ዕድሜዓለም

ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ ላይ “አንድነትም እንደ መአህድ ብርቱካንም እንደ አስራት” በሚል ርዕስ ጽሁፍ ወጥቶ ነበር። ፀሐፊው መአህድ ተመስርቶ በብቃት መንቀሳቀስ እንደጀመረ ከውስጥም ከውጪም የገጠመውን ፈተና አመላክተው፤ መሪውን ፕ/ር አስራትን ወደ እስር ቤት በመላክ ፓርቲውን እንዴት መቆጣጠር እንደተቻለ የራሳቸውን እይታ የጋዜጠኛው ማስታወሻ ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ በሰጠው ምስክርነት አስደግፈው አሳይተውናል። በንጽጽርም ከ10 ዓመት በኋላ አንድነትና መሪው ብርቱካን ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው ፀሐፊው በጊዜ በቦታና በድርጊት እያመሳከሩ ነግረውናል። 

 

ፀሐፊው ያነሱት ጉዳይ ትልቅ ሀገራዊና ወቅታዊ የመሆኑን ያህል የአንባቢን ትኩረት ያገኘ አልነበረም። በዚህ ፀሐፊ እምነት የዚህ ምክንያቱ አብዛኞቻችን ስሜታዊነት የሚያጠቃን፤ ወደነፈሰው መንፈሥ የምናዘወትር፤ ከእውነት ይልቅ ከሰዎች ጋር መወገን የሚቀልለን፤ ትናንትን መለስ ብሎ ማየት ስለነገም አርቆ ማሰብና መሥራት የሚከብደንና ዛሬ ስለ ቆምንበት ብቻ ማሰብ የምናዘወትር መሆናችን ነው።

 

ፀሐፊው ላነሱት ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን ቢሆን አንድነት ፓርቲ እንዲህ የመጨረሻ ውድቀት ላይ ባልደረሰ ነበር። ሌላው ቢቀር የብርቱካንን ጉዳይ ተዉትና ለምርጫው ትኩረት ስጡልን በማለት ዲፕሎማቶችን የሚለማመጡ ሀፍረተ ቢሶች ደፍረው ለመናገር ባልበቁ ነበር።

 

ፀሐፊው አንድነትም እንደ መአህድ፤ ብርቱካንም እንደ አስራት ብለው ሲነሱ መአህድን መልሰን ነብስ እንዘራበታለን አስራትንም ከመቃብር ልናገኛቸው እንችላለን ብለው ሳይሆን የፖለቲከኞቹ አካሄድ ከትናንቱ የዛሬው የማይሻል እንደውም ክህደቱ ብሶ መጠላለፉ ከፍቶ የቀጠለ መሆኑን በማሳየት በአንድነትና በብርቱካን ላይ መታየት የጀመረው መአህድን ለክስመት አስራትንም ለሞት ያበቃ ጉዳይ በቶሎ መፍትሔ እንዲገኝለት ለማንቃት የጥሪ ደወል ማሰማታቸው ነበር።

 

ግና ደወሉ ሊያነቃን አልቻለምና እነሆ አንድነት የራሱ በሚባሉ ሰዎች አስማሚነት በህወሓት ሰዎች ተጠልፎ፤ ፕሮግራሙን ለውጦ ከሕብረ ብሔራዊነት ዘቅጦ፤ የአማራ ተወካይ ተብሎና በምርጫ ደቡብና ኦሮምያ እንዳይደርስ ተከልክሎ (ኋላ በሽምግልና ትንሽ አግኝቷል) እንደ መአህድ አለ የለም የሚባል ፓርቲ ወደ መሆን እየወረደ ነው።

 

የሚያሳዝነው ‘ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል’ እንዲሉ፤ አንድነት ቀድሞ ያጎፈረውን ፀጉሩን እያዩና ካልገደሉት እንቅልፍ የማይወስዳቸው አመራሮቹ የሚነግሩዋቸውን የውሸት ጥንካሬ ከተግባራዊ እንቅስቃሴው ጋር መዝነው መረዳት የተሳናቸው ሰዎች ዛሬም እውነቱን ለማየት ዓይናቸውን መግለጥ ተስኗቸው ለአንድነት ህልውና ፍጻሜ ተባባሪ ሆነው መሰለፋቸው ነው።

 

አንድነት ወደ መድረክ ሲገባ “ተዉ! ረጋ ብላችሁ አስቡ፤ ገብቶ ከመለያየት አስቀድሞ በበቂ አጥንቶና ተዘጋጅቶ መጀመር ይበጃል” ያሉ ወገኖችን ወንጅለው ከፓርቲ ያባረሩት ሰዎች ዛሬ ከመድረክ ሰዎች ጋር መሥራት ስለማልችል ወደ መድረክ አልሄድም በግድ ሂድ የምትሉኝ ከሆነ ከአንድነት እለቃለሁ ማለታቸውን ሰምተናል። ወደ መድረክ አለመሄዳቸውንም በተግባር አይተናል። ይህን ካሉትና ካደረጉት ሰዎች ደግሞ አንዱ የፓርቲው የወቅቱ ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው በመሆናቸው በአሁኑ ሰዓት አንድነት በመድረክ ውስጥ ሕጋዊ ውክልና አለው ማለት አይቻልም።

 

ይህ ሁሉ ችግር በገሀድ ቢታይም ከራስ በላይ ነፋስ ያሉ ሰዎች ግን ዛሬም ስለ አንድነት ጥንካሬ፣ ዛሬም ስለ አመራሩ ትክክለኛነት ሲናገሩ ድፍረታቸው ይገርማል። እነዚህ ሰዎች አያድርገውና አንድነት ሞቶ በመቃብሩ ላይ አበባ ሲያስቀምጡም አንድነት የሞተው በአመራሩ ጥበብ በራሱም ጥንካሬ ነው ለማለት የሚገዳቸው አይደሉም።

 

ጽሑፋቸውን በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ ያስነበቡን ፀሐፊ ከብዙዎቻችን ቀድመው ነገሩን ለመረዳት የቻሉ ናቸው። ተረድተውም ሊሆን የሚችለውን ለማመላከትና ስጋታቸውን ለማጋራት መደረግ አለበት ስላሉትም ጥሪ ለማቅረብ ሞክረው ነበር። ሰሚ ጠፍቶ ዛሬ ለምናየውና ለምንሰማው በቃን እንጂ። ፀሐፊው የአንድነቱ ቀኝ አዝማች ማን ይሆን በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ካሰፈሩትና በማስታወሻየ ካስቀረሁት መልካም ፈቃዳቸውን ጠይቄ ጥቂት ብጠቅስ የጽሑፌን ጭብጥ በሚገባ ያስጨብጥልኛል።

 

“… በመአህድ ተ/ም/ፕሬዝዳንት ቀኝአዝማች ነቅአጥበብ በቀለና በደህንነቱ ሹም ክንፈ ገ/መድኅን መካከል የነበረውን ግንኙነት ምንም በማያጠያይቅ መልኩ ‘የቤት ልጅ’ የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ እማኝነቱን ሰጥቶ ዛሬ ይንገረን እንጂ በወቅቱ ይወራ የነበረ ስለመሆኑ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያስታውሳል። ያኔ ሽንጣቸውን ገትረው ለቀኝአዝማች ይሟገቱ የነበሩ እና ሌላውን በአፍራሽነት ይፈርጁ እና ያወግዙ የነበሩ ወገኖች ዛሬ ምን ይሉ ይሆን?

“የወ/ት ብርቱካን ጥንካሬ የአንድነትም ጅምር ያሰጋው፤ አስግቶትም ብርቱካንን በሕግ መሣሪያነት በሰበብ ያሰረው ወያኔ አንድነትንም እንደ መአህድ የማይጋፋም የማይጠፋም ፓርቲ አድርጎ ለማቆየት ተመሳሳይ ተግባር ከመፈጸም ይቦዝናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል።

“ለዕቅዱ ተፈጻሚነት ደግሞ እንደ ቀኝአዝማች ከኃላፊነቱ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚሰጠውን ገፀ-ባህርይ ተላብሶ የሚጫወት ሰው ማን ነው? የሚለውን ለመመለስ ቀርቶ ማን ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት አሁን የሚቻል አለመሆኑን ለዚህ ጽሑፍ ግብዐት ያነጋገርኳቸው የፓርቲው አባላትም ሆኑ የአመራር አባላት ገልፀውታል።

“ጊዜ መስተዋቱ ሁሉን ፍንትው አድርጐ ያሳየናል፤ የአንድነቱ ቀኛዘማች ተደብቆ እንደማይቀር ቢታመንም እስከዛሬው ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ብዙ ጠንካራ ሰዎች ከፓርቲው ሊያርቅም፣ ሊያባርርም፣ አልፎ ተርፎም በወይኔ ሠይፍ ሊያስቀላም ይችላልና የአንድነት ፓርቲ ጉዳይ በተናጠል የሀገራችን ጉዳይ በጥቅል የሚያሳስበን እና የወ/ሪት ብርቱካን ሕገ-ወጥ እስራት የሚያስቆጨን ወገኖች ሁሉ ጉዳዩን በንቃት ልንከታተል እና የአንድነቱን ቀኛዝማች ፈጥነን ልንደርስበት ይገባል መልዕክቴ ነው። …” ነበር ፀሐፊው ያሉት።

 

የአንድነቱ ቀኝአዝማች ያደርጋቸዋል ብለው የገለጹዋቸው ስጋቶቻቸው ሁሉ ተፈጽመዋል። ለእኛ ያስተላለፉት መልዕክት ግን ሰሚ አላገኘምና አንድነትን ሳንታደገው ቀረን። ፈትነን እንድረስበት የሚለው መልዕክታቸው ትኩረት አግኝቶ ቢሆን፤ የአንድነቱ ቀኝአዝማች እስከዛሬም ባላቆየ ፀሐፊው የሰጉትን ጥፋት ሁሉ ባልፈጸመም ነበር። ዛሬስ የአንድነቱን ቀኝአዝማች ከተግባሩ ለማወቅ የሚያስችለን ደረጃ ላይ አልደረስንም? እሱን ማወቅና ማጋለጡ አንድነት የመጨረሻ ህልውናውን እንዳያጣ አይረዳም? እኔ ቁርጠኝነቱ ካለ ከራስ በላይ ነፋስ ከሚል አስተሳሰብ ከተወጣ፤ በሀገር ቤት ያለው ፓርላማ ገብቶ ስለሚያገኘው ገንዘብና ነፃ ቤት ብቻ የሚያስብ ካልሆነ፤ በውጪ ያለው እነስየ መንግሥት ሆነው እኔ ምንስትር እሆናለሁ ከሚል ቅዠት ከተላቀቀ፤ አሁንም ቢሆን አንድነትን ማዳን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ደግሞስ መሪውን ብርቱካንን እስር ቤት አስቀምጦ ህሊና ላለው ሰው አንድነትን መርሳት እንደምን ያስችላል።

 

ስለሆነም በዕድሜዬ ያየሁትን፤ ተጽፎ ያነበብኩትን፤ በአንድነት ዙሪያ የተነገረ የተፈጸመውን በመቃኘት የአንድነቱ ቀኝአዝማች እገሌ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ። ሌሎችም የየራሳችሁን በማስረጃ አቅርቡና የአንድነቱ ቀኝአዝማች ማንነት ላይ በጋራ እንወስን። እነሆ እኔ ጀመርኩ፦

 

  • ወ/ት ብርቱካን ወደ ቃሊቲ ከመውረዷ ቀደም ብሎ የሥራ አስፈጻሚው አዝማሚያ አላማረንም ያሉ የምክር ቤት አባላት ፊርማ አሰባስበው የጠሩትን ስብሰባ ምን ተደረገና ነው ይህ ስብሰባ የተጠራው ሆስቴጅ እየተደረግን ነው ያሉ፤
  • በፓርቲው ጽ/ቤት በተካሄደ የመንግሥትና የግል ጋዜጠኞች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የብርቱካንን ፎቶ እያስቀደሙ ፓርቲ ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አሉ በማለት የተናገሩ፤
  • የፓርቲውን ማኅተም በመጠቀም ሠራተኞችን እንዳሻቸው የሚያባርሩና የሚቀጥሩ፤
  • ሥራ አስፈጻሚው ቃለ ጉባዔ እንዳይኖረው ያደረጉ፤
  • ሥራ አስፈጻሚው ለሁለት ቀናት ግምገማ አካሂዶ የደረሰባቸው ስምምነቶች ተጽፈው ለፊርማ እንዲቀርቡና ፀድቀው ተግባራዊ እንዲሆኑ ተብሎ ከተወሰነ በኋላ አፍነው ያስቀሩ፤ (ዝርዝሩን የሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ታምራት ታረቀኝ ተግባራዊነት የተነፈገው የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ በሚል ርዕስ በኢ-ሜይል አሰራጭተውታል)
  • ከሣምንታዊው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ሚያዝያ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ባደረጉት ቃለምልልስ

- ባዕድ የሆኑ በፓርቲው ውስጥ በአመራር ደረጃ መገኘታቸው ነው፤

- ፓርቲው ተጠልፎ መውደቁ የማይቀር ነው፤

- አንድ መዋቅራዊ ህልውና የሌለው ቡድን አለ፤ አንድ የፓርቲያችን የወጣት ቡድን ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራ ቡድን አለ፤

- ውይይት ላለማድረግ ወስነናል፤

- ደንብን የጠበቀ ውሳኔ የምንለው የት ደርሰናል የሚለው አሳሳቢ ሆኖብናል፣ አንዳንዴ ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፤

- በአቶ አምሃ ላይ የሚወሰደው ርምጃ በአጭር ቀናት ውስጥ ይፈጸማል፤ (አቶ አምሃ የሥራ አስፈጻሚ አባልና የጥናትና ምርምር ጉዳይ ኃላፊ ነበሩ)

  • • የብርቱካንን እስር ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማቅረብ ፓለቲካውን ያሳንሰዋል፤ አንድነትም ሆነ አንድነት አባል የሆነበት መድረክ ይህን አያደርጉም በማለት የተናገሩ (በስዊድን ለሚሰራጭ ራዲዮ)፤
  • • አንድነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በምርጫው ይሳተፋል፤ ወ/ት ብርቱካንን በቅድመ ሁኔታ አናቀርብም ያሉ፤ … ወዘተ (አዋሣ በተደረገ ስብሰባ ላይ)

 

እነዚህን የፈጸሙትና የተናገሩት ማን ናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ አንባቢ በሙሉ በአንድ ድምፅ የአንድን ሰው ስም እንደሚጠራ ርግጠኛ ነኝ። የአንድነት ዋና ፀሐፊን አቶ አስራት ጣሴን፤ በይፋ የተነገረና የተደረገ ነውና። አሁን ደግሞ ሥልጣን የማይፈልጉ መስሎ ለመታየት የዋና ፀሐፊነቱን ቦታ ለቅቄአለሁ ይላሉ። አሁን እንደውም ከቀድሞው የባሰ ለተግባራቸው አፈጻጸም የሚረዳቸውን ቦታ ነው የያዙት። በብዙ ምክንያት ዋና ፀሐፊ የተባለው ሰው ከታዛዥነት ያለፈ ሥራ ሊሠራ አይችልም። ስለሆነም አቶ አስራት ስሙ እንጂ የፀሐፊነት ተግባሩ ከእጃቸው አልወጣም ማለት ይቻላል። ትልቅ ኃይል ያለውን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊነት ሥልጣን ደግሞ ይዘዋል። ኢ/ር ግዛቸው ደንብ ላይ ያልሰፈረ ሥልጣን ላይ ነው የተቀመጡት። ተጠባባቂ ሊቀመንበር የሚባል የኃላፊነት ቦታ በደንቡ ላይ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም። ስለሆነም ኢ/ሩ በስልት እየተንሳፈፉ በአንጻሩ አቶ አስራት ሥልጣናቸውን እያሰፉና እያጠናከሩ ነው።

 

አንድነትና መአህድ ብርቱካንና አስራት የሚለው ከላይ በገለጽኩት ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ ላይ የተነበበው ጽሑፍ በዛን ወቅት መአህድ ውስጥ ይሠራ ነበር ብሎ ያሳየንን “የመርካቶ ሌባ ቀድሞ ሌባ ሌባ” ይላል እንደሚባለው አስቀድሞ መፈረጅን ጠንካራ አባላትን መወንጀልን ሰበብ እየፈለጉ ማባረርን የፕ/ር አስራትን ስም የሚያነሱትን በክፉ ማየትና ማሳደድን በአባላት መካከል መተማመን እንዲጠፋና ጥርጣሬ እንዲሰፍን ማድረግን አመራሩ በሌለ ስጋት ተወጥሮ ሥራ እንዳይሠራ ማድረግ፣ … ወዘተ ነው በአቶ አስራት ተፈጽሞ ያየነው። ስለሆነም የአንድነቱ ቀኝአዝማች አቶ አስራት ናቸው ለማለት በቂ መረጃ አለ እላለሁ። ተቃውሞም ተጨማሪም ያላችሁ ዓላማችን አንድነትን ማዳን አድርገን እንነጋገር። ተሸፋፍኖ ኑሮ የትም አላደረሰንም።

 

ዝም አንልም የሚል አዲስ ባህል የፈጠሩትና አንድነትን ለማስተካከል በሚል የሚታገሉት የፓርቲው አባላት እንደኛ ዝምታን ቢመርጡ አልያም በሞቀበት ማጨብጨብን ሥራቸው ቢያደርጉ ኖሮ ዛሬ ብርቱካን በሀገር ውስጥ አስታዋሽ አይኖራትም ነበር። አንድነትም እንዲህ ተዳካሞም ቢሆን አይገኝም ነበር።

 

ስለሆነም ዝምታ በዛሬው ዘመን ወርቅ አይደለም። ተለባብሶ ጉዞም የትም አያደርስም። ከሆነ በኋላ ከንፈር መምጠጥም ሆነ ቁጣ ማዥጎድጎድ የሚያስገኘው ፋይዳ ያለመኖሩን ቢያንስ በቅንጅት አይተናል። ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው ደጋፊም ካለፈው ያለመማሩ በሽታችን ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ የሚሳይ ነው። የትናንቱን እያወገዝን መልሰን ግን እርሱኑ እንፈጽማለን። ያልታደልን!

 

እስር ቤት በግፍ የምትሰቃየዋን ብርቱካንን እያሰብን ፓርቲዋ አንድነት የመጨረሻ ህልውናውን ከማጣቱ በፊት በምንችለው ሁሉ እንታደገው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንድነትን በማጥፋቱ ሥራ ላይ የተሰማሩትን እናጋልጥ። በጥላቻ ሳይሆን በሐቅ በመረጃ። ነብሳቸውን ይማርና የመአህዱ ቀኝአዝማች ለወያኔ ማደራቸውን ጋዜጠኛ ተስፋዬ የነገረን ፓርቲውም ርሳቸውም ከሞቱ በኋላ ነው። እኛ ግን የአንድነቱን ቀኝአዝማች ለማወቅ የአንድነትን ሞት መጠበቅ፤ ሌላ ነጋሪም መፈለግ የለብንም። እኔ ከላይ ለማሳየት በሞከርኩዋቸውና ከኢንተርኔት ማግኘት በሚቻሉ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቼ የአንድነቱ ቀኝአዝማች አቶ አስራት ጣሴ ናቸው ብያለሁ። ርስዎስ? እናንተስ? እንነጋገር፣ እንወስን፣ የምንችለውን እናድርግ። አንድነትን እንታደግ።


ዕድሜዓለም

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ