የቫቲካን ጥቅም ከኢትዮጵያ ክብር ይልቃል?!
(በኪዳኔ ዓለማየሁ)
ፋሺሽት ኢጣልያን ደግፋ ኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው የሰው ዘር እልቂትና ሌላም ከባድ ጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ በመደጋገም ተጽፎላት አሻፈረኝ ያለቺው የቫቲካን፤ ካቶሊካዊት መንግሥት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው ለመንቀሳቀስ (ለመዝመት ልበለው?) ቆርጣ የተነሳች መሆኑን የሚያመለክቱ ክስተቶች እየታዩ ነው። ለዚህም፤ 1ኛ/ በቫቲካን አማካኝነት አዲስ አበባ ሊከፈት ስለ ታሰበው ግዙፍ የሆነ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ እና 2ኛ/ ሰሞኑን ከፕሬዚዳንት ግርማ ጭምር ተገናኝተው ስለ ነበሩት፤ የቫቲካኑ መሪ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ልዩ ተወካይ፤ ካርዲናል ዲያስ፤ ኦፊሴልያዊ የኢትዮጵያ ጉብኝት በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል።
ትልቁ ጥያቄ፤ በተለይ ባሁኑ ጊዜ፤ ቫቲካን ምን ፍለጋ ወይም ለምን ዓላማ ነው ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረቺው የሚለው ነው። በአንድ በኩል፤ ቫቲካን ለኢትዮጵያ እምብዛም ከበሬታ እንደሌላት ግልጽ የሆነ ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው። በቅርቡ (እ.ኤ.አ በ1935-’41) እንኳ፤ ፋሺሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ወርራ የፈጸመቺው እጅግ አሰቃቂ እልቂት፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በቦምብና በመርዝ ጋዝ ጭምር የተጨፈጨፉት፤ 2000 ቤተክርስቲያኖችና 525፣000 ቤቶች የወደሙት እንዲሁም ሌሎች ከባድ ጥቃቶች የደረሱት በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍና ሙሉ ትብብር ነበር።
ከማይረሱት የፋሺሽት አሰቃቂ ወንጀሎች፤ በአዲስ አበባ ብቻ በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ 30፣000 አትዮጵያውያንን፤ ደብረሊባኖስ ገዳም ውስጥ የነበሩትን መነኮሳትና ካሕናት እንዲሁም አቡነ ጴጥሮስን ያለርሕራሔ መጨፍጨፋቸው ነው። በጊዜው የነበሩት የቫቲካን መሪ፡ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ከግፈኛው ሙሶሊኒ ጋር እጅና ጓንት በመሆን የኢጣልያ ሕዝብ እና የመንግሥታት ሕብረት (League of Nations) የተሰኘው ድርጅት ፋሺሽቶችን በመርዳት፤ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን እልቂት እንዲደግፉ አድርገዋል።
የፋሺሽቱ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ሲዘምት በቫቲካን ተወካዮች ሙሉ ቡራኬ ተሰጥቶት ነው የተሸኘው። የፋሺሽቱ ጦር ለጊዜው ያሸነፈ መስሎት አዲስ አበባ ሲደርስ፤ የደስታ መግለጫ ካቀረቡት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አንዱ የቫቲካኑ መሪ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ነበሩ። በተጨማሪም፤ የቱሪኖ ሊቀጳጳስ የነበሩት ባሰሙት መልእክት፤ አረመኔ የሆኑትን ኢትዮጵያውያንን ወደ ካቶሊክነት መለወጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው ነበር። ይህ አባባል የሚያስገርምበት ምክንያት፤ በሐዋርያት ሥራ ም/8 ከቁጥር 26 እስከ 39 እንደሚነበበውና በትውፊትም እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያውያን ክርሰቲያንነት የጀመሩት ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በጥቂት ወሮች ውስጥ፤ ማለት በ34 ዓ/ም ነበር።
ኢትዮጵያዊው የገንዘብ ሚኒስትር ከኢየሩሳሌም መልስ በሠረገላ ሆኖ ጋዛ ውስጥ ሲጓዝ፤ ፊልጶስ እንዳጠመቀው ተጽፏል። ለመሆኑ በዚያን ዘመን የኢጣልያኖቹ የጥንት አባቶች፤ ሮማውያን፤ ምን እያደረጉ ነበር? ሐዋርያትን እያሳደዱ እያሰቃዩ ይገድሉ አልነበሩምን? ኢየሱስ ክርስቶስንስ ሮማውያን አልነበሩም፤ አይሑዶችን ለማስደሰት ሲሉ፤ አሰቃይተው፤ ሰቅለው የገደሉት? አይሑዶች ኢየሱስ እንዲሰቀል ቢጮሁም ድርጊቱን የፈጸሙት የኢጣልያኖች አባቶች ሮማውያን እንደነበሩ የማይካድ ሐቅ ነው።
ታዲያ ክርስቲያንነቱንም ሆነ እስላምነቱን ከጥንት ጀምሮ የተቀበሉትን ኢትዮጵያውያንን፤ አረመኔዎች ናቸው ማለት አያሰገርምም?! ፋሺሽቶችን በመደገፍ፤ ቫቲካን በኢትዮጵያ ላይ ላደረሰቺው ከፍተኛ በደል የኢትዮጵያን ሕዝብ ይፋዊ የሆነ ይቅርታ እንድትጠይቅ በመደጋገም ቢጻፍላትም እስካሁን ጆሮ ዳባ ብላለች። አይሑዶችን ግን በመደጋገም ይቅርታ ጠይቃለች። ይኸንንም ያደረገቺው፤ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰቺውን በደል ያህል ፈጽማ ሳይሆን፤ የጀርመን ናዚዎች አይሑዶችን ሲጨፈጭፉ የተቃውሞ ድምጽ ባለማሰማቷ ብቻ ነው።
ያሁኑ የቫቲካን መሪ፤ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ከሶስት ዓመት በፊት እንደ ተመረጡ ከመጀመሪያ ድርጊታቸው አንዱ የሆነው የትውልድ ሐገራቸው ጀርመን ውስጥ በምትገኘው፤ ኮሎኝ ከተማ ባለው ምኩራብ (ሲናጎግ) በመሔድ አይሑዶችን ይቅርታ መጠየቅ ነበር። በዚያኑ ጊዜ፤ ሁለት ኢትዮጵያውያን ለብፁእነታቸው በቀጥታ እና ዋሺንግተን ዲ.ሲ. በሚገኘው የቫቲካን ኤምባሲ አማካኝነት ደብዳቤ በመጻፍ የኢትዮጵያን ሕዝብም በተመሳሳይ ክርስቲያናዊ ተግባር ይቅርታ እንዲጠይቁ አመልክተው ነበር።
ነገር ግን ከብፁእነታቸው አንዳችም መልስ ሳይገኝ ቀርቷል! ታዲያ፤ ቫቲካን አይሑዶችን ይቅርታ እየጠየቀች ኢትዮጵያውያንን ይቅርታ የማትጠይቅበት ምክንያት ምን ይሆን? ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በመሆኗ ይሆን? ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኗ፤ ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ እንዲደረግ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ለአውሮፓ እና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅቶችና ለአንዳንድ መንግሥታት የሚቀርብ አቤቱታ በብዙ ሰዎች እየተፈረመ ነው። ይህንን ተግባር እያከናወነ ያለው፤ “ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ” የተሰኘ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ካከናወናቸው ተጨባጭ ተግባሮች አንዱ፤ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ በቅርቡ አሜሪካን ሲጎበኙ በነበረበት ጊዜ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ስለ መጠየቁ ከባድ ጉዳይ እንደ ገና በማሳሰብ ሌላ ደብዳቤ አቅርቦላቸው መልስ ሳይገኝ ቀረ።
ስለ ድርጅቱ ዓላማና ተግባሮች ግንዛቤ ለማግኘት www.globalallianceforethiopia.org የተሰኘውን ድረ-ገጽ መጎብኘት ይቻላል። ቫቲካን ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር የምትንቀሳቀስበት ምክንያት ምን ይሆን? ለኢትዮጵያ ክብር ደንታ የሌላት ከሆነ ሌላው ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል መላምት ካቶሊክነትን ለማሰፋፋት መሆኑ ብዙ የሚያከራክር አይመስልም።
ኢትዮጵያን የካቶሊክ እምነት ተከታይ ለማድረግ ሲሞከር ይህ የመጀመሪያው አይሆንም። ቀደም ሲል፤ በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ የካቶሊክ ሃይማኖትን እንድትቀበል በተደረገው ጥረት ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዳለቁ የታወቀ ነው። ያኔም ቢሆን ዛሬ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሐገሩና በሃይማኖቱ የሚመጣበትን በማር የተሸፈነ መርዝ መቼም ቢሆን አይቀበልም። ስለዚህ፤ የቫቲካንን የሰሞኑ ሙከራ የሚመለከቱ ሁሉ መመለስ ያለባቸው መሠረታዊ ጥያቄ፤ ለውድ ሐገራችን ለኢትዮጵያ የሚበልጥባት የቱ ነው፡ ክብሯ ወይስ ጊዜያዊ ጥቅም? የሚለው ነው።
የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት በደማቸው ላቆዩልን ጀግኖቻችን ጥቂት እንኳ የምናስብ ከሆነ ፋሺሽቶችን ደግፋ ለደረሰው እልቂት ይቅርታ ሳትጠይቅ ከቫቲካን የሚገኘው ጥቅም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ከባድ ድፍረት የሚቆጠር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ያሁኑንም ትውልድ “እሳት ይወልዳል አመድ” ሊያሰኝ እንደሚችል ማሰብ ይገባናል።
“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሐ ሀበ እግዚአብሔር” (መዝሙር 68/31)



