ታምሩ ገዳ

አቡነ ፍራንሲስ በሕዝብ መሃል በመኪና ሲያልፉ ሕፃን ልጅ ተቀብለው ሲስሙ

በየትኛውም የእድገት ደረጃ ይሁን የፖለቲካ አመለካከት ወይም የሃይማኖት ስርአት ውስጥ ለሚገኝ ማህበረሰብ ሁነኛ መሪ ማግኘት ከእድሎች ሁሉ ትልቁ እድል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አይደለምም።

 

 

አቡነ ፍራንሲስ
አቡኒ ፍራንሲስ 


ለዚህ ይመስላል የሮማ ካቶሊክ ቤ/ክርስቲያን በቀርቡ 266ኛዋን መሪ (ፓፓ) ለመምረጥ የሃይማኖቱ አባቶች በቫቲካን ከተማ በተሰባሰቡበት ወቅት በ150,000ዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ቀጣዩ የሃይማኖታችን አባት ማን ይሆኑ? በማለት የምርጫው ውጤቱን ለማወቅ በታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰባስበው የነበረው። በዚህ የመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተካሄደው የመጪው የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አባት መረጣ ላይ የብዙዎቹ ምርጫ ሆነው የቀረቡት ከ120 ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮች ያሏት አገር ብራዚል ከሳኦ ፖሎ ከተማ የመጡት አርክቢሾፕ ኦዲሎ ሺረር ነበሩ። ለምን? ቢባል አርክ ቢሾፕ ኦዲሎ በቫቲካን ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ መነኮሳት ዘንድ ቀረቤታ ያላቸው አባት በመሆናቸው ነበር። ይሁንና የምርጫው ስነስርአት ሲጠናቀቅ አባ ጆርጁ ቤርጎባሌዮ የ1.2 ቢሊዮን ህዝብ (በአለማችን ላይ ያለው የካቶሊክ አማኞች ቁጥር) አባት ናቸው የሚለው ዜና ሲሰራጭ በዙዎች አባ ጆርጁ ቤርጎባሌዮ ወይም አባ ፍራንሲስ ማናቸው? የሚለው ጥያቄን መጠየቅ ጀመሩ። የብጹነታቸውን ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁት በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ አዲስ አባት አገኘን (we have a Pope!) ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል። ለወትሮው ፓፓው ለህዝቡ የሚጸልዩት ወይም ህዝቡን የሚባርኩት እርሳቸው ሲሆኑ በአሁኑ ግን እርሳችው ለተሰብሳቢው ህዝብ "እባካችሁ ጸልዩልኝ!" ሲሉ ተማጽነዋል።


ላለፉት ስምንት አመታት በፓፓነት ማእረጋቸው ሲያገለግሉ ቆይተው በህመም ምክንያት በቅርቡ ስልጣናቸውን በፍቃደኝነት የለቀቁት አቡነ ቤኔዲክት 16ኛውን በመተካት ስልጣኑን የተረከቡት አቡነ ፍራንሲስ አባታቸው ጣሊያናዊ የባቡር ላይ ሰራተኛ ሲሆኑ፣ የፋሺስቱን አገዛዝ በመሸሽ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ ፍሎረንስ በተባለች አነስተኛ አካባቢ መኖር ጀመሩ። ልጃቸው አቡነ ፍራንሲስ በ1936 እኤአ እዚያው አርጀንቲና ውስጥ ተወለዱ። ለድሆች እና ለተፈጥሮ ሃብት ተቆርቋሪ ከነበሩት ከቅዱስ ፍራንሲስ (ከሃብታም ቤተሰብ ተወልደው ስለድሆች እና ጭቁኖች መብት መከበር ሲሉ በሮም ጎስቋላ ስፍራዎች ከመጻጉዎች እና ከድሆች ጋር ይኖሩት ከነበሩት የኦሲሱ ቅዱስ ፍራንሲስ ናቸው) መጠሪያ ስያሜ ያገኙት አዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባት የሆኑት ብጹነታቸው ለድሆች ደህንነት እና እኩልነት የሚሟገቱ ታላቅ አባት እንደሆኑ ብዙዎች ይመስክሩላቸዋል።


አባ ፍራንሲስ በብዙ መልኩ ከቅንጦት እና ምቾት ካለው አለማዊ ኑሮ ይልቅ ዝቅተኛ የሆነ (ሎው ፕሮፋይል) የሚመርጡ ሲሆኑ፣ እነዚህ ምልካም ተግባሮቻቸው መካከል በቅዳሴ ጊዜ በአለማዊ ሰዎች ዘንድ ከተዋረዱት በእግዚአብሔር ፊት ግን እኩል ከሆኑት በቦይነስ አይረስ ከተማ ከሚገኙ የቀድሞ ሴተኛ አዳሪዎች ጋር አብረው በመጸለይ የሃይማኖታዊ አባትነታቸውን እና አርኣያነታቸውን አሳይተዋል። ከዚያም አልፎ ለስልጣነ ክህነታቸው ሲባል ለግላቸው የተመደበላቸውን ዘመናዊ ሌሞዚን መኪና ከእነ ሹፌሩ እርግፍ አድርገው በመተው (ሹፌሩን በማሰናበት) እራሳቸው በህዝብ የማመላለሻ አውቶቡስ በመገልገል የድሃው ህዝብ አካል መሆናቸውን አስመስክረዋል።

 

ወደእኔ ይመጡ ዘንድ ህጻናትን አትከልክሏቸው፣ አባ ፈራንሲዮስ ህጻን ልጅ ሲስሙ
ወደእኔ ይመጡ ዘንድ ህጻናትን አትከልክሏቸው፣ አባ ፈራንሲዮስ ህጻን ልጅ ሲስሙ


በአጠቃላይ አኗኗሯቸው ቀለል ያለ ኑሮን የሚመርጡት ብጹነታቸው ላቲን አሜሪካ ካፈራቻቸው የመጀመሪያው የሮማ ካቶሊክ ፓፓ ሲሆኑ፣ የእርሳችው መመረጥም በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ላላፉት 1300 አመታት ከአንድ አካባቢ (ከአውሮፓ ብቻ) ይመጣ የነበረው የፓፓነት ስርአትን በመለወጥ ፋኖ ወጊ ሆነዋል። ለዚህ ይመስላል በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በእስያ የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንዲሁም በርካታ የሀገር መሪዎች የብጹነታቸው ምመረጥን (viva il papa!!) በማለት እንደ ታላቅ ድል የቆጠሩት። ብዙዎችም ፓፓው ድህነትን በማስወገድ ዘመቻ እንዲሳተፉ ተማጽነዋቸዋል። ምንም እንኳን ብጹዕነታቸው በግላቸው ለምእመናኑ እና ለድሃው ህዝብ ቅርብ የሆኑ መንፈሳዊ አባት ቢሆኑም፤ የትውልድ ሀገራቸው አርጀንቲና በ1970ዎቹ እኤአ በነበረው ወታደራዊ ጁንታ ሳቢያ አገዛዙን በመቃወማቸው ብቻ ህይወታቸውን ላጡ ከ30,000 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ቤተክርስቲያኒቱ ተቃውሞዋን አላሰማችም የሚል ብርቱ ወቅሳ ቀርቦባታል። ይህንንም ወቀሳ በተመለከተ አቡነ ፍራንሲስ በ2010 እኤአ በአርጀንቲና ውስጥ ለሚታተም አንድ ጋዜጣ በሰጡት ሰፊ አስተያየት እርሳቸው ሰዎች እንዳይታሰሩ ሙያቸውን በመቀየር እንዲደበቁ ወይም ሀገራቸውን ጥለው እንዲሄዱ በማድረግ የታሰሩትም እንዲፈቱ በመሟገት የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን በመግለጽ ውንጅላውን አስተባብለዋል።

 

የቀድሞው ፓፓ አቡነ ቤኔዲክት 16ኛው (በግራ) ይቀመጡበት የነበረው ቦታ ላይ አዲሱ ፓፓ አቡነ ፍራንሲስ (በቀኝ) ተቀምጠዋል፤ ልዩነቱን ይፈልጉ!
የቀድሞው ፓፓ አቡነ ቤኔዲክት 16ኛው (በግራ) ይቀመጡበት የነበረው ቦታ ላይ አዲሱ ፓፓ አቡነ ፍራንሲስ (በቀኝ) ተቀምጠዋል፤ ልዩነቱን ይፈልጉ!


ቀደም ባሉት ጊዜያት በአንዳንዳንድ ምግባረ ብልሹ ካህናት የተነሳ ከሙስና አንስቶ ጨቅላ ህጻናትን የመድፈር እና መሰል ክሶች የቀረቡባት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቤቷ ውስጥ የተጋረጡት ችግሮችን ለመቅረፍ የአቡነ ፍራንሲስ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ በአባትነት መምጣት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም፤ አባጣ ጎባጣ የሆኑ መንገዶችን ለመጥረግ ብርቱ ፈተናዎች ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። የብጹነታቸው የግል ታሪክ ፀሐፊ የሆኑት ሴርጆ ሩቤን ስለአዲሱ ፓፓ ባህሪ ሲገልጹ "በእሁኑ ወቅት በለውጥ ጎዳና ላይ ያለን ይመስለኛል። ይህ ሁኔታ ግን ቀላል አይደለም። ብጹነታቸው ቤተክርስቲያኒቱ ወደ አደባባዮች (ጎዳናዎች) መውጣት ስትችል ብቻ ነው የህዝቡን ችግር መረዳት የምትችልው ብለው ያምናሉ (poor Church for the poor)።" ሲሉ ተናግርዋል።


በደግነታቸው እና በእውነተኛ ርህራሄያቸው በበርካታ የካቶሊክ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና ያገኙት አቡነ ፍራንሲስ የፓፓነቱን ስልጣን ከያዙ በሁዋላ እንኳን ያ ደግነት የተላበሰ ባህሪያቸውን ባለመለወጥ ሰሞኑን ከእርሳቸው ጋር ለሚኖሩ ካህናት እራሳቸው ምግብ አብስለው በማዘጋጀት እራት እንዲቋደሱ አድርገዋል። አርፈውበት በነበረ አንድ ሆቴል ውስጥም ለተስተናገዱበት ወጪ ከገዛ ኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት ከዚህ ቀደም የነበረውን የቀይ ምንጣፍ እና ልዩ መስተንግዶ ባህልን ወደጎን አድርገውታል።

 

አቡኒ ፍራንሲስ የሆቴል ሂሳባቸውን ሲከፍሉ
አቡኒ ፍራንሲስ የሆቴል ሂሳባቸውን ሲከፍሉ


ብጹነታቸው ባለፈው አርብ ጠዋት ላይ በቫቲካን ከተማ ከሚገኙ የዝቅተኛው ማህበረሰብ ክፍል ከሆኑት (ብሉ ኮላርስ) እየተባሉ ከሚጠሩት የቤተመንግስታቸው አትክልተኞች እና የጽዳት ሰራተኞች ጋር በጋራ በመሆን የህብረት ጸሎት ያደረሱ ሲሆን፣ በስተመጨረሻም እያንዳንዱን ሰራተኛ በግል አነጋግረዋል። ለወትሮው ለጳጳስ ወደ ተዘጋጀው የክብር መቀመጫ ከመሄድ ከምእምናን በስተሁዋላ በመቀመጥ እንደተራው ምእመናን ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ የጋራ ጸሎት አድርገዋል። ሰሞኑን ምእራባዊያኖች ባከበሩት የ40 ቀናት እና 40 ሌሊት ጾም (የሁዳዴ ጾም) ክፍል አንዱ የሆነው ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን ራት (Lord's Supper) የበላበት እና የሐዋሪያቶቹን እግር በማጠብ እነርሱም የእርሱን አርኣያነት እንዲከተሉ ትህትናውን ዝቅ ብሎ ያሳየበትን ምእራፍ በማስታውስ ብጹነታቸው ካሳል ዴል ማርሞ (Casal del Marmo) በተባለ የወጣት አጥፊዎች እስር ቤት በመሄድ ከሕግ ታራሚዎቹ ጋር አብረው እንደሚያሳልፉ ከቫቲካን የወጣው መግለጫ ያመለክታል።

 

 አቡነ ፍራንሲስ ከምእመናን ኋላ ተቀምጠው
 አቡነ ፍራንሲስ ከምእመናን ኋላ ተቀምጠው


የቤተመንግስት ነገር ከተነሳ ከላይ እንደተገለጸው ቀላል ኑሮን ዘወትር የሚመርጡት ብጹዕነታቸው አሁንም ወደ ቫቲካን ተዛውረው "በቢልዮን የሚቆጠረው ምእመናን አባት በመሆንዎ ለክብሮት ሲባል የቀድሞው የአቡነ ቤኔዲክት 16ኝውንና የቀደምት አባቶች ቤተመንግስትን ይረከቡ" ሲባሉ አሻፈረኝ በማለት፤ በፓፓው ምርጫ ሰሞን እዚያው ቫቲካን ውስጥ አርፈውበት በነበረው ባለ ሁለት ክፍል ሆቴል ውስጥ ለጊዜው መቀመጥን መምረጣቸው ተነግሯል። ይህ ማለት ቤተመንግስቱን ሙሉ በሙሉ አይጠቀሙሙበትም ማለት ሳይሆን ከመደበኛ ስራዎቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት እንግዶችን ለመቀበል፣ ስብስባዎችን ለማካሄድ ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ጎራ ማለታቸው አልቀረም። አብዛኞቹ ባለስልጣናት ስልጣን በያዙ ማግስት ዘመድ አዝማዶቻቸውን ለመጥቀም ሲሯሯጡ ወይም ቀደም ሲል አስቀይመዋቸው የነበሩ ወገኖችን ለማባረር አሊያም ከእነአካቴው ለማጥፋት ላይ ታች በሚሉበት አሁን ባለንበት በ21ኛው ክ/ዘመን፤ በየትኛውም ጎራ ይሁኑ በየትኛውም ስፍራ እንደ አቡነ ፍራንሲስ የመሰለ መንፈሳዊ አባት ማግኘት ለሃይማኖቱ ተከታዩች ብቻ ሳይሆን እምነት ለሌላቸውም (አለማውያንም) ቢሆን ጥሩ አርኣያ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።


ታምሩ ገዳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ