- የአቶ አለማየሁ አሰፋ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል የፖለቲካ ሃላፊ በደልና ሙስና

- የመ/ር የኔሰው ገብሬ መስዋዕትነትና የወያኔ ቅጥፈት

ዋካ (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በባለፈው ክፍል ሦስት ፅሁፌ ላይ አቶ አለማየሁ አሰፋ በዳዉሮ ዋካ ህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል በግልና በቡድን በመደራጀት የፈፀመዉን ሙስናና  ፈርጀ ብዙ ወንጀል በጥቂቱ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። ዛሬ በዋናነት የሰማዕቱን መምህር የኔሰው ገብሬን ህልፈትና ከህልፈቱም በኋላ የተሰራዉን የወያኔ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዉን በሚመለከት የተወሰኑ እውነታዎችን አስነብባችኋለሁ።

 

መ/ር የኔሰው የአዕምሮ በሽተኛ ነበር የሚል ድራማ ዋና አዘጋጅ የሃገሪቱን ፖለቲካ ከማዕከል ከሚመሩት መካከል እንደሚሆኑ መገመት ቢቻልምው በዳዉሮ ዋካ ግን ዋና አዘጋጅ ከመሆንም በላይ የተገበረው አቶ አለማየሁ  አሰፋ ነው። መቼም አንባቢያን ይሄ ደግሞ ማነው እንደማትሉኝ አምናለሁ። በባለፈው ክፍል ሦስት ጽሁፌ ላይ አስተዋዉቅያችኋለሁ። ከዚያም ወደ መጨረሻው እርሱ በዳዉሮ ህዝብ ላይ ካደረሰው በደል ጥቂት እላለሁ።

 

መቼም አንድ ህዝብን ወክዬ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተመርጬ ለህዝብ ጥቅም እየሰራሁ ነው ከሚል ፖለቲከኛ ባለስልጣን ጎን ለጎን የሰራዉን  ወራዳ ሥራ  ሙስናና ሌብነት መስማት በጣም ዘግናኝ መሆኑን በዉል እረዳለሁ።ቢሆንም አገሪቱ በምን ዓይነት ግለሰቦች እየተመራችና እንዴት ህዝብ ፍትህ አጥቶ እያለቀሰ እንደሚገኝ እኔም  በተጨባጭ አውቀው ስለነበረ በጥቂቱ ለማሳየት አስቤ ነው።

 

ያልታደለች እናት በልጅዋ ታነባለች እንዲሉ ዳዉሮን የሚገዛት የሚያደማትና የሚያስነባት ህዝቧንም እያሰቃየ ያለው ግለሰብና ቡድን ሲመቸው የሚቀማ ዞር ብሎ አልታየሁ ብሎ የሚሰርቅ ሌባ  ከህዝብ አናት ላይ ተቀምጧል።  መንግሥትን እያማና ወረዳ የከለከለው መንግስት ነው እኔ ምን ላድርግ ከአቅሜ በላይ ነው እያለ ኅዝብን ሲያታልል ከርሞ ዛሬ ህዝቡ በደል በዝቶበት ጥያቄውን ሲያመር ራሱን ከተጠያቂነት ለማውጣት ሲል ህዝብ በተቃዋሚዎች ቅስቀሳ በመንግስት ላይ ሳይነሳ አይቀርም የሚል መላምት ፈጥሮ ሌብነቱን በመሸሸግ በስልጣን ላይ ለመሰንበት ሲል መንግሥትን ከህዝብ ያጣላል። መንግሥትም ከህዝብ የሚገናኘውና መረጃ የሚያገኘው ከነዚሁ ሌቦች በመሆኑ እዉነቱን ማወቅ አልቻለም ወይም አልፈለገም ይመስለኛል።

 

የህዝቡ አመፅና ጥያቄን እውነተኛነት ለመረዳት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልከት።  መንግሥትም ሆነ አገሪቱን እየመራ ያለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቡድን  እዉን የዳዉሮ ዋካንና የአካባቢዉን  ህዝብ የልማት የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሎታል ? አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች እዉን እውነተኛ ለህዝብ የሚያስቡና በህዝብ የሚታመኑ የህዝብ ልጆች ናቸው ወይስ በተለያየ ጊዜ ህዝብንና መንግሥትን የዘረፉ ያጭበረበሩና ለህግ የሚያቀርባቸው የህዝብ ወገንተኝነት ያለው እውነተኛ ሥርዓት ያጡ ሌቦች? የዳዉሮ ዋካ ህዝብ ያቀረበው ጥያቄ እውነተኛ የልማትና የዴሞክራሲ የመልካም አስተዳደርና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ አይደለም ወይ?  ይህን ጥያቄ ለጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለማቅረብ የተንቀሳቀሱትን የህዝብ ተወካዮችንና የሃገር ሽማግሌዎችን ትልቅ ወንጀል እንደሰሩ ተቆጥሮ ከርቸሌ ሊያስወረውር ይገባል? ጠቅላይ ሚ/ሩስ ወደ እርሳቸው ቀርበው አላግባብ ተበደልን ልማት አጣን ባለሥልጣኖቻችን በደሉን አልተመቹንም  በሚል አቤቱታ ማቅረባቸው እንደሌባና እንደ ትልቅ ወንጀል ተቆጥሮ  የዳዉሮ ዋካን የአገር ሽማግሌዎች  ለእስር ሲያደርስ ምን አሉ? የህዝብ ጥያቄና በደል መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል የሚል አካል የመንግሥት ወገን ነው ወይስ ጠላት የሚሰኘው?

 

ጥያቄዉን ያቀረቡ የህዝብ ተወካይ የሆኑት አባት ሽማግሌዎች ወደ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ዘንድ ተበደልን ፍትህ ተዛባብን በአቅራቢያችን የነበረው የወረዳ ማዕከል አላግባብ ተነጠቀብን የሚል አቤቱታ በማቅረባቸው ብቻ ወደ በላይ አካል በመቅረብ አጋለጡን በሚልና ጥያቄው ለእነርሱ በደረጃው ሲቀርብላቸው ዉሳኔ ለመስጠት ባልቻሉ ብቃት በሌላቸው የግለሰብ ሎሌዎች ለእስርና እንግልት ሊዳረጉ ይገባል?

 

ዴሞክራሲያዊውን የዋካ ከተማና ዙሪያውን ህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ፍትሃዊ ምላሽ መስጠት ባይፈለግ እንኳ ምላሹ እስር ሊሆን ይገባል? ይህን የፈፀሙ ካድሬዎች እዉን ገዢዉን ፓርቲ በአግባቡ በማገልገል የህዝቡን ጥያቄ እየመለሱ ነው ወይስ ችግር እየፈጠሩ በህዝብና በመንግሥት መካከል ችግር እየፈጠሩ ይሆን? እዉን የመምህር የኔሰው ገብሬ ህይወት ማለፍ ከላይ የተዘረዘሩት የህዝብ ጥያቄዎች ፍትሃዊ ምላሽ ማጣት ወይስ አቶ አለማየሁ አሰፋ በስልክ ታዝዞ  እንዳዘጋጀው ቴያትር የአዕምሮ ህመም ይሆን?  ……. በርካታ አወያይ የሆኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ለእነዚህና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ትክክለኛና ተገቢ ምላሽ መስጠት ሲቻል ነው የህዝብ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ስለመኖሩ ማውራት የሚቻለው።

 

መ/ር የኔሰው ገብሬ ሰማዕት ወይስ የአዕምሮ በሽተኛ?

 

ስለ መ/ር የኔሰው ገብሬ በርካታ ሚድያዎች በወቅቱ የነበረዉን እዉነታ በሚገባ ዘግበዋል። እውነታው ያስደነገጠው ወያኔ ሃርነት ትግራይም እንደዚሁ የኔሰው በሽተኛ ነበርና ነው ራሱን ያቃጠለው የሞተው የሚል የአጠፋ ፕሮፓጋንዳ ሊያካሂድ ሞክሯል። በእውነት አሳዛኝ ነገር ነው። እስቲ አንድ ሁለት ጥያቄዎችን ላንሳ።

 

እብድ ሰው ፖሊስ ጣቢያና ወህኒ ቤት ታስሮ ያውቃል?  አንድ ሰው ፖለቲከኛ ነህ ህዝብን በመንግስት ላይ አነሳስተሃል ተብሎ ታስሮ ሰንብቶ ከዚያም ፍርድ ቤት ቀርቦ ከእስር በማስጠንቀቂያ የተፈታ ይህ ሁሉ ሁኔታ ሲከናወን ጤንኛ የነበረ በአንድ ሌሊት እንዴት እብድ ሊሆን ቻለ?   ራሱን ባያቃጥልና መስዋዕትነትን ባይከፍልስ ኖሮ ምን ይባል ነበር? ሰው ከሞተ በኋላ ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንም ሰዉን ለማሳመን ግን አይቀልም።

 

እንደው የወያኔን ፕሮፓጋንዳ ወሬ እውነት ነው አይደለም የሚል እሰጣ ገባ ዉስጥ ከመግባታችሁ በፊት እውነተኛዉን ነገር ላሳያችሁ። እውነቱ ይህ ነው ። በዳዉሮ ዋካ ህዝባዊ አመፅ ምክንያት በርካታ ሰዎች ታስረው ነበር።የታሰሩትን ግለሰቦች ስንመለከት በመጀመሪያ በፖሊስ የተያዙትና በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ነዋሪነታቸው ዋካ ከተማ ዉስጥ የሆኑና የህዝቡን ጥያቄ ወደ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ዘንድ አቅርባችኋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ነበሩ።

 

እነርሱን ፖሊስ በታዘዘው መሰረት አንድ የእድር አባል አርፈው እያቃበሩ ከነበሩበት ቤተ ክርስቲያን የቀብር ስፍራ ይዞ ሲያስራቸው፤ ህዝቡ በቁጣ በመነሳት አሁንስ በደሉ በዛብን፤ እውነት ነው ብሎ በደላችንን አውቆ መፍትሄ የሚሰጠን ሥርዓት ማጣታችን ሳያንሰን ወክለን ወደ በላይ አካል የላክናቸው ተወካዮቻችን ለምን ይታሰሩብናል በሚል ነው ፖሊስ ጣቢያዉን  የተቆጣጠረው። ዴሞክራሲያዊ ምላሽ አገኛለሁ ብዬ ሲጠብቅ ይባስ ተብሎ መርጬ የላኩኋቸው ተወካዮቼን ማሰር ምን ማለት ነው? ተወካዮቼን አሳስሬ ቤቴ አላድርም ፍቷቸው አሊያም እኔም አብሬ እታሰራለሁ በማለት የፖሊስ ጣቢያውን ዙርያ በመክበብ ሲጠብቃቸው አደረ። የዳውሮ ዋካ ህዝብ ኢትዮጵያዊ መሆኑንና ቆራጡነቱን በዚህ አጋጣሚ አስመሰከሯል።

 

ወጣት መምህር የኔሰው ገብሬም አመፁን ከሚያንቀሳቀሱትና ከሚያስተባብሩት እውጭ  ካደሩት ወጣቶች  መካከል አንዱ ነበር። በመሆኑም በዚህ ተግባሩ ከጓደኞቹ ጋር በፖሊስ ተይዞ በቁጥጥር ሥር እንዲሆን ተደረገ። ልብ በሉ እስካሁን ድረስ ወጣት የኔሰው የአመፅ አስተባባሪ፤ የልማትና የወረዳ ማዕከል ጠያቂ እንጂ የአዕምሮ በሽተኛ አልነበረም። ከበርካታ ጓደኞቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ውሎ በጊዜ ቀጠሮ ወህኒ ወረደ።

 

የመጀመሪያዎቹ የህዝቡን ጥያቄ ወደ በላይ አካል አድርሰው የተመለሱት ያገር ሽማግሌዎች በመታሰራቸው  የተቆጣው ህዝብ ለሁለተኛ ጊዜ ሌሎች ሽማግሌዎችን መርጦ  ወደ አቶ መለስ ዜናዊ ላከ። ሁኔታው ጠንከር ማለቱን የተረዳው መንግሥት በበኩሉ የታሰሩት በቶሎ እንዲፈቱ መመሪያ በስልክ በማተላለፉ በእስር የሚገኙ በርካታ ሰዎች ተለቀቁ። የኔሰው ገብሬም ከተለቀቁት ሰዎች አንዱ ነበር።ከእስር ከተፈታም በኋላ ቀሪዎቹን ጓደኞቹን   ወደ እስር ቤት በመመላለስ እየጠየቃቸውና እያፅናናቸው ይቆያል።

 

በፖሊስ ላለመያዝ ብለው ከዋካ ከተማ ዉጭ እዱርና ገጠር ከሚንከራተቱ በርካታ  ወጣቶች ባሻገር እወህኒ ቤት አብረዉት ታስረው የነበሩ ጓደኞቹ እነ ዳዊት ተፈራ ፣ ሰለሞን ተፈራ፣ ጥራቱና ሌሎችም ወጣቶች በተርጫ ከተማ በሚገኘው የማረቃ ወረዳ ፍ/ቤት በቀጠሮ ቀን ይቀርባሉ። ቀኑ በ2011-11-11 ዓርብ እለት ሲሆን በግምት ከጥዋቱ አራት ሰዓት ይሆናል( በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጥጣጠር ነው) በዕለቱ የኔስውና  አብዛኛው ህዝብ እነዚህ በህዝቡ አመፅ ምክንያት ያለአግባብ የታሰሩት ወጣቶች ይፈታሉ ብሎ ይጠብቅ ነበር።

 

ወንጀል  ያለባቸው ይመስል ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤቱን ጠይቋል በሚል ዳኛው ወጣቶቹን ወደ ወህኒ ቤት እንደገና እንዲመለሱና በእስር እንዲቆዩ ይወስናሉ። በችሎቱ ላይ የነበሩት የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሁሉ በድርጊቱ በጣም ያዝናሉ። መ/ር የኔሰው ገብሬም ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ በወቅቱ በድርጊቱ እጅግ በማዘን ያደረበትን ስሜት በከፍተኛ ተቃውሞ እዚያው ፍ/ቤት መግለፅና መናገር ይጀምራል።

 

ከፍርድ ቤት እንደወጣ ነገሩን አልተወም። ውስጡን እንዳብከነከነውና እንዳስጨነቀው ይቆያል። ከምሳ በኋላ በግምት ወደ ስምንት ሰዓት አካባቢ ለዳዉሮ ዋካ ህዝብ በደልና በአመራሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የተነሳ ራሱን ለመሰዋት ለማድረግ ይወስናል ለዚህም የሚረዳውን ዝግጅት አድርጎ ሲጨርስ ወደ ዳዉሮ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት አመራ።

 

በአዳራሹ ዉስጥ እኚያ  ህዝብን የበደሉት አመራሮች ቁጭ ብለው ሲወያዩ ያገኛቸዋል በድርጊታቸው አንጀቱ ያረረው መምህር የኔሰው ለዚህ ህዝብ ልማትና እድገት የሚወያዩ ይመስል  መቀመጣችሁ አስገርሞት፤ ይህ ህዝብ ትክክለኛ ፍትህ በአግባቡ ማግኘት እንዳልቻለ፤ የልማትና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ፍትሃዊ ጥያቄ እንደነበር፤ የዳውሮ ዞን አመራርና ፍትህ በአቶ አለማየሁ አሰፋ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ፤ የበላይ አካል እንዲሁም ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ጭምር ለዚህ ህዝብ ትኩረት የነፈጉት መሆኑን  ማረጋገጡንና ሙሰኞችና ሌቦች የሆኑትን የዞንና የክልል የፖለቲካ አመራሮች ከህዝብ ጫንቃ ላይ የሚያነሳ እንዲሁም የሚዳኛቸው ሥርዓት እንደሌለ ይናገራል።

 

በዚህም አላበቃም፤ የዚህ ተበዳይ ህዝብ ጉዳይ እጅግ እንዳሳዘነውና በበኩሉ መፍትሄ ነው ብሎ ሊወስድ የተነሳው እርምጃ ራሱን መስዋዕት ማድረግ መሆኑን ገልፆ ወጣቱም ትውልድ የህዝብን ዴሞክራሲያዊ  መብት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል አርማዉን አንስቶ እንዲታገልና ለድል እንዲበቃ መልዕክት በሚገባ አስተላልፎ  አመራሩ ከተሰበሰበበት አዳራሽ በራፍ ላይ በኪሱ በዕቃ ይዞት የነበረዉን ቤንዚን አውጥቶ በላዩ ላይ አርከፍክፎ እራሱን አቃጠለ። ይህ በስብሰባው አዳራሽ ከነበሩትና እሳቱን ለማጥፋት ከተሯሩጡት በኋላም ወደ ተርጫ ሆስፒታል ሲወሰድ በቦታው ከነበሩት ስዎች ያገኘሁት መረጃ  ነው ። እውነቱ ይህ ነው።

 

የህክምናው ሁኔታ በሆስፒታል

 

በደረሰበት ከፍተኛ ቃጠሎ ምክንያት በአቅራቢያው ወደሚገኘው ተርጫ ሆስፒታል ተወሰደ። አልጋ ተስጥቶት እንዲተኛ ተደረገ። ወዲያውኑ ያልተጠበቀና ያልተለመደ ሁኔታ በሆስፒታሉ ዉስጥ መታየት ጀመረ። መ/ር የኔሰው እተኛበት ክፍል ቀርቶ አካባቢው ሰው መድረስ እንዳይችል ተደረገ።

 

ሁኔታዉን በአስተማማኝ መልኩ ለመቆጣጠርና አንድም መረጃ እንዳይወጣ ለማድረግ ከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ታዘዘ። የህክምና ባለሙያዎች ጭምር ጠንከር ያለ መመሪያ ተሰጣቸው። ፎቶግራፍ ማንሳት በፍፁም እንደማይቻል ለሃኪሙ ተነገረው። ሃኪሞችም ሆኑ ረዳቶቻቸው ሞባይል ስልክ ይዘው ወደ የኔሰው ምርመራ ክፍል መግባት እንዳይችሉ ታዘዙ። የአዕምሮ በሽተኛ ከሆነ  ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ?  እውነቱን ለመናገር ይቸገሩ እንጂ ሃኪሞችም ሆኑ ፖሊሶች እኮ የዚያው ህዝብ ልጆች ናቸውና ነገ እውነቱን መመስከራቸው አይቀርም።

 

በተለይ የክስተቱ ወሬ ወደ ማዕከል ከተሰማ በኋላ ይመስላል ከቅዳሜ ጥዋት ጀምሮ ህይወቱ አልፎ ቀብሩ እስከሚፈፀም ድረስ ቁጥጥሩ እጅግ ጠንካራ ነበር። የስልክ መስመር ተዘግቶ ነበር። ያም ሆኖ ይህ እሳት የሚባል የኢትዮጵያ አለኝታ የሆነ ቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ ነባራዊ ሁኔታውን ከሥፍራው ከጅምሩ ጀምሮ ይዘግብ ነበር። እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ለዳዉሮ ዋካ ህዝብ ትልቅ ዉለታ ውሏል።

 

መ/ር የኔሰዉን ቅዳሜ ጥዋት ሄዶ አይቶት የነበረው አንድ ጓደኛዬ በስልክ እንደነገረኝ በጎብኚዎች ላይ ቁጥጥሩ እጅግ የጠበቀው ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ከፍተኛ ህክምና ሊወሰድ እንደሚገባና በሆስፒታሉ አቅም በህክምና ሊረዳ እንደማይቻል ከሃኪሞቹ ከተገለፀ በኋላ ሲሆን በተለይ በኢሳትና በሌሎች ሚድያዎች ጉዳዩ መዘገብ ሲጀምር ቁጥጥሩ የበለጠ እንደጠበቀ መረዳት ችያለሁ።

 

ይህ የሚያሳየን አንድ ትልቅ ነገር አለ። ወያኔ ዘወትር በጎ ሥምና መልካም ገድል እንዲኖረው ነው በውጭው አለም የሚሻው። እንጂ የህዝቡ ችግርና ጥያቄ ምንድነው እንዴት መፍትሄ ያግኝ የሚለው አይደላም የሚያሳስበው። በጣም ያሳዝናል።

 

ማግኘት የሚገባዉን የህክምና እንክክብካቤ ሳያገኝ ነው የየኔሰው ህይወት ያለፈችው።ሆስፒታሉም የገጠር ሆስፒታል ነው። የእሳት ቃጠሎ አደጋን የሚያክም የተለየ የህክምና ክፍልም ሆነ በዚሁ ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ ያለው አይደለም። ለህክምና ወደ ከፍተኛ ሆስፒታል እንዳይሄድና እንዳይታከም የተደረገው ከፖለቲካው አካላት ዉሳኔ ዉጭ ይህ ነበር ብሎ ለማሳመን የሚደረግ ሙከራ ከንቱ ድካም ነው።

 

የአዕምሮ በሽተኛ የነበረ ሰው ራሱን በእሳት ሊያቃጥል ይችል ይሆናል ብለን ማመን እንችላለን። ነገር ግን በሽተኛውን በወዳጅ በጓደኛ በቤተዘመድ ጭምር እንዳይጎበኝ መከልከል ለምን አስፈለገ? እኔ እንደ አንድ የዳዉሮ ማህበረሰብ አባል ከሆስፒታል የወጣ አስከሬን ወደ መኖሪያ ቤቱ ተወስዶ አድሮ ክርስቲያን ከሆነ ሥራዓተ ፀሎት ተደርጎለት ይቀበራል። እውን ይሄ ለምን በየኔሰው የተለየ ሆነ? እብድ ከሆነ ለምን ትሰረ? የተርጫ ወህኒ ቤት አማኑኤል ሆስፒታል መሆኑ ነው? በርካታ እውነታዎችን በማየት ከወያኔ ፕሮፓጋንዳ ጋር ማነፃፀር ይቻላል። ነገር ግን ጥረቱ ከንቱ ነው ሚዛንም አልደፋም።

 

የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን በሚመለከት

 

ህይወቱ ያለፈውና የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የተከናወነው ራሱን ባቃጠለ በሶስተኛው ቀን ሰኞ ዕለት ነበር። በበርካታ ባልተሰለፉ ወታደሮች አስከሬኑ ታጅቦ ወደ ቀብር ሥፍራው አምርቷል። ወታደሮቹ እንደብዛታቸው የደንብ ልብሳቸዉን ለብሰውና ወታደራዊ ማርሽ ቢኖረውና ቢያጅበው ኖሮ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ አንድ የጦር ጄነራል  የመጨረሻ ሽኝት እንጂ የአንድ “አዕምሮ በሽተኛ“ ቀብር አይመስልም ነበር።

 

የየኔሰው ህይወት እልፈት የእግር እሳት የሆነበት የዋካ ከተማ ህዝብ እንኳንና ታሞ ሊጎበኘው ቀርቶ አስክሬኑን እንኳን በክብር ለመሸኘት እንዳይችል መደረጉ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር። የወረዳ ርዕሰ ከተማነትዋን የተነጠቀችው ዋካ የነዋሪዎችዋንና የዙሪያዉን ህዝብ የወረዳ ማዕከልነት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አንግቦ መዋዕትነትን በክብር የከፈለ ልጇን የየኔሰዉን አስከሬን ለመቅበር የለመቻልዋ ደርሶባት የነበረዉን በደል አክብዶባታል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ መቼም ቢሆን የኔሰው ዋካ መቀበሩ አያጠራጥርም። ወደፊት የመታሰቢያም ሃዉልት ጭምር የሚዘጋጅለት ጀግና ወጣት ልጁን ሳይቀብር ቀረ የዳዉሮ ዋካ ህዝብ  የማይረሳ በደል!

 

የዋካ ከተማ ህዝብ በቀብሩ እንዳይገኝና አስከሬኑን እንዳይሸኘው ተፈለገ። ቤንዚን ስለሌለ የትራንስፖርት መኪና ከዋካ ወደ ተርጫ ዛሬ አይሰራም! ተባለና ትራንስፖርት ተቋረጠ  መኪና ቆመ።  ለቀብሩ ከዋካ ከተማ ወደ ተርጫ ለመጓጓዝና አስከሬኑን ቢቻል ዋካ ከተማ አምጥቶ በጀግና ክብር ለመቅበር ካልሆነም እዚያው አስክሬኑን ለመሰናበት  የተዘጋጀው ህዝብ በሙሉ ትራንስፖርት አጥቶ እመንገድ ላይ ቆሞ ሲንከራተት ዋለ። ሁኔታዉን ዘግይቶ የተረዳው የዋካ ከተማ  ህዝብ እርስ በራሱ በጎዳና ላይ እየተላቀሰ እርሙን አውጥቶ እንዳይቀብረው መከልከሉን ተገንዝቦ በከፍተኛ ቁጭት ወደ ቤቱ እንዲመለስ ተደረገ።

 

እውነት ለመናገር ዳዉሮ ነው ወይስ በሌላውም የአገሪቱ ክፍል የሞተ የአዕምሮ በሽተኛ በፖሊስ እየታጀበ  የሚቀበረው? እሳት ያቃጠላቸውና ወደ ሆስፒታል የገቡ በሽተኞችስ ጓደኛና ዘመድ እንዳያያቸው ፎቶግራፍም እንዳይነሱ የተከለከሉበትን ሰምታችኋል? በእርግጥ የዴሞክራሲና የነፃነት የፍትህ የልማትና የመልካም አስተዳደርን ጥያቄ አንስቶ መፍትሄ በማጣቱ ራሱን የቃጠለ ሰው አላልኩም።

 

የመ/ር የኔሰዉን የሰማዕትነት ክብር ስሙን ማነው ጥላሸት ሊቀባው የሞከረው?

 

መምህር የኔሰው ገብሬ እብድ ነበር የሚለው ዜና ምንም ያህል ሚዛን የሚደፋ ያለመሆኑን አይተናል። ኧረ ለመሆኑ የዚህ ድርሰት ዋና አዘጋጅ ማን ይሆን? ከወያኔ የበላይ አመራሮች አንዱ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ። ኧገሌ እንዳልላችሁ አላውቀዉም።

 

ነገር  ግን የዳዉሮው ህዝብ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ጥያቄ አፋኙ አለማየሁ አሰፋ ከአለቆቹ የተቀበለዉን መመሪያ በመቀበል ከሟች መምህር የኔሰው ገብሬ እህት ጀምሮ ከዳውሮ ዞን ፖሊስና ከተርጫ ሆስፒታል ለጨዋታው ይመቻሉ ብሎ ያመነባቸውን ግለሰቦች በመልመልና በማሰልጠን ድራማዉን እዉን አድርጎታል። እንደተረዳሁት አጠቃላይ የዉሸት ፍብረካዉን ፕሮጄክት የመራው እርሱ ነው። ይህንን ሲያደርግ ለወደፊት የስልጣን ዘመኑ ከአለቃው ቡራኬ ያግኝ እንጂ ከዚህ የከፋም ነገር ቢሆን ከማድረግ እንደማይመለስ ያለፈ ታሪኩን ማየት በቂ ነው።

 

በዚህም አድራጎቱ ሳይገታ ከኢትዮጵያ ወጥተው በተለያዩ የዓለም አገሮች በስደትም ሆነ በሌላ ምክንያት የሚኖሩትን የዳዉሮ ልጆች በተቃዋሚዎች የፖለቲካ ድርጅት ዘመዳችሁ ልጃችሁ ወንድማችሁ እህታችሁ… ወዘተ አባል ወይም ደጋፊ በመሆን መንግሥታችንን በኃይል ለመጣል እየሰራ/ች ነው በሚል የፈጠራ ወሬ ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ማስፈራራት እንዲደርስ እያደረገ ይገኛል።

 

በዚህ የተነሳ ብዙዎች የውጭ አገር ነዋሪዎች ቤተሰብ የሆኑት በየወረዳው አስተዳደር ካቢኔዎች በኩል ስልክ ደዉላችሁ ወደ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳትጠጉ ብላችሁ ንገሯቸው  የሚል ማስፈራሪያና መልዕክት አስተላልፏል። መምህር የኔሰው ገብሬ አብዶ ነው የሞተው አስገድደው እንዲያስብሉን ነው ቤተሰቦቻችን እየተጠየቁ ያለው   ይገርማል!

 

ታስታውሱ እንደሆነ በባለፈው ክፍል ሦስት ፅሁፌ አለማየሁ አሰፋ ማነው? ብዬ በመጠኑ ሥራውን ያነሳሁት  ይህ ግለሰብ  የሰማዕቱን ታሪክ ለማደብዘዝ በመሞከር በጥፋት ላይ ጥፋት በበደል ላይ በደል እየፈጸመ ይገኛል። ስለዚሁ የበደል አባት ታሪክ ትንሽ አክዬ   ፅሁፌን ልቋጭ።

 

ከአለማየሁ አሰፋ የበደል ስራዎች ዋና ዋናዎቹ

 

1. የዳዉሮ ዋካን ህዝብ ልጆች በጥላቻ ምክንያት ብቻ ከዳዉሮ ዞን የፖለቲካና የመንግሥት መዋቅር ቀስ በቀስ በሙሉ አስወግዷል። አራት የዞን ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች ቦታንና የዞኑን ዋና አስተዳዳሪና ምክትል አስተዳዳሪዉን ቦታ ለሚፈልገው ሲያድል አንድም የማረቃና የዋካ ህዝብ ምን ይለኛል አይልም። በሰሞኑን መዋቅሩ ስድስት ቁልፍ የፖለቲካና የአስተዳድር የዞን መዋቅር ዋካዊ እንዳይጠጋ አደረገ።

 

ህዝብ የሚፈልገዉን እንደማድረግ ከህዝብ የተተፉትን ወያኔ ካድሬው አድርጓቸው መከራዉን ያያል። ምንም ቢያደርግ ሌብነቱ ሊሸሸግ ከቶ አይችልም። የዋካ ልጆችን ለራስ ፈርቶ ከፖለቲካ ማራቅና ከሥራ ማባረር የትም አያደርስም።

 

ለፈገግታ እንዲሆናችሁ አንድ ቀልድ መሳይ እውነት ልንገራችሁ። አለማየሁ አሰፋ ከአንድ አመት በፊት የዳዉሮ ዞን አስተዳዳሪ የነበረውን ግለሰብ ከሥልጣን ለማንሳትይፈልጋል። ጌታውም አቶ ኃይለ ማርያም ቀጥል ብሎታል መቼም አለሱ ፈቃድ አይሆን። አስተዳዳሪው ከፍተኛ የህዝብ ፍቅር አለው። ሌባ አልነበረም።እሱን ከአስተዳዳሪነት በዘዴ ለማስወገድ ሲል የክልሉ ግብርና ኃላፊ ሊሆን ነው የሚል ወሬ ራሱ ፈጥሮ  በካድሬዎቹ ያስወራል።

 

ትንሽ ጊዜ ቆይቶ ደግሞ አይ አቶ መለስ ዜናዊ ፈልገውታል በከፍተኛ ደረጃ ሊሾም ነው የሚል ወሬ በተመሳሳይ ቻናሉ ይለቃል።ምርጫ 2002 ዓ.ም ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀርበውና መቼም ብቸኛ ተወዳዳሪ ነበርና ተመረጠ ተብሎ አንስቶት በዘዴ ወደ አዲስ አበባ ይልከዋል። በኋላ አቶ አለማየሁ ምን ይላል መሰላችሁ የህዝብ ፍቅርና ህዝባዊ መሠረት ያላቸውን ካነቀልክ መኖር ያስቸግራልና ነው አሁን ሄዶ እዚያ እጁን እያጨበጨበ እንቅልፉን ይለጥጥ ብሎት አረፈው። በስድስቱ የዞን አመራር መሃል አንድ ቀና የሚመስል ሰው ቢኖር እሱንም በዘዴ አባሮት በሙሉ ተቆጣጠረው። ዋካ መወለድ በዘመነ አለማየሁ መከራ ሆኗል። ህዝቡም እንደምታዩት ነው።

 

2. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የዳዉሮን ህዝብ ጥቅምና ኮታ ነጥቀው እወክለዋለሁ  እወደዋለሁ ለሚሉት ህዝብ ሲያደርጉት አቶ አለማየሁ አሰፋ እየተባበራቸው ለመሆኑ ጥርጣሬ አያስፈልግም።  ምሳሌዎችን ላንሳላችሁ።

 

ዳዉሮ ተጨማሪ ወረዳ በጠየቀ ወላይታ አንድ ወረዳ እንኳን ይጨመርልኝ ብሎ ህዝቡ ሳይጠይቅ እንዴት አንድ ጊዜ አምስት ወረዳ ያገኛል? ብሎ የጠየቀ አንድ የዳዉሮ ካድሬ ያየዉን መከራ አልነግራችሁም። ጥገኛ ትምክህተኛ ኪራይ ሰብሳቢ ነፍጠኛ…. ይቅርታ ይሄ ደግሞ የአማራ ደም ኑሯልና..   ብቻ የዳዉሮን ጥቅም አላስጠበቀም። ለዛሬው የህዝብ አምፅና ለተፈጠረው ችግር ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ እርሱ ነው። የህዝቡንም ጥያቄ ያፈነው እርሱ ነው።

 

የግልገል ግቤ ቁ.ሦስት የግድብ ሥራ ፕሮጄክት ላይ የሰራተኛ ቅጥርን በሚመለከት ከወላይታና ከዳዉሮ እኩል የሰው ሃይል ቅጥር እንዲፈጸም የነበረውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው አቶ ኃይለ ማርያም የአስተዳደር ሠራተኞችን ቅጥር እንዳሻቸው እንዲያደርጉ አለማየሁ የህዝቡን መብት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ሥራ አጥ ወገኑን አልረዳም። ወጣቱ የኔሰውም ከጓደኞቹ ጋር ካነሳው ጥያቄ አንዱ ሥራአጥ ሆነናል ተበድለናል የሚል ነበር በደሉ እውነት ነበር።

 

ከዳዉሮ ተርጫ ተነስቶ ጌና ቦሳ ወረዳን አቋርጦ ወደ ከምባታና ጠምባሮ አካባቢ የሚያስኬደዉን የመንገድ ሥራ የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን ፈጥረው በማሳመን የዳዉሮ ህዝብ ወገኖቹ ከሆኑት ህዝቦች እንዳይገናኝ ሆን ተብሎ በወላይታ በኩል ከወላይታ ጋር ብቻ ግንኙነት ይደረግ በሚል የመንገድ ልማቱን እንዲያጣ አቶ ኃይለማርያም ሲያደርግ አለማየሁ አለመቃወሙ ሳያንስ መንገዱ አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊያስረዳ ሲሞክር ያሳዝናል።

 

ኋላቀር በሚባሉ አካባቢዎች የሚሰሩትን የመንግሥት ሠራተኞችን በተለይም ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የሆኑ ባለሙያዎችን የሥራ ትጋት ለመጨመርና ወደ ገጠር ወርደው እንዲሰሩ ለማድረግ ከወጣው የደመወዝ ጭማሪ ጥቅም ከሁሉም የዳዉሮ ወረዳዎች በተለየ ሁኔታ ዋካ ከተማና አካባቢው የነበሩ ባለሙያዎችን ጥቅሙን በማሳጣት አካባቢዉን ባለሙያ አልባ አድርገዉታል። አስታዉሳለሁ አንድ የህክምና ባለሙያ ከተርጫ ሆስፒታል ወደ ሎማ ወረዳ ጥቅሙ ወዳለበት ሄዷል። የወረዳው ባለሙያ ጥቅሙን እንዲያጣና የዋካና የዙሪያው ት/ቤቶች መምህራን አልባ እንዲሆኑ አለማየሁ ሰርቷል። ማስተካከል ይቻለው ነበር። ለርሱ ቀላልም ነበር ግን የህዝቡ በደልና ልማት ስለማይሰማው ነው።

 

3. የዳዉሮ ወጣት በዳዉሮ ዉስጥ በስግሰጋ መልክ እንዳይሰፍር ቀጥታ መመሪያ የሰጠው አለማየሁ ነበር።  በዳዉሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ ዳዉሮ እንዳይሰፍር ከልክሎ  ወላይታ ይስፈር ብሎ የዳዉሮን ህዝብ ጥያቄ ባለመቀበል  የወላይታው ኃይለ ማርያም ጉዳይ አስፈፃሚ መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል አስመስክሯል።

 

4.  ህዝብን መናቅ መሳደብ ማስፈራርትና ማሸበር  ሥራው ነው። አለማየሁ በካድሬዎቹ በ1997ዓ.ም ምርጫዉን ተከትሎ ህዝብ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደተጨፈጨፈ ሁሉ በዋካና በዙሪያው ህዝብ ላይም የመልካም አስተዳደርና የፍትህ የልማትና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ለምን ህዝቡ አቀረበ አፉን ዘግቶ ለምን አይገዛልንም በሚል ምክንያት ብቻ መንግሥት በቀጣይ በህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ እንደሚያካሂድና ሞትን እንደሚረጭበት ለህዝቡ በካድሬዎቹ አንደበት ገልፆላቸዋል። አመፁን ያጋመው ይህ ነበር። እይስፈራሩ መግዛት ሊያከትም እንደሚገባ ህዝቡ ገዢውን ፓርቲ አሳይቶታል።

 

ይገርማችኋል የዳዉሮ ዋካ ህዝብ አዲስ ወረዳ ዛሬ ቢሰጣችሁ ይሻላችኋል ወይስ አለማየሁ አሰፋ ይወገድላችሁ ቢባል እኔ አለማየሁ ተወግዶልን ትንሽ አረፍ እንበል የሚለው የህዝብ ቁጥር የሚበልጥ ይመስለኛል።

 

5. የዳዉሮን ህዝብ የልማትና የወረዳ ጥያቄን በመድፈቅ ህዝቡን ሲረግጥና ሲያስረግጥ የነበረው  አለማየሁ ከጌታው ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተገባለትን ቃል ለሚቀርባቸው ሰዎች ያለአንዳች ፍርሃት መናገር ጀምሯል። የተዘጋጀለት ይዉለታው ክፍያ መደብ ሹመት ሲሆን በአንዱ አገር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሃታሼነት መሆኑን ያወራ ነበር። እስከሚሾም ሎሌነቱን ወደር በሌለው መልኩ መተግበር ይጠበቅበታል። ለዳዉሮ ህዝብ ሰላምና ዴሞክራሲ አለማየሁን በአንዱ አገር አምባሳደር አድርጎት እንኳ ህዝቡን ቶሎ ቢገላግለው ይሻላል።

 

6. በአማራ ህዝብና በአማርኛ ቋንቋ ላይ ያለውን ከባድ ጥላቻ በቃላት መግለጽ በፍፁም አይቻልም። ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ በህዝብ ላይ ያለው ጥላቻው  ከአለቃው ከአቶ በረከት ይበልጣል ብል አላጋነንኩም። የአማርኛ ቋንቋም ሆነ ሙዚቃ በማንኛዉም የደቡብ ኤፍኤም ሬዲዮ በፍፁም እንዳይተላለፍ በደብዳቤ በራሱ ዉሳኔ ማገዱን አውቃለሁ።

 

የሚገርማችሁ ነገር ባለቤቱ አማራ ናት። ልጆቹ የሚናገሩት በአማርኛ የመማሩት ደግሞ  በእንግሊዝኛ  ነው። እርሱ ግን አማራን ከማየት… ይላል እቤቱ አብራውስ የምትኖረዋን ሚስት ምን ይሰማት ይሆን? አይ የአገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች! ወይ አማርኛና የአማራ ደም ያለው መሆን እንደው ይገርማልኮ! እንደው  ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነትና በወንድማማችነት ተቃቅፈው የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን መቼ እናገኝ ይሆን?

 

የዳውሮ ዋካን ህዝብ የአስተአደር በደል፤ ለበደሉ ያደረገውን ትግል፤ ይህንን እነማን እንደፈጸሙበት ምንነታቸውንና ማንነታቸውን፤ እስካሁንም እየቀጠለ ያለውን ያልተቋረጠ የጭካኔ እርምጃ፤ ለዚህም መ/ር የኔስው ገብሬ የፈጸመውን መስዋዕትነት፤ በመስዋዕትነቱ ዙርያ የተፈጸመውን ታላቅ ገድል ሆን ብለው  ስም ማጥፋትና የወያኔ ሹሞችን ዝርክርክነትና ፀረ ህዝባዊነት ለማመላከት በአራት ክፍል ከፍዬ ለንባብ ያበቃሁትን ጽሁፍ በዚህ አጠናቀቅኩ።

 

ሆኖም ይህ ጽሁፍ መላውን የዳውሮ ዋካን ችግር አጠቃሎ የያዘ እንዳልሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። ባጠቃላይ ግን መሰረታዊውን ሁኔታ የሚጠቁም በመሆኑ ወደፊት ከኔ በተሻለ ሁኔታ ለማጥናት ለሚፈልጉና ለሚጽፉ በመንደርደሪያነት ይረዳል የሚል ግምት አለኝ።

 

ደጋግሜ  በሌሎች የህዝብ መገናኛ አውታሮች እንዳስታውኩት ሁሉ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በዳውሮ ዋካና አካባቢው ለብዙ ግዜ የኖርኩ በሥራ አለምም የቆየሁ በትምህርት ሥራ ሃላፊነትም ተመድቤ ህዝብን ያገለገልኩና የአቅሜን አድርጊያለሁ ብዬ የማምን ስሆን በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው የተፈጸመው ሁኔታ ስላነሳሳኝና  በፊት የማውቀውን ጨምሬ፤ ከሃገር ከወጣሁም በኋላ የተፈጸመውን እከታተል ስለነበር ይህንኑ ለአንባቢያን ለማቅረብ የተነሳሁ እንጂ የስነጽሁፍ ሰው ስላልሆንኩ የአማርኛ ግድፈቴን በአግራሞት እንዳታዩት አሳስባለሁ።

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ