል ህዝብን በጅምላ ወደሚጨርስ የሽብር ተግባር ይገባል የሚል ግምገማ የለንም። መንግሥት በደል ካደረሰበት ህዝቡ አሸባሪ ይሆናል ብሎ መነሳትም ልክ አይደለም የምንለው ለዚህ ነው። ስለዚህ እርሶ ጥብቅና የቆሙለት ኢህአዴግ ህዝቡ አሸባሪ ሊሆን ይችላል ሲል፤ እኛ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሸባሪነት ስነ ልቦና የለውም ነው የምንለው። የሚገርሞት ሌሎች ሀገሮች የፀረ ሽብርተኝነት ሕግን ያወጡት ዜጎቻቸውን ከሌሎች የተደራጁ ሽብርተኞች ለመጠበቅ እንጂ ዜጎቻቸውን በዚህ በመጠርጠር አይደለም።

 

በሁለተኛ ደረጃ ለሽብርተኝነት ተጋላጭነት ከሚጨምሩት ጉዳዮች አንዱ የውስጥና የውጭ ምቀኞች ናቸው ብለዋል። ይህን ለሁለት ከፍሎ ማየት ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ እና የውጭ በሚል። በሀገር ውስጥ ስንጀምር በእውነት ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ኢትዮጵዊያን በልማትና በዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆን የማይፈልገው እና ውስጡ የሚታወከው ለምንድነው? የሚለውን ስንፈትሽ ይህ በእውነት የኢህአዴግ ምናባዊ ክስ እንጂ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ሊኖር አይችልም። ይህን ምናባዊ ክስ ተጨባጭ ለማድረግ ማስረጃ ካለ እንዲቀርብልን ያስፈልጋል። ይህ ግን በምንም መንገድ ተፈጥሮአዊ አይደለም። ወደ ውጪ ከመሄዳችን በፊት ግን አንድ መረዳት የሚኖርብን ነገር ይኖራል። በሀገር ውስጥ አንድ አንድ ለሆዳቸው ያደሩ ባንዳዎች እንደሚኖሩ ጠፍቶኝ አይደለም። እነርሱም ቢሆኑ ሆዳቸውን ለመሙላት ከውጪ ኃይል ጋር ሊያብሩ ይችላሉ። የባንዳ ችግር በኢትዮጵያ ዋና ችግር ነው ብዬ አላምንም። ባንዳዎችን ኢትዮጵያዊያን እንዴት እንደሚቀጡና እንደሚያስተምሩ ተሞክሮ አለን። የውጪዎቹስ ቢሆን የእኛ ሰላምና ልማት ለምን ያበሳጫቸዋል? የሚለው ሲነሳ እኔ በግሌ ማንም ሀገር ቦነያ ጠላት ብለው ያሉዋቸው ኤርትራም ሆነ ጎረቤቶች ሶማሊያ በዕድገት በዴሞክራሲ ቢያብቡ ልመቀኝ የምችልበት ሁኔታ የለም። ይልቁንም ከዚያ ከሚገኘው ትሩፋት ለእኛም ይተርፋል የሚል መልካም ነገር ነው ያለኝ። ስለዚህ እኔ ምቀኛ ስለአልሆንኩ እነርሱም ምቀኛ ናቸው ብዬ ለማሰብ አልችልም። ልዮነታችንን እዚህ ጋ ያዩት ይመስለኛል። ቦነያ የሚደግፉት ፓርቲ የሌለ ጠላት አበጅቶ ይህንን ጠላት መከላከያ የሚል አፋኝ ሕግ ያወጣል። ፀሃፊ ቦነያ እንዲረዱልኝ የምፈልገው በውስጥም በውጭም አንድ አንድ አቅላቸውን የሳቱ እብድች የሉም አይደለም። እነዚህን ለመከላከል ግን ጤነኛ አስተሳሰብ ያለንን በሙሉ የሚያፍን ሕግ ማውጣት ተገቢ አይደለም። እስከ ዛሬ ባለን ልምዳችን ስንት የሻዕቢያን ቡድን እንደያዘ የገለፀልን ነገር የለም። ዝም ብሎ የሻዕቢያ ተላላኪ ከሚለው ክስ በስተቀር።

 

ቦነያ በፅሁፋቸው "... የህዝብ የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና ሌሎች ፍሬዎችን ተመጋቢነት ማረጋገጥ ሳይሆን፤ የግል የሥልጣን ጥማት በሽታቸውን ለማሳካት ሽብርተኛ ወይም ደግሞ የሽብርተኛ ድርጅት መሳሪያዎች የሆኑ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አሉ።" ይላሉ። ልክ ነው ሚዛኑ በራስ ነው። እርሶ አሁን የሚያገኙትን ሥልጣንም ይሁን ጥቅም ለማስጠበቅ ስለሚያጎበድዱ ሁሉም እንደ እርሶ ሊመስልዎት ይችላል። ሌላው ልክ ነገር አሁን ያለው ገዢ ፓርቲ የሥልጣን ጥሙ ስላልረካለት፤ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የተጋነነ የሽብር ወሬ በመንዛት ዜጎችን ያሸብራል። ለያዘው ሥልጣን ተቀናቃኝ ይሆናሉ የሚላቸውንም በሽብርተኝነት ስም ያስራል፤ ያንገላታል። ማወቅ ያለቦት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሥልጣን እንደሚወዳደሩ ሚስጥር አይደለም፣ ሥልጣኑን የሚፈልጉት ለሻዕቢያ ተቀጥረው ነው ማለት ግን ስድብ ነው። ሁሉንም በተበላሽ የራስ ሚዛን ማየት ተገቢ አይደለም። ቅድሚያ ሚዛኑን ማሰራት ነው።

 

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ፖለቲካዊ ዓላማ አለውን? የሚል ተገቢ ጥያቄ ጠይቀው ተገቢ ምላሽ ሳይሰጡ ዘለውታል። በእኔ እምነት የፀረ ሽብር ሕጉ ዋነኛ ዓላማው ፖለቲካዊ ነው። ሟች የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በ2003 መጀመሪያ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ "ስጋታችሁ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ይውላል የሚል ነው። ይህ ስጋት ብቻ ነው" ብለው ነበር። ይህ ስጋታችን ግን ጥቂትም ሳይቆይ በሰሜን አፍሪካና በዐረብ ሀገራት በተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ ወደ ሀገራችን ይገባል በሚል ስጋት ለሰላም የሚዘምረውን ወጣት ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌን እና ሌሎችን ለእስር ዳረገ። አንድ ጥያቄ ልጠይቆት አንዱዓለም ሽብር ሊፈፅም ማሰቡን በደም ምርመራ ተረጋግጦዋል? በእኔ እምነት በአንዱዓለም ላይ ሽብር ሊፈፅም ነው የሚል ማስረጃ አልቀረበም። የቀረበው ማስረጃ የእናት የአባቱ ልጅ (ወንድሙ) የት እንደሚገኝ በማኅበራዊ ድረ ገፅ ላይ ጠየቀ፤ በእጅ ስልኩ ላይ ከግንቦት ሰባት እንኳን አደረሰህ መልዕክት ደረሰህ (እንኳን አብሮ አደረሰን ብሎ መልስ ሳይሰጥ) የሚሉ ብቻ ናቸው። በዚህ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት ተባልን። በእጅ ስልካችን የማንፈልገው የማይመለከተን ስንት መልዕክት ይደርሰናል ጎበዝ። በእነ አንዱዓለም ፋይል ፍርድ ቤት ለምስክርነት ቀርቤ በእጅ ስልኬ የማልፈልገው መልዕክት ይደርስሃል ወይ? ተብዬ ተጠይቄ ነበር። የሰጠሁት መልስ አዎ! የሚል ነበር። ከየት ሲለኝ ለምሳሌ ከቴሌ ብዬ መልሻለሁ። በጅምላ ስልክ መላኪያ ዘመን ለሙስሊም ወንድሞቻችን እንኳን ለገና/ለጥምቀት በዓል አደረሳችሁ። እኛም እንደዚሁ ኢዴ ሙባሪክ እንባላለን። እስኪ እውነቱን እንነጋገር ስንት የኢህአዴግ አባላት የግንቦት ሰባት መልዕክት ይደርሳችሁዋል? እንዲሁም ስንት የግንቦት ሰባት አባላት የግንቦት ሃያ መልዕክት ይደርሳችሁል? ብለን እንጠይቅ። ቦነያ ፍርዱን ለእርሶ ትቼዋለሁ። ለማንኛውም የሞባይል ስልኮትን ይፈትሹት።

 

ወደ መጨረሻም ሕጉን የሚፈሩት ጠላቶች የተባሉት (እኛንም ይጨምራል) "የኢትዮጵያን ህዝብን ጥቅም ለማስከበር ካላቸው የደረሰ ቅንነት ሳይሆን አገሪቱን የደም እንባ ለማራጨት የሚፈልጉ በመሆናቸውና ሕጉ ይህን እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማስቀመጡ ነው።" ይሉናል። እኔ በግሌ ኢህአዴግ/መንግሥት ህዝብን የደም እንባ ማራጨት ስለሚፈልግ የሚል አቋም የለኝም። ሥልጣኑን የሚቀናቀኑትን ለማፈን ይጠቀምበታል ነው የምለው። በአጋጣሚው ደም ይፈሳል። እርሶ ባሉት ልክ ፍላጎት ካለን መንግሥት ለምን ፓርቲውን አይዘጋም? ሕጉ ደግሞ ብዙ መመርመሪያ መንገድ ስለሚፈቅድ መርምሮ ለምን እነዚህ ጥቂት የሚባሉ ሰዎችን ወህኒ አያወርድም? እንዲህ ዓይነት እኩይ አስተሳሰብ በጣም ያሳዝናል። ቦነያ የሕግ ባለሞያ ነኝ፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆነ መስሪያ ቤት ሰርቻለሁ ያለትን ሳስበው፤ እርሶ ያዘጋጁት የነበረው አቅጣጫ ተከትሎ ለሰራው መስሪያ ቤት አዘንኩለት። ለነገሩ ይህች ሀገር በእናንተ እጅ ወድቃ ነው በእንደዚህ ሁኔታ የምንገኘው። እርሶ በሚሰሩበት መስሪያ ቤት ጉዳይ ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንዴት ሊመለከቱት እንደሚችሉ ሳስብ ዘገነነኝ። የደም እንባ ሊያራጭ የተቋቋመ ፓርቲ አባል አይተው ደሞ ሲንተከተክ ጭምር። ኧረ! በኢትዮጵያ አምላክ እንደዚህ ካለ ጭፍን አመለካከት እንውጣና የሰለጠነ ፖለቲካ እንጀምር፤ የኢህአዴግ መሪዎች ይህንን መተማመን የሚጎዳን አካሄድ ለጊዚያዊ ጥቅም ስንል ማድረግ እንደሌለብን ደጋፊዎቻችሁን ማስረዳት ያለባችሁ ይመስለኛል። በምን መመዘኛ ነው እኔ የደም እንባ ሉያራጭ የተቋቋመ ፓርቲ ውስጥ አባል የምሆነው። በምንስ መመዘኛ ነው እኔ ለውጭ ኃይል ተላላኪ የምሆነው። ኧረ! ጎበዝ እየተስተዋለ።

 

ለማጠቃለል አንድነት ፓርቲ የፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ትግሉን ይቀጥላል፣ በዚህ ምክንያት የታሰሩ የሰላም ዘማሪዎችም አርበኞቻችን ነፃ እንዲሆኑ እንታገላለን። ለመረጃ እንዲሆኖ የሕገ መንግሥት ጥሰት ነው የምንላቸውን አንቀፆች ከፈለጉ የሕግ ባለሞያዎቻችን እንዲያውቁት ጥረት ይደረጋል። ከታገሱ ደግሞ በዝርዝር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲቀርብ ይፋ ይደረጋል። በተደራጀ መልክ።

 

ቸር ይግጠመን!! መጪው ዘመን ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥተን ዘመናዊ ፖለቲካ የምንጀምርበት እንዲሆን ምኞቴ ነው። ፈጣሪ ይርዳን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ