አቶ በረከት በሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ላይ
ግርማ ካሳ
አቶ በረከት ስምኦን አገር ውስጥ ለሚታተም የሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡትን አስተያየት አውራምባ ታይምስ ድህረ ገጽ ላይ ተለጥፎ አነበብኩት። የተለዩ በረከት ስምኦንን አላነበብኩም። ያው ድሮም የምናውቃቸው በረከት ስምኦን ናቸው፤ ብስለትና ትህትና የጎደላቸው፣ በሚቃወሟቸው ወገኖች ላይ የሚያከሩ።
ከመድረክ ጋር አብሮ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ አቶ በረከት ሲጠየቁ የመለሱት መልስ ብዙም አላስደሰተኝም። «አመጽን በግማሽ ልቡ የሚመኝና የሚሰብክ» ሲሉ መድረክን ይከሳሉ። መድረክ የመቻቻል ፖለቲካን የሚፈልግ ከሆነ፣ ለመቻቻል የሚያስፈልግ ቅድመ ሁኔታን ማሟላት እንዳለበት ይናገራሉ። «የድርድር ኳሱ ያለው በኢሕአዴግ ሳይሆን በመድረክ ሜዳ ነው» ይሉናል አቶ በረከት።
ቅድመ ሁኔታ የሚሉት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጡትም ፣ «መድረኩ የስነ መግባር ኮድ ተብሎ የሚታወቀውን መፈረም አለበት» ማለታቸው ሊሆን እንደሚችል እገመታለሁ።
በመኢአድ፣ እዴፓ፣ ኢሕአዴግ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ከሶስት አራት አመታት በፊት በተፈረመው እና የአገሪቷ ሕግ ሆኖ በፓርላማ በጸደቀው የስነ-ምግባር ኮድ መሰረት፣ የተቋቋመ የፓሪቲዎች ምክር ቤት አለ። ከዚህ የፓርቲዎች ምክር ቤት ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር ብቻ ኢሕአዴግ ለመወያየት ዝግጁ እንደሆነ አቶ በረከት ይናገራሉ።
መድረክ የስነ ምግባር ኮዱን ባለመፈረሙ የዚህ ምክር ቤት አባል ሊሆን አልቻለም። እንደ አቶ በረከት አባባል ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየት በሩ ተዘግቶበታል።
ይህ የምርጫ የስነ ምግባር ኮድ የተዘጋጀው ሲዊድን በሚገኝ በምርጫና በዲሞክራሲ ዙሪያ ምርምር በሚያደርግ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከሚደነግገው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ በተጨማሪ፣ ሌሎች ሁለት ሰነዶችን አዘጋጅቶ ነበር። እነርሱም የምርጫ ታዛቢዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚዘረዝረው የምርጫ ታዛቢዎች የሥነ-ምግባር ደንብ እና ምርጫውን የሚያንቀሳቅሰው አካላት (እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ) እንዴት መስራት እንደሚኖርባቸው የሚያመላክተው የምርጫ አስተዳደር የሥነ ምግባር ደንብ ነው።
በወቅቱ መድረኩ በአንዱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሶስቱም ሰነዶች ላይ ስምምነት እንዲደረስ ግፊት ቢያደርግም፣ ኢሕአዴግ የምርጫ ቦርዱን እና ታዛቢዎችን የሚመለከቱትን ሁለት ሰነዶች ወደ ጎን አድርጎ፣ ለምርጫ የሚወዳደሩት አካላት ላይ ብቻ ከሚያተኩረው ሰነድ ውጭ ለመነጋገር ፍቃደኛ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከመድረክ ጋር ያኔ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል።
ያኔ የሆነው ሆኗል። ያነ በተፈጠሩት ክስተቶች ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት አልፈልግም። አሁን ግን አገራችን ኢትዮጵያ በፊቷ የሚጠብቃት ብዙ ፈታናዎች እንደመኖራቸው የኢትዮጵያውያን አንድነትና መቀባበል የግድ አስፈላጊ ነው።
የመድረክ አመራር አባላት፣ ያኔ የስነ መግባር ሰነዱን አለመፈረማቸው በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ስናየው ሊያስኬድ ቢችልም፣ አሁን ባለንበት ወቅት ግን፣ ይህን ሰነድ በመፈረም ኳሱን ወደ ኢሕአዴግ ሜዳ ቢልኳት ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ቢያንስ ቢያንስ አቶ በረከት፣ «መድረክ አመጸኛ ነው» ለሚሉት ክሳቸው እንደምክንያት የሚያቀርቡትን አንድ ነጥብ ያሳጣቸዋል።
ይህን ስል አቶ በረከት ባቀረቡት አስተያየት መስማማቴ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ መድረክ ሰላማዊ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለ የድርጅቶች ስብስብ ነው። መድረኩና የመድረክ ድርጅቶች ያወጧቸውን መግለጫዎች፣ የሰጡትን ቃለ መጠይቆች ብንመለከት የሰላምና የፍቅር እንጂ የአመጽ ቃላቶች የተሰሙበት ሁኔታ የለም። አቶ በረከት ምን አይነት መረጃ ይዘው መድረክን የአምጽ ድርጅት አድርገው እንደፈረጁት ሊገባኝ በጭራሽ አልቻለም። አንድን ሰነድ አለመፈረም ከሆነ አመጸኛ የሚያስብለው እንግዲህ ብዙ ልንባባል እንችላለን።
አንድ ነገር ግልጽ ይሁንልን። ይህ የምርጫ ሰነድ ሕግ ሆኖ ወጥቷል። የመድረክ አመራርና አባል ድርጅቶች ያከብሩታል። ሕጋዊ ናቸውና። በመሆኑም ለሰላምና ለእርቅ የአገሪቱ ሕግ እንደመሆኑ የሚያክብሩትን አካላት፣ ፊርማ ካላሰፈራችሁ ብሎ ማግለል ተገቢ አይደለም።
ከዚሁ አርእስት ሳልወጣ አቶ በረከት መሳሳታቸውን የሚያሳይ አንድ ሌላ ነጥብ ላንሳ። ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር አንጃ ከሆነ ጋር ድርድር ማድረጉ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ ከተቀረው አንጃ ጋር በኬንያ ድርድር እያደረገ እንደሆነ እያነበብን ነው። እሰየው የሚያስብል ነው።
ነገር ግን አንድ ነገር ልብ እንበል። የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር የስነ ምግባር ኮዱን አልፈረም። ሆኖም ኢሕአዴግ ከኦብነግ ጋር ለድርድር ተቀምጧል። ታዲያ እዚህ ላይ ሁለት ሚዛኖች አናይምን ? አቶ በረከት የሚናገሩት ኢሕአዴግ እያደረገ ካለው ጋራ የሚቃረን አይደለምን ? ከኦብነግ ጋር መደራደር ከተቻለ ከመድረክ ጋር ያውም አገር ውስጥ በሰላም ከሚታገል ጋር አለመደራደር እንዴት ሊያስቸግር ይችላል ?
በሰሜን አሜሪካ በሚደረጉ ስብሰባዎች፣ የመድረክ አመራር አባላት በግልጽ ለሰላምና ለእርቅ ዝግጁ እንደሆኑ፣ ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ፣ የኢሕአዴግ ደጋፊ፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ሁሉም በአንድ ላይ መምጣት እንዳለበት እየተናገሩ ነው። በአቶ መለስ ዘመን የታዩ የልማት ውጤቶች እንዳሉ በመግልጽ፣ የኢሕአዴግ አባል እስከሚያስመስላቸው ድረስ፣ የልማቱ ተግባራት መቀጠል እንዳለበት ነው በይፋ ያስቀመጡት። በዳያስፖራ ካሉ ጥቂቶች፣ ጠንካራ ተቃውሞ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ኢሳት የተሰኘውም የሜዲያ ቡድን በአንዳንድ የመድረክ አመራር አባላት ላይ ጠንካራ ትችቶችን ሰንዝሯል።
በዚያኛው ወገን ደግሞ አይጋ ፎረም የተሰኘው አፍቃሪ ኢሕአዴግ ድህረ ገጽ በመድረክ ስብሰባ አቶ ስዬ አብርሃ ያቀረቡትን ጽሁፍ ለአንባቢያኑ ይፋ ሲያደርግ፣ ኢትዮጵያ ፈርስት የተሰኘውም ሌላ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ድህረ ገጽ ከመድረክ የሚሰሙትን ንግግሮች በአዋንታዊነት ዘግቧቸዋል።
ታዲያ ይህ በራሱ መድረኩ ለሰላምና ለእርቅ ያለውን ቁርጠኝነት አያሳይምን ? አቶ በረከት እንዳሉት አመጽን መስበክ ነውን? አይደለም።
መድረኩ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሰላም ባንዲራ እያውለበለበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ አይነቱን የአቶ በረከት ስምኦን አስተያየት መስማት ያሳዝናል። አይበጀንም። አይጠቅመንም። እራስን እንደትክክል ሌላውን እንደ ስህተተኛ፣ እራስን እንደ አገር ወዳድ፣ ሌላውን እንደ አገር ጠላት መፈረጅ መቆም አለበት።
የስነምግባር ኮዱ ሕግ እንደመሆኑ፣ የመድረክ አለመፈረም ችግር ሊያመጣ እንደማይገባውም፣ ለሰላም ሲባል መፈረሙም ችግር የለውም። ይህ በጣም ትንሽ ጉዳይ ነው። ትንሹ ጉዳይ ደግሞ በትልቁ ነገር ላይ እንዳንወያይ ሊያግደን አይገባም።
በመሆኑም ለሰላም ሲባል መድረኩ በአስቸኳይ የስነ ምግባር ኮዱን በራሱ አነሳሽነት በመፈረም ጉልህ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ እመክራለሁ። ይሄንንም ያደርጋል የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ።
መድረኩ፣ ከምንገምተውና ተስፋ ከምናደርገው ውጭ፣ በራሱ ምክንያቶች ሰነዱን መፈረም ፍቃደኛ ካልሆነ ደግሞ፣ ኢሕአዴግ ለኦብነግ እንዳደረገው፣ ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ መድረክን ጨምሮ ከማንም ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ መሆን ይኖርበታል። ይሄም የበለጠ ያስከብረዋል እንጂ አያሳንሰውም። ተቃዋሚ ማግለል፣ ማሰር፣ ማጥፋት አያስከብርም። ጀግንነትም አይደለም። ትንሽነት ነው። የኋላ ቀርነት ነው። ተቃዋሚን ማግባባት፣ ማሳመን፣ ከጎን ማሰለፍ ግን፣ ያ ትልቅ ጀግንነት ነው።
ለማጠቃለል አቶ በረከት ስምኦን ከተናገሩት ያስደሰተኝን አንድ አባባል ጣል አድርጌ ጽሁፌን ልቋጭ። «ይህ ሕዝብ የሚፈልገው የመጣህበትን መሰረት አይደለም። የመጣህበትን ብሄር አይደለም። የምትሰራለትን ስራ ነው» ነበር ያሉት።
ይህን አባባል ለምን እንዳሉ መተንተኑን እንተወውና በግርድፉ አባባሉን ካየነው ትክክለኛና የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜት ያንጸባረቀ እንደሆነ ነው የማስበው። የኢትዮጶያ ሕዝብ ከዘር፣ ከቋንቋ፣ ከጎሳ ከመሳሰሉ የኋላ ቀር መከፋፈሎች አልፎና ልቆ የሄደ ትልቅ ሕዝብ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
ግርማ ካሳ



