ተመስገን ደሳለኝ

ተስፋ ቆርጬ አላውቅም። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሳያጋጥመኝ ቀርቶ አይደለም። ብዙ ጊዜ ገጥሞኝ ያውቃል። ነገር ግን የብዙ ሀገራት ተሞክሮን ካየክ ተስፋ እንድትቆርጥ አይገፋፋህም። ለምን? ካልከኝ ብዙዎች ‹‹ሞቱ፣ ተቀበሩ›› ሲባሉ እንደ ገና መግነዛቸውን በጥሰው ሲያቸንፉ ታያለህና። በሀገራችንም ቢሆን ‹‹አለቁ፣ ደቀቁ›› የተባለላቸው ሟርቱን አቸንፈው አይተሀል። ‹‹እፍኝ የማይሞሉ…›› ሲባል የነበረበትንም ዘመን መቼም ትረሳዋለህ ብዬ አላስብም።

በእርግጥ ኢህአዴግ ‹‹ተስፋ መስጠት››ን እና ‹‹ተስፋ መንጠቅ››ን ከ‹‹ሚሊኒየም ግቦች›› እንደ አንዱ አድርጎ የወሰደው ይመስለኛል። አረ እንዲያውም ያለፉት 20 አመታት ‹‹ተስፋ እንደተጣለባቸው›› እና ‹‹ቃል እንደተገባባቸው›› እንደወጡ የቀሩ አመታት ናቸው።

ለምሳሌ ‹‹በቀን ሶስቴ ትበላለህ›› ከ20 አመት በፊት ይተነገረ የተስፋ ቃል ነበር። እናም ያ ሀያ አመት አልፎ እንኳንም በቀን ሶስቴ ልትበላ ቀርቶ፣ ለአንዴውም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢህአዴግ ሆዬም! ለሌላ 20 አመት የተስፋ ‹‹ቀጠሮ›› ሰጥቶሀል። እንዲህ ሲል ‹‹የኢህአዴግ እቅድ የሚሳካው፣ ኢህአዴግ 40 እና 50 አመት በስልጣን ሲቆይ ብቻ ነው››።

ኤርትራ ስትገነጠልም የነበረው ተመሳሳይ ነው። በወቅቱ ‹‹የሀገር አንድነት ፈራረሰ፣ ሀገር ተሸጠ›› ሲሉ ለተቃወሙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ‹‹ከዚህ በኋላ በኤርትራ በኩል አንዲት ጥይት አይጮህም›› የሚል ተስፋ ተሰጠ። ነገር ግን ተስፋው በህይወት የቆየው ለ8 አመታት ብቻ ነው። ከ8 አመት በኋላ ግን አንድ ጥይት ብቻ ሳይሆን ከአየር መቃወሚያ እስከ የአየር ሀይል ጄት፣ ከቢኤም እስከ ታንክ፣ ከእግረኛ እስከ ሜካናይዝድ፣ ከባዙቃ እስከ ዲሽቃ... ውሎ እና አዳራቸው በዛላንበሳ፣ በሺራሮ፣ በባድሜ፣ በሸንበቆ…. ሊሆን ተገደደ። ‹‹እንዲህም ብላችሁን ነበር? ታዲያ ስለምን ወደ ጦርነት ተገባ?›› ብሎ የጠየቀም የለ። ለነገሩ ቢጠይቅም ኢህአዴግ ምን ተዳዬ ነው። በተስፋ ላይ ተስፋ እየሰጠ መጓዙን ቀጥሏል።

እናም በ1996ዓ.ም ወረሃ ክረምት ‹‹ሶስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንከን የለሽ ይሆናል›› የሚለውን የተስፋ ቃል ደጋግመን ስንሰማ፣ ‹‹ምርጫ 97››ን ደጋግመን ተስፋ አደረግን። የሆነው ግን ምንድር ነው? ‹‹ጣትህን እቆርጣለሁ›› ከሚል ዛቻ እና ማስፈራሪያ ጀምሮ ‹‹ከቤትህ ትርው እንዳትል›› ብሎ እስከሚያስገድደው ለአንድ ወር ከቤት ውጭ የሚደረግ ሰልፍ እና ስብሰባ ማገጃ አዋጅ (በእርግጥ ከአንድ ወር በኋላም ቢሆን ይህ እገዳ ዛሬም አልተነሳም። እናም ውስጥ አዋቂዎች ለፈጣሪ አንድ ሺ አመት አንድ ቀን እንደሆነው ሁሉ፤ ለኢህአዴግም አንድ አመት አንድ ቀን ነውና ሰላሳ ቀን ወይም አንድ ወር የተባለው ሰላሳ አመት ነው ሲሉ ትርጓሜውን ነገሩን)፤ በጎዳና ላይ በጥይት ከመጨፍጨፍ ጀምሮ እስከ ሸዋሮቢት፣ ዝዋይ፣ ደዴሳ… የደረሰ እመቃ፤ ኮሮጆ ይዞ ከመሮጥ እስከ ዳግም ምርጫ ያየነው እና የሰማነው እንከን ነው።

‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የሚባል መንኮራኩርም ወደ ተስፋይቱ ምድር ይዞን ሊመነጠቅ እንደሆነ ተስፋ የተሰጠን በ2003 መስከረም ወር ነው። ከአይን የፈጠኑ ባቡሮችን ጨምሮ በአምስት አመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የሚያሰልፈን ‹‹ጃ ቀኝ›› እንደተጀመረ ያበሰሩን ‹‹ጆሮ ጠገብ›› አርቲስቶቻችን ነበሩ። አላሙዲን ከሰራው ግዙፍ የሚሊኒየም አዳራሽ በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ግዙፍ ዝግጅት። ሆኖም ይሄ የትራንስፎርሜሽኑ ሽለላ አመት ከመንፈቅ ያለፈው ቢሆንም፣ ነገሩ ሁሉ ‹‹መፅሀፉም ዝም፤ ኢህአዴግም ዝም›› እንደሆነ ነው።

እነዚህ ለዋቢነት የቀረቡ የተስፋ ቃል ናቸው። በተቀረ ሁሉም የተስፋ ቃሎች ይዘርዘሩ ቢባል የጋዜጣ አምድ ቀርቶ ቴሌቪዥኑ እና ሬዲዮኑ ለ24 ሰዓት ለፍፈውትም አይጨርሱት። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሲገጥመኝ እማረራለሁ እንጂ ተስፋ አልቆርጥም እያልኩህ ያለሁት። አዲሱ የሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት ታሪክ እንደሚነግረን ደግሞ ‹‹አብዝቶ መማረር›› ብሶት ይወልዳል። ብሶት ደግሞ… እንዳየነው እንደሰማነው ነው። ‹‹ብሶት የወለደው፤ ጀግናው…›› ጆሮ ገብ አዋጅ።

በእርግጥ እኔ እና አንተ በኢህአዴግ አብዝተን እንማረራለን። ኢህአዴግ ደግሞ ለምሬቱ ማስታገሻ ይሆን ዘንድ አብዝቶ ፊልም መስራት ላይ ተጠምዷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢቲቪ የሚቀርብ ዜና ሳይቀር የዶክመንተሪ ፊልም ሊሆን ምንም አልቀረው። አኬልዳማ፣ የእድር ዳማ፤ የመሬት ሽሚያ፣ የመሬት ችብቸባ፣ የፍትህ እመቤት፣ የፍትህ ጌታ፣ የሽብር አባት፣ የሽብር አክስት… አስታውሰህ የማትጨርሰው ርዕስ ያላቸው ፊልሞችን አይተሀል። ነገም ታያለህ። እንግዲህ እነዚህ ፊልሞች የ‹‹ተስፋው ቃል›› ለመምከኑ እንደምክንያት የቀረቡ ናቸው። የሚገርመው ደግሞ ልክ እንደ ሰራዊት ፍቅሬ ፊልም፣ በሁሉም ዶክመንተሪ ፊልሞች ደራሲው ራሳቸው፣ ተዋናይ ራሳቸው፣ ዳይሬክተር ራሳቸው መሆናቸው ነው። ገፀ ባህሪው የጄኪ ቻን ወይም የሀርሰን ፎርድ አሊያም የሚስተር ቢን ይሆን ለ‹‹ሰውየው›› ትወናው አይከብዳቸውም። ክብደቱ ለተመልካቹ ለአንተ ብቻ ነው።

ስለዚህም እነሆ ዛሬም ፊልም መስራቱ ቀጥሏል፡፡ የአንተ እና የእኔም ምሬት ጨምሯል። ከሸውራራ ፖሊሲ እና ከአፈፃፀም ድክመት ከመጡ ችግሮች ባሻገር የግብሩ አበዛዝ፣ የፕሬስ አዋጁ፣ የፀረ-ሽብር አዋጁ፣ የሊዝ አዋጁ፣… ሆድ አስብሰው ብቻ የሚያባሩ አይደሉም። ይልቁንም ልብን ያሸፍታሉ። ሸፍት፣ ሸፍት፣ ብረር፣ ብረር… እናም ድንገት እምር ብለህ ተነስተህ ‹‹ውረድ እንውረድ…›› ብትል ወይም ‹‹¬ጥራኝ ዱሩ…››ን ብታንጎራጉር...

የሆነ ሆኖ መንግስት በፍትህና ዕርት ከማስተዳደሩ ይልቅ ‹‹ጀት ነጋዴነቱ›› በሚገባ ተሳክቶለታል። የማይሸጠው የማይለውጠው ነገር የለም። በበረሃው ዘመን ሳይቀር ‹‹ሲታገል›› ሳይሆን ‹‹ሲነግድ›› የከረመ ይመስል ያየውን ሁሉ ይሸጣል። መልሶ ደግሞ ‹‹በአዋጅ›› ይወስደዋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት የመሬት ችብቸባውን ከአናብስቶቹ እስከ ግልገሎቹ ድረስ ያሉት ሹመኞች መደበኛ ስራቸው አድርገውት ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹የተወረረ መሬት አስመላሽ›› እና ‹‹የሊዝ አዋጅ›› የሚባል ፋሽን ተከታይ ሆነዋል። በእርግጥ ይህች ‹‹ወረራ›› የምትለውን ቃል ስትሰማ ሀገሪቱ እስከ ዛሬ በጣሊያን ስትገዛ ቆይታ ከ2002ዓ.ም በኋላ ነፃ የወጣች እንጂ፤ ‹‹ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር›› እያሉ ከፓትሪያርኩ እስከ ሼሆች ድርሳን የሚደርሱለት ኢህአዴግ ያስተዳደረ ላይመስልህ ይችላል። ነገር ግን ምን ታደርገዋለህ፤ ይሄ የኢህአዴግ ባህሪ ነውና እያወክ እንዳላወክ፤ እየሰማህ እንዳልሰማህ፤ ሌላ ተስፋ፣ ለሌላ አመት ተቀብለህ ትጓዛለ።

ከዚህ ባሻገር የግብር አይነቱ እና አበዛዙ ‹‹ቅኝ ገዢ›› ከተባለው ጣሊያን ሳይቀር የከፋ ነው፡፡ ኧረ የጣሊያኑ በስንት ጣዕሙ። የእነሱ እኮ ግፋ ቢል ለግራዚያኒ እና ለጀሌዎቹ ‹‹እንቁላል ገብር›› ነው፡፡ ያውም ሊያከማቹት ወይም ሊቸረችሩት ሳይሆን ጠብሰው ሊበሉት።

ለዚህም መሰለኝ፡-

“ሚኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ”

የሚል የቆየ ግጥም የሰማከው። እናም እመነኝ ኢህአዴግ ዛሬ እየጠየቀ ካለው ግብር የ‹‹እንቁላል ገብሩ›› በስንት ጣዕሙ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ይህም ሆኖ አባቶችህ ‹‹እንቁላል አንገብርም›› ብለው ‹‹እምቢኝ! አሻፈረኝ›› ብለው ዱር ቤቴ አሉ፡፡ እውነትም ‹‹እምቢኝ…›› እንዴት ደስ የሚል ቃል ነው እባክህ! እስከዛሬስ እንዴት ልንረሳው ቻልን? ማለቴ ከጣሊያንም ብሶ፣ እንቁላሉን ብቻ ሳይሆን ‹‹መጥበሻ›› እና ‹‹ማባያውንም›› ገብር ስንባል? እውነትም ‹‹እምቢኝ…እምቢኝ…››

ይሄም ሆኖ ለፈጣሪ ገለታ ይድረሰውና ዛሬ በሀገራችን ገባሪው ብቻ ሳይሆን፣ አስገባሪውም ደንግጧል፡፡ ለነገሩ እንዴት አይደነግጥ፤ ካለፈው አመት አጋማሽ ጀምሮ አስደንጋጩ በዝቶአል። የእኔ ሰው ገብሬ የተባለ ጀግና ኢትዮጵያዊ ‹‹እምቢኝ›› ብሎ ራሱን ሲያቃጥል። ሺ ምንተሺ የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች ‹‹ሳንፈልጋቸው ሃያ አመታቸው›› እያሉ ሲጮሁ፤ የአወሊያ ኮሌጅ የተማሪ ጐበዛዝት ‹‹ነፃነታችንን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተጋፍቶን እስከመቼ?›› ከማለትም አልፈው ‹‹ሆ›› ብለው ጮኸው፣ ለሌሎችም የታፈኑ ተማሪዎች አርአያ ሲሆኑ… እያየ እና እየሰማ መደንገጥ ይነሰው?

‹‹አሸባሪ›› ተብለው የታሰሩት ፋኖዎችም የዚሁ የድንጋጤው ሰለባ ናቸው። በእርግጥ እስር ቤቶቹ እስኪሞሉ ድረስ ‹‹አሸባሪዎቹ›ን እያነቁ ማሰሩ የሚቆም ላይሆን ይችላል፡፡ ሴት፣ ወጣት፣ እናት፣ አባት፣ አዛውንት፣ አሮጊት… ብቻ ምንም ሁን ምን፤ የትኛውም እድሜ ላይ ሁን ‹‹ሀገሬን፣ መብቴን…›› ካልክ እመነኝ አንተ አሸባሪ ነህ። በነገራችን ላይ እስር ሲነሳ በቅርቡ የተመለከትነው ‹‹የሽብር አባት›› የተሰኘው የኢቲቪ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ የሰማሁት ቃል ትዝ ስላለኝ ላስታውስህ። ‹‹ኤርትራ ለዜጐቿ እስር ቤት ሆናለች፡፡›› (በፊልሙ ላይ የሰማሁት ነው)

ኢቲቪ እስኪ አንዴ ድገመው? …

ግዴለም! እኔው እደግመዋለሁ ‹‹ኤርትራ ለዜጎቿ እስር ቤት ሆናለች፡፡›› ኢቲቪዬ እንደው በሞቴ አንድ ጥያቄ ላቅርብ ‹‹ኢትዮጵያስ ለዜጎቿ ፍራሽ እና ትራስ›› ሆና ይሆን? (ይቅርታ እርግጠኛ ስላልሆንኩ ነው)

የሆነ ሆኖ ስለእስር ከተነሳ አይቀር በአውሮፓ የሚኖር አንድ ወዳጄ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ስናወራ ድንገት የጠየቀኝን ጥያቄ እንደወረደ ላውርድልህ። ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ በስንት ይከፈላል?››፣ በ80 ብሔር ብሔረሰቦች ለወዳጄ ጥያቄ ፈጥኜ የመለስኩት መልስ ነው። ‹‹ተሳስተሃል›› ወዳጄም እንዲህ ፈጥኖ አረመኝ። በድጋሚም ሞከርኩ ‹‹በሶስት ይከፈላል። ሀብታም፣ ደሃ…›› አሁንም ተናግሬ ሳልጨርስ አቋርጦኝ ‹‹አይደለም›› አለኝ። በዚህ ጊዜም በትህትና ሙከራዬን ትቼ እራሱ እንዲነግረኝ ጠየኩት። ወዳጄም እረጋ ብሎ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ በሶስት ይከፈላል። እነሱም የታሰረ፣ ታስሮ የተፈታ እና ወደፊት የሚታሰር ተብለው›› ሲል ዘረዘረልኝ።

እናም በዝርዝሩ ተስማምቼ ፈገግ አልኩ። በሀዘን። ሆኖም ሆድ ባሰኝ። ነገር ግን ይሄ ትክክለኛ አገላለፅ መሆኑን ልክድ አልችልም። ምክንያቱም ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ያለውን ብታይ ኢትዮጵያውያን ወይ እስር ቤት ናቸው፣ ወይ ታስረው ተፈተዋል፣ ወይ ደግሞ ሊታሰሩ የተዘጋጁ ናቸው። በተለይም ሊታሰሩ የተዘጋጁ የሚለውን ትንሽ ፈታ ስታደርገው እንዲህ የሚል ትርጓሜ ሊሰጥህ ይችላል። ኢህአዴግ ለዘላለሙ በመንበሩ እንደተቀመጠ ይኖር ዘንድ ይፈልጋል። ሆኖም ይህ እውን ሊሆን የሚችለው በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን፤ ህዝቡን በሙሉ እስረኛ፣ ኢትዮጵያ የምትባለውንም ሀገር ወደ ግዙፍ እስርቤትነት በመቀየር ነውና፤ በሂደት እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን ያስራል፤ …አይናገርም፣ አይቃወምም፣ አይተችም፣ እምቢኝ አይልም፣ አደባባይ አይወጣም (ለድጋፍ ካልሆነ በቀር)…

በእርግጥ ሁኔታውን እንዲህ አስፍቼ ሳስበው በበኩሌ ሆድ ይብሰኛል። ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ግን አይሰማኝም። ስለምንስ ይሰማኛል? አምስት አሳ፣ አምስት ሺ፤ ሰባት ሰው፣ ሰባ ሺ መሆን እንደቻለ እያወኩ። አዎና ተስፋ አልቆርጥም። ግን ሰው እንደመሆኔ ሆድ ይብሰኛል። እንዲህ ሆድ የሚያስብስ ሲገጥመኝ። ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ አይሰንፍም። ሆድ ለማስባሱ ማለቴ ነው። አንዳንዴ ሳስበው በኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም ውስጥ ‹‹ህዝብን ሆድ ማስባስ›› የሚል የሰፈረ ይመስለኛል። ይሄ ግን ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡ ለእኛም ለእነሱም። ለምሳሌ ሆድ ከሚብሱን ቀናት በአንዱ ድፍን ሀበሻ ‹‹ሆድ ለባሰው፤ ማጭድ…›› ብሎ ከተነሳ፤ የሚያጭደው ቄጤማ እንደማይሆን ቅንጣት ታህል አትጠራጠር። ለዚህም ነው ደጋግሜ ሆድ አታስብሱን፣ አታማሩን፣ አትጨቁኑን፣ አታፍኑን፣ አትርገጡን፣ አታምታቱን፣ አታጭበርብሩን፣ አትዋሹን… የምለው።

በነገራችን ላይ እንዲህ ስል የኢህአዴግ የተስፋው ቃል የተፈፀመላቸው የሉም እያልኩህ እንዳይመስልህ። እንዲህማ ልልህ አልችልም። ኧረ በጭራሽ አልልህም። ለምሳሌ በአንተ ምድር፣ አንተ ወይም አባት እና እናትህ አጥንታቸውን በከሰከሱበት፤ ደመማቸውን ባፈሰሱበት ሀገር ሰፋፊ መሬቶችን ተቀራምተው ሲያበቁ ‹‹ሩዝ አምርቼ አጎርስሃለሁ›› የሚሉ ባዕዳን ገበሬዎች የተስፋው ቃል ወራሾች ሆነዋል። ወይም ሀገሬ ለእነሱ የተስፋይቱ ምድር ነች።

በየጊዜው ስለተሰሩ ወይም ሊሰሩ ስለታቀዱ ግድቦችም ደጋግመህ ሰምተሀል። ግልገል ጊቤ አንድ፣ ግልገል ጊቤ ሁለት፣ ግልገል ጊቤ ሶስት፣…. ጣና በለስ፣ ተከዜ እርግጠኛ ነኝ የብዙ የሀይል ማመንጫ ግድቦችን ስም ሰምተሀል። የግድብ ስም ከመስማትም አልፎ ተስፋ ተሰቶሃል። ‹‹ከዚህ በኋላ ሻማ ለልደት!›› አንዲት የአበል እና የማስታወቂያ ገቢ ሱስ በተጠናወታት አርቲስት አንደበት የተነገረ የኢህአዴግ የተስፋ ቃል ነው። ሆኖም የተስፋው ቃል ተፈፃሚ የሆነው ለአንተ ሳይሆን ለጅቡቲ ነው። …ጅቡቲ ጨለማ ነበረች፤ ኢህአዴግም ቃል ገባላት ‹‹ኢትዮጵያን አጨልሜ ለአንች ብርሃንን ያልሰጠውሽ እንደው፣ ከዋክብት ይርገፉ፣ ቀኜም ይካደኝ…›› እነሆም ቃሉ ተፈፀመ። በጅቡቲም ጨለማው ተገፎ ሃያ አራት ሰአት ብርሃን ሆነ።

ይሄም ሆኖ ደግሜ ደጋግሜ ሆድ ይባስህ እንጂ፤ ተስፋ አትቁረጥ እልሀለሁ። ምክንያቱም ሆድ ሲብስህ ትቆጣለህ፣ ከተቆጣህ… ያን ጊዜ ተስፋህ በሌሎች መዳፍ ሳይሆን በራስህ መዳፍ ይገባል። …በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አስርተ አመታት መጀመሪያ ላይ በሩሲያ ፈላጭ ቆራጭ በነበረው የዛሩ መንግስት ጭቆና የተማረሩ ሩሲያውያኖች በቁጣ ገነፈሉ። ገንፍለው ሲያበቁም ‹‹ዴሞክራሲ አሁኑኑ!›› ሲሉ ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ። ይህንን ቁጣ ያነሳሱት ታህሳሳዊያን (ዲሴምበሪስትስ) በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። እናም የዲሴምበሪስቶች ደጋፊ (አቀንቃኝ) የነበረው ታዋቂው ሩሲያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን በእነሱ አቆጣጠር በ1818 አመፁ ይበልጥ ይግም ዘንድ፣ ቁጣው ዳር እስከዳር ይደርስ ዘንድ ‘’The Story Of Pugachev’’ በተሰኘው መፃሀፉ እንዲህ ሲል ስንኝ ቋጠረላቸው።

There will rise, believe me, comrade

A star of captivating bliss, when

Russia wakes up from her sleep

And when our names will both be written

Oh the ruins of despotism

እመኑኝ ጓዶቼ…. እመኑኝ

የደስታችን አብሳሪ ኮኮቦች

የምስራቾቻችን ነጋሪዎች መብራት የጀመሩ እለት

እሩሲያ ከእንቅልፏ ትነቃለች

ያን ጊዜ....

ስማችን በገዥዎቻችን መቃብር ላይ ይፃፋል

በአምባገነንት ቅሪት ላይ ይነሳል

….አዎን! ወንድሜ ሆይ! እመነኝ ኢትዮጵያም ከእንቅልፏ ትነቃለች። ስማችንንም..!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ