ጃኬት አስወላቂው ጠቅላይ ሚኒስትራችን
ሰሞኑን፣ አንድ ግሩም መፅሐፍ እያነበብኹኝ ነው፡፡ ባለፈው አርብ ነው የወጣው፡፡ በዳንኤል ተፈራ የተፃፈና በዶ/ር ነጋሳ ጊዳዳ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ይዟል፡፡ አንድ ስሜቴን የኮረኮረውን ነገር ላካፍላችኹ ወድጃለኹ፡፡
እንዲህ ይነበባል (ከገፅ 24ዐ የተወሰደ)፡-
በመቀሌ የተካሄደው የሕወኃት ካድሬዎች ስብሰባ እንደተጠናቀቀ የተወሰደውን እርምጃ (እነ ስዬን ማባረር) ለኢህአዴግ ም/ቤት ለማቅረብ አባል ፓርቲዎች የተገኙበት ስብሰባ ተጠርቶ ነበር፡፡ ለእማኝነትም የሽማግሌዎችን ቡድን ይዘው መጥተው ነበር፡፡ የዛን ቀን መለስ ከፊት ለፊታችን ተቀምጦ ሪፖርት ሲያደርግ እየፎከረ ነበር፡፡ ስለ መቀሌ ውሳኔ ሲናገር «ጃኬታቸውን አስወልቀን ራቁታቸውን አባረርናቸው!» ነበር ያለው፡፡
ያን ጊዜ ንግግሩ አንድ ነገር አስታውሶኝ፣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በተመስጦ እያየኹት ነበር፡፡ የግንቦት 2ዐ በዓል በተከበረ ቁጥር የሚታዩ የደርግ ፊልሞች አሉ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ የኢህአዴግ ሰራዊት ሰሜን ሸዋ የደረሰ ጊዜ፣ መንግስቱ አ.አ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተማሪዎችን ሰብስቦ «ቂጣቸውን በሳንጃ!...» እያለ ነውረኛ ፉከራ ሲያሰማ የሚያሳይ ፊልም አንዱ ነው፡፡ መለስም «ጃኬታቸውን አስወልቀን!...» እያለ ሲፎክር ሳይ የመንግስቱ ፉከራ ትውስ ብሎኝ እጄን አነሳሁና «አስተያየት!» አልኩኝ፡፡ አከል አድርጌም «ይቅርታ!» አነጋገርህ መንግስቱ ኃ/ማርያምን አስታወሰኝ፡፡ «መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ!» አልኩት፡፡ ቤቱ በድንጋጤ ተናወፀ፡፡ በተለይ ከጎኔ ተቀምጣ የነበረችው ገነት ዘውዴ «እንዴት ከመንግስቱ ጋር ታወዳድረዋለህ?» ብላ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ ቤቱ ቀውጢ ሆነ፡፡ «ይቅርታ አድርጉልኝና አነጋገሩ ደስ ስላላለኝ ነው፡፡ ደግሞም መንግስቱን መሰልከኝ እንጂ ነህ አላልኩም» ስል ነበር ትንሽ ቤቱ የተረጋጋው፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የነጋሶ መንገድ፣ በዳንኤል ተፈራ፣
ከሚለው አዲስ መፅሐፍ የተወሰደ፡፡
¯¯¯«ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፣» ብለው ተርተዋል አበው፡፡ ከልምድ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ዓመት የራሱ ጉድ አለው፡፡ እያንዳንዱ ዓመት ዝናው ሲነገርለት የሚኖር ጉደኛ እንዳለው አላውቅም፡፡ አንዳንድ ዘመኖች ግን ተወርቶላቸው የማያልቁ ጉደኞች አሏቸው፡፡
አለቃ ገብረሃና እንዲህ አይነት ሰው ይመስሉኛል፡፡ ስንቱ ተነግሮ ያልቃል ስለ እሳቸው? እኔ በግሌ የምወደው የቤተመንግሥት ገጠመኛቸውን ነው፡፡
እንዲህ ነው፡፡
ግብዣ ይጠራሉ፡፡ እንደወትሯቸው ለብሰው ቤተመንግሥት ጎራ ሲሉ፣ በር ላይ ይከለክሏቸዋል፡፡ አለባበሳቸው ነበር ችግሩ፡፡ ተንደርድረው ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በግነዋል፡፡ «ጨዋ» መስለው ይመለሳሉ፡፡ ያለምንም ችግር ሰተት ብለው ይገባሉ፡፡ ጥሩ ቦታም ይሰጣቸዋል፡፡
ከግራም ከቀኙም ጨዋታው ደርቷል፡፡ ጮማው በየሳህኑ ተከምሯል፡፡ ጥጥ ይመስላል፡፡ ጠጁ ይንቆረቆራል፡፡ ድል ያለ ድግስ ቀልጧል፡፡ አስተናጋጆች ተሯሩጠው የእጅ ውሃ አቀረቡላቸው፡፡ ሁለት እጃቸውን አልሰጧቸውም፡፡ ቀኝ እጃቸውን ብቻ ታጠቡ፡፡
ሳህን ቀረበ፡፡ እንጀራ ቀጠለ፡፡ ሁለት ትላልቅ ቁርጥ አነሱ፡፡ ቀይ ወጥ ጨለፉ፡፡ ከአልጫውም ተደረገ፡፡ ሽንጡን ተሸክመው ነው የመጡት፡፡ የቤተመንግሥት ነገር፡፡ ቢለዋ ተሰጣቸው፡፡ ብድግ ብለው ከወደቀዩ ቆረጡ፡፡
«ብሉ እንጂ፣» አሏቸው ከጎናቸው የተቀመጡ አንድ ጨዋ፡፡
«እሺ፣» አሉ አለቃ፤ እንጀራ እየቆረሱ፡፡
ከወደቀዩ ጀመሩ፡፡ አጠቃለላቸው ያምራል፡፡ ብድግ አደረጉ፡፡ እጃቸውን... ወደ.... ወደ.... ወደ ኪሳቸው ላኩት፡፡ ኪሳቸውን አጎረሱት!!
አጠገባቸው የነበሩት ክው ብለው ባሉበት ደርቀው ቀሩ፡፡ ጨዋታቸውን አቆሙ፡፡ አለቃ ቀጠሉ፡፡ አሁን ደግሞ፣ ከወደ ነጩ፡፡ ኪሳቸው ዛሬ አለፈለት፡፡ በላይ በላዩ እየጎረሰ ነው፡፡ አዳራሹ በፀጥታ ተዋጠ፡፡ ዓይኖች ሁሉ በአለቃ ላይ አርፈዋል፡፡
«እንዴ፣ ምን ነካዎት?» ብሎ ጠየቃቸው፤ ተንደርድሮ አጠገባቸው የደረሰ አንድ አስተናጋጅ፡፡
«ምን ነው?» አሉት፤ ቀና ብለው፡፡
«የሚሰሩት ነዋ!» አላቸው ፊቱን ቋጥሮ፡፡ የጌታው ድግስ እየተበላሸ ነው፡፡
«የሚበላው ማለትህ ነው?» አሉት፤ ፈገግ ብለው፡፡ «የተጋበዘው እሱ እንጂ እኔ መች ሆኜ?»
እንደአለቃ ዓይነቶቹ «ጉደኞች» የሕብረተሰቡ ሕሊና ናቸው፡፡ የሞራል እሴቶች ይገለፁባቸዋል፡፡ እያዝናኑ ያስተምራሉ፡፡ በአርአያነት የተቀረፁ ናቸው፡፡ በምሳሌ ያስተምራሉ፣ ይመክራሉ፣ ይገስፃሉ፡፡ ሕፃኑም ትልቁም እኩል ይረዳቸዋል፡፡ ትውልድ ይማርባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአለቃ ጋር የሚመሳሰሉባቸው ብዙ ነገሮች የሉም፡፡ አለቃ፣ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ውጤት ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርት ያውቃሉ፣ ግዕዝ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ መለስ ግን፣ ከኢትዮጵያ የወሰዱት እምብዛም ነው፡፡ ሁለመናቸው ከፈረንጆች የተቀዳ ነው፤ እንደብዙዎቹ የያ ትውልድ አባላት፡፡ አለቃ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ነበሩ፡፡ መለስ፣ ማንንም አይፈሩም፡፡ (ከአዜብ በስተቀር ቂ... ቂ.... ቂ... ይቺ ቀልድ መሆኗ ነው፡፡) አለቃ፣ ከሚጠሉት የሚወዱት ያመዝናል፡፡ መለስ፣ ከሚወዱት የሚጠሉት ይበዛል፡፡ ብዙ ብዙ ልዩነቶች አላቸው፡፡
በአንድ ነገር ግን ይመሳሰላሉ፡፡ ሁለቱም በተናገሯቸው ቃላቶች ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ የመለስ ብዙውን ጊዜ በአርአያነትና በጥሩ ነገር የሚታወስ ባይሆንም፡፡
መስከረም ሳይጠባ ከመለስ ጉድ መሰማት የጀመርነው ገና ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት አንስቶ ነበር፡፡ ሕወኃት ትግራይን ነፃ እንዳወጣ ወደ ሊቢያ ጎራ ብለው ነበር፤ በሻዕቢያ አቅራቢነት፡፡ ጋዳፊ ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል፡፡ «እኛ የመናዊያን ነን፣» አሏቸው መለስ፡፡ ጋዳፊ በደስታ ከነፉ፡፡ ለካ ኢትዮጵያዊያንም አረቦች ናቸው፡፡ ኪሳቸው ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ መለስ እስከዛሬ ድረስ ይስቃሉ፡፡ ብዙ ሰዎችም አብረዋቸው ይስቃሉ፡፡
«ባንዲራ ጨርቅ ነው፣» ሲሉ ግን ማንም አልሳቀም፡፡ እንዲያውም፣ ብዙዎች ለኢትዮጵያ አለቀሱላት፡፡ በአባባሉ የጊዜው አደጋ ተገልጾበታል፡፡
«ለወላይታ አክሱም ምኑ ነው?» ያሉ ጊዜ ሕዝቡ አዝኗል፡፡ ለተዳከመው ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነበርና፡፡
ቀጠሉና፣ «መሃይምም ሚኒስትር መሆን ይችላል፣» ብለው አረፉት፡፡ የኢሕአዴግን ፕሮግራም ካስፈፀመ ሌላው ትርፍ ነው ብለው እቅጩን ነገሩን፡፡ ድንኳን ጥለው ለማልቀስ የከጀላቸው ነበሩ፡፡ ዓለም ግን ሳቀብን፡፡ አይ አፍሪቃ! ጉድሽ መቼ ነው የሚያልቀው?
ሌላም ሌላም ብለዋል፡፡ ብዘረዝረው ብዙ ነው የሚሆነው፡፡ በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ነገር ጣል ያደርጉልናል፡፡ እሳቸውም እኛም ሱስ ሆኖብናል፡፡ በቅርቡ እንኳን፣ ከምርጫ 2ዐዐ2 በኋላ፣ «ኢሕአዴግ፣ በፓርላማ ያለውን መቀመጫ በሙሉ ማሸነፉ፣ ዲሞክራሲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለመጠናከሩ ማስረጃ ነው፣» ብለውናል፡፡ ዓይናቸው እንኳን አልተርገበገበም፡፡ ይሄ አልበቃ ብሏቸው ደግሞ፣ «ዲሞክራሲያችን ለኢሰፓ አባላት እንኳን የተትረፈረፈ ነው፣» ብለው ጨምረውልናል፡፡ ምርቃት መሆኗ ነው፡፡ ክረምቷን የምንወጣባት፡፡
ይሄ ሁሉ በአደባባይ የተነገረ ነው፡፡ ከመጋረጃ በስተጀርባ ተጨማሪ እንደሚኖሩ ስንገምት ኖረናል፡፡ ያልጠረጠርነው፣ «በምርጫ ካርዳችን ደግመን ደጋግመን የመረጥናቸው» ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጃኬት አስወላቂ መሆናቸውን ነው፡፡
እድሜ ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ባለፈው ዓርብ እኝህን ጃኬት አስወላቂ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ተዋውቀናቸዋል፡፡
ይቀጥላል
ፀሐፊውን ለማግኘት፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



