እነ ‘አሽከር’ ወለተ አማኔል በአደዋ ድል ይታወሱ!
አትክልት አሰፋ (ቫንኩቨር-ካናዳ)
ከ116 ዓመት በፊት በዚህች እለት ድል የሚባል ታላቅ ነገር በዚያች ኢትዮጵያ የምትባል የአለም ግምባር የነበረችና መልሶ ደግሞ ደብዛዋ በጠፋ ሀገር ላይ ተበሰረ። እናም ታላቅ ደስታ ከታላቅ የደም ጎርፍ በሗላ ሆነ። ከድንቅ የጦር ውሎ ለጥቆ፤ ያለ አቻ የተደረገ የግንባር ለግንባር ጦርነት ከተጠናቀቀና የነ አትንኩኝ ባይ ምድር ላይ የደም ጎርፍ ከተጥለቀለቀ በሗላ በኢትዮጵያ ምድር ነጻነት ይፋ ተደረገ። በአለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ህዝቦችም ሰው መሆናቸውን፤ ማሸነፍ ምን ማለት እንደሆነ አውቀው የነጻነትን ተስፋ ይሰንቁ ዘንድ አፍታም አልወሰደባቸውም።
በዚህም የነጻነትን ትግል እኛም እንደነ… በማለት የጉዞ ጅማሮ ያደረጉ ጥቁር ህዝቦች ቁጥርም ተበራከተ። እናም እናም አሁን ለደረሱበት ደረጃ መነሾ አድዋ በተባለች በኢትዮጵያ በምትገኝ ትንሽ መንደር ላይ በተደረገ ታላቅ ጦርነት ድል በሗላ ተጀመረ።
በጦርነቱ እጅግ ብዙ ትእይንቶች ተካሄዱ። የአርበኞች ጀግንነት፣ የእናቶች ደጀንነት፣ የጦር ሰዎች ብልሀት፣ የአሽከሮች ገድልም ተስተዋለ። የእነኛ ያለ በቂ የጦር መሳሪያ ሀገር ድንበሬ ተነካ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ደምም በአደዋ ተረጭቷል። ደማቸው አጥንታቸው ቢከሰከስም በጦር መሳሪያ ከአፍ እስከደገፉ ጢም ብሎ ታጥቆ የናቃቸውን የሀበሻ ልጆች ሊወር የመጣው ጣሊያንም ከእነ ቅጥረኞቹ ያችን ምድር ሊለቅ አልቻለም። ድባቅ ተመታ።
አንዳንድ የዛሬ ዘመን ሰዎች ታዲያ ስለ አደዋ ድልና ስለ ኢጣሊያ ጦርነቶች ሲነሳ በኢትዮጵያዊያኖች ጉልበትና በጣሊያኖች እውቀት የተገነቡ ጥቃቅን መንገዶችን በማየት ምነው ጣሊያን ትንሽ በቆየ ሲሉ ይደመጣሉ። እነኝህ ሰዎች የጤና ችግር ሳይሆን የአስተሳሰብ ጥልቀት ያጡ መሆናቸውም በሌላ ወገን ይነገራል።
እነኝህ ፍጥረቶች ያላዩት ታዲያ እነኛ አባቶች ለዘመናት ከኢጣሊያም ሆነ ከእንግሊዝ ፈረንጆች ጋር በስልጣኔ ሰበብ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ አሻግረውም ለልጅ ልጆቻቸው የሚጥሉትን ጠባሳ ማየታቸውን ያለመገንዘባቸው ነው።
ሚኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ የተባለውም መጻኢውን ያዩ አባቶች የገጠሙት ነበር።
እንዲህ የሚመኙና የሚያስቡ ሰዎች ታዲያ ምነው የቅኝ ግዛትን ሰቆቃ ለብቻቸው በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የግፎች ግፍ ባዩት ያሰኛል። በእርግጥ እንድታዩት የሚገባ “ኢን ማይ ካንትሪ” የተሰኘ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ በሳሙኤላ ጃክሰንና በፈረንሳዊቷ ከያኒ ጁሊየት ቢኖቼ የተሰራ ፊልም ላይ የሳውዝ አፍሪካ ጥቁሮች ይደርስባቸው የነበረውን መካራ በእኛ እናቶችና አባቶች ቢ…ሆ…ን… ብለን ለመገመት እንኳን ያሳቅቃል።
እኔ ከመንገዱ.. ከስልጣኔው ምን አለኝ፤ ከነጻነቴ እንጂ። እኔ ከሚሰራው ግንብ ምን አተርፋለሁ ከኩራቴና ከማንነቴ እንጂ። ለእኔ በእውነት በእውነት ጣሊያን ሊያመጣልኝ የነበረው የስልጣኔ፣ የፋብሪካና የካሚዮን ጋጋታ ምን ጥብስ ሲያደርግልኝ፤ ለኔ ኩራቴ ከድህነቴ ጋር ያለች የዘላለም ክብሬ እንጂ።
ታዲያ ‘የቢሆን ኖሮ…’ አባዜ ያጠቃውና ጣሊያን ቢገዛን ኖሮ… የሚል ሰው ካለ በደቡብ አፍሪካ እናቶችና አባቶች ላይ ቅኝ ገዥዎች ያደረሱትን የሰቆቃ ትእይንት “ኢን ማይ ካንትሪ” ላይ ይመልከት።
አዎ በፈረንጆች የመዝናኛ መለስተኛ ስታዶዮም መሰል ቤት ውስጥ… ፈረንጆች እንዴት እንደሚዝናኑ ያያል። የመዝናኛውን ታሪክ በጽሁፍም ሆነ በንግግር ለመግለጽ ያጸይፋል። ግን እውነት መነገር አለበትና ያንን መከራ ያሳለፉ ሰዎች ታሪክ ‘ለቢሆን ኖሮ...’ ምኞት ጋላቢዎች ይጠቅማል በሚል መናገር ግድ ይላል…
አዎ በብረት ቅርጽ በተሰራ የወንድ ብልት ላይ ኮንዶም አጥልቀው የእናቶችን ማህጸን እንዴት ሲጫዎቱበት እንደነበር ትመለከታላችሁ። እናም ሲዝናኑበትና ሲያሽካኩበት በአይነ ህሊናችሁ እያያችሁ ትቆስላላችሁ። ያ ቁስል በእኔ አያቶች ላይ ደርሶ ህንጻ ይገንባ፤ መንገድ ይጠረግ የሚለኝ ካለ ከሰዎቹ.. ከእነኛ ይንን ግፍ ከፈጸሁት ፍጥረቶች እንዴት ለይቼ አኖረዋለሁ።?
ብቻ የአደዋ ጀግኖች ከዚህ ብቻ አይደለም ያዳኑን… ብዙ እጅግ ብዙ መከራ በላያችን ላይ እንዳይጣል ራሳቸውን ሰጡ። የልጆቼን፣ የልጅ ልጆቼን ስቃይ በደሜ ልጠብ ያሉ ኩሩ አበውና እመው ራሳቸውን ሞት ለሚባል ከባድ ሸክም አሳለፉ። ለእኛ ለልጆቻቸው።
በወረራው ጊዜ ጦርነቶች ስማቸው በእጅጉ የሚነሱ የጦር ጀግኖችን ማንሳት፤ የጦሩ መሪ የነበሩትን አጼ ምኒሊክን ማወደስ፣ እነ አሉላ አባነጋን ማስታወስ፣ ቀኛዝማች በሻህ፣ ራስ መኮንን፣ ራስ ሚካኤልንና ራስ ወሌን፣ አንስቶ በያመቱ ማስታወስ እጅግ ያኮራል።
አፉ ጎራዴ የለው አሽሟጣጭ
ባሹ አባ ሳንጃ ባንዳይኑ አፍጣጭ።
የተባለላቸውን ባለ አንድ አይናውን የጦር መሪ እያሰቡ መኩራት እንዴት ይነሰን።
ለአደዋ ድል ብርቱ ተጋዳይ፣ ብልህ የጦር መሪና አስተዋይ ሴት እቴጌ ጣይቱን ያስታወሰ… ልቡ በደስታ ከመራድ ውጭ ምን ሊመጣለት ነው። እነኝህ ሁሉ ጀግኖች ታዲያ ለ116 አመታት የታወሱ ናቸው። ለቀጣይም ሊታወሱ ይገባል።
ዛሬ ግን ከጀርባ በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉ፣ በሙያቸው ለአርበኞች ከሗላ ደጀን የነበሩ ሴቶችን ነጥሎ ማሰብ ግድ ይለናል። እነኛ ሴቶች ታዲያ ሞልቶላቸው ስማቸው ሊታወስ የሚችሉ ላይሆኑ ይችላሉ። አድሏቸውም እቴጌ ላይባሉ ይችሉ ይሆናል። እኛ ግን እቴጌ ብለን ውለታቸውን ልንከፍል የሚገባን የእቴጌዎች፣ የመኳንንቶች፣ የጦር መሪዎችና የጀግኖች አገልጋይ (አሽከር) የነበሩ የአደዋ ታሪክ ሰሪ ሴቶችን ነጥሎ ማሰብ የታሪክ ግዴታው እኛ ላይ የተጣለ ይመስለኛል።
ታዲያ ስለ እነኝህ ሴቶች በስፍራው የነበሩ፣ በጦርነቱ አውድማ ራሳቸውን ያሳተፉ በጊዜው ጨቅላ ልጅ ተብለው የራስ መኮንንን እጅ ይዘው ተከትለው ወደ አደዋ የዘመቱ… በሗላም በአጼ ሀይለስላሴ ጊዜ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለብቻቸው ማለት ይቻላል ያዘጋጁ ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማሪያም በዚያ በወረራ ጊዜ፣ በዚያ የጦርነት ምስቅልቅል ሰአት፣ በዚያ ውጣ ውረድ በበዛበት ወቅት ታላቁን ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ ያበቁ ሰዎች የሚሏቸውንና በምስክርነት በማስታወሻቸው የ”ሕይወቴ ታሪክ” መጽሀፋቸው ላይ ያስቀመጡትን እንይ… እንዲህ ይላሉ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ስለ እነኝህ ሴቶች ሲያወጉ…
“…አጎቴ አለቃ አብዩ (የዚያን ጊዜ ሳያደብርን ለቀዋል) መስተንግዶ ለራስ አመጡ። ለታላቅ ወንድሜ ላብዩም ስንቅ አመጡለት፤ ደግሞም ለጭነት አንድ አጋሰስ፣ አንድ ሴት አገልጋይም አመጡለት።
ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች፤ ወለተ አማኔል። የእንኮዬ ወለተ ማሪያም ልጅ። እኛው ጋር ያደገች ነች።) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፣ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፣ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል። እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፣ ከሰፈርን በሗላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች። ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች።
እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እነደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታወሰኛል።
የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል። በመጨረሻው ምድሩን ስገምተው የአደዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል።…” ይላሉ በአደዋ ጦርነት ጊዜ አንድ ፍሬ ልጅ ሆነው። በራስ መኮነን ስለሚወደዱ ብቻ 150 ጥይት ተሰጥቷቸው ከዘማቾች ጋር ተቀላቅለው ወደ ዘመቻ ያመሩትና በጓደኞቻቸው የተቀናባቸው ተክለሐዋሪያት ተክለማሪያም በማስታወሻቸው።
ይለጥቁናም…”፡…ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳው ስመለከተው፣…” ይላሉ ተክለሐዋርያት “…የኢትዮጵያን መንግስት ነጻነቱን ጠብቀው፣ እዚህ አሁን ያለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ሀይሎች መሆናቸውን አልስተውም። ታዲያ ራሴ ለራሴ ጥያቄ ያቀርባል። የኢትዮጵያ መንግስት የተባለው ተቋም ላገልጋዮቹ ውለታ መላሽ ሆኗል ወይ? የዚህን አመላለስ ለመስጠት ሳስበው፣ እልቅ የሌለው መንገድ ይገጥመኛል። ሲሄዱ መኖር ይሆንብኛልና የማልዘልቀው እየሆነብኝ፣ እየተከዝኩ እተወዋለሁ። የእለቱን፣ ያሁኑን ብቻ ለማሰብ ባጭሩ እታገዳለሁ። ይህ ሁሉ ድኩምነቴን ይመሰክራል።” ይላሉ ተክለሐዋርያት በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለተሰራው ታላቅ ድል ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አገልጋዮች ዋጋቸውን አለማግኘታቸው እንዴት እንደሚያንገበግባቸው ሲገልጹ።
ዛሬ ግን ለኛ የነጻነት ትንፋሽ ግንባር ሳይሆኑ የግንባር ስራ ሲሰሩ የኖሩ አገልጋይ ሴቶችን ልናስባቸው፣ እኛ የእነኝህን አኩሪ ትውልድ ሰዎች ልንዘክራቸው ይገባል። ተክለሀዋርያትን እንዳንገበገባቸው ቢሞቱም የእነሱን ታላቅ ተጋድሎ በሚያምር ብእራቸው ከትበው አኑረውልናልና የዚያ ከ116 አመት በፊት በድል የተጠናቀቀ ጦርነት ዋንኛ ባለቤቶች የሆኑት አገልባዮች ወይንም በዚያን ዘመን አጠራር አሽከሮች (ባሪያ) ዋንኛ አስተዋጽኦ አድርገዋልና እነሱን ማሰብ ሀላፊነት ተጥሎብናል። እነሱን… እነ ወለተ አማኔልን በውስጣችን ማክበርና መዘከር ግድ ይለናል።
አበቃሁ!
ለከርሞ ይበለን



