እንግዲህ ቴዲ አፍሮ የፈለገውን ቢያፈቅር ወይም በፈለገውና ባልፈለገው ቢፈቀር የኛ ጉዳይ አይደለም። ‘ቴዲ አፍሮ የኛ ነው’ ለሚሉትም ‘ተስፋ ቁረጡ!’ ማለት ጥሩ ምክር ሊሆን አይችልም። አንድ በሩቅ የማውቃት ወጣት ሶማሌ አለች። ከወደ ደቡብ ሶማሊያ እና ቆንጆ ናት። ኢትዮጵያዊ በገጠማት ቁጥር ኃይለኛ ስልኳን ላጥ ታደርግና የቴዲ አፍሮን ዘፈን ታሰማለች። ‘ምን እንደሚል አላውቅም፤ ግን ዘፈኑንም እሱንም እወዳቸዋለሁ’ ትላለች። ‘ደሞ ባንቺ የተነሳ ሞቃዲሾን እና አዲስ አበባን በፌዴረሽን ወይም በኮንፌዴረሽን ስለመቀላቀል እንዳይዘፍንልንና ዳግም እስር እንዳይገባ’ እላለሁ በሆዴ። ዳህላክና ኢየሩሳሌም ከደረሳቸው ቀጣይዋ ሞቃዲሾ የምትሆን እየመሰለኝ።

 

 

‘ሞቃዲሾ ያለሽው

ልቤን የወሰድሽው

ታንኮች እንዳይግጡሽ

እንደው ምን ልሁልሽ?

ድንበሩ የቱ ጋ ነው

ድንበር የሚሉት፣

ልባችን ተጣብቆ እያዩት።

ኧረ የቲኤፍጂ ያለህ

የኢሕአዴግ መጫወቻ፤

ታንኩን ውሰድና መንገድ ስጠን

ለፍቅራችን ብቻ

ጃህ! ጃህ! ሞቃዲሾሾሾሾ!!’

 

‘እነ ታማኝ በየነ አሥመራ መጡ’ ሲባል ደስታችንን መቆጣጠር አልቻልንም። ሰፈራችን አሥመራ ዓይነ ብርሃን ሆስፒታል አጠገብ ነበር። ከሰፈራችን ወደ አሥመራ አብዮት አደባባይ ለመሄድ ጉዞ ጀመርን። ልቅም ብለን ነው የወጣነው። በግራ በኩል ሲኒማ ጣናን፣ በቀኝ በኩል የአስመራ ቤተመንግሥትን የግንብ አጥር አሻግረን እየቃኘን፣ ባይስሮይ ደረስን። በዚያን ጊዜ ምርጥ ምርጥ የአሥመራ ፎቶ ቤቶች የሚገኙት ባይስሮ ነበር። ፎቶ ዙላና ፎቶ ሐረር ትዝ ይሉኛል። እኛም ለማስታወሻ ይሆን ዘንድ ከፎቶ ዙላ ገብተን ቆንጆ ፎቶ ተነሳን። አሁን ድረስ በእጄ አለ።

 

ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ካልታጠፉ የባይስሮይ መንገድ ካቴድራል’ጋ ሲደርስ ያልቃል። ወደ ቀኝ ታጥፈን፣ የትራፊክ መብራቱ’ጋ ስንደርስ እንደገና ወደ ግራ ታጠፍንና በካቴድራል ሥር አድርገን ኮሚሽታቶን ተያያዝነው። የኮሚሽታቶ የዛሬው ሓርነት ጎዳና መጨረሻም አብዮት አደባባይ ይጨምራል። በዓሉ ግርማ የተረከላቸው እነዚያ ዘምባባዎች ያን ጊዜም ነበሩ። ሁሌም ውብ ናቸው። እነሱን አንዴ ያያቸው ሰው መቼም ሊረሳቸው አይችልም። አሥመራ ያን ጊዜም በጣም ንጹህ ናት። እታገኝና ውሾቿንም ለማየት እድል ገጥሞኛል።

 

አሥመራ አደባባይ ተሰርቶ አላለቀም፤ ግን ጢም ብሎ ነበር። ሰልፋችንን ይዘን እየተፈተሽን ገባን። ታማኝ እየተውረገረገ ግልብጥ ብሎ ለወጣው የሙዚቃ አፍቃሪ አሥመራ ላይ ታይቶ የማይታወቀውን የማስተዋወቅ እና የማዝናናት ስልቱን ሲነሰንሰው አደባባዩ ሙሉ አፉን ከፍቶ ቀረ። በብሔራዊ ደረጃ ተዋቅሮ፣ ቁሳቁሱንና ባለሙያዎቹን ሰብስቦ ሕዝብን በነጻ ለማዝናናት ከአዲስ አበባ የመጣ ሁሉአቀፍ የሙዚቃ ቡድን አሥመራ ላይ ትርዒት ሲያደረግ፣ የመጀመሪያ ላይሆን ይችላል፤ እነታማኝ ታዋቂ መሆን ከጀመሩ በኋላ ግን ያ የመጀመሪያ ነበር። የአሥመራ ወጣቶች ጥሎባቸው የመሃል ሃገር ዘፈንና ዘፋኞችን ይወዳሉ። የሺመቤት ዱባለ (ትመስለኛለች) ባሕላዊ ዘፈኗን ስታቀልጠው አደባባዩ በደስታ ተናወጠ። የአስመራ ወጣቶች ጥሎባቸው የመሃል ሃገር ዘፈንና ዘፋኞችን ይወዳሉ። ንዋይ ደበበ ወደ ማይክራፎኑ ብቅ ሲል፤ ሁሉም አበደ። የአስመራ ወጣቶች ጥሎባቸው የመሃል ሃገር ዘፈንና ዘፋኞችን ይወዳሉ። በተለይ አንዲት አከለ ስንኩል የነበረች ወጣት ንዋይን አለቀውም አለች። እያስደገመችውና አብራው እየደነሰች ተመልካቹን አንጫጩት። የአሥመራ ወጣት ለመጨረሻ ጊዜ ከመሃል ኢትዮጵያ የመጣን አገር አቀፍ የሙዚቃ ባንድ ለመመልከት እድል የገጠመው በዚያን ጊዜ ነበር። ከዚያ በኋላ ያለውን ባላውቀው አይፈረደብኝም።

 

የአውሮፓው ዘፋኝ Mauro የሚጫወተው የ1987ቱ፣

“ቦኖ ሴራ

ቦኖ ሴራ ሲኞሪና

ቦኖ ሴራ

ሲኞሪና ቻዎ! ቻዎ!” ከወደ አሥመራ ዘግየት ብሎ ገብቶ ነው መሰለኝ እንደ ጉድ ይደመጥ ነበር።

 

በMauro ዘፈን በየዳንስና መጠጥ ቤቱ የሚውረገረግ ሞልቷል። ከMauro እኩል እጁን ወሰ ሰማይ ሰቅሎ “In the moonlight after midnight….” የሚለው ተቆጥሮ አያልቅም። አሥመራ ውስጥ፣ የኪሮስ አለማየሁ “አንጉአይ ፍስስ” ታዋቂ ነበር። የጸሐዬ ዮሃንስ “ተባለ እንዴ” ተወዳጅ ነበር። አድማጩ ሌላ ትርጉም ሰጥቶት የነበረው የታረቀ ተስፋሂወት ዘፈን በስፋት ይኮሞኮም ነበር። ሰውነተ─ቀጭንና ጸጉረ ረጅም የሆኑት የአሥመራ ቆነጃጅቶች የመሃል ሃገር ወጣት ላይ ዓይናቸው ከተከሉ፤ አያነሱም። ከልብ አፍቃሪና ቆንጆዎች ናቸው። ሌላው ፋሽን ልብስ ቀርቶ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ እንኳ ያምርባቸዋል። የቀይ ባሕር ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከላይ ቀይ ሹራብ ነበር የሚለብሱት። ያውም እዚያው አሥመራ የተሰራ። የመሃል ሃገር ወጣት ወንድን እያፈቀሩ ስለሚያደርጉት ልዩ ልዩ ነገር በየጊዜው ይወራል። ‘ተያይዘው ወደ ሱዳን ጠፉ’ም የዚያ ምድብ አባል ነበር። ግን የሚያፈቅሩት ወንድ ‘ሰው’ ስለሆነ እንጂ ‘ዘፋኝ’ ስለሆነ አልነበረም። ዛሬም ያ የተለወጠ አይመስለኝም።

 

በአንድ የወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ውስጥ የሚሰራ አንድ ጓደኛ ነበረን። የአዲስ አበባ ልጅ ነው። አሥመራ ዋናው ፖስታ ቤት አጠገብ ከሚገኙ ሕንጻዎች ከአንዱ ላይ ተከራይቶ ይኖር ነበር። አልፎ፣ አልፎ እዚያው አካባቢ ካለው ከታዋቂው ‘አልባ ባር’ ሻይ እንጠጣለን። አንድ ቀን ቤቱ ስንሄድ በጣም ተከፍቶ አገኘነው። እናም ለምን እንደተከፋ ሳናውቅ ማዘን ጀመርን። ብዙ ደቂቃ ቆይተን ነበር ስላስከፋው ጉዳይ የጠየቅነው። መልሱ አሳዛኝ ነበር። ተዳብሎት ይኖር የነበረው ወጣት፣ የባሕር ኃይል አባል ነበር። ምጽዋ ስትያዝ ካለቁት የባሕር ኃይል አባላት አንዱ ሆኗል። የባሕር ኃይሉ አባል ከጓደኛችን ጋር የአፓርታማቸውን የወር ክፍያ እየተጋሩ መኖር ከጀመሩ ቅርብ ጊዜያቸው ነበር። ለአጭር ቀናት የሥራ ጉዳይ ነበር ወደ ምጽዋ ያቀናው። ባማሩ ፍሬሞች የተዋቡት ፎቶዎቹ አሁን ድረስ ትውስ ይሉኛል። እነዚያን ፎቶዎች እያየን አዘንን። ባናውቀውም የምናውቀው ያህል ተሰማን። ጓደኛችንም የሟቹን ንብረቶች ለማ እንደሚሰጥ ግራ ገብቶት ነበር። የአዲስ አበባ ልጅ መሆኑን እንጂ ሌላ ጠለቅ ያለ መረጃ ስለሌለው የወላጆቹን አድራሻ ከወዴት አግኝቶ መርዶውን እንዴት እንደሚነግራቸው አስጨንቆታል። በዚያን ጊዜ የወላጆቹን ሆነ የዘመዶቹን አድራሻ የሚያውቅ ሰው ብቻ ነበር ከጭንቅ ሊገላግለው የሚችለው እንጂ እኛ አልነበርንም። አንድ ሰው ወጥቶ ለዘላለም ስለመቅረቱ ወላጆች ሊያውቁ አለመቻላቸው ሲታሰበን፣ በጣም አስከፋን። ምንም ማድረግ ስላልቻልልና ማድረግም ስለማንችል፣ የአሥመራ ምሽትም በጊዜ ጭር የማለት ሁኔታ አስፈሪ በመሆኑ፣ የማጽናኛ ቃላትን አስረክበነው ፎቶዎቹ ከፊታችን አልጠፋ እያሉ ወደ ሰፈራችን አቀናን።

 

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጽ/ቤቱ ገብተን አናገርነው። ንብረቱን ሁሉ ፍቅረኛው ወደ አዲስ አበባ ወስዳለች። ቤተሰቡ መርዶውንም በዚያው እንደሚሰሙ ነገረን። ‘የአሥመራ አፍቃሪዎች እንዲያ ናቸው’ አለን። ደስ አለን። በደንብ የምታውቀው አንዲት ወጣት ነበረችው ለካ! …..ስታፈቅረውም “ዘፋኝ ነው፤ ወይም በሚቀጥለው ዓመት ነጠላ ክሊፕ ይለቃል፤

 

‘እምባይሶራ ሆቴል፣ ጉርጉሱም የባሕር ዳርቻ’

ለማንም ክፍት ናችሁ ምነው ለኔ ብቻ’ እያለ ያቀነቅናል” ብላ አልነበረም።

 

ከዚያች ውብ ከተማ ብዙ ውብ የፍቅር ታሪኮች አሉ።

 

ከቀይ መስቀል ዋናው ጽ/ቤት አጠገብ ሼል ነዳጅ ማደያ አለ። ከሼል ፊት ለፊት በጣሊያን ጊዜ ሲኒማ ሮማ፤ ከጣሊያን በኋላ ሲኒማ አዲስ አበባ ነበር። ሥሩ የትራፊክ መብራት አለ። ከሲኒማ ቤቱ ጀርባ ካሉ የሚያማምሩ ቤቶች መካከል አንድ የሙዚቃ ት/ቤት ነበር። አንድ የሐረርጌ ልጅ የሆነ ጓደኛዬ በትርፍ ጊዜው ጊታር መምታት ይማር ነበር። አንድ ቀን ተያይዘን ሄድን። ለነገሩ ጊታርም ባይሆን አንድ የሙዚቃ መሳሪያ መሰልጠን እንዳለብኝ ሁሌም አስብ ነበር። የሙዚቃ ማሰልጠኛውን ከማየትና ጓደኛዬን ከማበረታታት ባሻገር ያለኝ የጊዜ ሁኔታ ሥልጠናውን እንድጀምር አላደረገኝምና ቅር እያለኝ ሳልጀምረው በዚያው ተውኩት።

 

ያ ጓደኛዬ አንዲት ልጅ ተዋወቀ። ደሞ ሰፈሯ እኛ የምንኖርበት አጠገብ ነው። የሃገር ፍቅር ማኅበር ኃላፊዎች ከነበሩት መካከል፣ አሁን ስማቸውን የዘነጋዋቸው አንድ ሰው ይኖሩበት ከነበረው ሕንጻ ላይ ነበር ቤተሰቦቿ የሚኖሩት። በጣም ቀይና አፍላ ወጣት ናት። ቅላቷ ወደ ክልስነት ያደላል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ገና አልጨረሰችም። በፍቅር ለማበድ ጊዜ አልፈጀባትም። ብን አለች። በጣም ራሷን ትጠብቅ የነበረች አፍላ፣ ራሷን ረሳች። ልብሷን እንደነገሩ ለብሳ ያልጠበተረ ጸጉራን እንደ እብድ ከወዲያ ወዲህ እየነሰነችው ‘እከሌን ፈልጌ ነው’ ስትለን ሮጠን ከሽንት ቤትም ቢሆን ጎትተን እናመጣዋለን። እንዲያ ካላደረግን ከደጅ አትሄድም። እንዲያውም ትሰድበናለች። መጀመሪያ ሰሞን እሷ ታፍረን ነበር። ከትንሽ ጊዜ በኋላ እኛ ማፈር ጀመርን። “እኔ ባፈቀርኩት እናንተ ምን አገባችሁ” ትለናለች። ተደናግጠን ጊዜ ሳንፈጅ ጓደኛችንን ፍለጋ እንራወጣለን። በጊታሩ ቦታ እሷን እንዲያቅፍ አደረግችውና በትርፍ ጊዜው የሚሰለጥነውን ጊታር ትቶ እሷን ማቀፍ ጀመረ። ጓደኞዬን እስክለየው ድረስ እንደዚያ ነበር።

 

በአንድ ወቅት ሐረርጌ ይህን ጓደኛዬን ፍለጋ ሄድኩኝ። በወላጆቹ የድሮ አድራሻው ፈልጌው አገኘሁት። ሚስት አግብቷል። የአንድ ልጅ አባትም ሆኗል። የሰርጉን አልበም አውጥቶ አሳየኝ። በሐረርጌ ኦሮሞ የአለባበስ ባሕል ሽር ብሎ ያከናወነውን ሰርግ አየሁት። ሙሉ ነጭ ልብስ ለብሷል። በሆዱ አቅጣጫ ጩቤ ሻጥ አድርጓል። አፍሮ ጸጉሩ ላይ ቀይ አበባ ሰክቷል። አልበሙን አድንቄ ስሰጠው “የመጨረሻ ፎቶ ሥር ያለውን ፎቶ አየኸው?” አለኝ። በእውነት አላየውም። መልሴንም ሳይጠብቅ እራሱ አውጥቶ አሳየኝ። ያቺ የሰፈራችን ቆንጅዬ ነበረች። “አሁንም ትገናኛላችሁ?” ጠየኩት።

 

“ከሞተ ሰው ጋር መገናኘት ቢቻል እንዴት ጥሩ ነበር” አለኝ።

በጣም አዘንኩኝ።

“ቪዛ ባገኝ…..” ብሎ ሲጀምር፣

“ምን ልትሆን?” አልኩት። መቸኮል አልነበረብኝም።

“አሥመራ ሄጄ ከመቃብሯ ላይ የጽጌረዳ አበባ አስቀምጥ ነበር”

‘እሷ’ጋ ሄዳለሁ’ የሚል መስሎኝ ነበር የተቻኮልኩት።

 

አሥመራ ካሉት መቃብሮች ሶስቱን አውቃለሁ። የካቶሊክ፣ ምጽዋ መውጫ አጠገብ ያሉትን የብሪትሽ ሴሜተሪ እና ቤት ገርጊሽ ያለውን። አሥመራ ዙ፣ ከብሪትሽ ሴሜተሪ አጠገብ ነው ያለው። ቤት ገርጊሽ ማለት ጎርጊስ ቤተክርስቲያን ማለት ነው። የጎርጊስ ቤተክርስትያን መቃብር ከቤተክርስትያኑ ብዙም ሳይርቅ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ያለው። ከፍ ካለው የመቃብር ሥፍራ መጀመሪያ የሚታየው የራስ ተስፋዬ በራኺ መቃብር ነው። በጥሩ ሁኔ በእምነበረድ የተሠራ ነው። አጠገቡ ተቀምጫለሁ። አሁን ረሳውት እንጂ መች ተወልደው መች እንዳረፍፉ ከመቃብራቸው ላይ ያነበበኩት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልተረሳኝም ነበር። ፎቷቸውም ጭምር። ከዚያ መቃብር ላይ ሆኖ ወደ ምጽዋ አቅጣጫ ያለውን ተያያዥ ተራራና ሸለቆ ማየት ያስደስታል። የብሪትሽ ሴሜተሪ፣ የቤት ገርጊሽና የአሥመራ ዙ አካባቢዎች ለፍቅር የሚመቹ ናቸው። ረጃጅም የባሕር ዛፎች የሚታዩባቸውና ንጹህ ናቸው።

 

መቃብሯ ከብሪትሽ ሴሜተሪ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ። ከዚያ ለመቀበር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች መሞት ያስፈልጋል።

 


ጸሐፊውን በዚህ ኢሜይል ሊያገኙት ይችላሉ። This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ