አዲሱ ባላባት

አክሊሉ ሙላት

መሻሻል ይሆን ወይ መገዛት በንጅነር፤

እነፊት አውራሪን ተክቶ በዶክተር?

 

የዲግሪ አልባ መሪ አድርጎ ኋላ ቀር፤

ይመረጥ ይሆን ወይ ላዋቂ መገበር።

 

የጦሩን ሽልማት እያውለበለበ፤

ዲግሪን ኒሻን አርጎ ራሱን ‘የካበ፤

ከወንበር ተነሱ መጥቷል ያ ተማሪ፤

የዛሬው ደጃዝማች ያሁን ፊት አውራሪ።

 

ክቡር ባለማረግ ምሩቅ ተሸላሚ፤

የመጻፍለባላቢ አዋቂ አራሚ።

በዩኒቨርስቲው ጦር በኮሌጁ ሜዳ፤

ያዕምሮውን ጥይት ቦንቡን ያፈነዳ።

 

ይላል “እኔኮ ነኝ ድንቁርናን ረቺ፤

የማይም ነጻ አውጭ ሰንሰለቱን ፈቺ።

የቀለም አርበኛ እጅጉን አስፈሪ፤

ደጃዝምች አትበሉኝ ወይንም ፊትአውራሪ።

 

ለኔ ደስ የሚለኝ እቅጩን ብናገር፤

ዘመናዊ መዕረግ ዶክተር ወይ ኢንጅነር።

 

አረ እባካችሁ ተነሱ ከወንበር፤

አዲሱ ባላባት ደርሷል አሉ ከበር።

ተጻራሪ ሀሳብ እንዳትናገሩ፤

ከርሱ በላይ የለም የሚያውቅ በአገሩ።

 

ካሁኑ ተረዱ በሰአቱ እወቁ፤

በኋላ እንዳታፍሩ እንዳትሳቀቁ።

 

አስራ አምስት አመት ዩኒቨርስቲ ዘምቶ፤

ክፍ ያለውን ውጤት አምጥቶ ከመቶ።

 

ባለ ሶስት ኒሻን ነው የቀለም አክራሪ፤

ቢ ኤ፣ ማስተርና ዶክትሬት ደርዳሪ።

 

ይግባችሁ ለናንተም የበላይ መሆኑ፤

ተመስክሮለታል ዲግሪ ነው ሚዛኑ።

አይናችሁን ድፉ ውደቁ ስገዱ፤

ቃሉን ተቀበሉ ይግባኝ አይሻም ፍርዱ።

 

ተውት አጠይቁት በሙያ ‘ንዲሰራ፤

ያ’ምሮው ባላባት መሀይሙን ይምራ።

 

አያስብ ለራሱ ማይም ነው ጭሰኛ፤

ላዋቂ ተገዥ ገባሪ ምርኮኛ።

 

የበላይነትን፣ ሥልጣንን ፍለጋ፤

በዙፋን በርጩማ ቤተ መንግስት አልጋ፣

አዲሱ ባላባት ሊንሰራፋ ብሎ፤

ችሎት ላይ ከረመ ከሙያው ኮብልሎ።

 

ድምጹን አጎርንኖ ሲጮህ ሲያስፈራራ፤

ባላባት ሆን ብሎ ሲፎክር ሲያጓራ፤

ላንዲት ሰዓት እንኳን ቁም ነገር ሳይሰራ፤

ባለ ዲግሪ ሞተ ምንም ሳያፈራ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ