ግርማ ደገፋ ገዳ

የመለስ ቦላሌ “ቦላሌ” ከመሆኑ በፊት ቁምጣ ነበር። አዲስ አበባ ለትምህርት ሲመጣ ቦላሌ ሆነ። ማገብት ጠርቶት ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ሲመለስ እንደገና ወደ ቁምጣ ተለወጠ። ዳግም ወደ ቁምጣ ሲቀየር፣ ሃሳቡ ኃይለኛ ቁምጣ ሆኖ ለመቅረት ነበር። ይሁንና አንዴ ቦላሌ አንዴ ቁምጣ እየሆነ፤ ራሱን እየቀያየረ በረሃ ከረመ። የሓርነት ድርጅቱ ተለዋጭ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ደረጃም ደረሰ። ድርጅቱ በገንዘብ ጠብሽ በተቃጠለበት በአንድ ወቅት፣ የአድዋን ባንክ መዝረፍ አማረው። አምሮትም ዝም አላለም፤ ድርጅቱን ሚሊዮን በሚሊዮን የሚያደርጉ ዘራፊዎችን መረጠ።

 

የመለስ ቦላሌም ዘራፊ ብቻ ሳይሆን የዘራፊዎቹ አስተባባሪ ወይም አዘራፊ እንዲሆን ተወሰነ። ደስ እያለው ዘራፊዎቹን እየመራ አድዋ ባንክ ደረሰ። መጥፎነቱ ባንኩ ውስጥ ያለው ገንዘብ “አልዘረፍም!” ብሎ ገገመ። እሱ ብቻ አይደለም፣ ዘራፊዎቹም ሬሳቸውን በየመንገዱ ላይ ዘረገፉት። የመለስ ቦላሌ ግን ምንም ጉዳት ሳይደርስበት፤ ከአድዋ ባንክ እንዳማሪያም፣ ከእንዳማሪያም እገላ በረሃ በሁለት ቀናት በሮ ደረሰ።

 

ቦላሌውን፣ እገላ በረሃ ያሉ ጓደኞቹ “እንኳን በደህና መጣህ” አላሉትም። ስብሰባ ተቀምጠው ቅጣት አወረዱበት። ከቅጣቱ አንዱ ጄሪካን መሸከም ነው። ቦላሌው ማለዳ፣ ማለዳ እየተነሳ እንደ ድንጉላ ንብ የውኃ ዘር ካለበት እያሰሰ ውኃ ያመጣል። ጓደኞቹ ዋሻ ውስጥ እግራቸውን ሰቅለው፣ ቦላሌው እንደ ቦቴ በሚያመጣው ውኃ፤ ሲፈልጉ ሻወር፣ ሲፈልጉ ዱቃ እየጠመቁ ይለበልቡታል። ከዚያ በኋላ እየቀናው መጣ። የሓርነት ድርጅቱ የፕሮፓጋንዳ ክፍል ኃላፊም ሆነ። አቶ ዮሴፍ የተባለ ታጋይም የአዜብ ቀሚስን ከገዳሪፍ አመጣለት። እሱን እየለበሰ፣ ጓደኞቹን እያመሰ ፖለቲካውን አጧጧፈው። “ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዥ ናት!” ብሎ ሲከራከር “ትክክል!” አሉት። ድጋፋቸው የማይነጥፍ መሆኑን ሲያውቅ “የትግራይ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት? ሳይሆን፤ የኤርትራ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት?” ብሎ አነስተኛ መጽሐፍ ጻፈ። “ጎበዝ” ብለው አጨበጨቡለት።

 

ተክሉ ሃዋዝን ደብዛውን አጠፉት። አረጋዊ በርሄን እና ግደይ ዘርዓጽዮንን ከሶና ገፍቶ ከግንባሩ ከፍተኛ አመራር ላይ አሰናበተ። በረሃ የተጀመረው ከተማም ቀጠለና የራሱን የትግል አጋሮቹን ዋጣቸው። ምሽግ ውስጥ አብረው ይተኙ፣ አብረው የውጊያ እቅድ ያወጡና የፖለቲካ መስመራቸውን ይቀይሱ የነበሩትን ሰለቀጣቸው። ታምራት ላይኔ፣ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ቢተው በላይ፣ ተወልደ ወ/ማሪያም፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ እና ሌሎቹንም ደፈጨጫችው። ክንፈና ሃየሎም ነፍሳቸው የት እንደደረሰች ባናውቅም፤ ሥጋቸው ተደፍቶ ቀርቷል። ቦላሌው “ወይ ወንድሞቼን!!” እያለ በአደባባይ ቢያነባም፤ ዛሬም ድረስ ከአዞ ምድብ ያለዩት ሞልተዋል። ከደጋፊም ሆነ ከተቃዋሚ፣ ይህንን ቦላሌ ከልቡ አገልግሎ ያልተጣለ ጥቂት ነው። እንደ ቆዳ ተለፍቶ፣ እንደ ሌጦ ተፍቆና እንደ ሸንኮራ ተመጦ የትም የተወረወረውን ጎጆው ይቁጠረው። ሌንጮ ለታ፣ በየነ ጴጥሮስ፣ አባተ ኪሾና ነጋሶ ጊዳዳ፤ ከሃዲዱ የመንደርደሪያ ጠርዝ ላይ የተነጠፉ ሰዎች ነበሩ። ቦላሌው እየጎመዳቸው አለፋቸውና ዛሬ የጋምቤላው ፕሬዚዳንት አቶ ኦማት ኦባንግ እና ምክትላቸው’ጋ ደርሷል። በዚህ ቦላሌ ያልተነካ ማን አለ?

 

…..ኦሞ ሸለቆ ነዋሪው ይፈናቀላል፤ መሬቱ በስግብግቦች ዶዘር ይገላበጣል። የጋምቤላ መሬት ‘ሻሞ’ እየተባለ ነው፤ ሁሉም ድርሻውን ለመንክስ ሩጫ ነው። ዋካ ውስጥ መምህር ራሱን ያቃጥላል፤ ቆላድባ ሌላው መምህር ራሱን ይሰቅላል። አዴት(ጎጃም) ላይ ቤቶች በግሬደር ይፈርሳሉ፤ በሃዋሳ በሙስና ይታነጻሉ። ሆሳዕና ውስጥ መሬት እንደ ወፍ ዘራሽ ጎመን ይቀነጠሳል፤ ስልጤ ላይ “ኡኡ! የፍትህ ያለህ” በዝቷል። ሚዛን ተፈሪ ሱቆች በመደዳ ይታሸጋሉ፤ የጊቤ ሕዝብ ከቀዬው ይባረራል። የኦጋዴን ጎጆዎች እንደ ችቦ ይነዳሉ፤ እነቦላሌዎችም እሳቱን ይሞቃሉ። ቆቃ ውስጥ መርዝ ይደፋል፤ ነዋሪው ሞቱን ያፍሳል። የአወልያ ኮሌጅ፣ የወለጋ፣ የጎንደር፣ የሃሮማያና የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁም ስቅላቸውን ያያሉ። ቤተክርስትያናት ይታመሳሉ፤ መስኪዶች ይተራመሳሉ። የባነኑ የጦር መኮንኖች ማጎሪያ ውስጥ ይጣላሉ። ከፍተኛ ሲቪል ባለሥልጣናት እስር ቤት ይወረወራሉ። ለመብቱ የሚከራከር ዜጋ ሁሉ ሽብርተኛ ይባላል፤ የትም ሃገር ያልታየ ፍርድም ይጫንበታል። በሩቅ ርቀት ባሉ ዜጎች ላይ የሞትና እድሜ ልክ መልእክት በአደራ ይላክላቸዋል። እርዳታ ለማኙ የቦላሌው መንግሥት እርዳታ የሚለምኑ ትናንሽ ድርጅቶችን ዘግቷል። መሬትና ንብረትን ብቻ ሳይሆን የሙያ ማኅበራትንም ወርሷል። ቦላሌው ምንም የቀረው ነገር የለም። ሶማሊያን ያስለቅሳል። የኤርትራ ጉዳይ አልተቋጨም። የኬንያን ድንበር ደስ ባለው ጊዜ ይሰብራል። አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ይሳደባል። ሁማን ራይትስ ዋችን ይነክሳል። ሲፒጄን ያስነጥሳል። ከሁሉም ዜጋ፣ ከሁሉም ድርጅት፣ ከከተማው መሬት፣ ከገጠሩ እርሻ፣ ከሰማዩ ሳተላይት፣ ከራዲዮ ፍሪኮንሲው፣ ከየቤቱ ቴሌቪዥን፣ ከየጣራው ዲሽ፣ ከገበሬው፣ ከሰራተኛው፣ ከተማሪው፣ ከአስተማሪው፣ ከጠበቃው፣ ከጋዜጠኛው፣ ከዘፋኙ፣ ከደራሲው፣ ከስፖርተኛው፣ ከጤና ባለሙያው፣ ከታክሲ አሽከርካሪው፣ ከሥራ ፈላጊው፣ ከስቴዲየም ቲፎዞው…..ከሁሉም ጋር ተናክሷል። እሺ ይህ ቦላሌ ከማን ጋር ነው መኖር የሚፈለገው? …..ባለስትራን ወደ ወርቅ፤ ብዙ ቶን ቡናን ወደ ዜሮ ከሚለውጡ አስማተኞች’ጋ?...

አስማቱ ደግሞ የሚሰራው እንዲህ ነው፦

“ተመልከት! …..ይህ ባለስትራ ነው አይደል?”

“አዎ፤ ባለስትራ ነው።”

“አሁን ጉዱን ላሳይህ”

“እሺ”

“አይንህን ጨፍንልኝ”

“ጨፍኛለው”

“ወርቅ!!”

“ዋ! የሚገርም ነው። …..ራሱ የአዶላን ወርቅ! …..እንዴት ለወጥከው?”

 

“ወሬ አታብዛ፤ ብሔራዊ ባንክ ውሰደው!”

 

በየቤቱ የታጨቀው በደል ወደ ተባበረ ሕዝባዊ አመጽ ሊቀየር ጥቂት ምክንያቶች ሲቀሩትም፤ ቦላሌው ከአንድ ልብ ሰቃይ ሳይሆን ልብ አውራጅ ልብወለድ ጋር ብቅ ይላል። የአፍሪካ መሪዎችን ለማጥፋት፣ ወደ ሶማሊያ መዝመት፣ አባይን መገዳደብ፣ አዲስ አበባን ባግዳግ ማድረግና አኬልዳማን ከመሳሰሉ ልብወለድ ትረካዎች ጋር።

 

ስለ እውነት ለመነጋገር አብዛኛው የአፍሪካ መሪዎች ምናቸው ይጠፋል? ራሳቸውን በራሳቸው አጥፍተው የጨረሱ ናቸው። ሥልጣን ከመያዙ በፊት ዲናሬ ያልነበረው የዴሞክራት ካባ ለባሽ አምባገነን መሪ፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የምእራባውያንን መሪዎችን የሚበልጥ ገንዘብ አቁቶ ይገኛል። አንዴ ቁምጣ አንዴ ቦላሌ እየሆነ መከራውን የሚያየው ጨርቅም፤ የአውሮፓ እውቅ ዴዛይነሮች ካላዩኝ ማለት ያመጣል። ሳያፍርም በያመቱ መስከረም የተመድ ስብሰባ ወቅት ከጎናቸው ይቀመጣል። እሱ ብቻ አይደለም፤ በተመድ መድረክ ላይ ስለሙስና እና ስለሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ኮራ ብሎ ያስተምራል። ምርጥ፣ ምርጥ ልጆቻቸውንም አህጉሪቱ ባላት ምርጥ፣ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አያስተምሩም። ምክንያቱም ልጆቻቸው የሃገራቸውን ብሔራዊ ፈተና ለማለፍ የማይችሉ ብሔራዊ ሰካራሞች ናቸው። ለትምህርት ሳይሆን አረቄ ለመያዣ የሚሆን ትላልቅ ጭንቅላት ነው ሲያስበይዱ የሚከርሙት። የመለስ ቦላሌ ልጆችም እዚያ ውስጥ አሉበት። ቦላሌውም፣ መስከረም ሲጠባ የተመድ ሕንጻ ውስጥ እየተሽቀዳደሙ የቁራ ጩኸት ከሚያሰሙት፣ የልብስ ፋሽን ከሚያሳዩትና አዳራሹ ውስጥ ስድብ ከሚለማመዱት አንዱ ሆኗል። የሞቃድሾ፣ የወንዞች፣ የባግዳድና የአኬልዳማ ጉዳይም ያው እንደ አፍሪካ መሪዎች ጉዳይ ነው፤ ለውጥ የለውም። ይልቅ ለሚቀጥለው ደሞ፤ ስለወንዞች፣ ከተማዎችና የደምመሬት ሳይሆን፤ ተደራሲያኑ ስለደመና፣ ነጎድጓድ፣ መብረቅ፣ ክዋክብትና ጨረቃ የሚያወሩ ልብወለዶችን ነው ጓጉቶ እየጠበቀ ያለው።

 

ለመለስ ቦላሌ ምሳሌ የሚሆኑ አንጋፋ ቦላሌዎች አሉ። ሰላሳ ዓመት ሙሉ በወኔና በጭካኔ፣ “ወደር የሌለኝ ዴሞክራት ነኝ!” ሲል የነበረው የሙባረክ አንደበት፤ ዛሬ በእግሩ መቆም አቅቶት በተኛበት “እኔ አላደረኩም!” ብቻ ነው መልሱ። ከሥልጣን በኃይል ከመወገዱ በፊት በነበሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ፤ ሕዝቡ እንዳይቀረጥፈው የተለያየ አማራጭ እያቀረበ ይለፈልፍ የነበረው ፕሬዚዳንት፤ ከሥልጣን ከተወገደ ጥቂት ወራት በኋላ መናገር አቅቶት ቃሬዛ ላይ ተጠቅልሏል። የሚገርመው ነገር ቃሬዛው ላይ እንኳ አይንቀሳቀስም። የሱ ሕይወት፤ ያስራቸው፣ ይበድላቸው፣ ያንገላታቸው፣ ያሰድዳቸውና ይዘርፋቸው በነበረው ዜጎች እጆች ላይ ወድቃለች። ዋናው ምክንያትም የተለያየ ስም እየሰጠ ሰላማዊ ዜጎችን እምሽክ ማድረጉ ነው እንጂ፤ ሌላ አይደለም።

 

ቃሬዛ ላይ ተጠቅልላ መላወስ እንኳ ያቃታት የሙባረክ እጣ ፋንታ ብዙ ነገር ነበራት። አስፈሪ ክብር፣ ተዝቆ የማያልቅ ገንዘብ፣ በኮማንዶዎች የተከበበ ቤተመንግሥት፣ በሄሊኮፕተር የሚጠበቅ መኝታ ቤት፣ ገንዘብ ያሳበዳቸው ልጆች፣ ማሰርና መጨፍጨፍ የተጠናወታቸው ጓደኞች፣ ዜጋውን መዘቅዘቅና መቀርጠፍ ያሰከራቸው ዘመዶች፣ አይዞህ ባይ መንግሥታት እና ሌሎችም። ዛሬ የሙባረክ ሕይወት ሁሉንም አጥታለች። ታንክ የለም። ማናፋት የለም። ማሰር የለም። መግደል የለም። መዝረፍ የለም። ቴሌቪዥን የለም። ጋዜጣ የለም። ራዲዮ የለም። “እሳቸው …..ሆ! …..ስማርት ናቸው!” የለም። “ሙባረክ ከስልጣን ከወረደ መካከለኛው ምስራቅ አለቀለት!” እሱም የለም።

 

ችግሩ፤ የሙባረክን ፕሬዚዳንታዊ ውርደት አይቶ የሚማር ቦላሌ አለመኖሩ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቦላሌዎች፣ ዩኒቨርሲቲ ሊገቡ የማይችሉ ልጆቻቸውን በሰረቁት ገንዘብ ውጭ ሃገር ልከው ያስተምራሉ እንጂ፤ ራሳቸውን ‘የሙባረክ ቃሬዛ’ ከሚባል ትልቅ ኮሌጅ አያስተምሩም። እንዲያውም እንደዚያ ዓይነት ዜና በቴሌቪዥናቸው ሲመጣ፤ ሚስታቸውን “ኡ! ይደብራል …..እባክሽ ዝጊው!” ነው የሚሉት። የመለስ ቦላሌም ተመሳሳይ ነው። ልክ እንደ ሙባረክ በምርጫ ሲሸነፍ፤ አሸናፊዎችን ማሰር፣ የፖለቲካ ድርጅታቸውን መሰረዝ፣ ስልካቸውን መቁረጥ፣ ጋዜጠኞችን ማባረር፣ ዜጋውን ማጎርና “ሽብርተኞች ናቸው!” ማለትን ነው ዋሻው ያደረገው። አንዱ ገዳይ ከአንዱ ገዳይ የሚኮር ው ያንን ነው፤ ቃሬዛውን አይደለም።

 

የመለስ ቦላሌ ዛሬ ቴሌቪዥኑን አጥለቅልቆታል፤ ደግነቱ ሃገሪቱ አንድ ብቻ ነው ያላት። ጋዜጣ ላይ እሱ ብቻ ነው የሚዋኘው። “ኦ! እሳቸው ስማርት ናቸው!” ቀጥሏል። “እሳቸው ከስልጣን ከወረዱ ያፍሪካ ቀንድ ትርምስምሱ ይወጣል!” ተጧጡፏል። “የሚሊኒየሙ ጎል አፈር ድሜ ይግጣል” ማቆሚያም የለውም። “ምን ነካችሁ? እሳቸው’ኮ የልማት መሪ ናቸው!” ትራክተር ሰጧቸው። “ድህነትን በክንዳቸው ለመደቆስ ቆርጠው የተነሱ ቦላሌ ናቸው” ዘፈን ሁሉ ወጥቶለታ። “ኔፓድ እሳቸውን የመሰለ ሊቀመንበር ማግኘቱ ከባድ እድል ነው!” ይህንንም ሳያፍሩ አውርተዋል። “እሳቸው ጂ-ኤይት ላይ ካልተገኙ አፍሪካ አለቀላት!” በለው! እንዲያም ተብሏል። ለነገሩ ይህን ሁሉ ያልተባለ አምባገነን መሪ የለም። “ስማርት ናቸው!” እሷ’ማ በሽበሽ ናት። ሁሉም “ብልህ፣ አርቆ አሳቢ፣ የዋህ፣ ሩህሩህ፣  ግና፣ አብዮተኛ፣ ሃገር ወዳድ፣ መልስ በኪሱ፣ ሊቁ ሰው፣ ፈጣሪን አክባሪ፣ አይናቸው ይወጋል፣ እድሜው ይርዘምልን፣ ቅንድቡ ሲያምር፣ ደሞዛቸው ትንሽ ናት፣ መጽሐፍ ብቻ ነው ያላቸው፣ ፈረንጅ የጻፈውን ብቻ ነው የሚያንበለብሉት” አስብሉኝ ብለው ተብለዋል። የመጨረሻዋ እለት ግን፤ “ሌባ፣ ዘራፊ፣ ቀማኛ፣ ገዳይ፣ አናቂ፣ ክፉ፣ ጨካኝ፣ አራጅ፣ ሴሰኛ፣ ቃሚ፣ ቃራሚ፣ ሺሻም፣ ትምባዃም፣ አረቄያም፣ አረመኔ፣ ስግብግብ፣ የስልጣን ጥመኛ፣ ይገደል፣ ይሰቀል፣ አሥር ቢሊዮን ነው ያለው፣ ስዊዝ ባንክ አካውንቱን ይዝጋልን” ነው የጠበቃቸው። የመለስ ቦላሌንም አፉን ከፍቶ እያዛጋ የሚጠብቀው ያ ነው። ሕዝቡን ማፈኑን እስካላቆመ ድረስ፤ የአጋዚ አፈሙዝ፣ የአይጋ አልጋ፣ የአፓርታይድ መንደር፣ የውጭ መንግስት፣ የኢፈርት ቦርድ፣ የአዜብ ቀሚስ፣ የሳሞራ ቆርቆሮ፣ የቻይና አስፋልት፣ ኢትዮጵያ ፈርስት፣ ልደቱ አያሌው፣ አየለ ጫሚሶ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ የሃምሳ ምርጫዎች ወግ እና ያፍሪካ ሕብረት ሃያ ፎቅ አያድኑትም። በእንደዚህ ዓይነት ጋሻዎች እየተከላከለ ራሱን ከሕዝብ የቁጣ ማእበል ያተረፈ መሪ የትም አልታየም።

 

“ተመልከት! …..ይህ የቡና ቁልል ነው አይደል?”

“አዎ፤ የቡና ቁልል ነው”

“አሁን ጉዱን ላሳይህ”

“እሺ”

“አይንህን ጨፍን”

“ጨፍኛለው”

“ዜሮ!!”

“ዋ! የሚገርም ነው። የት ገባ ያ ሁሉ ቡና?”

“ምላስህ እንዳይቆረጥ!”

እንዲህ ዓይነት አስማትም አያድንም።

 

የመለስ ቦላሌ፣ በሥልጣን ላይ ለመበስበስ የማያደርገው የለም። የጎረቤት ሃገራትን ተቃዋሚ ድርጅቶች ያደራጃል፣ ያሰለጥናል፣ ያስታጥቃል፣ ያፋጃል። የራዲዮ ጣቢያ ይፈቅዳል። በአዋሳ፣ በናዝሬት፣ በድሬዳዋ፣ በአዲስ አበባና በአክሱም ዓመታዊ ስብሰባቸውን ይደግሳል። …..የሊቢያው መሃመድ ጋዳፊ ከዚያ በላይ አድርጓል። ለግብጽ፣ ለቱኒሲያና ለኒ ር የስለላ ድርጅቶችና አፋኝ ባለሥልጣናት፤ ስብሰባ መደገስ አይደለም የተቃዋሚዎቹን አንገት እያነቁ እንዲያመጡለት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከስክሷል። አስፋልትና ሕንጻ ገንብቷል። በመጨረሻዋ ሠዓት ግን ማንም አላተረፈውም። በሕልሙ እንኳ ሊመጡ ከማይፈቅዳቸው ዝርዝሮች ውስጥ በሌለ ቱቦ ውስጥ ተወትፎ ተያዘ። አሁን የጋዳፊን አሟሟት የተመለከተ ቦላሌ፣ በዜጋው ላይ እየቀለደ ለመቀጠል እንዴት ያስችለዋል? ጸጉሩን እየጎተቱ ቂጡን እንዳይዠልጡት፣ ‘ጸጉር የለኝም!’ ብሎ ነው? በመኪና እየጎተቱ እንደ ሃለዊን እንዳይጫወቱበት ማነው የሚከለክላቸው? ጥይት ከማይበሳው ውድ መኪና ውስጥ ሲደበቅ የነበረውን ሰውነት፤ ወደ ሬሳነት ለውጠው ገበያ ውስጥ ቢያሰጡት ውርደት አይደል? ከጎኑ ያሉት ጓደኛ የሚባሉት ሌሎች ቦላሌዎችም ድንበር ጥሰው ሲጠፉ፣ ሲከዱት፣ በየጫካው ሲደበቁ፤ የነሱ እዳ በልጆቻቸውና በሚስቶቻቸው  ርባ ላይ እየሮጠ ሲከመር ማየት ጤንነት ነው?

 

የመለስ ቦላሌ በቅርብ ጊዜ ካመጣቸው ብልጣ ብልጥነት አንዱ፣ “በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከመሪዎች ጋር ሳንሾካሽክ ቪድዮ ቅረጹኝ” ማለቱ ነው። ለዚህም፣ በካኑ ፈረንሳይ ላይ ተካሂዶ በነበረው የግሩፕ ስምንት ስብሰባ ወቅት፣ ከሕንድና ከደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጋር ያደረጋቸው ሹክሹክታዎች እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። የሁለት ወሮበሎች ወግ የተባለው ሰባራ የፕሮፓጋንዳው ማሽንም፣ የቦላሌውን ስማርትነት ለ‘ስማርትነት መፈክር’ አንጋቢዎቹ አሳይቷል። የሚታለሉትና ለማታለል የሚሞክሩትም የፈረደባቸውን እነቅንድቡን ነው። “ኦ! እሳቸው ስማርት ናቸው። የውጭ መሪዎችን በጆሯቸው እየነገሩ ማሳደም ሁሉ ይችላሉ!” ብለውታል። “ከኢንግላንድ ንግሥት ጋር ተጨባበጡ!” የተባለ የፕሮፓጋንዳ ቂል ዜና ሰርተው፣ ቂል ፍለጋ የአየር ሞገዱ ላይ ይሰቃዩ ነበር። “ቦላሌው ረሃብን በኢትዮጵያ ታሪክ ሊያደርግ ነው” ብለው ያስወራሉ፤ ረሃብ ታሪክ ሳይሆን ወደ ጂኦግራፊ መለወጡን ሕዝቡ እያወቀው። …..ቦላሌው አንድ ነገርም ደጋግሞ አሳይቶናል። ከአካባቢ አየር ጥበቃ ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ተጠቅሞ፣ በኤርትራ ላይ ማእቀብ ሲያስጭን። የአፍሪካን አህጉራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የተወከለበትን ወንበር በመሸጥ፤ ኢሳያስ አፈወርቂንና አስተዳደሩን ቀጣለሁ ብሎ በኤርትራ ላይ የማእቀብ ዓይነት ሲያስደራርብባት። የአዶላና የለገደንቢ ወርቅን እንዳሻው ማድረጉን ስለሚያውቅ፤

 

ኤርትራ “ወርቅ ላፍስ ነው!” ባለች ማግስት፣ ያንን ወርቋን እንዳታንቆላልጨው ችግር ሊፈጥርባት ሲፈራገጥ። እንግዲህ ሁለት ቦላሌ አለኝ ተብሎ ሁለት እንጨት ላይ መንጠልጠል አይቻልም! አንዱን መምረጥ ግድ ነው! …..ወይ ኢትዮጵያን ወይ ኤርትራን?

 

አንድ ጓደኛዬ የምርጫ 1997 ሰሞን “የመለስ ቦላሌ ስማርት አይደለም” አለኝ። ምርጫው ካለፈ ጥቂት ዓመት በኋላ “የመለስ ቦላሌ ስማርት ነው” አለኝ። ሰሞኑን ደግሞ የአህባሽ እስላማዊ አስተምህሮ ሲመጣ “የመለስ ቦላሌ ስማርት አይደለም” አለኝ። የመለስ ቦላሌ መቼም ስማርት ሆኖ አያውቅም። በሱ የድርጅትና የመንግሥት መሪነት ዘመን፤ ከፍርሃቱ የተነሳ የብዙ ሰው ሕይወት ጠፍቷል። የብዙ ብሔረሰብ አባላት ታርደዋል። ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ አንዱን ከአንዱ አጨራርሷል። ያ በቂ አይደለም ብሎ ስለሚያምን ረጅሙን የሃይማኖት እልቂት ጎዳና እየ መረው ነው። ከኢትዮጵያ ገበሬ የውጭ ገበሬ፣ ከኢትዮጵያ ዛፍ የውጭ ክብሪት፣ ከኢትዮጵያ እህል የውጭ ሩዝ መርጧል። በኢትዮጵያ መሬት ኢትዮጵያውያንን ሳይሆን ውጪውን መቀለብ ተያይዞታል። ሳትወድ በግድ በረሃብ የምትሰቃይ፣ በረሃቧ ምክንያትም የስድብ ውርጅብኝ ከያቅጣጫው የሚጎርፍባት ኢትዮጵያ፤ ምን እዳ አለባት የሌቦችና የሰዳቢዎቿ ቀለብ ሰፋሪ የምትሆነው? …..ያ፣ የመለስ ቦላሌ ስማርት ላለመሆኑ መደርደር ከምንችላቸው ምክንያቶች መካከል መጨረሻው ላይ የሚጻፈው ነው።

 

የአንድ ሃገር መሪ በየምክንያቱ የሚያስርና የሚገድል ከሆነ፤ እሱ ስማርት አይደለም። ከዙፋኑ ላይ ጎትተው እስኪጥሉት ድረስ ለመዘፍዘፍ ከመረጠ፤ እሱ ስማርት አይደለም። የአንድ ወጣት እድሜ ድረስ ስልጣኑ ላይ ከተሰፋ፤ እሱ ስማርት አይደለም። ሙሉ ጊዜውን የጎረቤት ሃገራት ጉዳይ ላይ ካቃጠለ፣ የሁሉም ነገር መሪ እኔ ብቻ ነኝ ካለ፣ እሱ ብቻ እንዲለፈልፍል ብዙ መድረክና ሰዓት ከሰረቀ፣ ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ካስቆረጠ፣ “በሉ ቻዎ …..ጋምቤላ ሄጃለው” የሚሉ ዓለም አቀፍ ዘራፊዎችን ከሰበሰበ፤ እሱ ስማርት አይደለም። “ከዛሬ  ምሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የደህንነትና የጸጥታ ኃይሎች በአንድ እዝ ስር ተጠቃለው፣ በቦላሌው ስር ሆነዋል! …..ሁልሽም ተጠንቀቂ!!” ካለ፣ በማግስቱም ከተማውን በብረት ለበስ ከባድ መሣሪያዎች ካጥለቀለቀና ዜጋውን በስናይፐር መረፍረፍ ከ መረ፣ እሱ ስማርት አይደለም፤ ገዳይ እንጂ!

 

የመለስ ቦላሌ ይሄንን ሁሉ የሚያደርገውም “ስማርት” ስለሆነ ሳይሆን በአጭሩ ፈሪና መሄጃ ስለሌለው ነው። በምርጫ 1997 ደብረዘይት ሄዶ ተደበቀ የሚባለው የመለስ ቦላሌ፤ እንደው በመጨረሻው የኢትዮጵያ ምርጫ እለት የት ይሆን የሚደበቀው? …..የአይጥ ጉድጓድ ውስጥ? ቃሬዛ ላይ? ሩዋንዳ? …..የት? …..አሜሪካ እንደሆን፣ በታሪኳ ገዳይ መንግሥትን የሚመራ የሰው ሃገር መሪን ተጠቅማበት እንጂ፤ በምድሯ ደብቃ አታውቅም ይባላል። …..ቦላሌው ተስፋ ቁረጥ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ