እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ) 

 ባለፈው ሳምንት እንዳይታተም ከተከለከለው መፅሐፋችን (ፀሐፊዎቹ እኔና ሠርክዓለም ፋሲል ነን) የተወሰነ ቀንጭቤ ማቅረቤ ይታወሳል። የተቀነጨበው ፅሑፍ የሚተነትነው በምርጫ 97 ሳቢያ የተጨፈጨፉትን ንፁሃን ዜጐች ጉዳይ እንዲመረምር በፓርላማ ተቋቁሞ የነበረው አጣሪ ኮሚሽን፣ በወህኒ ቤት ተገኝቶ የቅንጅት አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ያነጋገረበትን ታሪካዊ ስብሰባ ነው።

 

 

የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት እስረኞቹን ከሰበሰቡ በኋላ ንግግር በማሰማት ጀመሩ።  

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 በመጀመሪያ ልንጠይቃችሁ የምንፈልገው፣ ይህ ስብሰባ በቪዲዮ ይቀረፅ ወይስ አይቀረፅ? የሚል ነው።

 / ብርሃኑ ነጋ

 ወደዚህ ስብሰባ ከመምጣችን በፊት፣ ለመነጋገር ዕድል አላገኘንም። ማን እንደሆናችኹ አናውቅም። አልተነጋገርንም። ለምን እንደመጣችሁ አናውቅም። የተወሰነ ጊዜ ስጡንና እንነጋገር።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 ለምን እንደመጣን እንነግራችኋለን። ከዚያ በፊት ግን ራሳችንን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን።

1. እኔ፣ ፍሬህይወት ሳሙኤል እባላለኹ። በደቡብ ክልል የጠ//ቤት / ነኝ። የአጣሪ ኮሚሽኑ / ነኝ።

2. አቶ ወልደሚካኤል መሸሻ፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ምክትል / ናቸው።

3. አባ ኤዋስጣጢዮስ /ክርስቶስ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀጳጳስ ናቸው። የኮሚሽኑ አባል ናቸው።

4. ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፣ ፕሮቴስታንት፣ የኮሚሽኑ አባል።

5. / ሐረገወይን ጣሰው፣ በፌዴራል አገር ውስጥ ገቢ፣ ዐቃቤ ህግ ናቸው። የኮሚሽኑ አባል።

6. ምትኩ ተሾመ፣ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የኮሚሽኑ አባል።

7. / መኮንን ዲሳሳ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ የኮሚሽኑ አባል። የኮሚሽኑ አባላት እኛ ብቻ አይደለንም። ሌሎቹ ሥራ ስለተደራረበባቸው መምጣት አልቻሉም።

 ይህ ኮሚሽን የተቋቋመው በአዋጅ ቁጥር 478 1998 . መሠረት ነው። አዋጁ «በሰኔና በጥቅምት በተነሱት ግርግር፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ መሆኑን ማጣራት» ነው የሚለው። ኮሚሽኑ 11 አባላት አሉት። ዛሬ እዚህ የተገኘነው 7ሰዎች ነን። ጠዋት ነበር ለመምጣት ያቀድነው። አልተሳካልንም። ሥራችንን ለመሥራት ቅፅ አዘጋጅተናል። እዚህ የመጣነው ይሄን ቅፅ ልንሰጣችኹ ነው። የምትሰጡን መረጃ ካለ ልንቀበላችኹ ነው። ወደእናንተ ከመምጣታችን በፊት፣ ከዕድር ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረናል። ከእነሱ ጋር ተከታታይ ስብሰባ አድርገናል። በእኛ በኩል፣ ስለተከሰተው ችግር ብዙ ልታስረዱን ትችላላችሁ ብለን ገምተናል። ሆስፒታሎች አነጋግረናል። ሆስፒታሎችን ብቻ ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ 560 የህክምና ተቋማትን አነጋግረናል። ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር የተከሰተ ችግር አለ ወይ? የሚጠቅመን መረጃ ካለ፣ እንድትሰጡን ነው የመጣነው።

 / ብርሃኑ ነጋ ምላሽ ሊሰጧቸው ብድግ አሉ።

 / ብርሃኑ ነጋ

 ሰምተናችኋል። ቅድም ባልነው መሠረት፣ ለመነጋገር ምንም ዕድል ስላላገኘን፣ ለመወያየት ትንሽ ጊዜ ስጡን።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 ቅፅ አለ። ቅፁን እያንዳንዳችኹ ናችሁ የምትሞሉት (የምትነጋገሩበት ምክንያት የለም ዓይነት መንፈስ ይታይባቸዋል)

 / ብርሃኑ ነጋ

 «ችግሩን ፈጥራችኋል» ተብለን ተከሰናል። እኛ በበኩላችን ደግሞ፣ «ችግሩን ፈጥረዋል» የምንላቸው ሰዎች ናቸው እናንተን የመረጧችኹ። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ያደርገዋል። መነጋገር አለብን።

 የአጣሪ ኮምሽኑ ሰብሳቢ

 ቅፁን ውሰዱና እዩት።

 / ብርሃኑ ነጋ (አቋርጠዋቸው)

 እሺ አልን እኮ። ቅፁን አሳዩን። የመጣችሁበትን ምክንያት ነግራችኹናል። ማን እንደሆናችኹ አውቀናል። ትንሽ ጊዜ ደግሞ ለእኛ ስጡን።

 ብርቱካን ሚዲቅሳ

 አዋጁንም ማየት እንፈልጋለን።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 ጥሩ፡፡ ትንሽ ጊዜ እንሰጣችኊለን። አዋጁንም ማየት ትችላላችሁ። 10 ደቂቃ በኋላ እንመለሳለን።

ሰብሳቢው ሲወስኑ፣ የኮሚሽኑ አባላትን አላማከሩም። ሁሉም ብድግ ብለው ወጡ። ከመጋረጃው በስተጀርባ ባለው አዳራሸ ቆይተው ይሁን፣ ወይም ደግሞ ከአዳራሹ ውጭ ይውጡ አላወቅንም። «ከመጋረጃው በስተጀርባ መሆናቸው ይታይ» የሚል አንድ ድምፅ ከመ ከላችን ተሰማ። «ተው፣ተው» የሚለው ስለበዛ ግን፣ የትም አልደረሰም። / ብርሃኑ ነጋ ከተቀመጡበት ብድግ ብለው (ፊት ወንበር ላይ ነው የሚቀመጡት) ፊታቸውን ወደእኛ አዞሩ።

 / ብርሃኑ ነጋ

 ጊዜ የለንም፡፡ ያለችን 10 ደቂቃ ነች። አጠር አጠር ያለ አስተያየት መሰንዘር ትችላላችኹ።

/ ብርሃኑ ነጋ ይህንን ተናግረው እንደጨረሱ፣ ብዙ ተከሳሾች እጃቸውን አወጡ። ለመናገር ዕድል የተሰጣቸው አንድ ተከሳሽ እንዲህ አሉ

 አንደኛ ተናጋሪ

 ይህንን ኮሚሽን ህዝቡና ተቃዋሚዎች እውቅና አልሰጠውም። ሲቋቋም በፓርላማ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ቅሬታቸውን ገልፀዋል። እኛን ለማነጋገር የመጡት በህዝብ ዘንድ አመኔታ እንድናሳድርላቸው ነው።

 ሁለተኛ ተናጋሪ

 ከዚህ አጣሪ ኮሚሽን 6 ሰዎች ለቀዋል። የለቀቁበት ምክንያት በቴሌቪዥን በግልፅ አልተነገረም። ኮሚሽኑን የለቀቁት ነፃ ይሆናል ብለው ስላላመኑ ብቻ ነው።

ከዚህ በኋላ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለመናገር ከተቀመጡበት ብድግ አሉ።

 / መሥፍን ወልደማርያም

 ለየት ያለ ሃሳብ አለኝ። ወደድንም ጠላንም ተሹመዋል። ባለመናገር የምናተርፈው ነገር የለም። ምንም ቢጠይቁን መናገር አለብን። በእኔ በኩል፣ ማንም ቢጠይቀኝ፣ ምላሽ እሰጣለኹ። እውነቱን ለመናገር ዕድሉን መጠቀም አለብን። ፖለቲካ ውስጥ ሳንገባ፣ ከሰብዓዊ መብት አኳያ ብቻ ያለውን ጉዳይ መናገር እንችላለን፡፡ ቅፁን ሳየው፣ ይህንን በመሙላት የምንጐዳው ነገር የለም።

 ፕሮፌሰር መሥፍን የተናገሩት ነገር የሁሉንም ተከሳሾች ስሜት ስለነካ፣ በተበታተነ መልኩ ለመናገር ዕድል እንዲሰጣቸው ለማሳየት ተቀስፈው የነበሩት እጆች እንደድንገት ጫካ ሆኑ።

 ቀጥሎ ዕድል የተሰጣቸው፡-

 ሶስተኛ ተናጋሪ

 /ቤት አንከራከርም ብለናል። ፍትህ አናገኝም ብለናል። በመርህ ደረጃ መናገሩ ጥሩ ነው። የኮሚሽኑን ጥያቄ ተቀብለን የምናነጋግራቸው ከሆነ ግን፣ የተጣራሰ (Contradiction) ነገር ነው የሚሆነው። በፍርድ ቤቱ ላይ ከወሰድነው አቋም ጋር አይሄድም።

 አራተኛ ተናጋሪ

 እኛን የሚፈልጉን በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት (ለሊጂትመሲ) ለማግኘት ብለው ነው። ሆኖም፣ በቀጥታ እምቢ ልንላቸው አይገባም። ዲፕሎማሲያዊ አይሆንም። የማንተባበርበትን ምክንያቶች እንግለፅላቸው። ቅደመ ሁኔታ እናስቀምጥላቸው። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉ ከሆነ፣ ልንተባበራቸው እንደምንችል እንግለፅላቸው።

 አምስተኛ ተናጋሪ

 የተቋቋሙበት ዓላማ እኮ ዋነኛውን ጉዳይ የሚያቅፍ አይለም። የግጭቱን መንስዔ የማይመረምሩ ከሆነ፣ ሌላው ምን ትርጉም አለው? የግጭቱን መንስዔ እስካልመረመሩ ድረስ፣ እኛ ከእነሱ ጋር የምንሠራው ነገር ትርጉም የለውም።

 / ብርሃኑ ነጋ

 አሁን የሚታየኝ ሁለት ሃሳብ እንዳለ ነው። በአንድ በኩል፣ ማነጋገሩ ጥሩ ነው የሚል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዋጋ የለውም የሚል። ስለዚህ፣ ያለው አማራጭ፣ ሰዎቹ ሲመለሱ፣ ሊያናግሯቸው የሚፈልጉ ባሉበት እንዲቆዩ ሊያናግሯቸው የማይፈልጉት ደግሞ፣ አዳራሹን ለቀው ወደ መተላለፊያው እንዲወጡ ነው። አዳራሹን ለቀው የሚወጡት ሰዎች ለምን እንደወጡ ትንሸ ገለፃ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በዚህ ትስማማላችኹ?

 አብዛኛው ተከሳሽ በዶ/ አባባል ተስማማ። ልክ እዚህ ነጥብ ላይ ስምምነት ላይ ሲደረስ (የሚገርም አጋጣሚ) የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ወደ አዳራሹ ተመለሱ። ብቻቸውን ነበሩ።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 ጨረሳችኹ?

 / ብርሃኑ ነጋ

 እሺ ጨርሰናል።

 ሰብሳቢው መለስ ብለው ለቀሪዎቹ የኮሚሽን አባላት ምልክት ከመስጠታቸው በፊት ተከትለዋቸው ገቡ። ሰብሳቢው ቀደም ብለው ወደአዳራሹ ተመልሰው «ጨረሳችኹብለው ጠይቀው፣ ትንሽ ጊዜ እንዲጨመርልን ተጠይቀው ተመልሰው ስለነበር፣ ቀሪዎቹ የኮሚሽን አባላት ሰብሳቢውን ተከትለው የገቡት፣ ተጨማሪ ጊዜ እንደማይሰጠን ለማሳየት እንደሆነ ተሰምቶኛል። ለስንት ደቂቃዎች እንደተወያየን ሰዓት አልያዝኹም። የኮሚሽኑ አባላት በየቦታቸው ቁጭ እያሉ፣ / በፍቃዱ ደግፌ እጃቸውን አወጡ።

 / በፍቃዱ ደግፌ

 ለመድፈር አይደለም። ግን፣ ቁጭ ያላችሁት ራቅ ብላችኹ ስለሆነ፣ ለመደማመጥ እየተቸገርን ነው። ወደታች ወርዳችኹ ፊት ባሉ ወንበሮች ላይ ብትቀመጡ ጥሩ መደማመጥ ይኖረናል።

 የኮሚሽኑ አባላት ጥያቄውን በመቀበላቸው ከፍ ካለው መድረካቸው ላይ ለቀው እኛ ተከሳሾች ባለንበት አካባቢ የሚገኙ ወንበሮች ላይ ቁጭ አሉ። / በፈቃዱ ሌላ ሃሳብም ነበራቸው።

 / በፈቃዱ ደግፌ

 ለመድፈር አይደለም፣ ስትናገሩ በደንብ እንድናዳምጣችኹ ቆማችኹ እንድትናገሩ ሃሳብ አቀርባለኹ።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ (ቁጭ እንዳሉ። የዶ/ በፈቃዱን ጥያቄ አልተቀበሉትም)

 ለእኛ ቃል የሚሰጠን ሰው በነፃነት ነው የሚያነጋግረን። መጥተው የምሥክርነት ቃላቸውን የሚሠጡን መታወቂያ ይሰጣቸዋል። ይሄ መታወቂያ ችግር እንዳይደርስባቸው ለመከታተል የሚያመች ነው። ለእኛ የምሥክርነት ቃሉን በመስጠቱ ብቻ ማንም ላይ ችግር መድረስ የለበትም። እኛ ስንሠራ፣ የታሪክ ተወቃሽነት፣ የህሊና ተወቃሽነት እንዳለብን እናውቃለን። እኛን  ላለማነጋገር ከወሰናችኹ፣ የጋራ ውሳኔ ከሆነ አላውቅም። እናንተ የምትሉትን ለመሥማት ነው የመጣነው።

 የተከሳሾችን አቋም ለመግለፅ / ብርሃኑ ነጋ ከተቀመጡበት ብድግ አሉ። ሰብሳቢውን እየተመለከቱ መናገር ጀመሩ።

 / ብርሃኑ ነጋ

 ይህን የአጣሪ ቡድን የማቋቋም ጉዳይ፣ ቅንጅት ቀደም ብሎ የያዘው አቋም መሆኑ ይታወሳል። የሰኔው ግርግር ከተነሳ በኊላ፣ የችግሩን ምንጭ የሚያጣራ አካል እንዲቋቋም ቅንጅት በይፋ ጠይቆ ነበር። መንግሥት ግን እምቢ አለ። ለማንኛውም፣ ከእናንተ ጋር ምን ችግር እንደሚታየን ማስረዳት እፈልጋለኹ። ችግሩ የሚነሳው፣ ከሾማችኹ አካል ማንነት ጋር ነው። እኛ «የችግሩ ፈጣሪ ነው» የምንለው አካል ነው እናንተን የሾማችኹ። ይህ ሁኔታ እኛን ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከተን መገመት ትችላላችኹ። ችግሩ በዚህ አያበቃም። ሌሎችም አሉ፡-

 1. ችግሩ እንዴት እንደተፈጠረ ማጣራት አትችሉም። ይህንን እስካላደረጋችኹ ድረስ ደግሞ፣ ዓላማችሁ ገና ከጅምሩ ተበላሽቷል ማለት ነው። የችግሩን ምንጭ ካላጣራችኹ፣ የምትነሱት ከየት ነው?

 2. በኮሚሽኑ አባላት ላይ ጥርጣሬ አለን። ይህን ስንል፣ ሁላችኹንም ማለታችን አይደለም። በአንዳንዶቻችኹ ላይ ማለታችን ነው። የኮምሽኑ አባል ከሆኑት የሃይማኖት አባቶች መካከል አንዱ፣ «የቅንጅት አባላት ጥፋተኛ ናቸው» ብለው በቴሌቪዥን ላይ በግልፅ ተናግረዋል።  ከእሳቸው ገለልተኝነት አንጠብቅም።

 አሁን በጋራ የወሰነው፣ የተወሰነው ፎርሙን ለመሙላት ስለማንፈልግ አዳራሹን ለቀን እንወጣለን። የተወሰነው ደግሞ፣ ፎርሙን ለመሙላት የምንፈልግ ስለሆነ፣ ወደኊላ ቀርተን እናነጋግራችኊለን። ይህን ስልን፣ ለእናንተ ያለን ከበሬታ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው። ህጋዊነታችኹን እናከብራለን። እናንተንም እናከብራለን።

 / ብርሃኑ ነጋ ንግግራቸውን እንዳጠናቀቁ፣ ሰብሳቢው፣ ቁጭ ባሉበት ምላሽ ሰጧቸው።

 የአጣሪ ኮምሽኑ ሰብሳቢ

 ጥሩ። አንድ የምለው ነገር አለ። ፎርሙን አሁን መሙላት የምትፈልጉ፣ ትችላላችኹ። መሙላት የማትፈልጉት ግን፣ ይሄ የመጨረሻው አይደለም። ፎርሙን ውሰዱና፣ ቀስ ብላችሁ አስቡበትና፣ ሃሳባችኹን ከለወጣችኹ፣ በኋላ ላይ ሞልታተኹ ልትልኩልን ትችላላችኹ።

 ሰብሳቢው ይህን ካሉ በኋላ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም ከመቀመጫቸው ብድግ በማለታቸው፣ ሰብሳቢው የሚናገሩትን አቋርጠው እንዲናገሩ ፈቀዱላቸው።

 / መሥፍን ወልደማርያም

 ፎርሙን አይቼዋለኹ፡፡ ፎርሙ የሚጠይቀው ስለእኔ ብቻ ነው። የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ግን ሀገራዊ ነው። ጥያቄዬ፣ በሌላው ላይ ስለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መናገር አልችልም ወይ? የሚል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ እናንተን በሚመለከት ጥርጣሬው ቢኖረኝም፣ በእኔ በኩል ላነጋግራችኹ ፍቃደኛ ነኝ። 3 ምክንያቶች፡-

 1. እግዚአብሔር አለ። እሱ ይፈርዳል። እሱ ይመለከታል።

2. ህሊና አለ። እሱን ማምለጥ አይቻልም።

3. ህጉ አለ። ህገመንግሥቱ አለ። የሞቱ ሰዎች፣ አካለ ጐደሎ የሆኑ ሰዎች እውን ህገ መንግሥቱን ጥሰው ነው? ህሊናችኹን ይዛችኹ መፍረድ ትችላላችኹ።

እኔ የምፈልገው ህሊናችኹ ላይ መጫን ነው። ይህንን ጭነት እንዴት እንደምታራግፉት የራሳችኹ ፋንታ ነው።

ፕሮፌሰሩ ከተናገሩ በኋላ፣ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ምላሽ ሰጧቸው።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 ለህሊናችን እንጠየቃለን። ከመካከላችኹ ማንም ሰው ፍቃደኛ ከሆነ እናነጋግረዋለን። እርስዎ እንዳሉን፣ ከህሊና የሚያመልጥ የለም።

/ ኃይሉ አርአያ እጃቸውን ስላወጡ፣ እንዲናገሩ ዕድሉ ተሰጣቸው።

 / ኃይሉ አርአያ

 / መሥፍን ያነሷቸው ነገሮች፣ ክቡር ነገሮች ናቸው። የህዝብ እሴቶች ናቸው። የእግዚአብሔር ነገር ተነስቷል። ግን ዛሬ የእግዚአብሔር ፈራጅነት ጠፍቷል። የሃማይኖት አባቶች የሉም። ቢኖሩ ኖሮ፣ እዚህ ችግር ውስጥ አንገባም ነበር። የህገመንግሥት ጉዳይ ተነስቷል። ችግሩ፣ ህገ መንግሥቱን ማክበር የሚገባቸው ሰዎች፣ ሊያከብሩት አለመቻላቸው ነው፡፡ ካራገፍናቸው ነገሮች አንዱ ህሊና ነው። ይሄ ነው ስንቃችን። ከዚህ አኳያ፣ በኮሚሽኑ ላይ ምን ዓይነት አመኔታ ነው ሊኖረን የሚችለው?

 / ኃይሉ አርአያ ተናግረው ከጨረሱ በኋላ፣ ከኮሚሽኑ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ቄስ ደረጀ ለመናገር ተነሱ። እሳቸው፣ የዶ/ በፈቃዱ ደግፌን «ተነስታችሁ ተናገሩ» ሃሳብ የተቀበሉት ይመስላሉ።

 ቄስ ደረጀ

 የምለው አለኝ። እዚህ ያላችሁትን፣ በስማችኹ እናውቃችኋለን። እናከብራችኋለን። መጠራጠራችኹ ትክክል ነው። መጠራጠር አለባችኹ። በእኛ በኩል ግን፣ ምን ይዘን እንደምንሠራ ልነግራችኹ እፈልጋለኹ።

 1. እግዚአብሔር አለ። እንኳን በአደባባይ የተደረገውን ይቅርና፣ በልብ ውስጥ ያለውን ነገር የሚያውቅ እግዚአብሔር አለ። ከእሱ መደበቅ አይቻልም።

2. ህሊና አለ። ከህሊና ማን ማምለጥ ይችላል? ህሊናችንን ይዘን ነው የምንሠራው። «እናምልጥህ» ብንለው እንኳን፣ ልናመልጠው አንችልም።

3. ታሪክ አለ። ታሪክ ይፋረደናል። የምንሠራውን ነገር ለታሪክ ነው ትተን የምናልፈው። ከታሪክ ማምለጥ አንችልም።

4. ህዝብ አለ። ይህ ሁሉ ሲደረግ የነበረ ህዝብ አለ። ይመለከተናል። ይታዘበናል። ከነዚህ ነገሮች ማምለጥ አንችልም። መረጃ ከሰጣችኹ፣ የእኛ ኃላፊነት ነው። «ንገሩን» የምንላችኹ፣ አክብረናችኹ ነው። ከተቀበላችኹን ጥሩ ነው። «እምቢ» ካላችኹም ውሳኔያችኹን እናከብራለን። ስንመጣ ይህን ታሳቢ አድርገን ነው። ፎርሙን ሳትሙሉ የምትሄዱ ሰዎች፣ ሂዱና ተነጋገሩበት። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

 ቄስ ደረጀ ተናግረው ከጨረሱ በኋላ፣ ፎርሙን መሙላት የሚፈልጉ ሰዎች ወደኋላ ሲቀሩ፣ ብዙዎቻችን ወጣን። ከዚያ ሁሉ ተከሳሾች መካከል የቀሩት ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ 7 ብቻ ነበሩ። ከቀሩት መካከል እርጉዟን ሠርክዓለምን ጨምሮ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረበትም።  

የአጣሪው ኮሚሽኑ አባላት የተሞሉትን ፎርሞች ከሰበሰቡ በኋላ፣ ውጭ ያሉት ሰዎች ወደ አዳራሹ እንዲመለሱ ተደርገው፣ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ የመሰናበቻ ንግግር አደረጉልን።

 የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ

 በስብሰባው ወቅት ላሳያችሁት ጨዋነት አመሰግናለኹ። ከፍተኛ ዲስፒሊን ነው ያሳያችኹት። የሰጣችኹንን መረጃ እናጣራለን፡፡ መረጃው ከእኛ ጋር ነው የሚቆየው። ችግር ከደረሰባችኹ ንገሩን።

 የአጣሪው ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ ፖሊሶች ከውጭ ተጠርተው ተረከቡን። ቢያንስ 2 ሰዓት ከጐናችን አልነበሩም። ግማሽ ፍቺ ልበለው? ....

የተቀነጨበው አበቃ!

 // መለስ ዜናዊ «ለኢሠፓ አባላት እንኳን ተትረፍርፏል» ያሉትን ዲሞክራሲ ተነፍገን ይሄንን ታሪካዊ መፅሐፍ ማሳተም ያለመቻላችን ሁልጊዜ ይቆጨናል። በውስጡ ብዙ ቁም ነገሮችን የያዘ መፅሐፍ ነው፤ ሕዝብ የማያውቀው። በዚህ አጋጣሚ መፅሐፉን ለማሳተም መንግሥት እንዲፈቅድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ፀሐፊውን ለማግኘት፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ