ኢሳት ፤ ታማኝና ሲድኒ
እሁድ ኦገስት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.
(ከኢትዮጵያ ዛሬ ባልደረባ - አውስትራሊያ [ሲድኒ])
ዙሪያ ገባዬን ቃኘሁት። አዳራሹ ጢም ብሏል። በወጉ የምቀርባቸው ፣ በዓይን የምለያቸው ፣ ከቶም የማላውቃቸው. . . በርካታ ሰዎች ከበውኛል ። ሴቶቻችን ከወንዶቻችንም በዝተው ይታያሉ። ታዳጊ ወጣቶች ደግሞ ፎቁ ላይ ተኮልኩለዋል። ሁሉም አቆብቁቦ የሚጠብቀው ውዱን የመብት ተሟጋች፣ አርቲስት ታማኝ በየነን ነው።
ዛሬ በአውስትራሊያ የተለያዩ ከተሞች የሚደረገው የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የመክፈቻ ቀን ነው። ወይም በአጋጣሚ ሊሆን ችሏል። እንደ ተያዘው ዕቅድ ቢሆን ኖሮ ሜልበርኖች ነበሩ ይህን ዕድል ያገኙ የነበረው። ችግሩ ግን በበረራ መስተጓጎል ሳቢያ ታማኝ ትላንት መድረስ አልቻለም። ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው። ዛሬ የሲድኒ ነች። ሜልበርኖች አንድ ሳምንት መታገስ ይችላሉ።
ታማኝ ሲድኒ የደረሰው ከ2 ሰዓት በፊት ነበር። ከአልጋ ከወረደ ከ4 ቀናት በኋላ፣ የየኤፖርቶቹን አታካች ቆይታና ረዥሙን የአየር ጉዞ በሰላም ፈጽሞ ሲድኒ መድረሱ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን እፎይ አሰኝቷል።
እፎይታው ደግሞ መነቃቃት ፈጥሯል። ሁሉም ፈካ-ጓጓ ብሏል። ጉዳዩ የኢሳት ነው። ኢሳት ደግሞ አውስትራሊያ በሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ግዙፍ ስፍራ ያለው ሚዲያ ነው። በሲድኒ ያሉ ያገሬ ልጆችም በእህት ከተሞች እንዳሉት ወገኖቻቸው ሁሉ ከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት አላቸው። ኢሳት የኛ ነው ይላሉ።
ዞር ዞር ስል የማየው የታዳሚው ስብጥርም ይህንኑ ያረጋግጣል።. . . በስተቀኜ ራቅ ብለው የተቀመጡትን 3 ደስተኛ ወጣት ሴቶች አየኋቸው። ጓደኛሞች ናቸው። በሲድኒ ምድር በተዘጋጁ የአበሻ መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ሁሉ ጠፍተው አያውቁም። የውይይት መድረኮች ላይ ግን ድርሽ አይሉም። ዛሬ ግን ኢሳትን ሊደግፉ "ድንቁን ልዑኳን" በጉጉት ይጠባበቃሉ። በየአፍታው ጥምዘዝ እያሉ የመግቢያውን በር ሲቃኙ አየኋቸውና ስለ ኢሳት ልቤን ሞቃት።
ከወጣቶቹ ለጥቆ ባለው ረድፍ ላይ ደግሞ ሁለት ወጣት ወንዶች ይታዩኛል። ነፍሳቸውን ለጌታ የሰጡ አማኒያን መሆናቸውን አውቃለሁ። በአንድ አዳራሽ ውስጥ አብረን ስንገኝ ግን ዛሬ የመጀመሪያ ጊዜያችን ነው።
ከቤተክርስቲያን ውጪ አገራዊ ተሳትፎ እንደነበራቸው የማላስታውሳቸው ወጣቶች ፤ ረመዳን ያላዳከማቸው ጿሚዎች . . . አረጋዊያንና ታዳጊዎች ሁሉ በአዳራሿ ታድመዋል። ኢሳት ሁሉንም ባንድ ያቆመች የኢትዮጵያዊነት ፍቅር መገለጫ መስላ ታየችኝ። እናም ደስ አለኝ።
ላፍታ ሀሳቤን ወደ ታማኝ ወሰድኩት። ያለ መኝታ የቆየባቸውን ቀናት አሰብኳቸው። ከ20 ሰዓታት በላይ በረራ ላይ ማሳለፉን አሰላሁት። ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሲድኒው ኪንግስፎርድ ስሚዝ አየር ማረፊያ አቀባበል ስናደርግለት የአይኖቹን መቅላት አስተውዬ ነበር። አሁን ደግሞ ሻወር ወስዶ ቁርስ ከመቅመሻ ብዙም ያልዘለለ ጊዜ ብቻ ነው የተሰጠው። "ታድያ እንዴት ይሆን ድካሙን ተቋቁሞ ፕሮግራሙን ማስኬድ የሚችለው?" ብዬ ሳስብ ስጋት ገባኝ።
በዚያው አፍታ ሞቅ ያለ ድምጽ ከሀሳቤ አናተበኝ። ሰዉ ሁሉ ከወንበሩ እየተነሳ ነበር። የሁሉም ፊት መግቢያው በር ላይ ተተክሏል። ፈ-ገ-ግ-ታ! የፈካ ፣ የረካ ፣ የእንኳን መጣህ ፈገግታ! እናም ጭብጨባ። የጋለ ጭብጨባ። . . . ታማኝን አየሁት። ፊቱ በደስታ ያበራል። እንኳንስ ጉዞ ያደቀቀው ሊመስል - ጭራሽ እንቅልፉን ጠግቦ የተነሳ ነው የሚመስለው። ምን አይነት የመንፈስ ጽናት ቢኖረው ነው?
* * *
. . . ግጥሟን ያስደመጠችው እህት ከመድረኩ ስትወርድ ጭብጨባው ቀለጠ። ውብ ግጥም ነበር። ከሷም በፊት የቀረቡት 2 ግጥሞች ድንቅ ነበሩ። "ሲድኒ ገጣሚያን አሏት" አልኩ ለራሴ።
እንሆ አሁን የእሱ ተራ ሆነ።
ታማኝ እንደወትሮው ታማኝ ሆነ። ዛሬም ወዛም ፣ ዛሬም ቁምነገራም ነበር። በስሜት እንደተሞላ ፣ ፍቅርን እየዘከረ ፤ስለ ኢሳት እየዘመረ አዳራሹን አስደመመ። የታዳሚው ስሜትም እኩል እየናረ ፣ እኩል ዘና እያለ አንድ ሰዓት ተኩል ዘለቀ። . . . ታማኝ ዝም ብሎ አይተችም ፤ የማያወላዳ መረጃውን እንሆ ብሎ ያስፈትሻል እንጂ። በጭፍንም አያወድስም ፤ ምክንያቱን ዘርዝሮ ጭብጡን ያስቋጥራል እንጂ።
. . . በየምዕራፉ አዳራሹ ይወጠራል። ቁጭት ፎቅ ይሰራል። እልህ "ማነህ?' ይላል። ታማኝ ግን ለዚህም መላ አለው ። ስሜትን ረገብ ፣ መንፈስን ዘና የሚያደርግበት ክህሎት አላጣም። አርቲስት ነፍሱ ምንጊዜም የሳቅ ምንጭ መሆኑን ታውቅበታለችና። . . .ቁም ነገሮቹን የሚቋጥርባቸው አውራ ማሳረጊያዎችም አሉት። በዝርዝር ያቀረባችውን ነጥቦች ሸብ የሚያደርግባቸው ሀያል አገላለጾች። ይሄኔ አዳራሹ በጭብጨባ ይቀልጣል። "ልክ ነህ!" ፣ "የውስጤን ተነፈስከው!" ፣ "ዓይኔን ገለጥክልኝ!" የሚል ዓይነት ጭብጨባ። ቿ! ቿ! ቿ! . . .
አንዴ ደግሞ እንዲህ አለ፦ ". . . አቶ መለስ ነፍሳቸውን ይማርና ኦ! - ማለቴ ፈጣሪ ወደ ጤናቸው ይመልሳቸው። ወደ ስራቸው ግን ዳግም አይመልሳቸው ። . . ." ይህን ሲል የተስተዋለውን የታዳሚውን ስሜት ማሳየት ያዳግታል። በተስፋ የተሞረደ ፣ በፈገግታ የታሸ ፣ የብዙዎች የጋራ ድምጽ። . . .በቃላት የማይገለጽ ፣ የአብሮነት ቃና ያለው ልዩ ድምጽ።
" . . .!!! " የሚል። አብሮም ጭብጨባ። በቀላሉ ያልበረደ ጭብጨባ።
አዳራሹን የሞላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የኢሳት ወዳጅ መሆኑን ያውቃል። የኢሳትን ወሳኝ ሚናና የቀጣይነቱን መሰረት ግን ያላሰቡበት ሰዎች ነበሩ። ዕድሜ ለታማኝ - ኢሳትና ታዳሚው በመዋደድ ብቻ እንዳይቀሩ ውል የተፈጣጠሙ መሰሉ። "ኢሳት የኛ ነው " የሚለው ታዳሚ "ኢሳት የሚዘልቀውም በእኛው ድጋፍ እንጂ ነው" የሚለውን ቁም ነገር በውስጡ አገዘፈ። "እንዲኖርልን- እንረዳዋለን" ሆነ ቋንቋው።
የታማኝን ዝግጅት ተከትሎ የተካሄደው የጨረታ ፕሮግራምም የዚሁ ቃል-ኪዳን ቀዳማይ መገለጫ ሆነ። በሳቅ ፣ በፉክክርና በፍቅር የተሳሰረ አዳራሽ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ለኢሳት መደገፊያ የሚሆን ዳጎስ ያለ ገቢ ማሰባሰብ ቻለ።
* * *
ኢሳትን ‹ልሳኔ› ያለው ታዳሚ ፍቅሩን ገልጾ አልጠገበም። ማምሻውን ደግሞ የኢሳት ‹ልዩ ልዑክ› ሆኖ ከመጣው ከአገሩ ታማኝ ልጅ ጋር ገበታ ቀርቦ ተጨማሪ ርዳታ ማድረጉን ወደደ።
በማራኪው የካንተርበሪ ስፖርት ክለብ ሬስቶራንት ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ረድፍ ይዘው የተዘጋጁ ረጃጅም ጠረጴዛዎችን እየከበቡ ተሰየሙ። ጨዋታው ደራ። ማዕዱ ቀረበ። ከታማኝ ጋርም አብረው ተቋደሱ።
እኩለ ለሊት እስኪቃረብ የጦቢያው ተሟጋች ወንበሩን እየቀያየረ በየግሩፑ ከተሰየሙ የኢሳት አፍቃሪዎች ጋር ልባዊ ጭውውት ሲያደርግ አመሸ። ይህ ብርቱ ሰው የድካም ጠብታ አልታየበትም። ከወገኖቹ ጋር ማምሸቱ ልዩ ጉልበት ሰጥቶታል። ስለ ኢሳት መትጋቱም የመንፈስ ስንቅ ሆኖታል። አገሬን ብሎ መዋተቱ ለነፍሱ ሀሴት ሆኗታል። . . .ፅኑ ሰው።
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ታማኝ ሜልበርንን ጨምሮ በ4 የተለያዩ ከተሞች ፕሮግራሞች ይኖሩታል። የኢሳት አፍቃሪዎች ከተወዳጁ የአገር ልጅ ጋር አብሮ በማሳለፍ ኢሳትን ለመርዳት በጉጉት ይጥብቃሉ።



