የታሰረ ብዕር (አንዱዓለም በቀለ)
አንዱዓለም በቀለ (ስዊዘርላንድ)
(ግጥሙን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)
ታገልንለት ያሉት የሰው ልጅ ነጻነት፣
የመጻፍ የማንበብ ...
የሃሳብ ነጻነት የመናገርን መብት፣
በቁምጣ በሸበጥ የተፋለሙለት፣
ደም ያፈሰሱለት ህይወት የሰዉለት፣
እኛም ዕልል ያልነው የተደሰትንለት፣
የታሰረ ብዕር በቃ ቀን ወጣለት፣
ብለን የጮህንለት የተደሰትንለት፣
… የዲሞክራሲን መብት፣
ገና በዕንጭጩ ጦር ተሰበቀበት፣
ብዕርን እንደ ቦንብ እንደ አዳፍኔ ፈሩት፣
ሃቅን በከተበ አሸባሪ አሉት፣
በሰዓታት ዕድሜ ህግ ተበጀለት፣
ችሎትና ዳኛ ባልተገናኙበት፣
ፍርድ ተባለና ወህኒ ወረወሩት፣
ከፈጣሪ በላይ ሰግደው በሚያመልኩት፣
ከልብ በሚያምኑት ብረት አቆሰሉት፣
አቁስለው ላይገድሉት፣
ገድልው ላያጠፉት፣
ሃቅ ሃቅ ነውና ቢከር ላይበጥሱት፣
በርግጥ ግን ሞከሩት፣
ሞክረው ላይዘልቁት፣
በሥልጣን ታውረው ሃቅን ረገጡት፣
ደፈሩት … ሞከሩት፤
የናትናኤልን እውነት ሊያቀጭጩት፣
የውብሸት ታዬንቀለም ሊበርዙት፣
ዳዊት ቢታሰርም ጽናቱን ላያስሩት፣
የስክንድርን ብዕር በጥይት ሊያቆሙት፣
... ገበዙ ሞከሩት፣
የቀለምን ጅረት ችለው ላይከትሩት፣
የሃቅን ውቅያኖስ ችለው ላያነጥፉት፣
... ላይዘልቁ ሞከሩት፣
በዓለም ህዝብ ፊት ሊያፍሩበት ደፈሩት።
ወይ አለማስተዋል አለማየት ዞሮ፣
አምና በሰርካለም ጉዞውን ጀምሮ፣
በርዕዮት ዓለሙ ዛሬም ህያው ሆኖ፣
አሰርን ያሉት ብዕር እግረ ሙቅ ሰብሮ፣
አሳፈርን ያሉትን መልሶ አሳፍሮ፣
ቀበርነው ያሉትን እሱ ቀድሞ ቀብሮ፣
ሃቅ አለመሞቱን አስተምሮ መክሮ፣
ዓለም ጉድ አስብሎ ተደንቆ ተከብሮ፣
የታሰረው ብዕር ...
ለሽልማት በቃ ዳግም ብረት ሰብሮ።
አንዱዓለም በቀለ (ስዊዘርላንድ)
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



