“ልጄ እንደ አባቱ የነፃነት ታጋይ እንደሚሆን አምናለሁ” ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል
ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ነች። በምርጫ 97 ወደ ወህኒ ቤት ከተላኩት ጋዜጠኞች ውስጥም አንዷ ነበረች። ወደ 18 ወራት በእስር ቤት ቆይታለች። የወለደችውም በወህኒ ቤት በታሰረችበት ወቅት ሲሆን፣ ሕፃኑ ሲወለድ ከክብደት በታች በመሆኑ ማሞቂያ ወይንም ኢንኩቤተር ውስጥ እንዲገባ በፖሊስ ሆስፒታል ሐኪሞች ተወሰነ። የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ግን ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሕፃን ናፍቆት እስክንድር ማሞቂያ ውስጥ እንዳይገባ ፈረዱበት።
ማሞቂያው ያለው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመሆኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕፃኑን ለማስገባት ከወላጆቹ አንዳቸው መፈረም የግድ ይላል። ሰርካለም ፖሊስ ሆስፒታል በመተኛቷ ሄዳ መፈረም አልቻለችም። እሰክንድር ደግሞ እስር ቤት በመሆኑ ሄዶ እንዲፈርም በእስር ቤቱ ኃላፊዎች አልተፈቀዱለትም። እናም ሕፃኑ ማሞቂያ ውስጥ ሳይገባ ቀረ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ እና በፍጹም ጤና አደገ።
ባለፈው ሰኔ 12 የአምስተኛ ዓመት ሻማውን ለኮሰ። ወደ ስድስተኛ ዓመቱ ጉዞ ሲጀምር መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. አባቱ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በታጣቂዎች ተያዘ። ሕፃኑ ናፍቆት እያያ እና እያለቀሰ ታጣቂዎቹ እስክንድርን በሰንሰለት አስረው ወሰዱት። እስክንድር በ20 የኢህአዴግ የሥልጣን ዓመታት ለ8ኛ ግዜ ወህኒ ተጥሎ በጭለማ ቤት ውስጥ ከጭለማ መልዕክተኞች ጋር ተፋጧል።
ናፍቆት ዛሬ አባቱ የት እንዳለ እናቱን ይጠይቃል፤ በዚህ ዕድሜው ጥላቻን ጸንሶ እንዳያድግ እናቱ ሰርካለም በጥንቃቄ እያስታመመችው ነው። አባቱ ውጭ ሀገር መሄዱን እና በቅርቡም እንደሚመጣ እየነገረችው በተስፋ ይዛዋለች። ሆኖም እንደአባቱ የሠላም እና የነፃነት አርበኛ እንዲሆን አጥብቃ እንደምትሻ ሰርካለም በቀጣዩ ጽሑፏ ገልጻለች። ጽሑፉ የተገኘው ሀገር ቤት ከሚታተመው ”አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ነው። ... የሰርካለምን ሙሉ ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!



