የ2012 ዓ.ም. 29ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች
ከመጋቢት 14 - 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ ሃያ ዘጠነኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከየካቲት መጋቢት 14 - 20 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ እንደቀደሙት ሳምንታት ሁሉ ባሳለፍነውም ሳምንት በአገር ቤትም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮሮናን የተመለከቱ ዜናዎችን የሚያስተካክል አልነበረም። አሁንም ይህ የዓለም ውጋት የኾነው ወረርሽኝን የተመለከቱ ዜናዎችን የሚስተካከል አልነበረም። አሁንም ይህ የዓለም ሕመምና ውጋት የኾነው ወረርሽኝን የተመለከቱ ዜናዎች በደቂቃዎች ልዩነት ሰዎች እንደዋዛ የሚረግፉበት ኾኖ ቀጥሏል።
በየዕለቱ የሚሰሙ ዜናዎችም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ያለመቻሉን የሚያመለክቱ መኾናቸው ደግሞ መጨረሻውን ለመገመት አዳግቷል። በዓለም በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ720 ሺህ በላይ ደርሷል።
በኢትዮጵያ ደግሞ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በይፋ የተነገረ ሪፖርት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች 21 ደርሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ስለዚህ በኢትዮጵያ 19 የቫይረሱ ተጠቂዎች በለይቶ ማቆያ ሕክምና እያገኙ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ ለየት ያለ ኾኗል።
ይህም ሁለት ታማሚዎች ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ማገገማቸው መነገሩ ነው። ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ ከቫይረሱ ያገገጁ ሰዎች መገኘታቸውን ያመላከተ ነው። እስካሁን ሕይወቱ ያለፈ አለመኖሩም በመልካም የሚታይ ነው። አንዲት ቫይረሱ የተገኘባት ግለሰብ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላት እንደኾነ ታውቋል። ይሁንና የዚህ ወረርሽኝ ሥጋት ገና ካሁኑ የአገር ኢኮኖሚ እየቆረጠሙ፣ ዜጐችን እንቅስቃሴ እየገደበና በሥነልቦና ደረጃ ጭንቀቱ እንዲያይል እያደረገ ነው።
አንቱ የተባሉ የዓለማችን አገሮች ዜጐቻቸው በዚህ በሽታ ከፊት ለፊታቸው እስከወዲያኛው ሲወድቁ ቀና ማድረግ ተስኗቸው ጉልበት እያጡ መኾኑን ያየ፤ የኢትዮጵያስ ዕጣ ፈንታ ቢያሳስብ አይገርምም። በዚህ የአገር ሥጋር የኾነውን ወረርሽኝ መላ ለማለት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስገራሚ አሳዛኝ አስደሳች ክስተቶችንም እያስመለከተ ነው።
የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽም በዚህ ወረርሽኝ ዙሪያ በኢትዮጵያ እየኾነ ያለውን አንዳንዶቹን ክስተቶች አስመልክቶ ያጠናከርነው ሪፖርት እናስቃኛለን። ከዚህ ወረርሽኝ ባሻገር ሌሎች ክዋኔዎችም በዚሁ ሪፖርት ላይ ተካትተዋል። የኮሮናውን ያህል ባይሆንም፣ ጆሮ ካገኙ ሌሎች ዜናዎች መካከል በብልጽግና ፓርቲና በሕወሓት መካከል በንብረት ክፍፍል ላይ የተፈጠረው ውዝግብ አንዱ ነው።
ብዙዎች ሰሞናዊ መረጃዎች በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያወጣው ኢዜማ፤ በቫይረሱ ለሚጠቁ ወገኖች ለይቶ ማቆያና ሕክምና መሥጫ ማዕከላት ዝግጅት በአማራጭነት ሰዎች ያልገቡባቸው ኮንዶሚኒየሞች ለዚሁ አገልግሎት መዋል ይገባቸዋል ብሏል። ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ በአነጋጋሪነቱ ሊጠቀስ የሚችለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፤ ኢትዮጵያ ለኮሮና ቫይረስ ሊሆን የሚችል ባህላዊ መድሃኒት ላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ ይፋ ከማድረጓ ጋር የተያያዘው መረጃ ነው። ይህ ጉዳይ ብዙዎችን የተለያየ ሐሳብ እንዲሰነዝሩ ያደረገ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተፈጠረው ግጭት በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከዚሁ ቫይረስ ክስተት ጋር የተያያዘ ነው።
ከእስር ለማምለጥ የተደረገው ሙከራ ግን መክሸፉ ተነግሯል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ፤ ሰዎች በቤት ተወስነው እንዲቀመጡ የተሠጠውን ማሳሰቢያ በተፈለገው ሁኔታ ባለመተግበሩ በከተማዋ በአንዳንድ አካባቢዎች በመዘዋወር በድምፅ ማጉያ ግንዛቤ ሲያስጨብጡም ነበር። በማግስቱ እሁድ መጋቢት 20 ቀን 2012 የአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል እንዲረጭባቸው ተደርጓል። ይህ የመርጨት ተግባር ወደ 43 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መኾኑም ተነግሯል። እነዚህንና በሌሎች የሳምንቱ አንዳንድ ክንውኖችን በተለያዩ ምልከታዎች በማዋዛት በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍት የተሰናዳው ጥንክር እንደሚከተለው ቀርቧል።
ገበያውና እኩዩ ተግባር
ባለፉት ሁለት ሦስት ሳምንታት ሸመታ የጦፈበት ነበር ማለት ይቻላል። በዋናነት ከኮሮና ሥርጭት መከላከያ ጋር የተያያዙ ግብአቶች የበዛ ሸማች ነበራቸው። አልኮልና ሳኒታይዘር ለመግዛት በየከነማ ፋርማሲዎችና ለተወሰኑ ቀናት ደግሞ በሸማቾች ማኅበራት መደብር የነበሩ ሰልፎች የግብይቱን ፍላጐት ያሳያሉ።
ይህ ብቻ ሳይኾን የሚኾነው አይታወቅም በሚል ምግብ ነክ ምርቶችም ከወትሮው የተለየ የግብይታቸው መጠን ከፍ ብሎ ታይቷል። በሰሞኑ ግብይት ሒደት ዋጋ ከመጨመር አንፃር የታዩ ያልተገቡ ተግባራት ጐልተው የታዩ ሲሆን፤ ይህንን ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ እርምጃ ስለመወሰዱ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ብቻ ከ1400 በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ የአንዳንዳቹ ነጋዴዎች ዋጋ ጨምረው ሲሸጧቸው የነበሩ ምርቶች ተወርሰው መልሰው በሸማቾች ማኅበራት በኩል እንዲሸጡ መደረጉን የከተማዋ ንግድ ቢሮ ያሳወቀ ሲሆን፤ ይኸው እርምጃ ቀጥሏል። የንግድ ቢሮው መረጃ ጨምሮ እንደገለጸው፤ ባልተገባ ዋጋ ሲሸጡ የተያዙ ነጋዴዎች ንብረታቸው ተወርሶ መደብራቸው ይታሸጋል። በዚሁ ተግባራቸውም ለሕግ ይቀርባሉ። የተወረሰባቸው ንብረት መልሶ እንዲሸጥ ሲደረግም ከሽያጩ የተገኘው ገንዘብ በልዩ ካዝና ይቀመጣል። ይህ የሚኾነው ነጋዴዎቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ተከራክረው ካሸነፉ ገንዘቡ ሊመለስላቸው የሚችል በመኾኑ በክርክሩ ካላሸነፉ ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ እንደሚደረግ ይጠቁማል።
ከሰሞኑ የኮሮናና የግብይት ሒደቱን በተመለከተ ሊጠቀሱ ከሚችሉ እኩይ ተግባራት ውስጥ ግን፤ አልኮልን ከውኃ ቀላቅለው ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦች መያዛቸው ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሠጠው መግለጫም፤ ድርጊቱን በማውገዝ ድርጊቱን ከሰው ሕይወት ማጥፋት ጋር አያይዞታል። በእርግጥም ይህ ድርጊት ዜጐችን በእጅጉ አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ፤ በዚህ ሰዓት እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸሙ ደግሞ ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር። (ኢዛ)
ኮሮናና የመንግሥት የኢኮኖሚ ጉዳዮች እርምጃ
ኮሮናን ለመከላከል በሳምንቱ አጋማሽ መንግሥት ተጨማሪዎችን እርምጃዎችን ወስዷል። በዚህም መሠረት ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ግምጀ ቤት (ገንዘብ ሚኒስቴር) አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንዲሆኑ መወሰኑ አንዱ ነው። ከዚህ ጐን ለጐን በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ እየተፈጠረ ባለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መጠነኛ ማስታገሻ ይኾናል የተባሉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። አንዳንድ በወጪ ንግድ ዘርፎች ለሚገጥማቸው ቀውስ ማገገሚያ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለ16ቱ የግል ባንኮች 15 ቢሊዮን ብር እንዲያቀርብ መወሰኑ ነው።
ይህ ውሳኔ ባንኮች ፈጥኖ ችግሩ ለታየባቸው እንደ አበባና ሌሎች የወጪ ንግድ ዘርፎች ለተበደሩት ብድር ማራዘሚያና ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ እድል ለመሥጠት የታሰበ ነው። ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ የሕክምና ዕቃዎች እና ሌሎች ተያያዥ ምርቶች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ የተወሰነበትም ነው። ሌሎች መሰል እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን፤ ኢኮኖሚው የበለጠ እንዳይጐዳ ሌሎች እርምጃዎች የሚጠበቁ እንደኾነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ በወረርሽኙ ምክንያት ገና በጠዋቱ ችግር ውስጥ እየገባ በመኾኑ ይህንን ችግር የበለጠ ሰፍቶ አደጋው አደገኛ እንዳይኾን በዚህ ሳምንት እንደተወሰዱ ያሉ ሌሎች እርምጃዎች የሚያሹ መኾኑን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም አሁን ከኢኮኖሚው አንፃር ከተወሰዱት ሰሞናዊ እርምጃዎች ሌላ አሁን ውሳኔ የሠጠባቸው ጉዳዮች ታይተው ተጨማሪ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ከአንዳንድ አገሮች ሰሞናዊ ውሳኔ አንፃር ኢኮኖሚያቸውን ለመጠበቅ ሠራተኞች እንዳይበተኑ ለማድረግ የብድር ወለድ ቀንሰዋል። ኮርፖሬት ታክሳቸውና ሌሎች ታክሶችን በመቀነስ ችግሩ እንዳይሰፋ እያጣሩ በመኾኑ በኢትዮጵያም ይህ መኾን አለበት ብለው የሚሞግቱ አሉ። ይህም ቢሆን ግን ኢኮኖሚው ጉዳት እየታየ ነው። ለዚህ እንደምሳሌ የሚወሰደው 150 ሺሕ የሚደርስ ሠራተኞችን የያዘው የአበባና የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ነው።
ይህ ዘርፍ በተለይ የአበባ ኤክስፖርት ከሰባ በመቶ በላይ ቀንሷል። ይህንን ሁሉ ሠራተኛ የያዘው ይህ ዘርፍ ሽያጩ በ30 በመቶ ብቻ ከተወሰነ ይህንን ሁሉ ሠራተኛ ምን ይኾናል የሚለው አሳሳቢ ስለነበር መንግሥት ከዘርፉ ተዋንያኖች ጋር በመኾን ከተወያየ በኋላ፤ የብድር ማራዘሚያ እንዲያገኙና ሌሎች እገዛዎች እንዲደረግላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም በመኾኑ ቢያንስ ለሦስት ወር ሠራተኞች ይዘው ለመቀጠል መስማማታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።
በአገልግሎት ዘርፉም ቢሆን በተለይ የቱሪዝም ዘርፍ እጅጉንም የሆቴል አገልግሎት ቢዝነስ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ገበያው ተመቷል። ብዙ ሆቴሎች ሥራ አቁመዋል ወደሚባልበት ደረጃ ላይ ናቸው። ስለዚህ ይህንን የመታደግ ሥራ የሚጠበቅ ነው። (ኢዛ)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ
በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይ በአፍሪካ ገናና ስም ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጦስ ከኾነባቸው የቢዝነስ ዘርፎች ቀዳሚው ነው።
በአራቱም አቅጣጫ በየዕለቱ የሚበሩት የአየር መንገዱ አውሮፕላኖች ዛሬ እንደልባቸው ተነስተው አይበሩም፤ አያርፉም። ለወትሮ በቦሌ አየር መንገድ ማረፊያና መነሻ ሜዳ ላይ ቆይታቸው አጭር የነበሩ አውሮፕላኖች ዛሬ በዝተው እየታዩ ነው። በዚህ ሳምንት ደግሞ ወደ 72 የበረራ መዳረሻዎቹ እንዳይሔድ ተከልክሏል። አየር መንገዱ እንደ ከዚህ ቀደሙ አትርፌያለሁ ብሎ ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ አይጠበቅም።
ባለፉት ሦስት ወራት እንኳን 195 ሚሊዮን ዶላር ማጣቱ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ከዚህም በኋላ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት ከ72ቱ ሌላ ተጨማሪ በረራዎች ለማስቆም የሚገደዱ ከኾነ ደግሞ በኪሣራ ስሙ ተነስቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 2012ን ወይም 2020ን መክሰሩን የሚገልጽበት የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል። (ኢዛ)
የሀብት ማሰባሰብ
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰት ከተሰማ ወዲህ ችግሩን ለመቀነስ በመንግሥት ውሳኔ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች አንዱ ለመከላከሉ የሚኾን ሀብት ወይም ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ አንዱ ነው። ለዚህም ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ነው። የሕብረተሰቡም ምላሽ በበጐ የሚታይ ነው።
በአዲስ አበባ ደረጃም በምክትል ከንቲባው የሚመራው የእርዳታ አሰባሰብ በተለየ የሚታይ ኾኗል። ዜጐች ቤታቸውን፣ የንግድ ተቋማቸውን፣ ሆቴላቸውን ጭምር መንግሥት ለለየቶ ማቆያና ማከሚያነት እንዲገለገልበት እየሠጡ ናቸው። በየዕለቱ ይህ የሚሰማ ሲሆን፤ በዚሁ መነሻነት የክልል ከተሞች ውስጥም ተመሳሳይ ድጋፍ እየተሠጠ መኾኑ ችግሩ፤ ቢሰፋ ለይቶ ለማቆየትና ለሕክምና የሚኾን ስፍራ ከወዲሁ ለማዘጋጀት ያስቻለ ኾኗል። እስካሁን በአዲስ አበባ ከ44 ሺሕ በላይ ለሚኾኑ ታካሚዎች የሚኾኑ ቦታዎች መሰናዳታቸው ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል ማለት ይቻላል። ትምህርት ቤቶች ለሁለተኛ ጊዜ ለተጨማሪ 15 ቀን ዝግ ኾነዋል። የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ከቤት እንዲሠሩ ተወስኗል። ለወትሮ በየዕለቱ ባለጉዳይ የሚያሰጥባቸው የኢሜግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ሁነት ኤጀንሲ ያሉ መሥሪያ ቤቶች ፓስፖርት መሥጠትና ማደስ አቁመዋል። ከተወሰኑ ተቋማት በቀር ብዙዎች ክልከላ ቀጥሎባቸዋል።
ሌላው ቀርቶ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይቆዩ ተብለው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ተዘግተው ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው። ከዚህ ውሳኔ የተደረሰው በግቢያቸው ተወስነው እንዲቀመጡ የተላለፈው መመሪያ በአግባቡ ባለመተግበሩና አደጋ ሊሆን በመቻሉ ነው። በዚህ ተማሪዎችን በመሸኘት ሒደት ላይ በመንገድ ላይ መኪና ተገልብጦ የሁለት ተማሪዎች ሞት መሰማቱ ከሰሞኑ በአሳዛኝነቱ የሚጠቀስ አጋጣሚ ኾኗል። በሁሉም አቅጣጫ አገልግሎቶች ከሥራቸው እንደተስተጓጐሉ ትምህርት ቤትና መሰል ተቋማት የመዘጋታቸው ዋናው ጉዳይ ዜጐች ከቤት ኾነው እንዲያሳልፉ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዝ በመኾኑ ነው።
በተግባር የታየው ግን ይህ ያለመኾኑ እያሳሰበ ነው። በሳምንቱ አጋማሽ ለቅኝት አዲስ አበባን ተዟዙረው የቃኙት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዲፈጸሙ የወጡ መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበራቸውና ሰዎች ችግሩን እንደ ችግር እያዩት አለመኾኑን የሚያሳስብ መኾኑን ነው። እንደ እርሳቸው ሥጋት የምርመራ ሒደቱ በጥልቀት ቢካሔድ ሊኖር የሚችለውን ልዩነት በማስታወስ፤ ሰዎች መመሪያዎችን ያለማክበራቸው አደጋ በመኾኑ መመሪያዎቹ ይተገበሩ ዘንድ የጠየቁበት ሳምንት ነበር። (ኢዛ)
የጅቡቲ ነገር
በዚህ ሳምንት ከተሰሙ ዜናዎች መካከል ጅቡቲ ከ800 በላይ የሚኾኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የወሰዳቸው እርምጃ ይጠቀሳል። ጅቡቲ በእነዚህ ኢትዮጵያውያን ላይ እርምጃውን የወሰደችው በሕገወጥ መንገድ የገቡ ናቸው በሚል ሲሆን፤ እነዚህ በግዳጅ የተመለሱት ኢትዮጵያውያን በድሬዳዋ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ ናቸው ተብሏል።
ለ14 ቀን በዚሁ ለይቶ ማቆያ የሚቆዩ ሲሆን፣ ከ14 ቀን በኋላ አስፈላጊ ማጣራትና ምርመራ ተደርጐ ወደየመጡበት ክልል የሚላኩ ይኾናል ተብሏል።
ከእነዚህ ተመላሾች ውስጥ አራቱ ሙቀት የታየባቸው በመኾኑ፤ የደም ናሙናቸው አዲስ አበባ ተልኮ በተደረገ ምርመራ ኮሮና ቫይረሱ ነፃ መኾናቸው ተረጋግጧል።
ከ814ቱ ተመላሾች በለይቶ ማቆያው (ድሬዳዋ) ለ14 ቀን በሚቆዩበት ጊዜ ሙሉ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ሲሆን፤ ቆይታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በሚዘጋጁላቸው ትራንስፖርት ይሸኛሉ ተብሏል። እንደ መረጃው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከጅቡቲ እየመጡ ነው። (ኢዛ)
በኮንቴይነር ውስጥ ሞተው የተገኙት 64 ኢትዮጵያውያን
አገር ከኮሮና ወረርሽኝ ጭንቅ ውስጥ ባለችበትና ዜጐችን ለመታደግ የተለያዩ ሥራዎች በሚሠራበት በዚህ ወቅት ከወደ ሞዛምቢክ የተሰማ አንድ ዜና በአሳዛኝነቱ የሚጠቀስ ነው።
ይህም በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር በኮንቴይነር ውስጥ የታጨቁ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 64ቱ ሕይወታቸው ማለፉን የሚያመለክት ነው። እርግጥም ይህ ዜና አስደንጋጭ ነበር። (ኢዛ)
የአሜሪካ ኤምባሲ መዘጋት
የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ በተለያየ መንገድ የንማገለጽ ስለመኾኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ። በዲፕሎማቲክ ከተማነቷ የምትታወቀው አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና የተለያዩ አገሮች የሚገኙባትም ነች። ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዳንዶቹ ቢሮዋቸውን ለጊዜው ስለመዝጋታቸው እየገለጹ ነው። በዚህ ሳምንት በይፋ ኤምባሲዋን በመዝጋት የምትጠቀሰው አሜሪካ ነች።
አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በወጣው መግለጫ ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጋር በተያያዘ ላልተወሰነ ጊዜ የኤምባሲው አገልግሎትና እንደማየሸጥና እንዲዘጋ አስታውቋል።
ኤምባሲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከቫይረሱ ሥርጭትና የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጋር ተያይዞ ኤምባሲውን ላልተወሰነ ጊዜ መዝጋቱን አስታውቋል። በኤምባሲው የሚሠጡ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደማይኖሩም እወቁልኝ ብሏል። (ኢዛ)
ኢዜማ ያልተላለፉ ኮንደሚኒየሞች ለለይቶ ማቆያ ይዋሉ ብሏል
ኮሮና የምርጫ ሰሌዳውን እያዛባው ነው
በአገር ደረጃ ሥጋት የፈጠረውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ ተደጋጋሚ መልእክቶችና መግለጫዎችን በማውጣት ከሚጠቀሱ ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ኢዜማ ነው።
በዚህም ሳምንት ኢዜማ በፓርቲው መሪ በኩል ባወጣው መግለጫ ሙሉ ኃይላችንን የኮሮና ቫይረስን ጫና ለመቋቋም ማዋል እንደሚገባ በማስገንዘብ ወረርሽኙ አገር አቀፍ የደኅንነት ቀውስ በመኾኑ በጋራ ልንከላከለው ይገባል ብለዋል። በተለይ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ የሚያስፈልግና ኢኮኖሚውን ለመታደግም ሊወሰዱ ይገባቸዋል ያሉዋቸውን የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች የጠቆሙበት ነው።
በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ለነዋሪዎች ያልተላለፉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አስፈላጊው መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለለይቶ ማቆያና ሕክምና መሥጫ እንዲውል ፓርቲው አሳስቧል። ፓርቲው በዚህ ሳምንት ያወጣው መግለጫ ስለቀጣዩ ምርጫም የጠቀሰው ነበር።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንዳይስፋፋ መንግሥት እየወሰደ ካለው ውሳኔ አንፃር በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ከአሁኑ ተፅዕኖ መፍጠሩንም አስታውሷል።
በመኾኑም በቀጣዩ ሊሆን የሚችለውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳና ተያያዥ ጉዳዮችን ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን እየመከረ ውሳኔ መሥጠት እንደሚኖርበትም ኢዜማ አስታውቋል።
ኢዜማ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቋረጠው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲመለስ የጠየቀበትም መግለጫ ሠጥቷል። (ኢዛ)
ታራሚዎች ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለማምለጥ የተደረገው ሙከራ መክሸፍ
መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ግርግር ተፈጥሮ ነበር። ይህ ግርግር በማረሚያ ቤቱ አንድ ዞን ውስጥ እሳት እስከመነሳት ደርሶም ነበር። መንግሥት እንዳረጋገጠውም በዕለቱ የተፈጠረው ችግር አንዳንድ እስረኞች ለማምለጥ ሙከራ ያደረጉበት ጭምር የነበረ ሲሆን፤ ይህ ሙከራ ግን መክሸፉን ገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዳመለከተው ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተወሰኑ የሕግ ታራሚዎች ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በተደረገው ጥረት ከሽፏል።
አንዳንድ ታራሚዎች ከሕግ ውጭ ያነሱት ጥያቄ ሁከት ለመፍጠር እና ከማረሚያ ቤቱ ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ እንደነበርም ጠቅሷል። በማረሚያ ቤቱ በአንድ ዞን እስከመነሳት ደርሶ እንደነበርና ይህም በማረሚያ ፖሊስ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሏል መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ከማረሚያ ቤቱ የማምለጥ ሙከራ ያደረጉ የሕግ ታራሚዎች በሕግ የሚጠየቁ መኾኑንም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቀዋል። (ኢዛ)



