“ከተሸነፍን ላሸናፊው አቅፈን ሥልጣን በማስረከብ አዲስ ታሪክ እንሠራለን” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
“በምርጫው ያሻችሁን ምረጡ፤ ግን ሰላምን አስቀድሙ፤ ያሻችሁን ምረጡ ግን እኩል መድረክ መፈጠሩን አረጋግጡ” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 8, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞናዊ ንግግራቸው ውስጥ በምርጫ ዙሪያ ያደረጉት አንድ ንግግራቸው ተጠቃሽ ነው።
ምርጫን በተመለከተ “ያሻችሁን ምረጡ” የሚለውን ይህንን ንግግር ያደረጉት ከትናንት በስቲያ ወደ አማራ ክልል ተጉዘው በአምስት ቢሊዮን ብር ይገነባል የተባለውን የመንገድ ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
የቀጣዩ የምርጫ ግባቸው ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማካሔድ ስለመኾኑ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምርጫው ሰላማዊና ነፃ ኾኖ እንደሚካሔድ አመልክተዋል።
በዚህ ዙሪያ ያላቸውን እምነት “የምርጫ ሒደቱ ሰላማዊ የኾነ፣ ለሁሉም እኩል እድል ተፈጥሮ ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት ይኾናል” በማለት ገልጸዋል።
በተለይ በቦታው በመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያው ላይ ለተገኙት ተሳታፊዎች “በምርጫው ያሻችሁን ምረጡ፤ ግን ሰላምን አስቀድሙ፤ ያሻችሁን ምረጡ ግን እኩል መድረክ መፈጠሩን አረጋግጡ” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫው ብንሸነፍ ለአሸናፊው አቅፈን ሥልጣን በማስረከብ አዲስ ታሪክ እንሠራለን፤ ካሸነፍን ደግሞ ኢትዮጵያ ወደሚገባት ብልጽግና ለማውጣት ቀን ከሌት እንሠራለን በማለት፤ በቀጣዩ ምርጫ 2013 ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት አንጸባርቀዋል። (ኢዛ)



