ሰውነት! (ማህሙድ እንድሪስ - ከአዲስ አበባ)
ሰውነት
(ማህሙድ እንድሪስ - ከአዲስ አበባ)
ሰውነቴን አሞኛል!
እዚህ ቦታ ይሰማኛል፣
ሰውነቴን ልታጠበው፤
ሲል ይሰማል የሰው ልጅ ሰው።
ይህ ሰውነት ማለት፣
ስጋችን ነው እንዴ፤ በእውነት?
እንደኔ እንደኔ ከሆነማ፣
ምናልባት ባገኝ የሚሰማ፣
ህሊናዬ ነው ሰውነቴ፤
ማሰብ ማስረዳት መረዳቴ፣
ሀቅን መቀበል መስጠቴ።
ያለቀለት የሞተማ፣
አይቃወም አይስማማ፣
የሚሉትን መች ሲሰማ፣
በቃ ሰውነት የለውማ።
ትንኝ፣ ጥንቸል ወይ አንበሳው፣
ስጋና ደም ሆሉም አለው፣
የሌላቸው ሰውነት ነው፣
ለሰው ብቻ የተሰጠው።
ምን ቢጎላ በግዝፈቱ፣
እኔ መቸም አይታየኝ የዳይኖሰር ሰውነቱ።
ፍጥረት ሁሉ አካል አለው፣
ሰውነት ግን ለሰው ልጅ ነው፣
ባጠቃላይ የምስማማው፤
ሰውነትስ ህሊና ነው፣
ከሰው በቀር ማንም የለው።



