አማኑኤል ዘሰላም
ምንጩ ሳውዲ አረቢያ የሆነው፣ ከነዳጅ በሚገኝ ሚሊዮን ዶላሮች የሚደገፈውና መረቡን በአለም ዙሪያ ሁሉ የዘረጋው፣ የዋሃቢዝም የእስልምና አክራሪነት፣ በአለማችን ትልቅ ችግር እየፈጠረ በብዙ አገሮች አለመረጋጋትን ያመጣ እንደሆነ፣ የአለምን ሁኔታ በቅርበት የሚከታታል ያጣዋል ብዬ አላስብም።

 

አል ሻባብ፣ አል ካይዳ፣ አንሳር አሊዝላም ፣ ቦካ ሃራም የመሳሰሉ ጸረ-ሰላምና ሽብርተኛ ቡድኖች መሰረታቸው፣ ይሄው ዋሃቢዝም ነው። ዋሃቢስቶች፣ እንኳን ከእስልምና ውጭ ያሉ እምነቶችን ሊታገሱ ቀርቶ፣ ከነርሱ የቁራን አተረጓገም የተለየ አተረጓገም ውጭ፣ ቁራንን የሚተረጉሙ ሌሎች ሙስሊሞችን ሳይቀር አይቀበሉም። ከነርሱ አመለካከትና እምነት ውጭ ያሉ የሌላ እምነት ተከታዮች በሙሉ፣ እነርሱ ትክክለኛ ወደሚሉት እስልምና ካልመጡ በቀር «መጥፋት አለባቸው» ብለው የሚያምኑ ናቸው።

 

ሳውዲ አረቢያ፣ የእስልምና ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች (መካና መዲና) ያሉባት አገር ናት። የሳውዲ ሙፍቲም፣ ፖፑ ለካቶሊኮች እንደሆኑት፣ ለሱኒ ሙስሊሞች መንፈሳዊ አባት ናቸው። በቅርቡ እኝህ ዋሃቢስቱ የሳውዲ አረቢያው ሙፍቲ የተናገሩት፣ ስለዋሃቢዝም ምንነት በግልጽ የሚያመላክት ነው። «በአካባቢያችን ቤተ ክርስቲያን መሰራት የለበትም። የተሰራም ካለ ደግሞ መፍረስ በማለት ነበር ከዋሃቢዝም እስልምና ውጭ ሌላ እምነትን ማስተናገድ እንደማይችል በግልጽ ያሳወቁት።

 

ከሁለት አመታት በፊት በወጣቶች እንቅስቃሴ የተነሳው የግብጽ አብዮት፣ ሙባረክ ከስልጣን እንዲነሱ አደረገ። ዋሃቢዝምን መመሪያው ያደረገው የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት፣ በየመስኪዶቹ ስለተደራጀ በቀላሉ ምርጫውን አሸነፈ። ሞርሲ የአገሪቷ ፕሬዘዳንት ሆኑ። አዲስ ሕገ መንግስት የመጻፍ ስራ ተጀመረ። ሕገ መንግስቱ ከሻሪያ ጋር የተገናኘ እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጀ። ክርስቲያኖችና አክራሪ ያልሆኑ ሙስሊሞች ተቃወሙ። ሞርሲ ግን እስልምናን የበላይ የሚያደርግ፣ ለሌሎች እምነቶች እውቅና የማይሰጥ ሕገ መንግስት አስጸደቁ። ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ክርስቲያኖች ባሉባት ግብጽ፣ የእስላማዊ መንግስት ተቋቋመ። ከሙባረክ አምባገነንነት ግብጽ ወደ እስልምና አክራሪነት ተሸጋገረች። የበጋው አብዮት ወደ ክረምት ጭጋግ ተቀየረ። ከእሳት ወደ ረመጥ ይሉታል ይሄ ነው።

 

በኢትዮጵያ የእስልምና መንግስት በኃይል ለማቋቋም የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ አውጥተው፣ በሳውዲዎችና ግብጾች ተረድተው፣ በነርሱም ሰልጥነው፣ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ዋሃቢስቶች አይኖሩም ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። እነዚህን አክራሪዎችን ተከታትሎ፣ የገንዘብ ምንጫቸውን አድርቆ፣ አክራሪነት እንዳይስፋፋ የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ መወጣት፣ ከማንም መንግስት የሚጠበቅ ነው። በዚህ ረገድ የአገሪቷን ሕግ ተከትሎ አክራሪነትን ለመከላከል የሚደረግ ማናቸውም አይነት እርምጃን አልቃወምም።

 

ነገር ግን አክራሪነትን ለመዋጋት በሚል ሽፋን፣ የበለጠ አክራሪነትን የሚያስፋፋ፣ ለአገር የማይጠቅም፣ የአገሪቷን ሕግ የማያከብር ተግባራትን መፈጸም ግን፣ እያንዳንዱን ዜጋ ሊያሳስብና ሊያስቆጣ የሚገባ ነው።

በአገራችን በሙስሊሞች መካከል በተፈጠረው ችግር አማካኝነት፣ የተወሰኑ ወገኖች በሽብርተኝነት ክስ መታሰራቸው ይታወቃል። የነዚህን ወገኖችን መታሰር ተከትሎ ፣ ከዚህ በፊት ለአንባቢያን ባቀረብኩት ጽሑፍ ፣ የሚከተለውን ምክር ለኢሕአዴግ አመራር አባላት አቅርቤ ነበር።

 

«በመስኪዶች ሰላማዊ ተቃውሞ ማሰማት፤ የመጅሊስ አመራሮች እንዲለወጡ መጠየቅ «ሽብርተኛ» ሊያሰኝ አይገባም። በመሆኑም ከሳውዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸውን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸው፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። እነርሱን በማሰር የሚገኝ አንዳች ጥቅም የለም። ዜጎች ተቃውሞ ስላሰሙ የሚታሰሩበት አሰራር መቆም አለበት። ኢሕአዴግ በዚህ አንጻር ከኃይል እርምጃዎች ተቆጥቦ ማስተዋል ያለበት እርምጃ እንዲወስድ እመክራለሁ»

 

በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አንድ ዘገባ አቀረበ። የቀረበው ዘገባ፣ የኢቲቪ ሪፖርተሮች፣ በታሰሩ ወገኖች ላይ የቀረበውን የፍርድ ቤት ሂደት ተከታትለው የዘገቡት ዘገባ አልነበረም። በፍርድ ቤት የቀረቡ ሰነዶችን አላነበቡም። ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ አልገለጹም። ነገር ግን እጆቻቸው በካቴና ከታሰሩ እስረኞች ጋር፣ በእሥር ቤት የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ነው ያቀረቡት።

 

እስረኞቹ ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ። አስቀድሞ ተጽፎ እንዲናገሩ የተሰጣቸው ይሁን እውነቱን ለማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም እስረኞቹ የተናገሩትን ይዘን፣ «እንዲህ ነው» ወይም «እንደዚያ ነው» ልንል አንችልም።

 

ይልቅስ ብዙዎቻችንን ያሳሰበና ያሳዘነ ጉዳይ ቢኖር እስረኞቹ በመጀመሪያ ደረጃ በቴሌቭዥን እንዲናገሩ መደረጉ ነው። ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ወቅት፣ አስቀድሞ በፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚገባን ነገር በሜዲያ ማውጣት፣ ሂደቱን የፍርድ ሂደት ሳይሆን የፖለቲካ ሂደት አድርጎታል።

 

የአገሪቷ ሕገ መንግስት ፍርድ ቤቶች ነጻ እንደሆኑ ይደነግጋል። ነገር ግን ኢቲቪ ያቀረበው ፕሮግራም በቀጥታ የፍርድ ሥርዓቱን የሚንድ ሆኖ ነው የተገኘው። የዜጎችን ሕገ መንግስታዊ መብቶች የሚጋፋ፣ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሰጥ በፍርድ ቤት ሥራ ላይ ጣልቃ የሚገባ ጎጂ ተግባር ነው።

 

የታሰሩ ወገኖች ጥፋተኛ ይሁኑ አይሁኑ ገና ፍርድ ቤት አልወሰነም። ፍርድ ቤት እስካልወሰነ ድረስ ማንም ወንጀለኛ ጥፋተኛ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። ኢቲቪ እነዚህን ሰዎች አቅርቦ ኑዛዜ ማናዘዙ በሕግም ሆነ በሞራል አንጻር ተቀባይነት የሌለው፣ ኢሕአዴግን እንቃወማለን የሚሉ ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግን የሚደግፉ ሁሉ ሊያወግዙት የሚገባ ነው። አንድ በሉ!

 

እነዚህ እስረኞች በኢቲቪ ቀርበው ቃለ መጠይቆችን ሲሰጡ፣ ጠበቆቻቸው በአካባቢው አለመኖራቸውን መርሳት የለብንም። ሕገ መንግስቱ ዜጎች የጥብቅና መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ዜጎች በፍርድ ቤትም ሆነ በፖሊስ ፊት ሲቀርቡ ከጠበቆቻቸው ጋር የመመካከር፣ ጠበቆቻቸውም በነርሱ ስም ምላሽ እንዲሰጡ የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ኢቲቪ ከማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር፣ ጠበቃዎቻቸውን አልፈው፣ በአቋራጭ እስረኞችን ማናዘዛቸው ትልቅ ስህተት ነው። ሁለት በሉ!

 

«እስረኞቹ ቃለ መጠይቆች ሲሰጡ በውዴታና ነው ወይንስ ተገደው ?» ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል። «እስረኞቹ ድብደባና ስቃይ ስለበዛባቸው ነው ባለስልጣናቱ መስማት የሚፈልጉት የተናገሩት» የሚሉ ወገኖች አሉ። እስረኞች መደብደባቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ባይኖርም፣ አለመደብደባቸውንም የሚያሳይ መረጃ የለም። በመሆኑም በዚህ ረገድ ኢሕአዴግ ግልጽ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል። ሶስት በሉ!

 

እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ነው፣ ኢሕአዴግን እንደግፋለን የሚሉ ወገኖች፣ በሚደግፉት ድርጅት አመራር አባላት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ የሚከተሉትን ነጥቦች የማስቀምጠው።

  1. በኢቲቪ የተላለፈው ፕሮግራም እንዲቀናበርና እንዲተላለፍ መመሪያ የሰጡ ባለስልጣናት፣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሊጠየቁ ይገባል። ኢሕአዴግ ሃላፊነት የሚሰማው እንደሆነ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ሲናገሩ እንሰማለን። እንግዲህ ሃላፊነት ከሚሰማው ድርጅት የሚጠበቀው ለተሰሩት ስህተቶችና ጥፋቶች የአመራር አባላቱ ተጠያቂ ሲሆኑ ነው።
  2. የታሰሩ እስረኞች በኢቲቪ ሆነ፣ ጠበቆቻቸው በሌሉበት፣ የተናገሩት ሁሉ በፍርድ ቤት እንደ መረጃ እንዳይቀርብ፣ ከጠበቆቻቸው ጋር ያለ አንዳች ገደብ እስረኞቹ መገናኘት እንዲችሉ መደረግ አለበት።
  3. ከሳውዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ የዋሃቢዝም አክራሪነትን ማስፋፋታቸውን የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘባቸው፣ በአዋሊያና በመስኪዶች ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ፣ ሰላማዊ ሙስሊም ወገኖቻችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ያሉት ችግሮች በሙስሊሞቹ በራሳቸው እንዲፈታ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ቅንነት ያለበት ንግግር ብቻ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጠው።

 

ዜጎችን በማሰር፣ ዜጎችን በቴሌቭዥኝ በማዋረድና በማሳነስ አገር አትለማም። ዜጎች ጥፋተኛም ቢሆኑ የሰብአዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል። የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ከኢሕአዴግ አመራሮች መመሪያ ተቀብለው፣ የሚደግፉት ድርጅታቸው በሚያደርጋቸው መልካም የልማት ተግባራት እንድንተባበር እንደሚገፋፉን ሁሉ፣ ድርጅታቸው የሚያደርጋቸውን ጎጂና አሳዛኝ የሰብአዊ መብት ረገጣን በአስቸኳይ እንዲያቆም በመጠየቅ፣ በአመራር አባላቱ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

 

በዚህ አጋጣሚ የኢቲቪን አሳዛኝ ዘገባ እንደመሳሪያ በመጠቀም፣ ጉዳዩ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ሳይሆን የኃይማኖት ጉዳይ እንደሆነ ለማቅረብ የምንሞክር ካለን፣ ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ነው እላለሁ። በኃይማኖት ጉዳይ ላይ «እንደዚህ ነው እንዲዚያ ነው» ብሎ፣ ለጊዚያዊ ትንሽ የፖለቲካ ትርፍ ብለን፣ የሚገነባ፣ የሚያስታርቅና የሚያቀራርብ ሳይሆን፣ ነገሮች የበለጠ ወደ ከረረ ሁኔታ የሚወስድ እንቅስቃሴ ባናደርግ መልካም ነው። ከገዢው ፓርቲ ጋር ችግር ስላለን ብቻ፣ ከተቀጣጠለ ሊበርድ የማይችልን እሳት ባንለኩስ ይሻላል።

 

ኢሕአዴግን የምንቃወምበትና የምናወግዝበት ብዙ የተጨበጡ ምክንያቶች አሉ። እስከሚገባኝ ድረስ ግን ላለፉት 20 አመታት ኢሕአዴግ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መልካም በማድረግ እንጂ የእምነት ነጻነትን በመጋፋት አይታማም። ኢሕአዴግ የኃይማኖት ነጻነትን የተጋፋ አይመስለኝም። በኢሕአዴግ ዘመን፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነው መስኪዶችን የገነባው። ከሃያ አመታት በፊትና እና አሁን በአዲስ አበባ ብቻ ያሉትን የመስኪዶች ቁጥር ማወዳደሩ ብቻ ይበቃል። ሙስሊሞች በታላቁ ስታዲየም በፈለጉበት ወቅት ተሰባስበው ለመስገድና ለመጸለይ የተከለከሉበት ጊዜ የለም። የፈረሱ፣ የተቃጠሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉት፣ የተዘጋ ፣ የፈረሰ ወይንም የተቃጠለ አንድም መስኪድ የለም። ተቃውሞዎች ስናቀርብ፣ በተቻለ መጠን እውነትን ይዘን ብንቃወም ጥሩ ነው።

 

በነገራችን ላይ ፣ ኢቲቪ ያቀረበው አሳዛኝ ድራማ በሙስሊሙ እስረኞች የተጀመረ አይደለም። ከዚህ በፊትም አኬልዳማ የተሰኘ አሳዛኝ ድራማ ቀርቦ እንደነበረ መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ኃይማኖትን ከዚህ እናውጣ። ጥያቄው የኃይማኖት ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው የሕግ፣ የሞራልና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነው።


አማኑኤል ዘሰላም
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ