ናኦሚ በጋሻው ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

“ምርጫ ቀልድ ነው። መድረኩ ግን መሳተፉ ይበጀዋል” በሚል ርዕስ አቶ ግርማ ካሣ የጻፉትን መጣጥፍ ኢትዮሜዲያ ላይ ወጥቶ አነበበኩ። ርዕስ አመራረጣቸው የሚያስደንቅ ነው። ርዕሱን በመመልከት “ምን ማለታቸው ነው? ቀልድ ነው ብለው እንዴት ተሳተፉ ይላሉ” ብዬ ወዲያው ነበር ጽሑፉቸውን ያነበብኩት።

 

በእንግሊዘኛ ጽሑፍ በማቅረብ የሚታወቁት አቶ ይልማ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል ለአቶ ግርማ መልስ እንዲሆን በአማርኛ “በቀልድ ምርጫ መሳተፍ ምን ትርጉም አለው?” በሚል ርዕስ ለአንባቢያ በመጣጥፍ ያቀረቡት። ይህንንም መጣጣፍ ኢትዮጵያ ዛሬ የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ አንብቤዋለሁ።

 

አቶ ግርማ እና አቶ ይልማ ምርጫው ቀድል እንደሆነ ተስማምተዋል። አቶ ግርማ እንደዚያም ሆኖ ምርጫውን መሳተፍ እንደሚገባ ስምንት ግልጽ ነጥቦች አስቀምጠዋል። ከጽሑፋቸው እንዳነበብኩት አቶ ይልማ፣ አቶ ግርማ ያቀረቡት መከራከሪያዎች የተሰማሟቸው አይመስልም።

 

አቶ ግርማ ያቀረቡት ነጥቦች እንደ እኔ ግምት ወደ ጎን ሊደረጉ የሚገቡ ነጥቦች አይመስሉኝም። በአቶ ይልማ ውስጥ የሚቀጣጠለው የጀግንነትና የቆራጥነት ወኔ ቢገባኝም ትግል ሊመራ የሚገባው አቶ ግርማ እንዳሉት በማስተዋልና በጥበብ ይመስለኛል። “ትግላችንን በስሜት ላይ አናድርገው፤ ነገር ግን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ይሁን” ነው ያሉት። “ገና አልጠነከርንም፤ ህዝቡን በሚገባ አላደራጀነውም። በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ትዕግስትና ጥንቃቄ ይጠይቃል” ነው አቶ ግርማ የሚሉት።

 

አንድ ቦታ ላይ አቶ ይልማ መድረኩ በምርጫ በመሳተፉ ምንም ውጤት እንደማያመጣ ሲያስረዱ “የበሰለን እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” የሚለውን ምሳሌ አቅርበዋል። ትክክል ናቸው። አቶ ግርማም ይሄንኑ እኮ በግልጽ በመጀመሪያው ላይ ለማስረዳት ሞከረዋል። አቶ ግርማ ግን አልፈው የሄድቡት ሁኔታ አለ። እንጀራውን በምጣድ ከመጣዱ በፊት የተቦካ እንጀር መኖር አለበት። እንጀራው ሳይቦካ አይጋገርም። ካልተጋገረ ደግሞ በሰለ አልበሰለም የሚለው ክርክር ሊኖር አይችልም።

 

አንድ ነገር ስለፈለግነው አይሆንም። ስለተመኘን መድረስ የምንፈልግበት ቦታ መድረስ አንችልም። አሁን ካለንበት ተነስተን መድረስ ምንፈልግበት ቦት ለመድረስ፣ በመካከሉ ረጅም መንገድ መጓዝ ይጠይቃል። በመሃከል የሚመጡትን መሰናክሎች ማለፍ ይጠይቃል። አላስፈላጊ ግጭት ከገዢው ፓርቲ ጋር መኖር የለበትም። አቅምንና ልክን ማወቁ ይበጃል።

 

ከገዢው ፓርቲ ጋር ግጭት ከመጀመር በፊት ህዝብን በሚገባ ማደራጀታችን፣ መሪዎች ቢታሰሩ ትግሉ በቀጣይነት የሚመራ አካል መዘጋጀቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በምርጫ ዘጠና ሰባት ህዝቡ ተንቀሳቅሶ ነበር። ነገር ግን በሚገባ ያደራጀውና የሚመራው አካል ስላልነበረ በቀላሉ በወያኔ/ኢህአዲግ ሊታፈን ችሏል። አቶ ግርማ የሚሉት ከምርጫ ዘጠና ሰባት እንማር ነው።

 

ስለዚህ የአቶ ግርማ መከራከሪያ በጣም አሳማኝና ያለውን ሁኔታ ያገናዘበ ነው እላለሁ። ድርጅታዊ ሥራ ሳይሰራ፣ በስሜት መንቀሳቀስ ያኔም ለቅንጅት አልበጀም፤ አሁንም ለመድረክ አይበጅም።

 

አቶ ግርማ ምርጫውን መሳተፍ ለምን ጥቅም እንዳለው ካስረዱ በኋላ ጽሑፋቸውን የደመደሙት የሚከተለውን በማለት ነበር፤ …

 

“… አይ አሁንም ”በምርጫው መሳተፍ አይገባም” የሚል አቋም የሚይዙ ወገኖች ካሉ ደግሞ፤ የመከራከሪያ ነጥባቸውን ለመስማት ዝግጁዎች ነን። አንድ ሁለት ብለው የምርጫውን ቦይኮት ጥቅም ያስረዱን። ያላቸውን አማራጮች ያቅርቡልን። መከሰስ፣ መተቸት፣ መሳደብ በጣም ቀላል ነው። መፍትሔ ማምጣት ግን ፍፁም የተለየ ነገር ነው። ሌሎች ድርጅቶች የሚሠሩትን ማጣጣል አንድ ነገር ነው። ሠርቶ ማሳየት ግን ሌላ ነገር ነው። …”

 

አቶ ግርማ በጣም መሰረታዊ ጥያቄዎችን ነው ያቀረቡት። አቶ ግርማ ለጠየቁት ጥያቄዎች ግን ከአቶ ይልማ ጽሑፍ መልስ አላገኘሁም። አንድ የጠቀሱት ነገር ቢኖር ምርጫውን ቦይኮት በማድረግ የህወሓትን ሌጂቲሜሲ ማሳጣት ይቻላል የሚለው መከራከሪያ ብቻ ነው።

 

“… የኔ ጥያቄ የተቃዋሚው ጎራ ነን እያሉ የአቶ መለስ ፓርላማ ውስጥ የተሳተፉ አንዳንድ አሉ፣ እስቲ እንደው ለእነዚህ አዛውንቶች ሥራ ከመስጠት በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ትርፍ አገኘ? እስቲ አሥራ ስምንት ዓመት አብሮ ከመሥራት ያመጡትን ጥቅም ይንገሩን? እስቲ ያሳለፉት አንድ ሕግ ካለ ይጥቀሱልን? በማንም ያልተመረጠ ካድሬ መጫወቻ ከመሆንና ለህወሓት ሌጅትሜሲ ከመስጠት በስተቀር ሌላ ምን የሚያሳዩት አለ? …” ነበር ያሉት አቶ ይልማ።

 

አቶ ግርማ፣ ይመስለኛል የሌጂትሜሲን ጥያቄ ከጅምሩ አንስተው የተነተኑት፣ አቶ ይልማ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ምርጫውን ቦይኮት ማድረግ ያስፈልጋል በሚል የሚቀርበው መከራከሪያ እርሱ በመሆኑ ነው።

 

ሌጂትሜሲ የሚለው ላይ ላተኩር። ላለፉት አሥር ዘጠኝ ዓመት የአቶ መለስ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በሕግና በዲሞክራሲያዊ ዘንድ የተመረጠ ተደርጎ አይወሰድም። በሌላ አባባል በህዝቡ ዘንድ ሌጂትሜሲ የለውም። በጠመንጃ የሚገዛ አምባገነን አገዛዝ ነው። በህዝቡ ዘንድ የሚያገኘውም ሆነ የሚያጣው ሌጂትሜሲ የለም። በመሆኑም አቶ ይልማ ህወሓት ሌጂትሜሲ ማግኘት እንደሌለበት ሲናገሩ ኢትዮያውያንን ሳይሆን የውጭ ሀገር ዜጎችን አስበው መሆን እንዳለበት እገምታለሁ።

 

በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫውን ቦይኮት ማድረግ ህወሓት በምዕራባውያን ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል የመከራከሪያ ነጥባቸውን በቀጥታ የሚቃረን አስተያየት ሰጥተው እናነባለን። መድረክ ከምርጫው እራሱን ቢያገል ምዕራባውያን ሌላ አማራጫ እስከሌላቸውን ወያኔ/ኢህአዲግ በአካባቢው መረጋጋት እስካመጣ ድረስ አቶ መለስን መደገፋቸው አይቀርም የሚለውን የአቶ ግርማ መከራከሪያ ነጥብን በመቃወም፤ “ምርጫው የሚካሄደው በኢትዮጵያውያኖች ለኢትዮጵያ ከሆነ የፈረንጆች መቀበልና አለመቀበል በዚህ ውስጥ ምን አገባው። በህወሓት መንግሥትን ሕገ-ወጥ አገዛዝ እሳት የሚነደው ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ ፈረንጅ? ታድያ መድረኩ መጨነቅ ያለበት ስለ ህዝቡ ወይስ ስለራሱ? ትላንት ኬንያ ውስጥ የተጭበረበረ ምርጫ ሲካሄድ ፈረንጆቹ’ኮ ተቀብለውት ህዝቡ ነው እኮ አይሆንም ያለው። እስቲ በታሪክ ተበዳዩ ሳይጮህ ዳኝነት የተጠራበት ጊዜ ወይንም ቦታ ይነገረን?” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

 

የፈረንጆች መቀበልና አለመቀበል በዚህ ውስጥ ምን አገባው የሚል ጥያቄ አቶ ይልማ የሚጠይቁ ከሆነ ታዲያ እርሳቸውም ህወሓት በምዕራባውያን ሀገራት ስለሚያገኘው ተቀባይነት ወይንም ሌጂትሜሲ ለምን ይናገራሉ? የትኛው ነው የርሳቸው አቋም?

 

እንግዲህ እዚህ ላይ አቶ ይልማ ባዶ እጃቸውን እንደቀሩ እናያለን። አቶ ይልማ ብቻ ሳይሆን የአቶ ይልማ አይነት አስተያይተ ያላቸው የስሜት ማርገብገቢያ ከማውለብለብ ውጭ ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔት ላይ የመሰረተ አስተያየት የመስጠት ችግር እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው።

 

አቶ ይልማ ሌላ መከራከሪያዎች ካላቸው ያቀርቡ። እስከ አሁን ባለው ግን የአቶ ግርማ መከራከሪያዎች በጣም አሳማኝ ናቸው ባይ ነኝ። ምርጫውን አለመሳተፉ ጥቅም ላያመጣ ቢችልም ትልቅ ጉዳት ግን ይኖረዋል!


ናኦሚ በጋሻው

( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ሎንግ ቢች፣ ካሊፎርኒያ

ሚያዝያ 29 ቀን 2002

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ