ለወራት ተቋርጦ የነበረው የአስመራ በረራ ዳግም ተጀመረ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ አቋርጦት የነበረውን በረራ ዳግም ጀመረ
በረራውን አቋርጦ የነበረው በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ጦርነት ጋር የተያያዘ እንደኾነ ይታመናል
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 23, 2021)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለወራት አቋርጦት የነበረውን የአስመራ በረራ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በድጋሚ መጀመሩን አስታወቀ።
አየር መንገዱ በረራውን አቋርጦ የነበረበት ምክንያት ባይገለጽም፤ የበረራው መቋረጥ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ጦርነት ጋር የተያያዘ እንደኾነ ይታመናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ለ20 ዓመታት በረራ አቋርጦ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ አስመራ በመሔድ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተቋረጠውን ግንኙነት ዳግም ለማስቀጠል የሚያስችል ስምምነት ከተደረገ በኋላ ዳግም በረራ እንዲጀምር ተደርጓል።
ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም በረራ የጀመረው ሐምሌ 2010 እንደነበር ይታወሳል።
አየር መንገዱ የኤርትራ በረራው በተጀመረ በአንድ ዓመት ብቻ ከ130 ሺህ በላይ መንገደኞችን ወደ አስመራ እና አዲስ አበባ ማጓጓዝ መቻሉ መገልጹም አይዘነጋም። (ኢዛ)



