በየመን ዩኤንኤችሲአር ያስገነጥላል፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያጨበጭባል
አምላክሥራ ግሩም
ለአንዳንድ ጉዳይ ወደ UNHCR ቢሮ ጎራ ስል ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ የቢሮው ብልሹ አሠራር ያናድደናል - ለኢትዮጵያዊያን። ሰሞኑን እንኳ የስደተኛነት ማረጋገጫ ማንዴቴ ላይ ስሜ ሲጻፍ የቃላት ግድፈት አስተካክሉልኝ ብዬ አንድ የዘለሉዋትን ፊደል ለማስተካከል 10 ቀን ነው ያመላለሱኝ። ሙሉ ስሜን ቢሆን ስንት ወር ያመላልሱኝ ይሆን? ይህ ታዲያ ለኢትዮጵያዊያን ነው። ኢራቂ ከሆኑ መስተንግዶው ፈጣን ነው።
ቢሮው በአንድ ወቅት የስደተኛው ጉዳይ ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ያወጣው መግለጫ ላይ ጠቆም አድርጓል። የእነሱ ፍርሃት ከወለደው ጥብቅ ቁጥጥር ፖሊሶች ስደተኛው ላይ እንደፈለጉ እንዲሆኑ አርጓቸዋል። የ5 ወር ነፍሰ ጡር በድብደባ አስወርዳለች ስሞኑን ከህክምና ማስረጃዋ ጭምር ቃል-ምልልሱን ለንባብ አበቃለሁ። ከዩን ግቢ ውስጥ ለፖሊስ አሳልፈው የሰጡት ኢትዮጵያዊ 3 ዓመት በእስር ተሰቃይቶ ቢወጣ ማንዴቱን ግን ሊያገኝ አልቻለም? ከአንድ የስደተኛ ጉዳይ ጽ/ቤት የማይጠበቅ መብት የመጣስ ሁኔታ ተደጋጋሚ ይታያል። ይህ ነው እንዴ የUNHCR ዓላማ?
ከዚህ ... ከዚህ ... የባሰ ግን ለእኔም ሆነ ለሌሎች ሀገር ወዳድ ስደተኞች የውስጥ ቁስል የሆነን ነገር አለ። አጋጣሚ ብሎ ወደ ውስጥ መግባት ከተቻለ በር ላይ ለምዝገባ የሚቀርበው ጥያቄ ሕሊና ይፈታተናል። ስም? … ይባልና ... ዜግነት ሲጠየቅ ሱማሌ ወላ ኦሮሞ ወላ ኢትዮጵያ ወላ ኤርትራ … የሚል ጥያቄ ይቀርባል። ይሄ ከፋፍለህ ግዛ የዘር ወረርሽኝ በስደት ሀገር ሠላም መንሳቱ አንሶ በUNHCR ቢሮ ውስጥም ችግሩ ጎልቶ ኦሮሞ ሌላ ሀገር ተደርጎ ሲመዘገብ መቼ ተገንጥሎ ነው? ማሰኘቱ አይቀርም። ሳናውቀው እነሱ ገንጥለው ... እነሱ እውቅና ሰጥተው ዜግነት ’ኦሮሞ’ ብላችሁ ተመዝገቡ ሲሉን እንዴት ውስጥ አይቆስል? ለእንደ እኔ አይነቱ ማንነትን ፍለጋ አያስኳትንም? ከሁለት ብሔረሰብ ተወላጅ ለሆነ ማለቴ ነው። ”የመን ታይምስ” ላይ ቃለ-ምልልስ ለማድረግ የፈለኩበት ዋና ዓላማ ያልተገነጠለች ሀገሬን ገንጥሎ እውቅና ለመስጥት ለUN ማን መብት ሰጠው? በሚል ነበር። ጋዜጠኛው ከሀገራቸው ሁኔታ አንጻር ቀንሶ ዓላማዬን አከሸፈው እንጂ …
ከኩሩ ኢትዮጵያዊነቴ (ሐበሻነቴ) ቀጥሎ ኦሮሞነቴ ኩራቴም ክብሬም ነው። ይህ ነገር ሁሌ ስለሚከነክነኝ በአንድ ወቅት አንዱን የUN ቢሮ ፕሮቴክሽን ኦፊሰርን ጠየኩት።
“ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ራሱን የቻለ እውቅና አልተሰጠውም። በእናንተ ቢሮ ግን እንደ አንድ ሀገር ተቆጥሮ ዜግነት ’ኦሮሞ’ ወይስ ’ኢትዮጵያ’ ትላላችሁ … የመን ያለ UNHCR ቢሮ ራሱ ገንጥሎ ራሱ እውቅና ሰጥቶ አንድን ክልል ሀገር አድርጎ ብሔርን ዜግነት አድርጎ 1950 የጄኔቫ ኮንቬንሽን ያዛል ወይ?” አልኩት።
“ምን ቸገረኝ ሀገር ስንላቸው ኦሮሚያ ይላሉ፤ ኦሮሚያ የት ነው ስንላቸው ምስራቅ አፍሪካ ይላሉ እንሞላለን።” ... ”ምን ቸገረኝ” ማለቱ ከእሱ የማይጠበቅ ሆኖ ቢያናድደኝም ማንዴት መሰረዝን እንደማስፈራሪያ አርገው በሚያዩ አምባገነን ፕሮቴክሽን ኦፊሰሮች ባሉበት ቢሮ ምንም መናገር አልቻልኩም። ጥያቄ ማቅረቤን ግን ቀጠልኩ። ”ካርታ ላይ ግን አይተሃታል?” አልኩት። የኦሮሚያ ክልል ካርታ አሳየኝ።
”አሃ! ... እኔም ዜግነት አማራ ወይም ትግሬ ብል ትሞላልኛለህ?” ለህገሬ ብቻ ሳይሆን ወገኔንም ክብር የነሳውን መልስ የሰማሁት በዚህን ሰዓት ነው። ስድቡን ልተወውና “የፈለከውን ማለትማ አትችልም። ኦሮሞ ካልክ እሞላለሁ ከፈለክ ከተማ ከፈለክ ካምፕ እንደልብህ መኖር ትችላለህ ሪሴትልመንት ከፈለክ ግን የለም” አለኝ። “ለምን በወገኔ ትጫወታላችሁ?” ለሚለው ጥያቄዬ ምላሹ፤ ”ከቢሮ ውጣ!” ተብዬ የሄድኩበትን ጉዳይ ሳልነጋገር መውጣት ሆነ ዕጣዬ። ይህ ከሆነ ሁለት ዓመት አለፈው። አሁንም አሠራሩ ያው ነው። አደን ከሚባለው የየመን ሁለተኛ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተቆረቆረ አልቀረስ የሚባል ካምፕ ውስጥ ከዛሬ ነገ መፍትሔ እናገኛለን ብለው በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በድንኳን ውስጥ በአስቃቂ ሁኔታ ይኖራሉ። መጨረሻቸው ምን ይሆን? በበሽታና በረሃብ ተሰቃይተው ያለመፍትሔ መቆየትስ እስከመቼ?
UNHCR ላልተገነጠለ ሀገር እውቅና መስጠቱ አስገራሚ ነው። በየመን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ለምን? አለማለቱ ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ ነው። በሥራ ሰበብ ወደ የመን እየመጡ ችግር ደርሶባቸው ወደ ኤምባሲ ጎራ ያሉ አጥጋቢ መልስ ሳይሆን፤ ሞራል የሚያደቅ ነገር ሰምተው መመለሳቸው የተለመደ ነው። ይህንን የመንን የረገጠ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። ተበደልን ብለው ፍትህ ፍለጋ ጠፍተው ወደ ኤምባሲ ጎራ ያሉ ለበዳዮቻቸው ተመልሰው ሲሰጡ ለማየት ታድለናል። ለዜጎቹ መብት ማስከበር ያልሆንን ”ለገረድ አልመጣንም” የሚሉ ሠራተኞች ያቀፈ ኤምባሲ ... የአንድነት ኢትዮጵያ ልጆች በሁለት ዜግነት እውቅና ሰጣቸው። የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር ያልሞከረ ኤምባሲ ተልዕኮው ምንድን ነው? የመን ውስጥ እኛ ከለመድነው የዳቦና ቂጣ አይነት ለየት ባለ መለኩ የሚዘጋጅ በእነሱ አጠራር (ኩደም) እና (ኮብዝ) የሚባል አለ። እሱን ፍለጋ እሱን ለቀማ ይሆን ተልኳቸው?
ለፓስፖርት ዕድሳም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ወደ ኢምባሲ ጎራ ያለውን የአማራ ልማት፣ የትግራይ ልማት፣ ... ማኅበር አባል ካልሆናችሁ ግልጋሎት አንሰጥም፤ ትንሽ ትልቁን ወሬ አቀባይ አቶክቷኪ አድርገዋል። ይህን ወሬ አላደረጓቸው። ይሆን? ቂ ... ቂ ... ቂ ... ወይስ ከ40 ዓመት ትግል ስለተደረገት UNHCR በመዝገብ ሊያስገነጥል ኤምባሲው ያጨበጭባል?
አምላክሥራ ግሩም



